“ሶስተኛው ሪፐብሊክ” የቶሮንቶ ስብሰባና የኢትዮጵያ መጪው ዘመን (ክፍል አንድ)

ልጅ ተከሌ (ኦታዋ – ካናዳ)

ቦታው ኤድመንተን ውስጥ ነው። ስብሰባው የኦጋዴን ማህበረሰብ ስብሰባ። ተናጋሪው ኦባንግ ሜቶ። የምስራቅ ጫፍና የምእራብ ጫፍ ወግ። ሰሜንና ማእከሉ መነጋገርና መግባባት በተሳናቸው ግዜ፡ የምእራቡ ኢትዮጵያዊ የምስራቁን ኢትዮጵያ ሲያግባባውና ሲሸመግለው። “እኛ ኢትዮጵያዊያን” ብሎ ጀመረ ኦባንግ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ብሎ ሲጨርስ፡ በመካከል ግን አንዲት የኦጋዴን ሴት ተነሳችና “who the hell are you to tell me that I am an Ethiopian? I am not Ethiopian. You have to apologize for calling me an Ethiopian” አለችው። ወረደችበት። ወደ አራት መቶ የሚጠጉ የኦጋዴን ተወላጆችና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አዳራሹን ሞልተውታል። ኦባንግ አልደነገጠም። እንዲህ ያለውን ጥያቄና ፍጥጫ ለምዶታል።