የአባይና ጣና፤ የግድብ ገመና፦ የጐንቻው!
ጐጃም ባህርዳርን እንደተረገጡ፤
‘ፔዳን’ የዘረፉ፤ ‘ፓሊን’ የሟጠጡ፤
ብረት ከፋብሪካው፤ ሞተር እያወጡ፤
ወንበር፤ጠረጴዛ፤ስልክ እየቆረጡ፤
ወናውን ያስቀሩ፤ቢሮ አገር ያነጡ፤
ትውልድ መመማሪያ ተቋማት ያሳጡ፤
ዳቦም መጋገሪያ ጉልቻ የዋጡ፤
ጥፍት ምግባራቸው በተንኰል ያበጡ፤
አገር እምብርት ላይ ደም እየመጠጡ፤
ሃያ ዘመን ባልገው በዓለም ሲቀመጡ፤
የጐጥ ‘ጉጅሊዎች’ አበሻን ሲቀጡ፤
ለሚሊዮን ሲቃ ደንታ የማይሰጡ፤
ገድበው ሕዝብ-አገር በአሳር እያሳጡ፤
በደም የከበሩት የተንበላጠጡ፤
አቅም ቢሰጣቸው ‘የደደቢት ፎጡ’፤
ጣናንም አባይን ካፈር ባሰመጡ።
ከጠላት ተዳርተው ‘እየሸረሞጡ’፤
የታሪክ፤የሐገር ማተብ የቆረጡ፤
‘ኪታብ’ ያረከሱ፤ የተመላለጡ፤
ሲዘርፍ እንዳልኖሩ፤ጥሪት ሲሟጥጡ፤
ከመቸ ወዲህ ነው የሚሽቆጠቆጡ፤
እንዳዛኝ ቅቤ አንጓች፤ የሚንቆራጠጡ፤
በአባይ ጣና ግድብ እንዴት አፍ አወጡ፤
‘ባህር ማዶ’ ተሻግረው እየቀላወጡ፤
‘እናት አገር ጥሪ’፤የወር ደመዎዝ ስጡ፤
የአባይ ‘ቦንድን’ ግዙ፤ ነፍሳችሁን ሽጡ፤
‘ኢንቨስትመንት’ አምጡ፤ ‘ሺህ ዶላር’ አዋጡ፤
በአጽማችሁ ይታነጽ የባጡ፤ የቆጡ፤
አገር አያውቅ ይሆን ‘ሲያስማሙን’ ሊሸጡ።
መተማ ጋምቤላን፤ ሃራጅ እየሸጡ፤
ባድመን በሰባ ሺህ በደም የለወጡ፤
ኢትዮጵያን አካሏን እየቆራረጡ፤
ዛሬ ከመሻሸ በአባይ ሊሸቀጡ፤
የሰው አዙዎቹ በደም የሰመጡ፤
እትብት ማተብ ክደው ጽንስ እየቆረጡ፤
ለስልጣን፤ለንዋይ፤ ሰክረው የቋመጡ፤
ስድ አድገው በመረን ምግባር ያልታነጡ፤
በሐገርና ሕዝብ ታሪክ የዘቀጡ፤
ደረቅ ልሳናቸው ለጥፋት የመጡ፤
ወንዝ የሚያነጥፉ፤ ሐይቅ የሚመጡ፤
እንደዚህ ከመሸ አባይ የሚሮጡ፤
ምን ቢያቃዣቸው ነው እንዲህ የቀነጡ፤
ሊገድቡ አይደለም ቀጥፈው የሚንጣጡ፤
‘ቦንድ’ መናጃ እንጅ ማዕበል እየናጡ።
ካናዳ፤አሜሪካ፤ አውሮፓ ተላጡ፤
የሱማሌ ጀሌ፤የጐጥ ‘ተኩላዎች’ እየመራረጡ፤
እንደ እቃ ተጭነው በሚገላበጡ፤
አንዳች ጋግርታሞች፤ ሰው የሚራገጡ፤
ውይይት አይሹም አንሰው ሲያንጓጥጡ፤
‘ከዲያስፓራው’ ቁጣ ሸሽተው ላያመልጡ፤
ከአዳራሽ ተባረው ‘ዋሻቸው’ ሲሮጡ፤
በበር ተንደርድረው ጓዳ ፈረጠጡ፤
ገድለዋት ኢትዮጵያን በስሟ አያላግጡ።
ሃያ ዘመን ሕዝብን የተፈናጠጡ፤
አገር-ሕዝብ አክስረው በግል የናጠጡ፤
ዐይን የላቸው ጉዶች፤ ደረቅ ያፈጠጡ፤
በልተው አይጠረቁ፤ አጽም የሚግጡ፤
ውል-ልክ የሌላቸው ግብር ያልተቀጡ፤
በጨለማው ነግስው በቀን የማገጡ፤
በ59ኛው ደቂቃ እሚንጣጡ፤
ግድብ ቦይ-ቀደዳ የሚወጠወጡ፤
የለውጡን ማዕበል አቅጣጫ ሊያሳጡ፤
የሚያዘናጉበት ሌላ መላ ቢያጡ፤
ክተት ሲዳዳቸው በጦር ሊቀናጡ፤
በግፍ የተካኑት ዋሽተው የዘቀጡ፤
ግራ ሲገባቸው ይጨብጡት ሲያጡ፤
ሰሚኒያ ‘ቢሊዮን’ መዋጮ ሊቀጡ፤
አባይ ጣና ብለው አዲስ ወሬ አመጡ።
ምን ሰምተው ነው ዛሬ ‘ነብይ’ የሚያሪጡ፤
አባይና ጣና ዲስኩር የለጠጡ፤
ይልቅ የዘረፉን ይመለስ በቅጡ፤
ባልከፈሉት እዳ ቅዥት ከሚያምጡ፤
ጣናን ሊያዋልዱ መንታ በየሸጡ፤
አባይን ከትረው ጓሯችን ሊያጠጡ፤
የቁጥሩ ሊቃውንት ‘አሃዝ’ የሚፈልጡ፤
ደርዘን ዜሮ አባዝተው የሚቅበጠበጡ፤
ሰማኒያ ቢሊዮን እዳ የሚያንጡ፤
ሲገፉት በኖሩ፤ ከዳጥ ወደ ማጡ፤
እየተጣደፈ ፍርድ በምድር ቀውጡ፤
ዓለም ወይስ ‘ነብይ’ የተለዋወጡ፤
ጽድቁ እንኳ ቀርቶብን ኩነኔው በቅጡ፤
እርም አንጀራ አጥጦን ማሰፈራሪያው ወጡ፤
በአባይ ጣና ወሬ ጮማ እየቆረጡ፤
ምን ያገሱብናል ጮቤ እየረገጡ፤
ሽሮ አሳረሩብን መለስ አለቅጡ።
የጐንቻው! [email protected]