ደቂቀ ሰይጣን
ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ (1426-1460ዓ ም) በዘመናቸው አምልኮ ጣዖትን አስቆማለሁ ብለው ቆርጠው ተነሥተው ነበር፡፡ ይህንን ነገር ለማስቆምም ሦስት ዓይነት መንገድ ለመጠቀም አሰቡ፡፡ መምህራንን እየላኩ ሕዝቡን ለማስተማር፣ ለማስተማርያ የሚሆኑ ድርሰቶችን እንዲዘጋጁ ለማድረግና ራሳቸውም ለማዘጋጀት፣ በመጨረሻ ደግሞ ከዚህ ሁሉ የተሻገረውን ለመቅጣት፡፡
በተለይም በአምልኮ ጣዖት የተያዙትን፣ ይህንንም አምልኮ ከሕዝቡ ገንዘብ ለመሰብሰብና ሕዝቡን ለማታለል ሲሉ የሚያካሂዱትን ሰዎች የሚከታተሉ፤ ባለሥልጣናቱ በድብቅ ይህንን ተግባር ሲያከናውኑ፣ አንዳንድ ካህናትም ከሁለቱም ወገን ሆነው ሲያጭበረብሩ፣ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችም በዚህ ባዕድ አምልኮ ውስጥ ሲነከሩ እየተከታተሉ ለንጉሡ መረጃ የሚሰጡ ሦስት ሰዎችን መድበው ነበር፡፡
ዘርዐ ክርስቶስ፣ ተዐውቀ ብርሃንና ገብረ ክርስቶስ የሚባሉት እነዚህ ሦስት ሰዎች ወደ ባዕድ አምልኮ የሚሄዱትን፣ በድብቅ ይህንን ተግባር የሚያከናውኑትን፣ በተለይም የቤተ መንግሥት ሰዎች ሆነው ለሕዝቡ የባዕድ አምልኮ ክፉ አርአያ የሚሆኑትን እንዲጠቁሙ፣ ተከታትለውም እንዲያሲዙ፣ አስይዘውም እንዲያስቀጡ ንጉሡ ሥልጣን ሰጥተዋቸው ነበር፡፡
በዚህም መሠረት እነዚህ ሦስት ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ፤ ከባዕድ አምላኪዎች ጋር ባዕድ አምላኪ እየመሰሉ፣ ከሕዝቡም ወሬ እየሰበሰቡ፣ ያዩትንና የሰሙትን ለንጉሡ በማቅረብ በባዕድ አምልኮ የተጠመዱ ሰዎችን እንዲቀጡ ያደርጉ ጀመር፡፡ በመጀመርያው አካባቢ ለኅሊናቸውና ለፈጣሪያቸው ታማኝ በመሆን በትክክልም ተመክረውና ተዘክረው አልመለስ ያሉትን፣ በአምልኮ ባዕድ ፍቅር ልባቸው የነደደውን፣ ለሕዝቡ ክፉ አርአያ የሆኑትን፣ ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግና ማን ይናገረናል ብለው ይህንን ተግባር የሚፈጽሙትን እየጠቆሙ ያስቀጡ ነበር፡፡
እየቆዩ ግን ግእዛቸው ተለወጠ፡፡ ይህንን ሥልጣናቸውን የጉቦ መቀበያ፣ የመደለያ መብያ፣ የሙክት መዋዋያ፣ የዝምድና መመሥረቻ፣ የሀብት ማከማቻ፣ የቂም መወጫ፣ የጠላት መቅጫ እያደረጉት መጡ፡፡ ጉቦ አልሰጥ ያሏቸውን ያላጠፉትን አጠፉ ብለው ይከሷቸዋል፤ እስከ ሞትም ያስፈርዱባቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በሌላ ነገር የተጣሏቸውን አምልኮ ባዕድ ሲፈጽሙ አገኘናቸው ብለው ለንጉሡ አሳልፈው ይሰጧቸዋል፡፡ የገዛ ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው የሚፈጽሙትን ክፉ ሥራ ሁሉ እየሸፈኑ አይተው እንዳላዩ ያልፏቸዋል፡፡ እነርሱ አንድ መንደር ሲደርሱ ሙክት ያላረደ፣ የከረመ የጠጅ ጋኑን ያልከፈተ፣ ምንጣፍ ያላነጠፈ፣ እግር ያላጠበ ሁሉ ዓይን ይጉረጠረጥበታል፣ ጣት ይቀሰርበታል፡፡
ሕዝቡ በእነዚህ ሦስት ሰዎች ግፍና ጭካኔ ሲማረር ስማቸውን ‹‹ደቂቀ ሰይጣን- የሰይጣን ልጆች›› ብሎ አወጣላቸው፡፡ ሕዝቡ እነዚህን ሦስት ሰዎች ‹ደቂቀ ሰይጣን› ያላቸው ስለ አራት ነገር ነበር፡፡ በአንድ በኩል ጥቂት እውነት ይዘው ብዙ ሐሰት ስለሚጨምሩበት ነው፡፡ ሰይጣን ጥቂት እውነት ይኖረዋል፡፡ ሔዋንን ‹‹የሰማይና የምድር ንግሥት›› ሲላት የተናገረው በከፊል እውነት ነበር፡፡ ‹‹የምድር ንግሥት›› መሆኗ እውነት ነው፡፡ ‹የሰማይ ንግሥት› ግን አልነበረችም፡፡ እነዚህም ሰዎች ጥቂት የሚመስል እውነት ይይዙና የቀረውን ነገር እነርሱ እጅን እግር፣ አንገትና ደረት፣ ጀርባና ፊት ሞልተውበት ያቀርቡታል፡፡ ነገር ዐዋቂዎች፣ ወግ አሣማሪዎች ስለነበሩ የሰማ ሁሉ ያምናቸዋል፡፡
ሁለተኛ ደግሞ እውነትን መደራደርያ ስለሚያደርጓት ነው፡፡ አንድ ሰው የተባለውን ጥፋት ሲፈጽም ካዩት ወንጀሉ ወይም ጥፋቱ አይታያቸውም፡፡ ይህንን የሰውዬውን ጥፋትና ወንጀል እንደ መደራደርያ በመጠቀም ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅም እንጂ፡፡ ሰውዬው የተባለውን ካደረገ፣ የታዘዘውን ከፈጸመ፣ የሚገባውን ከሰጠ የከፋውን ወንጀል ቢፈጽም እንኳን የታየው እንዳልታየ፣ የተሰማው እንዳልተሰማ፣ የተፈጸመውም እንዳልተፈጸመ ይታለፍለታል፡፡ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነ ግን ከሆነው በላይ እንዳደረገ ተቆጥሮ፣ ስሙ ጠፍቶ፣ ግብሩ ከፍቶ፣ ቀንድና ጅራት ተጨምሮለት ለጥብስ ይቀርባል፡፡ የሚጠይቁት ጉቦና ለሰጭ አስቸጋሪ በመሆኑም የተነሣ ሕዝቡ
እነዚያው መጡልህ ደቂቀ ሰይጣን
ጠጅ በገበታ ሥጋውን በጋን
እያለ ይዘፍን ነበር፡፡
ሦስተኛው ደግሞ ሥልጣናቸውን የቂማቸው መወጫ ማድረጋቸው ነው፡፡ ከዚህ በፊት በርስትም በሚስትም፣ በከብትም በዶሮም የተጣላቸውን፤ ይቀናቀነናል ይገዳደረናል የሚሉትን፤ ይንቀናል ያቃልለናል ብለው የሚገምቱትን ሁሉ የፈጠራ ክስ እያዘጋጁ፣ ያንንም እያሣመሩና እየቀባቡ ያቀርቡ፣ አቅርበውም ያስቀጡ ነበር፡፡ ‹ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል› እንዲሉ ባለ ጊዜዎች ነበሩና ጣል ያሉት ይጣላል፣ እሠር ያሉት ይታሠራል፣ ግደል ያሉት ይገደላል፡፡
አራተኛውና ‹‹ጉንዳንን ዝም ካሉት አናት ላይ ይወጣል›› እንደተባለው ሕዝቡን ሁሉ ያስገረሙት የንጉሡን ልጆች፣ ሚስቶችና ወንድምና እኅቶችን ጭምር እየከሰሱና እያሳጡ ግምሾችን ማስገደላቸው፣ ከፊሎችንም ማሣሠራቸው ነበር፡፡ ያን ጊዜ በእነዚህ ‹‹ደቂቀ ሰይጣን›› ውንጀላ ከታሠሩት መካከል ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በኋላ የነገሡት የንጉሡ ልጅ በዕደ ማርያምም ይገኙበት ነበር፡፡
የእነዚህ የደቂቀ ሰይጣን ግፋቸው በየቀኑ እየጨመረ፤ በትራቸው እየጠነከረ ሲሄድ ሕዝቡ አቤቱታውን ለንጉሡም ለእግዚአብሔርም ማቅረብ ጀመረ፡፡ በመጀመርያው አካባቢ ንጉሡ ሊሰሙት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ‹‹አንድ ሰይጣን የያዘው ሰው ሲጠመቅ ጎረቤቱ ሁሉ ይለፈልፋል›› እንደሚባለው ሕዝቡ ከጥፋቱ ይልቅ ቅጣቱን ተጠይፎ ስለመሰላቸው ቸል ብለውት ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ከበደ ሚካኤል
አይጥ ስትጠግብ ስታበዛ ሩጫ
ሄዳ ታሸታለች የድመት አፍንጫ
እንዳሉት፤ ወይም ደግሞ የታክሲ ጥቅስ ጸሐፊው ብሩክ ‹‹ሟች ከመሞቱ በፊት ይንቀዠቀዥ ነበር›› እንዳለው ነገሩ ከቤተ መንግሥቱ ባለሟሎችም አልፎ ወደ ራሳቸው ወደ ንጉሡም መጣ፡፡ እነዚህ ሰዎች የልብ ልብ ተሰማቸውና ራሳቸው ንጉሡን በየሄዱበት መክሰስና ማማት፣ አምተውም ማሳማት ጀመሩ፡፡ ከየት መጣ የማይባል ሀብትና ከብት፣ ማርና ወተት እያትረፈረፋቸው ይታይ ጀመር፡፡ ‹የማያድግ ልጅ አራስ ቤት እያለ ዳንኪራ ይመታል› እንዲሉ ቀድሞም ያለ ዐቅማቸው የያዙትን ሀብት አላውቅበት ብለው ሥራቸው ሁሉ አሥረሽ ምችው ሆነ፡፡
ሁኔታው ያሠጋቸው ንጉሥ ነገሩን ማስተዋል ጀመሩ፡፡ በዚህ ወንጀል ከታሠሩት፣ ተይዘውም ከተገደሉት ብዙዎቹ ያለወንጀላቸውና ያለ ጥፋታቸው መሆኑን፤ አንዳንዶቹም ለዚያ የሚያበቃ ጥፋት አለመሥራታቸውን እየተረዱት መጡ፡፡ ዘርዐ ጽዮን ያንን በግፍ የሰበሰበውን ሀብትና ንብረት ጥሎ፣ ልጅና ሚስቱን በትኖ ግዞት ተላከ፡፡ በተላከበት ግዞትም በዚያው ሞቶ
አዙረህ አዙረህ ሀገሬ መልሰኝ
በሹም የታዘዘ አፈር አታልብሰኝ
የተባለው ምኞት ሳይደርስልት በማያውቀው ሀገር ተቀበረ፡፡ ተዐውቀ ብርሃንም ‹‹የሞኝን ጓደኛ ዘንዶ በጅራቱ ሲይዘው እርሱ በአናቱ በኩል ይመጣል›› እንደተባለው ከዘርዐ ጽዮን መማር አቅቶት በግፍ ላይ ግፍ ሲጨምር ተይዞ ግዞት ተላከና በዚያው እንደ ባልንጀራው ሞቶ ቀረ፡፡ ከሁሉም የተረፈውና የመማርም የመታረምም ዕድል የነበረው ገብረ ክርስቶስ ነበር፡፡ ‹የሚያድግ ልጅ አይቀየምህ፣ የሚሞት ሽማግሌ አይርገምህ› ይባላልና እርሱ ባለ ጊዜ በነበረ ሰዓት ያለ ስሙ ስም ሰጥቶ ያለ ግበሩ ግብር አውጥቶ ያሳሠረው በእደ ማርያም በአባቱ በዘርዐ ያዕቆብ ምትክ በ1468 ዓም ሲነግሥ ቀጥቅጦ ገደለውና መጨረሻው ሳያምር ቀረ፡፡
ሦስቱ ደቂቀ ሰይጣን ተግዘውና ተቀጥቅጠው ቢሞቱም በግብር አኽለው፣ በግእዝ አስመስለው የወለዷቸው ልጆቻቸው ግን ብዙዎች ናቸው፡፡ ሥልጣናቸውን ለራሳቸው መጠቀሚያ፣ የጠሏቸውን ለመበቀያ፣ ለጉቦና መደለያ መቀበያ፣ ለወዳጆቻቸው መጠቃቀሚያ የሚያደርጉ፤ ተሰሚነታቸውንና ቀራቢነታቸውን ተጠቅመው ወንጀለኛውን ንጹሕ፣ ንጹሑን ወንጀለኛ የሚያደርጉ፤ እንዲህ እናደርግሃለን፣ እንዲህ እናስደርግሃለን፣ ከንጉሥ እናጣላሃለን፣ ከክብር እናሳንስሃለን እያሉ ሲያስፈራሩ የሚውሉ አያሌ ልጆች ዛሬም አሏቸው፡፡
እንደ ወላጆቻቸው እንደ ሦስቱ ደቂቀ ሰይጣን ጊዜያቸው አልቆ በቆፈሩት ጉድጓድ እስኪገቡ፣ ‹በመረጥሽው ዳኛ ትረች፣ በቆረጥሽው ዱላ ትመች› ነውና ባሠሩት ማሠርያ እስኪታሠሩ፣ ባወጡት መመርያ እስኪቀጡ፣ ባስፈረዱበት ፍርድ እስኪፈረድባቸው ድረስ፣ ‹ደረቴ ይቅላ፣ ሆዴ ይሙላ› ብለው የሚዘባነኑ፤ የማይነካውን ነክተው ኤሌክትሪክ እስኪይዛቸው ድረስ አርድ አንቀጥቅጥ እንደለበሰ የኦሪት ካህን በየሄዱበት ሲያርዱ ሲያንቀጠቅጡ የሚውሉ፤ ዛሬ ትናንት፣ ነገም ዛሬ የሚሆን የማይመስላቸው ደቂቀ ሰይጣን ዛሬም አሉ፡፡ ‹የሰው ልጅ ታሪክ የሚመሰክረው ሰው ከታሪክ አለመማሩን ነው› እንደሚባለው ከትናንቱ ደቂቀ ሰይጣን ያልተማሩ ተረፈ ደቂቀ ሰይጣን ዛሬም አሉ፡፡
ደቂቀ ሰይጣን ስማቸው ማራኪ ነበር፡፡ ዘርዐ ጽዮን ማለት ‹የጽዮን ዘር፣ ልጅ› ማለት ነው፤ ተዐውቀ ብርሃን ማለት ‹ብርሃን ተገለጠ፣ ታወቀ› ማለት ነው፤ ገብረ ክርስቶስ ማለትም ‹የክርስቶስ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ ግብራቸውና ስማቸው ግን ፈጽሞ የሚገናኝ አልነበረም፡፡ ዛሬም እንደ ደቂቀ ሰይጣን ማራኪና አጓጊ የሆኑትን የማዕረግና የሥልጣን ስሞች ይዘው ግብራቸው ግን የሰይጣን የሆኑትን አንዳንድ ኃላፊዎች፣ ባለ ሥልጣናት፣ ባለሞያዎች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ አሳላፊዎች፣ መኮንኖችና ባለሟሎች እኛም
አትዋል ይዋሉብህ አትምከር ይምከሩ
በቆፈሩት ጉድጓድ ሳይገቡም አይቀሩ
ብለን ልናሳፍራቸው ልናሸማቅቃቸው፤ ብሎም ለሰው የሚያቀምሷትን ጽዋ ጎንጨት እንዲሏት ልናደርጋቸው ይገባል፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ስለሆነ በተመሳሳይ ሚዲያ ማቅረብ ክልክል ነው