አባ ፊልጶስን ፍለጋ (ክፍል ሦስት)
|
አዲሱ የዓባይ ድልድይ
|
ኅዳር 24 ቀን ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት ከአዲስ አበባ ተነሥተን ጉዟችንን ወደ ሰሜን ምዕራብ አደረግን፡፡ ድንበሩ ሰጠ መኪናውን እያገላበጠ፣ እኔ ከጎኑ ተቀምጬ፣ ኤልያስና ቀለመወርቅ ከኋላ ሆነው በጫንጮ በኩል ወጣን፡፡ በዘመነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶባቸው ከነበሩት ቦታዎች አንዷ የሆነችውን፣ ታቦቷም በዘመነ ሱስንዮስ ወደ ጎንደር ሔዶ በዘመነ ምኒሊክ የተመለሰውን፣ ታሪኳም ‹ዜና ፍልሰታ ወምጽአታ ለታቦተ ማርያም› በሚለው ጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴና አዞዞ ተክለ ሃይማኖት በሚገኘው መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈላትን ደብረ ጽጌን ተሳልመን፤ የብዙ ቅዱሳን መፍለቂያ የሆነውን አስቀድሞ ደብረ አስቦ፣ በኋላም በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ1437 ዓም በድላይ ከሚባለው የአዳል ገዥ ጋር ተዋግተው ድል ካደረጉ በኋላ በጸሎት የተራዷቸውን የደብረ አስቦ መነኮሳት አመስግነው፣ ለገዳሙም ርስት ሰጥተው በዚሁ ዓመት ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› ሲሉ የሰየሙትን ገዳም እንዲሁ በሩቁ እየተሳለምን ወረድን፡፡
የፍቅር እስከ መቃብሮቹ በዛብህና ሰብለ ወንጌል የተቀበሩባትን ጎሐ ጽዮን ማርያምን አልፈን የዓባይን በረሃ ቁልቁል ተያያዝነው፡፡ ምንም እንኳን ጃፓኖች መንገዱን እንደገና ቢሠሩትም የዓባይ በረሃ ግን ለጃፓንም የሚመለስ አይመስልም፡፡ ጋራው አሁንም ድንጋይ ያወርዳል፡፡ መንገዱ ይገመሳል፡፡ አንዳንዴም ተጠባብቆ መተላለፍ ግዴታ ይሆናል፡፡
አስደናቂውን የዓባይን ድልድይ አልፈን ሽቅብ ወደ ደጀን አመራን፡፡ ደጀን እምብዛም አልተለወጠችም፡፡ በርግጥ አንዳንድ ፋብሪካዎች ወደ አካባቢው በመምጣታቸው ሽር ጉድ የምትል ከተማ ትመስላለች፡፡ ዕድገቷና ታሪኳ ግን አይመጣጠንም፡፡ አሁንም ከወዲህም ከወዲያም ለሚመጡ መንገደኞች የምሳና ቁርስ መመገቢያነቷን ግን አልተወችም፡፡
|
የታደለች ፓሪስ፣ በሞጣ መንገድ ላይ በስሟ የሚጠራ የገጠር ሻሂ ቤት አላት
|
ትዝ የሚለኝ አንድ ጊዜ ወደ ሰሜን ስናመራ እዚህ ምግብ ልንበላ እንወርዳለን፡፡ አራት ሆንና አንድ ምግብ ቤት ገባን፡፡ ምግብ ቤቱ አንዲት እናት ራሳቸው ሠርተው የሚሸጡበት ዓይነት ነው፡፡ አስተናጋጇ ደግሞ ልጃቸው ናት፡፡ አራታችን አራት ዓይነት ምግብ አዘዝን፡፡ ልጃቸው ልትነግራቸው ገባች፡፡ እኒያ እናት ወገባቸውን በመቀነት ታጥቀው መጡ፡፡ ‹‹እናንተ ናችሁ አሁን ምግብ ያዘዛችሁት?›› አሉን፡፡ እኛም መለስን፡፡ ‹‹በሉ ልጆቼ ለአራታችሁ አራት ዓይነት ምግብ መሥራት አልችልም፤ ተስማምታችሁ አንድ ምግብ እዘዙ›› አሉን፡፡ ስቀን አንዱን አዘዝን፡፡
|
ወደ ኣባያ በረሃ መውረጃ
|
መጣ ምግቡ፡፡ መቼም ጣዕሙ እስካሁን በዓይኔም በአፌም ይሄዳል፡፡ ለቤታቸው የሠሩትን መሆን አለበት የሰጡን፡፡ ለነገሩ የአሁኑን አላውቅም እንጂ የደጀን ምግብ መልካም ነበር፡፡ በተለይ እንጀራቸው ከትሪው ይበልጥ ነበር፡፡ በመካከሉ እንጀራው እያለ ወጡ አለቀ፡፡ አንድ ጊዜ ጨመሩልን፡፡ ግን አሁንም እንጀራው ንክች አላለም፡፡ ልጃቸውን የወጥ ጭማሪ ጠየቅናት፡፡ እርሷም ልትነግራቸው ገባች፡፡ ወገባቸውን በመቀነት እንደታጠቁ መጡ፡፡ ጎንበስ አሉና በአምስቱ ጣታቸው እንጀራውን እያነኮቱ፡፡ ‹‹እንዴ ይሄማ የነካካ እኮ ነው፤ ብሉ፡፡›› እያሉ ፈተፈቱት፡፡ በሳቅ ፈርሰን ምግቡን ሳንበላው አትርፈነው ወጣን፡፡
| የበላይ ዘለቀ ሐውልት (ብቸና) |
የደብረ ማርቆስን መንገድ ትተን ወደ ሞጣ መንገድ ታጠፍን፡፡ የበላይ ዘለቀን ሀገር ብቸናን አገኘናት፡፡ በመሐል ከተማው ላይ በበላይ ስም አደባባይ ተሠርቷል፡፡ በላይም በልጅጉን እንደያዘ ምስሉ ይታያል፡፡ እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን ያፈራውንና በፍቅር እስከ መቃብር ላይ የፊታውራሪ አሰጌንና የፊታውራሪ መሸሻን ጦርነት ለማስቀረት ካህናቱ ከዲማ ጊዮርጊስ ጋር ይዘውት የወጡትን ብቸና ጊዮርጊስን ለማየት ከከተማው ወጣን፡፡ አንድ አምስት ኪሎ ሜትር እንደ ተጓዝን ግን መንገዱ ለሁለት ተቆርሶ ታርሶ አገኘነው፡፡ እንዲያውም ከመካከላችን አንዱ ፊታውራሪ መሸሻ ወደ ዲማ ሄደው የዲማ ጊዮርጊስ ቅጽር ጸጥ ብሎ ባገኙት ጊዜ ያሉትን እያስታወሰን ወደ መንገዳችን ተመለስን፡፡
| የዲማ ጊዮርጊስ መገንጠያ |
የአቡነ ተከስተ ብርሃንን፣ የአቡነ ተክለ አልፋንና የአቡነ ቶማስን በኣት ዲማ ጊዮርጊስን እያለፍን ነው፡፡ በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት (1374-1406ዓም) የተተከለው ዲማ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበሩት አቡነ ተከስተ ብርሃንና በንጉሥ ልብነ ድንግል(1501-1533 ዓም) ዘመን የነበሩት፣ በፊትም በኋላም የማየት ሥልጣን የተሰጣቸው አቡነ ተክለ አልፋ የጸለዩበትና ያስተማሩበት ታላቅ ገዳም ነው፡፡ አንዱ ባለ ቅኔ እንዲያውም ‹ተክለ አልፋ በሰዶምና በገሞራ ጊዜ ቢኖሩ ኖሮ አይተርፉም ነበር›› ብሎ ተቀኝቷል፡፡ ለምን ይመስላችኋል፡፡ ‹‹እስኪ ተወያዩበት›› አለ የሦስተኛ ክፍል የአማርኛ መጽሐፍ፡፡
|
የደብረ ወርቅ ማርያም መግቢያ በር
|
ዲማን አልፈን ከዘመነ ኦሪት እስከ ዘመነ ወንጌል ታላላቅ ሥራዎች የተሠሩባትን ደብረ ወርቅ ማርያምን አየናት፡፡ በደብረ ወርቅ ውስጥ ‹ወይኒቱ› የምትባለውና ቅዱስ ሉቃስ እንደሳላት የሚነገረው የእመቤታችን ሥዕል፣ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በድላይን ድል ካደረጉ በኋላ የማረኩት የበድላይ የብረት ልብስ፣ የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ የወርቅ ዘውድ፣ ደጉ ዮሐንስ የሰጧቸው ስንክሳሮች፣ ዐፄ እስክንድ(1471-87) የሰጡት ባለ ሥዕል ብራና፣ በገዳሙ ታላቅ ተጋድሎ ያደረጉት የቅዱስ አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ መስቀል፣ የዐፄ እስክንድር ልጅ እቴጌ ማርታ የሰጡት አርባዕቱ ወንጌል፣ ንግሥት ዘውዲቱ የሰጡት ባለ ወርቅ ጉብጉባት ካባ፣ ራስ መኮንን የሰጡት የመጾር መስቀል እና ሌሎችም በሙዝየሙ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ዐፄ እስክንድርም የተቀበሩት እዚህ በመሆኑ መቃብራቸው አሁንም ይታያል፡፡
|
ደብረ ወርቅ ማርያም
|
ደብረ ወርቅን ለቅቀን ተገነጠልንና ወሎንና ጎጃምን እንዲያገናኝ አዲስ በተሠራው መንገድ ወደ መርጡለ ማርያም አመራን፡፡
| የዐፄ እስክንድር መቃብር |
ታሪኳን ከኦሪት ጀምራ፣ ከታቦተ ጽዮን ጋር ተሣሥራ፣ በእቴጌ ሰብለ ወንጌል ታላቅ የሕንፃ ጥበብን አስመስክራ፣ ከግራኝ የተረፈ ቅርሷን እስከ ዛሬ የምታስጎበኝ ናት መርጡለ ማርያም፡፡ የግራኝም ካባ ያለው እዚያ ነው፡፡
|
መርጡለ ማርያም
|
እጅግ የገረመኝ ነገር ግን የመርጡለ ማርያምን ቅርሶች በሚገባ የያዘው ሙዝየም ሲሠራ ታላቁን አስተዋጽዖ በኅዳር 1983 ያደረጉት ባለፈው ሥርዓት የግብርና ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ገረመው ደበሌ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ነገር በዚያ ዘመን ስለነበሩት ባለ ሥልጣናትና እምነታቸው የነበረኝን ሃሳብ የሞገተ ነው፡፡ የመርጡለ ማርያምም ካህናት እስከዛሬ ስማቸውን በጠዋትና በማታ ያነሡታል፡፡
አዳራችን ሞጣ ላይ ሆነ፡፡
ሞጣ ቀራንዮ ምነው አይታረስ
በሬሳላይ መጣሁ ከዚያ እስከዚህ ድረስ
ተብሎ የተገጠመውን እያስታወስን ሞጣ ላይ አደርን፡፡ በማለዳ ከሞጣ ተነሥተን የአባያን በረሃ ተያያዝነው፡፡
ባሕርዳር ተነሥተው ሞጣ እስከሚደርሱ
ዐሥር ወንዞች አሉ ሕዝብን የጨረሱ
ብለው ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ነበር የሞጣ ባሕርዳር መንገድ ባለፈው መንግሥት ጊዜ የተሠራው፡፡ መንገዱ ወይ ጥገና አይጎበኘውም ወይም ጥገና አይበቃውም፡፡ እኛ ያጠፋነው በዚህ መንገድ ላይ ስንሄድ ንስሐችንን ጨርሰን አለመምጣታችን ነው፡፡ ባሕርዳር የደረስነው በስግደትና አስተብርኮ ነው፡፡ የብዙ ሊቃውንት ማፍሪያ የሆነውን አዴት መድኃኔዓለምን ተሳልመን በደብረ መዊዕ በኩል ገሠገሥን፡፡
ደብረ መዊዕ ማርያም የተተከለችው በ16ኛው መክዘ ነው፡፡ ንጉሥ ሱስንዮስ ወደ ካቶሊክ እምነት በገቡ ጊዜ በደብረ መዊዕ ታላቅ የሊቃውንት ጉባኤ ተደርጎ ነበር፡፡ እነ አባ ተስፋ ኢየሱስ፣ እነ አባ ዘጊዮርጊስ ዘዋሸራ፣ እነ አባ እንጦንስ፣ እነ አባ ግርማ ሥሉስ ዘውይት በጉባኤው ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ጉባኤው በመምህር አካለ ክርስቶስ እየተመራ ስለ ተዋሕዶ እምነት ጥልቅ ውይይት አደረገ፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ መሆናቸውን የሰማው የሱስንዮስ ጦር በድንገት መጣና ከበባቸው፡፡ ጥቅምት 19 ቀን 1621 ዓም 7000 ካህናትንና ምእመናንን ፈጃቸው፡፡
ደብረ መዊዕ ማለት የማሸነፊያ ቦታ፣ ተራራ ማለት ነው፡፡
አለፍን ወደ ባሕርዳር ከተማ፡፡ እኛ ከተማ ስንደረስ የብሔር ብሔረሰቦች በዓልን ለማስተናገድ ሸብ ረብ እያለች ነበርና ሞቅታ ላይ ነበረች፡፡ እኛም ከቅዳሜ ገበያ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚወስደው መንገድ በኩል አድርገን ወደ ምክር ቤቱ አቅጣጫ ተጓዝን፡፡ ባሕርዳር ጊዮርጊስ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በጎንደር ዘመን የመጡ ሚሲዮናውያን ያርፉባቸው ከነበሩ ቦታዎች አንዱ ዛሬ የባሕርዳር ጊዮርጊስ የተተከለበት ቦታ ነው፡፡ ፖርቹጋሎቹ የሠሩት ሕንጻ ዛሬም ለደብሩ የዕቃ ቤት ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡
|
ባሕርዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ
|
ከተማዋን በዓባይ ድልድይ በኩል አልፈናት ወጣን፡፡ ዓባይን ለሁለተኛ ጊዜ ማቋረጣችን ነው፡፡ በፎገራ ሜዳ በኩል ስናልፍ ታላቁ ሊቅና ቀልደኛ አለቃ ገብረ ሐናን አስታወስን፡፡ ሀገራቸው ናባጋ ጊዮርጊስ በስተግራችን በኩል ነው፡፡ የተሾሙበትን የአቡነ ሐራን ገዳም ደግሞ በስተ ቀኝ በኩል አልፈነዋል፡፡ አለቃ ተከስሰው ወደ ዐፄ ምኒሊክ ችሎት የመጡት የአቡነ ሐራን ገዳም እህልና ገንዘብ ለገበሬ በመስጠታቸው ነበር፡፡ በዘመናቸው ድርቅ መጣና ገበሬዎቹ ቢቸገሩ አለቃ የገዳሙን ገንዘብ አውጥተው አደሏቸው፡፡ በዚህም ካህናቱ ከስሰዋቸው አዲስ አበባ መጡ፡፡ በዚያውም እንጦጦ ራጉኤልን ለመሾም በቁ፡፡
አዲስ ዘመን ላይ ስንደርስ ወደ ደብረ ታቦር ተገነጠልን፡፡ አስፓልቱ እንደ ኑግ የተለጠለጠ ነው፡፡ ሽር ብትን ማለት ብቻ ነው፡፡ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አፈ መምህር ገብረ ሥላሴና የሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎች ክርስቲያናዊና ወንድማዊ የሆነ አቀባበል ነበር ያደረጉልን፡፡ የጎንደሩ ሙሉቀን አስቀድሞ ደብረ ታቦር ደርሶ ነበር፡፡ አፈ መምህር ገብረ ሥላሴ አስፈላጊውን የትብብር ደብዳቤ አዘጋጅተው፣ በሚያስፈልግ ሁሉ ለመተባበር ስልካቸውን ሰጥተው ነበር የሸኙን፡፡
አሁን ጉዟችን
እኔ እየተከተልኩ እሷ እየመራችኝ
ስማዳ ስማዳ ስማዳ አገባችኝ
ወደ ተባለላት ስማዳ ነው፡፡ መልካም መንገድ፡፡