ለትልቁ ዓሣ፣ ትንሽ መያዣ


አንዳንዴ ትልቅ ነገር እንመኛለን፣ እንሻለን፣ እናስሳለንም፡፡ ትልቅ ሀብት፣ ትልቅ ሥልጣን፣ ትልቅ ትዳር፣ ትልቅ ቤት፣ ትልቅ ዘመድ፣ ትልቅ ትምህርት፣ ትልቅ ሥራ፣ ትልቅ ቢሮ፣ ትልቅ ድርጅት፣ ከፍ ያለ እንጀራ፣ ከፍ ያለ ደመወዝ፣ ከፍ ያለ ጓደኛ፣ ከፍ ያለ ጸጋ እንመኛለን፡፡ መመኘቱ በራሱ አንድ ነገር ነው፡፡ የሀገሬ ሰው ‹ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ› ይላልና፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አፍርንጅ ሲጨምርበት ‹ጨረቃን ለመምታት ወርውር፣ እርሷን እንኳን ብትስት ከከዋክብቱ አንዷን ታገኛለህና› ይላል፡፡ አፍሪካዊ ወገኖቻችንም ‹ለንጉሥነት ብትጸልይ ቢያንስ ጭቃ ሹምነት አታጣም› ይላሉ፡፡
ቀጣዩና ዋናው ጥያቄ ግን የተመኘነውን ብናገኘው፣ ያሰብነውን ብንደርስበት፣ የፈለግነውን ብንጨብጠው፣ አያያዙን እንችልበታለን ወይ? ነው፡፡ ያገኘነውን ነገር ለማስተዳደር፣ ለመያዝና ለመከባከብ የሚያስችል ዐቅም አስቀድመን አከብተናል ወይ? ‹ሳያርሱ ዝናብ መመኘት ጎርፍ አምጣ ማለት ነው› የሚል አጎት ነበረኝ፡፡ ለምንመኘው ነገር የሚበቃ ዝግጁነት ከሌለ የሚመጣው ነገር በረከት ሳይሆን መርገም ይሆናል፡፡ ምሕረት ሳይሆን መዓት ያወርዳል፡፡ 

 እንዴው በትንሹ በሀገራችን ታላላቅ ቤት የገነቡና ታላላቅ አጥር ያጠሩ ሰዎችን ጠጋ ብላችሁ ብትጠይቋቸው ቤቱን ከመሥራቱ በላይ ቤቱን ማስተዳደሩ እንደሚከብዳቸው ታያላችሁ፡፡ አሥር ክፍል ቤት፣ ባለ ሦስት ፎቅ፣ አራት መኝታ ቤት፣ ሁለት የልጆች ክፍል የሚለውን እንጂ እነዚህን ሁሉ መኖርያ አድርጎ ለማስተዳደር ምን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ሀብትና የሰው ኃይል ያስፈልጋል? የሚለውን አንዳንዶቹ ቀድመው እንዳላሰቡበት መታዘብ ትችላላችሁ፡፡

ያለ ዕድሜ ጋብቻና ያለ ዕድሜ መውለድን ዓለም እየተቃወመው ያለው ማግባት ወይም መውለድ ክፉ ስለሆነ አይደለም፡፡ ነገር ግን ማግባትም መውለድም ኅሊናዊ፣ አካላዊ፣አእምሯዊና ማኅበራዊ ዝግጁነት ስለሚጠይቅ ነው፡፡ ያለበለዚያ ‹ልጂቱ ልጅ ወልዳ› የሚባለው ወይም ደግሞ
‹አንዲት ልጅ አግብቼ ነፍስ ያላወቀች
ስወጣ ስገባ አባባ እያለች›
የተባለው ነገር ይደርሳል፡፡ ሚስትነትና ባልነትን ያልተረዱ፣ ይህንንም ለመፈጸም የሚያስችል አካላዊ ብቃት የሌላቸው፣ ቤት ማስተዳደርን ከልምድ እንኳን ያላዩ፣ ወይም ለማየትና ለመማር በሚያስችል ዐቅም ላይ የሌሉ ሰዎችን ወደ ትዳር ማስገባት እንዲጠፉም እንዲያጠፉም መፍረድ ይሆናልና፡፡
ሕንዶች እንዲህ ይተርታሉ፡-
ሁለት ዓሣ አጥማጆች ዓሣ ሊያጠምዱ ወደ አንድ ወንዝ ወረዱ፡፡ አንደኛው ልምድ ያለው ሲሆን ሌላኛው ጀማሪ ነው፡፡ ልምድ ያለው ዓሣ አጥማጅ ዓሣውን ያጠምድና በትልቅ መያዣው ውስጥ ይከትተዋል፡፡ ብዙ ጊዜም ታላላቅ ዓሣዎችን ነው የሚያጠምደው፡፡ ጀማሪው አጥማጅም ያኛውን እያየ ማጥመጃውን ወደ ወንዙ ይወረውር ነበር፡፡ ትንንሽ ዓሣዎችን ሲይዝ ወደ ማጠራቀሚያው ያስገባቸው ነበር፡፡ ታላላቅ ዓሦችን ሲይዝ ግን መልሶ ወደ ወንዙ ይጨምራቸዋል፡፡ ይህንን እያየም ያ ልምድ ያለው ዓሣ አጥማጅ ይገርመው ነበር፡፡ ትልልቁን እየጣለ ትንንሹን ሲሰበስብ፡፡ ምናልባትም ባለማወቅ ይሆናል አለና፡-
‹ከትንንሹ ይልቅ ትልልቁ ዓሣ እንደሚጠቅምህ አታውቅም?› አለው፡፡
‹አውቃለሁ› ሲል መለሰለት፡፡
አሁን ይበልጥ ግራ ገባው፡፡
‹ታድያ ይህንን እያወቅክ ለምን ትልልቁን ዓሣ ስትይዝ መልሰህ ወደ ወንዙ ትከተዋለህ?› አለና ጠየቀው፡፡
‹የያዝኩት ዕቃ ትንንሽ ዓሣዎችን ብቻ የሚይዝ ነው፡፡ ለትልልቅ ዓሣ የሚሆን ዕቃ የለኝም፡፡ ለዚህ ነው የምመልሳቸው› አለው፡፡
አንዳንድ ሰው ምኞት ብቻ ነው ያለው፡፡ ምኞት ያለ ዝግጁነት፣ ያለ ሐኪም ምክር እንደሚወሰድ መድኃኒት ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል፡፡ ውጭ ሀገር ለመሄድ የሚመኝ እንጂ ውጭ ሀገር ቢሄድ ሊያደርገው የሚችለውን ለማወቅ፣ ልምድ ለመቅሰምና ለመጠየቅ የሚፈልግ ማን ነው፡፡ ገንዘብን የሚመኝ እንጂ ቢያገኘው እንዴት ሊያስተዳድረው እንደሚችል ዕውቀት ሸምቶ የሚጠብቅ ማን ነው፡፡ ከታች ሆኖ ላይኛውን ሥልጣን የሚመኝ እንጂ እዚያ ሲደርስ ሊመራበት የሚችለውን ዕውቀት፣ ዝግጁነትና ዐቅም የሚያካብት ማን ነው?
የሀገራችን ሰው ‹ዕብድ የያዘው መልክ አይበረክትም› ይላል፡፡ መልኩ ሳይሆን መልኩን ማን ነው ያዘው? ነው ወሳኙ ማለቱ ነው፡፡ ማግኘቱ ሳይሆን አያያዙ፡፡ መውለዱ ሳይሆን አስተዳደጉ፣ ሀብቱ ሳይሆን አስተዳደሩ፣ ሥልጣኑ ሳይሆን አመራሩ፡፡ ዝናው ሳይሆን አጠባበቁ፣ ዕድሉ ሳይሆን አጠቃቀሙ፡፡
በሀገራችን ታሪክ የሚያስቆጩ የሚባሉ እንደ ታላላቅ ዓሦች የሚቆጠሩ ዕድሎች አምልጠውናል፡፡ አንድነታችንን ይበልጥ ለማስተሣሠር፣ ከድህነት ለመውጣት፣ ልዩነቶቻችንን ለመፍታት፣ የኋላ ቁርሾዎቻችንን ለመፋቅ፣ የፖለቲካ ሂደታችንን ለማዘመን፣ አስተዳደራችንን ለማሠልጠን፣ ድንበራችንንና ክብራችንን ለመጠበቅ፣የሚያስችሉ ዕድሎች፡፡
እነዚህን ዕድሎች ሳንጠቀምባቸው የቀረነው ዕድለ ቢስ ስለሆንን አልነበረም፡፡ ዕድሎቹን ለመጠቀም የሚያስችል ብስለት፣ ጥበብ፣ ታጋሽነት፣ ዐቅም፣ ፖለቲካዊ ዝግጁነት፣ ሆደ ሰፊነት፣ ቆራጥነትና ለሀገር አሳቢነት ቀድመን ባለመያዛችን እንጂ፡፡ የያዝነው ዕቃ ትንሽ ያጋጠመን ዓሣ ግን ትልቅ ሆነና ማስቀመጫ አጣን፡፡ የነበረን አማራጭም ዕድሎቻችንን ሁሉ ወደመጡበት መወርወርና እንዳልመጡ ማድረግ ነበር፡፡
ያ ልምድ የሌለው ዐሣ አጥማጅ ሁለት አማራጮች ነበሩት፡፡ አንደኛው ለዕቃው የሚመጥን ዓሣ ማጥመድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለዓሣው የሚመጥን ዕቃ ማዘጋጀት፡፡ እርሱ ግን ለዕቃው የሚመጥን ዓሣ ማጥመድን መረጠ፡፡ ስለዚህም ከዕቃው በላይ የሆነ ዓሣ ሲያጋጥመው ወደ ወንዙ መመለስን መረጠ፡፡ ትልቁን ዓሣ ማጥመድ፣ ዕድልም ችሎታም ይጠይቃል፡፡ ትልቁን ዓሣ ማግኘት ለብዙ ጊዜ የሚያደክመውን ተግባር በአንድ ጊዜ ለማድረግ መቻል ነው፡፡ ከብዙ ዓሦች የሚገኘውን ገቢ ከአንድ ዓሣ ማግኘት ነው፡፡ ለሌላ ዕድል በር የሚከፍት ገንዘብ በአንድ ጊዜ መዛቅ ነው፡፡ ግን ማስቀመጫው ከሌለ ምን ዋጋ አለው?
ሳንጠቀምባቸው ያመለጡንን ዕድሎች ብንገመግማቸው አንዱ ምክንያት ይህ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለ ዕድሉ እንጂ ስለ ዕድሉ አያያዝ ያቀረብነው ወይም የያዝነው ነገር ባለመኖሩ፡፡ ዕድሎች መቼም ቢሆን ይኖራሉ፡፡ ትናንትም፣፣አሁንም፣ ነገም አሉ፡፡ ዕድለኛ ያልሆነ ሰውም የለም፡፡ የዕድሎቻችን ዓይነቶች ይለያያሉ እንጂ፡፡ ዕድል በደጁ የማታልፍለት ሰው የለም፤ ነገር ግን ዕድሎችን ለመጠቀም ዝግጁነታችን ይለያያል እንጂ፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ዕድል የለም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ መጥፎ ዕድል ማለት ያለ ዝግጁነት የተገኘ ዕድል ማለት ነው ይላሉ፡፡
ለፖሊሲዎች የሚሆኑ ሰዎችን ማምጣትና ለሰዎች ዐቅም የሚሆኑ ፖሊሲዎችን መንደፍ ይለያያሉ፤ ለመዋቅር የሚሆኑ ሰዎችን ማምጣትና ለሰዎች የሚሆን መዋቅር መቅረጽ ይለያያሉ፡፡ ታላላቅ ሃሳቦችን አምጥቶ ታላላቅ ሃሳቦችን ሊይዙና ሊተገብሩ የሚችሉ ዐቅም ያለቸው ሰዎችን ከማምጣት ይልቅ ለታናናሽ ሰዎች የሚመጥኑ ሃሳቦችን የምናጠምድበት ጊዜ አለ፡፡ ምክንያታችን ደግሞ የያዝነው ዕቃ ትንሽ መሆኑ ነው፡፡ እኛም ለዓሣው የሚመጥን ዕቃ ከማምጣት ይልቅ ለዕቃው የሚመጥን ዓሣ መጥመድ ስለምንፈልግ፡፡
ሰውን እናትና አባቱ አንድ ጊዜ ይወልዱታል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ራሱን ለአዳዲስ ዕድሎች መውለድ የራሱ ድርሻ ነው፡፡ አንዲት ሴት ለመውለድ ዘጠኝ ወር ሙሉ ትዘጋጃለች፡፡ በሂደት ልጁ ልጅ ይሆናል፡፡ እርሷም እናት፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በውስጧ ብዙ ኩነቶች ይከናወናሉ፡፡ እርሷንም ልጇንም የሚለውጡ፡፡ የተፈጥሮ ሂደት ሲያበቃም ልጁም ልጅ ሆኖ ይወለዳል፣ እርሷም ወልዳ እናት ትሆናለች፡፡
ራስን ለተሻለ ዕድል መውለድም እንዲሁ ነው፡፡ መፈለግ ብቻውን ዋጋ የለውም፤ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት መጣጣር፣ ብናገኘው ለሚያስፈልጉን ነገሮች መዘጋጀት፣ ለማስተዳደር የሚሆን ዐቅምንም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቀድመው ሳይደረጉ የሚመጡ ታላላቅ ዕድሎች እያዘንን የምንጥላቸው ታላላቅ ዓሣዎች ነው የሚሆኑት፡፡
ሴትዮዋ ለጸሎት በቆመች ቁጥር ትልቅ ሀብት ስጠኝ እያለች ትለምን ነበር፡፡ ከብዙ ልመናዋ በኋላም አንድ ሀብታም ሰው አገባችና ሀብት ላይ ወደቀች፡፡ ያገባችውም ሰው ብዙም ሳይቆይ ዐረፈና ያንን ሁሉ ሀብት እርሷ ወረሰችው፡፡ በቤቱ ውስጥ ብዙ አገልጋዮች፣ ብዙ ከብቶች፣ ብዙ አጋስሶች ነበሩ፡፡ በየቦታው አያሌ ገባሮች፣ አራጣ ተበዳሪዎች፣ ጉልተኞችና ከብት አርቢዎችም ነበሩ፡፡ በየጊዜው ሙግትና ጭቅጭቅ አያጣውም፡፡ ከአስገባሪዎችና ከገባሪዎች ጋር ክርክር አለው፡፡
ይህንን ሁሉ ውጣ ውረድ በየጊዜው እያለፈች መሄድ ሰለቻትና ወደረሳችው ፈጣሪዋ ተመለሰች፡፡ ‹‹ምነው አምላኬ እንዲህ ያለው ጣጣ ውስጥ ከተትከኝ፤ እንዴት እንዲህ ያለ የመከራ እንጀራ ውስጥ ትጥለኛለህ› እያለች ታማርር ነበር፡፡ አንድ ቀን ፈጣሪዋ ተገለጠና፡፡
‹ለምን ታማርሪኛለሽ›  አለና ጠየቃት፡፡
እርሷም ‹ ለምን አላማርርህም፤ እንዲህ ያለ ወጥመድ ውስጥ ስትከተኝ፣ አንዱን ስፈታው ሌላ ይመጣል፤ አንዱን ስጨርስ ሌላ ይተካል› አለችው፡፡
‹ያኔ የለመንሽኝን ልመና ታስታውሽዋለሽ‹ አላት
‹አዎ፣ ሀብት ስጠኝ ብዬ ለምኜሃለሁ› አለችው፡፡
‹ታድያ ሀብት እንጂ ጥበብ መቼ ለምነሽኛል፡፡ እንቺኮ የለመንሽውን አላጣሽም፤ የለመንሽውን የምታስተዳድሪበት እንጂ› አላት፡፡
‹አየሽ ገንዘብ ማግኘትና ባዕለ ጸጋ መሆን ይለያያል፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ሥራ እና ዕድል ብቻ ይበቃሉ፡፡ ገንዘብን ለማስተዳደር ግን ዕውቀትና ችሎታ ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብ ያገኙ ሁሉ ባዕለ ጸጋዎች አይሆኑም፡፡ ባዕለጸጋዎች ገንዘባቸውን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ማስተዳደርም የሚያውቁ ናቸው፡፡ መልክ ያላቸው ብዙዎች ናቸው፣ መልካቸውን ማስተዳደር የሚችሉ ግን ጥቂቶች፤ ሥልጣን ያላቸው ብዙዎች ናቸው፣ ሥልጣናቸውን ማስተዳደር የሚችሉ ግን ጥቂቶች፤ ዝና ያላቸው ብዙዎች ናቸው፣ ዝናቸውን ማስተዳደር የሚችሉ ግን ጥቂቶች፤ ቤት ያላቸው ብዙዎች ናቸው፣ ቤታቸውን ማስተዳደር የሚችሉ ግን ትቂቶች፤ ትዳር ያላቸው ብዙዎች ናቸው፣ ትዳራቸውን ማስተዳደር የሚችሉ ግን ጥቂቶች፤ ዕውቀት ያላቸው ብዙዎች ናቸው፣ ዕውቀታቸውን ማስተዳደር የሚችሉ ግን ጥቂቶች፡፡ ያገኙትን ነገር ለመጠቀምና ለማስተዳደር የሚያስችል ዐቅም ከሌለ፣ አንድን ነገር ማግኘት ብቻ ታላቅ ነገር አይደለም፡፡› አላት፡፡
እኛም ይህንን ሰምተን ‹ይህች ጥፊ ለአርሳኒ ናት› አልን፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በተመሳሳይ ሚዲያ መጠቀም አይፈቀድም