የመለስ ዜናዊን የመረጃ አፈናን በህዝባዊ ኃይል እንበጣጥሳለን!

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በአገር ውስጥ የሚገኙ የመረጃ መረቦችን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፤ ከውጭ አገራት የሚተላለፉ የሬድዮና የቴሌቪዥን ሞገዶችን በይፋ በማፈን ኢትዮጵያ አገራችን በመረጃ ከዓለም የተነጠለች ደሴት ለማድረግ ተግቶ ይሠራል፤ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብም ያወጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ለሙያቸው ክብር ያላቸው ጋዜጠኞችን በክሶች ብዛት፤ በእስርና እንግልት እንዲሁም ከአቅማቸው በላይ በሆነ የገንዘብ ቅጣት እንዲሸማቀቁ በማድረግ እውነት ዘጋቢ ስታጣ የኢትዮጵያ የመረጃ አየር በውሸት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል።

መለስ ዜናዊ “የመረጃ አውታሮችን በሙሉ ከተቆጣጠርኩ እና እውነትን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች እንዳይኖሩ ካደረግሁ ህዝቡ እኔ የማወራውን ውሸት አምኖ ይቀበላል፤ ፀጥ ብሎም ይገዛልኛል” ብሎ ያምናል። ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እነዚህን የመለስ ዜናዊን የትዕቢት እሳቤዎችን ዋጋ ማሳጣት ከቀዳሚ ተግባሮቻችን አንዱ ነው ብሎ ያምናል።

በአገራችን ውስጥ አዎንታዊና ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ የምንፈልግ ወገኖች በሙሉ ከዚህ በታች ለተመለከቱት ሁለት ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ይኖርብናል ብሎ ግንቦት 7 ያምናል።

  1. በመለስ ዜናዊ የሚመራው የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ የግንቦት 7 ሬድዮና ሌሎችም አገር ወዳድ የአጫጭር ሞገድ ስርጭቶች በተከታታይ ያፍናል። የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬድዮዎች እንደወቅቱ አሳሳቢነት ይታፈናሉ። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ስርጭትን ለማፈን በራሱ በመለስ ዜናዊ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል። በግብፅ ህዝባዊ አብዮት ወቅት አልጀዚራም ታፍኖ ነበር። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሚዲያን ለመቆጠጠር ምን ያህል የተቀነባበረ ሥራ እየሰራ እንደሆነ ነው። ለዚህ የሚኖረን አፀፋዊ ምላሽ ምንድነው? በአገራችን ውስጥ ህዝባዊ አብዮት ሲነሳ የምጠቀመው የመረጃ መረብ ምንድነው?
  2. ጋዜጠኞች በሚደርስባው ተከታታይ ወከባ፣ እስርና ቅጣት ምክንያት ሥራቸውን በነፃነት መከወን አልቻሉም። እውነት ተናግሮ ከመሰቃየት “ዋሽቶ ማደርን” የሚመርጡ የስም ጋዜጠኞች ቁጥር እየበረከተ ነው። ለእውነቱ የቆሙ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኞች ቁጥር በየእለቱ እየተመናመነ ነው። አሁን በአገር ውስጥ ያሉት ሃቀኛ ጋዜጠኞችም በአገዛዙ ዓይን ውስጥ በመሆናቸው መታዘብና መዘገብ የሚችሉት ነገር እጅግ ውስን ነው። ይህንን አሳሳቢ የሆነውን የጋዜጠኛ እጥረትን በምን እንከላከላለን? ህዝባዊው አመጽ ሲነሳ ሁኔታውን ተከታትለው ለኢትዮጵያም ለዓለምም የሚዘግቡልን ጋዜጠኞችን ከየት እናገኛለን?

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከላይ የተመለከቱት ሁለት ጥያቄዎችን አንስቶ ሲመክርባቸውና መፍትሄዎችንም ሲያፈላልግ ቆይቷል። ንቅናቄያችን እነዚህ ጥያቄዎች ነፃነታችንና አገራችን የምንወድ ወገኖችን ሁሉ ሊያሳስቡ የሚገቡ ናቸው ብሎ ያምናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ምንም እንኳን ችግሮቹ ውስብስብ ቢሆኑም በደንብ ከታሰበባቸው እና ጥረቶቻችንን ማስተባበር ከቻልን የመለስ አገዛዝን የመረጃ አፈና መበጣጠስ እንችላለን ብሎ ያምናል። ችግሮቹ ዝርዝር ጥናት የሚፈልጉ ቢሆንም ለሁለቱ ዓበይት ችግሮች የሚከተሉት ሁለት አጠቃላይ መፍትሄዎች መስጠት ይቻላል ብሎ ግንቦት 7 ያምናል።

  1. የሚዲያ አውታሮች ታፍነዋል ብለን ተስፋ ቆርጠን አናውቅም፤ ወደፊትም የትኛውም የአፈና መጠን ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። የመለስ አፈና በጠነከረ መጠን ምላሻችን እየባሰ መምጣት ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በጋራ መቆም ይኖርብናል። በየጊዜው ለአፈና የማይመቹ ስርጭቶችን መጀመር እና አገዛዙ ሊቆጣጠራቸው የማይችሉ የመረጃ ልውውጥ ዘዴዎችን በሥራ ላይ ማዋል ይገባናል። ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከመጠቀም አንስቶ ከሰው-ወደ-ሰው ወደሚተላለፍ ባህላዊ የመረጃ ቅብብሎሽ ድረስ ያሉትን አማራጮች በሙሉ ለመጠቀም ዝግጁዎች ነን። በደንብ ከታሰበበትና በሚገባ ከተደራጀን የመለስ አገዛዝን የመረጃ አፈና መበጣጠስ የሚቻልባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው።
  2. ፕሮፌሽናል ጋዜጠኞችን በማሰርና በማዋከብ የተፈጠረን ክፍተት በህዝባዊ ጋዜጠኝነት መሙላት ይኖርብናል። ከእንግዲህ እያንዳንዱ ዜጋ ራሱን እንደ ጋዜጠኛ መቁጠር ይኖርበታል። ዜጎች እጃቸው ውስጥ የገቡ መረጃዎችን ለእውነት ወደ ቆሙ የሚዲያ አካላት እና/ወይም ወደ ኢንተርኔት ብሎጎች፣ ዩ ቱብ፣ ፌስ ቡክ እና መሰል አውታሮች ወዲያውኑ የሚያስተላልፉበት መንገድ ሊመቻች ይገባል። ኢትዮጵያዊውን ወገናችንን ሁሉ ጋዜጠኛ ካደረግነው ከኛ የሚያመልጥ ዜና እንዳይኖር ማድረግ እንችላለን። አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን አቅም በፈቀደ መጠን የጋዜጠኛ መሠረታዊ መገልገያዎች – ለምሳሌ፡ እስክሪብቶና ወረቀት፣ ካሜራና የድምጽ መቀረጫ እንዲይዙ እናሳስባለን። በኪሳችን ይዘን የምንዞረው ተንቀሳቃሽ ስልካችንን ለድምጽና ምስል መቅረጫነት መገልገል ይኖርብናል። ምስሎችንና ድምፆችን ከተንቀሳቃሽ ስልካችን ወደ ኢንተርኔት ወይም ኢሜል ማስተላለፊያ ገመዶች ከኪሳችን መጥፋት የለባቸውም። መልዕክቶች ከተላለፉ በኋላ የስልካችንን ቀፎ የማጽዳት ልማድንም ማዳበር ይኖርብናል። ህዝባዊ ጋዜጠኝነት የራሱ ድክመቶች የሉትም ማለት አይደለም። ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት የሚፈለግባቸው በርካታ ጊዜዓት እንዳሉ ምንም ጥርጥር የለውም። በቅርቡ እንገባበታለን ለምለው ህዝባዊ አብዮት ግን ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት በህዝባዊ ጋዜጠኝነት ካልታገዘ ወቅቱ የሚፈልገውን አገልግሎት መስጠት አይችልም።

መለስ የሚዲያ አውታሮችን በመቆጣጠርና በማፈን፤ ጋዜጠኞችን በማዋከብ ኢትዮጵያን ከዓለም እይታ ሊያርቃት ቆርጦ ተነስቷል። እኛ ደግሞ መለስ ፈጽሞ ባላሰበውና ሊቆጣጠረው በማይችለው መንገድ መጥተንበታል። ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ የዜና አውታሮች ድረስ ያሉትን አማራጮችን እንጠቀማለን። ከአሁን ጀምሮ ነፃነት የጠማው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ጋዜጠኛ ነው። አንዳችም ነገር ከእይታና ከዘገባ አያመልጥም።

መሮናል!!! የመለስ ዜናዊ አፈና በጭራሽ አያቆመንም። “የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በቃ!” ብለናል።

በቃ!!! ጋዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጉደስ!!!