የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ለ4ኛ ጊዜ የተከራየው ሳታላይት ጃም ተደረገ
በዘረኛውና አፋኙ የወያኔ አገዛዝ ተደጋጋሚ አፈና እየተካሄደበት ያለው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ኢሳት ለ4ኛ ጊዜ የሳታላይት ጣቢያ ለመቀየር የተገደደ ቢሆንም በአዲሱ የሳታላይት በአዲሱ ሳታላይት ላይ የተጀመረው ስርጭት ከአንድ ቀን ባነሰ ጊዜ ከፍተኛ ጉልበት ባለው የሳታላይት ሞገድ መጥለፊያ መመታቱን ኢሳት አስታወቀ።
የመለስ ዜናዊ አፋኝ አገዛዝ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ለመገደብ በሚያካሁደው አምባገነናዊ እርምጃ በአገር ውስጥ የሚታተሙት ነጻ ጋዜጦችን ፍቃድ በመከልከል፤ ፍቃድ ያገኙትን ደግሞ በማስፈራራት፤ በማወክና የህትመት ዋጋ በመጨመር መንቀሳቀስ እንዳይችሉ እያደረገ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከአገር ውጪ ወደ ኢትዮጵያና አካባቢው በሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚደረጉ ስርጭቶችን በሙሉ ለማፈን ከፍተኛ የሆነ የአገሪቱን ሃብት እያፈሰሰ እንደሚገኝ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ሳይቀር ስለሰብዓዊ መብት አያያዝ ይፋ በሚያደርግበት አመታዊ ሪፖርቱ ገልጾአል::
ህዝባችን ምንም አይነት ነጻ የሆነ መረጃ እንዳያገኝ እና ከወያኔ የዜና ማሰራጫዎች የሚተላለፉትን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ብቻ እየተጋተ እንዲኖር ለማድረግ ከደሃው ህዝባችን ጉሮሮ በተነጠቀ ገንዘብ ነጻና ገለልተኛ የሆነ መረጃ የሚያስተላልፉትን መገናኛ ብዙሃን የሚያፍን መሳሪያ በውድ ዋጋ ከቻይና እየተገዛ አገልግሎት ላይ መዋል በጀመረበት በዚህን ሰዓት ቁጥሩ ከ3 ሚሊዮን በላይ የሆነው የአገሪቱ ዜጋ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገልጾ በአገዛዙ በኩል ለውጪ መንግስታት የልመና ጥሪ ቀርቦአል። ወያኔ በአገሪቱ ውስጥ አስፍኛለሁ ስለሚለው እና በየዕለቱ ዜጎችን የሚያደንቁርባቸው ፍትህ፤ እኩልነት፤ ልማት እና እድገት እውነት በምድራችን ላይ የሚታዩ ቢሆን ኖሮ የሌሎች መገናኛ ብዙሃን መኖር እነመለስ ዜናዊን ይህንን ያህል ሊያስፈራ የሚችልበት ወይም ለልማት እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ሊውል ይችል የነበረ ብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ እየተደረገ በቀን አንድ ሰዓት ብቻ ከሚተላለፈው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ እስከ በሳምንት 2 ቀን ብቻ የሚተላለፈው የኢህአፓ ሬዲዮ ለመጥለፍ ባላስፈለገ ነበር የሚሉ ብርካታ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ኢሳት ስርጭቱን ወደ አገር ቤት ከጀመረበት ቀን አንስቶ የወያኔ አፈና ለአንድም ቀን እንዳልተለየው የሚናገረው የኢሳት መስራች ቦርድ፤ ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል ፍሬ እስኪያፈራና በአገራችን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት እስኪረጋገጥ ድርስ ኢሳትን በገንዘብ ወይም በሞገድ ጠለፋ ለማዳከም ወያኔ የሚያደረገውን ማናቸውንም አይነት መሰናክሎች ተቋቁሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ለማገልገል የሚያስችለውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት በፈረንጆች አቆጣጠር ከአፕሪል 14 ቀን 2011 ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እና አካባቢዋ ስርጭት እያደረገበት ያለው አዲሱ ሳታላይት አፕስታር (APSTAR) 2 አር በመባል የሚታወቅ እንደሆነና ይህ ጣቢያ ቀደም ሲል ስርጭቱ ይተላለፍበት ከነበረው ታይኮም 5 አጠገብ የሚገኝ ሆኖ በ ሲ ባንድ 76.5 ድግሪ ኢስት ሆርዞንታል፣ ፍርኩዌንሲ 3840 ሜጋ ሄርዝ፣ ሲምቦል ሬት 27500 መሆኑን ን ከኢሳት የተሰጠ መግለጫ ያስረዳል። ኢሳት በውጪ የሚገኝ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገር ቤት ላለ ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ይህንን አዲሱን ሳታላይት ፍሪኩዌንስ በማሰራጨት እንድትተባበር ጥያቄ አቅርቦአል።
የወያኔን አፈና ለመቋቋም ተብሎ በ8 የተለያዩ አጫጭር እና መካከለኛ ሞገዶች በሳምንት 3 ቀናት ጠዋትና ማታ ወደ አገራችን ስርጭት የሚያደርገውን የግንቦት 7 ድምጽ ሬዲዮን ጨምሮ፤ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ፤ የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ |ዶቼ ቬሌ| ፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሬዲዮ እና የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ሬዲዮም እንዲሁ እጂግ በጣም ብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተደረገ ከፍተኛ የሆነ የሞገድ ጠለፋ እየተካሄደባቸው በአገር ውስጥ የመሰማት ችሎታቸው ክፉኛ የተጎዳ መሆኑ ታውቋል።