የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያ እንደገቡ ተዘገበ
አቡጊዳ – ነሕሴ 22 ቀን 2002
ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ የሚገኙ በለድሃዋና ኤልዋክ የተሰኙ ከተሞች እያመሩ እንደሆነ፣ በዶሎ (ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለች ለሶማሌና ለኬንያ ቅርብ የሆነች ከተማ) ያሉ ምንጮችን በመጥቀስ አዲስ ነገር ድህረ ገጽ ዘገበ።
በተጨማሪ ወደ ስድስት ሺህ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በዶላ ከተማ ላለፉት ሶስት ሳምንታት እንደሰፈሩም አዲስ ነገር አክሎ ጠቅሷል።
በቅርቡ አቶ መለስ ዜናዊ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በተለይም የአፍሪካ ሕብረት ወታደሮችን ለመጠበቅ፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ሊገቡ እንደሚችሉ መግለጻቸዉ ይታወሳል። ተያይዞም አልሻባብ የተሰኘዉና ከአልካይዳ ጋር ግንኙነት ያለዉ ቡድን፣ በቅርቡ ሞቃዲሾን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸመ ሲሆን በሞቃዲሾ ያሉ የአፍሪካ ሕብረት ወታደሮች ትልቅ አደጋ ላይ እንዳሉም በሰፊዉ ተዘግቧል።
ወደ ሞቃዲሾ ወደ ምትወስደዉ ወደ በለትዌኔ ከማምራት፣ በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ወደ ሚገኙት በለድሃዋናና ዔልዋክ ከተሞች የኢትዮጵያ ወታደሮች ማምራታቸዉን በተመለከተ ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት ሲሰጡ «ወደ ሞቃዲሾም መሄዳቸዉ አይቀርም። ነገር ግን በሶማሊያና በኬንያ መካከል ያለዉ ድንበር ከወዲሁ በመቆጣጠር፣ የአልሻባብ ተዋጊዎች ከሞቃዲሾ ሲባረሩ ማምለጫ እንዳይኖራቸዉ ለማድረግ ተብሎ የታሰበ ሳይሆን አይቀርም» ሲሉ የአካባቢዉ ቀዉስ ወሳኝ ደረጃ ላይ እንዳለ አስረድተዋል።