ለሰለባ የመጣ ልብስ ቢጥሉለት አይመለስ:: በዮሐንስ እ ተመስገን

በአሁኑ ወቅት የአሜሪካን አምባሳደር በኢትዮጵያ ሆነው የሚያገለግሉት ቡዝ ለአውራ አምባ ታይምስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ዙሪያ ከሰሞኑ የታወቁና አንቱ የተሰኙ ጸሃፊዎች በሰጡት አስተያየት ላይ የታየኝን ለማከል ነው ዛሬ ለመጻፍ የተነሳሁት::

ጉዳዩ አምባሳደሩ “የኢትዮጵያ ህዝብ የምርጫውን ውጤት ተቀብሎታል” ማለታቸው ከእውነት የራቀና ያሳዘናቸው መሆኑን የማደንቃቸውና የማከብራቸው ብሩህና ምስጉን ኢትዮጵያውያን ጸሃፊዎች ባማረ ሁኔታ ገልጸውታል::

ይህንንም መልስ የሰጠው የአሜሪካ ተወካይ በመሆኑ ብዙም ልናዝን ልንነጋገርበትም ሆነ ልንተችበት መሞከሩ የአሜሪካንን ፖሊሲ እውነተኛ ገጽታ ካለመገንዘብ የሚመጣ የዋህነት ያስመስልብናል::

ይኄው የአሜሪካ መንግስት ነው በአንድ በኩል ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲ እያለ ሲለፍፍ በሌላ ወገን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይ መከራና የሰብዓዊ መብት ረገጣ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን እንደ መለስ ዜናዊ አይነት በዓለም በዕኩይነቱ አቻ የሌለው አምባገነን መሪ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ሲደግፈው የሚታየው። ጥቅም እንጂ ሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲ ወይም የሰው ልጅ ጣዕርና ዕልቂት ምኑም ያልሆነው የአሜሪካ መንግስትና የዚሁ ፖሊሲ አራማጅ መሪዎቹ ወደ አንድ ሚሊዮን የተጠጋ ህይወት የጠፋበትን የሩዋንዳ የእርስ በርስ ፍጅት ዳር ሆነው ሲያዩ ዓለም ታዝቧል:: በአንጻሩ በነዳጅ ክምችት ሃብቷ የምትታወቀውን ኢራቅ በሀሰት ውንጀላ መውረር ለሚለፍፉት ዲሞክራሲ ሰብዓዊ መብት ወይም ለሰው ልጅ ያላቸው ተቆርቋሪነት በወረቀታቸው ላይ ያስፍሩት እንጂ ከጥቅም በኋላ ያለ እንደ አስፈላጊነቱ የሚመዘዝ ካርድ እንጅ ዋነኛ ምክንያት ስላልሆነ በአምባሳደር ቡዝ መልስ ማዘን አያስፈልግም እኚህ አምባሳደር ልምዳቸው ታይቶ ከላይቤርያ ከዚያም ዛምቢያ ተሹመው ጥሩ ውጤት ለሀገራቸው ስላመጡ ነው በእድገት ወደ ኢትዮጵያ የተዛወሩት::

በአሜሪካን አይን ተልእኮአቸውን በትክክል የተወጡ አምባሳደር ናቸው:: ከእኛ ማዕዘን ሲታይ ደግሞ ንግግራቸው ከእውነት የራቀ ነው ካልን ጠንክረን እንዳልሆነ ማሳየት እንጅ ለርሳቸውና ለመንግስታቸው እውነት ብለው ያመኑበትን እኛ ግን ውሸት የሆነ የምንለውን ነገር እንዴት ይዋሻሉ ብለን እሰጥ አገባ ብንል ግዜ ማጥፋት ከመሆኑም በላይ መካሰስ በምድር ላይ ያለውን እውነታ የሚቀይር አይሆንምና እንደማንኛውም ዜና ዜና ነው ብለን ማለፍ ነው ያለብን የሚል ነው እምነቴ::

በአጭሩ ለመግለጽ ለኛ ችግር መፍትሄ የምንሆነው እኛ እንጂ የአሜሪካ መንግስት ወይም የሀገሩን ጥቅም ሊያስጠብቅ የተላከ አምባሳደር አይደለም:: ጄንዳይ ፍሬዘር የተባለች የቀድሞ የአሜሪካን ዲፕሎማት መለስ ዜናዊን ከመጋረጃ በስተጀርባ ገንዘብ እርዳታ እንድናደርግልህ ሶማሊያን ውረር ብላው መለስ ዜናዊ ሲሸልል ሲያቅራራ ወደሰላሳ ሽህ የተጠጋ ህይወት ያለፈበትና በመቶ ሽህ ሰዎች የተሰደዱበትን ጉዳይ በስንት ብር እንደተዋዋለ ሳይናገር ጋዜጠኞች ጠርታ አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግስት ጦሩን ወደሶማሊያ እንዳያስገባ መክረናል ይህን ምክር መቀበል ያለመቀበል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ እንጂ የኛ አይደለም ስትል መለስ ዜናዊም የሷ ውሸት ሳይገርመው ብሩን ተቀብሎ ወረራውን ፈጽሟል:: ለመለስ ዜናዊም ውሸት ምኑም አይደለም እንዲያውም ከሁሉም መሪዎች በውሸቱ ከፍተኛውን ቦታ ሳይዝ ይቀራል?

እንዲህ ነው እንግዲህ ከላይ ያለው ቁማር ፖለቲካና እጅ የመጠማዘዝ ጨዋታ:: እውነት እኩልነት ዴሞክራሲ የህግ የበላይነት ተጠያቂነት የፕሬስ ነጻነት የሀገር ልዕልና ሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዮች ህዝብ እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው ክስተቶች እንጂ ከእውነት የራቁ ቁማርተኛ ፖለቲከኞች የሚወዱት ነገር አይደለም:: የነርሱ እውነትና እድገት የሚባለው በሾኬ ተጠላልፎ ማን ብዙ ወሰደ ማን ብዙ ሰረቀና ተጠቀመ ነው::
ታድያ ጄንዳይ ፍሬዘር መርጣ መልምላ የላከችብን ቡዝ “ምርጫውን ህዝብ ተቀብሎታል” ማለቱ አያስደንቅም:: በ”ዲፕሎማሲያዊ” አነጋገርስ ሲመነዘር? የኢትዮጵያ ህዝብ የምርጫውን ውጤት ባይቀበለው ኖሮ በህዝባዊ ተቃውሞ ሰደድ እንደ ሌላው ህዝብ ለአለም ያሳይ ነበር ማለቱ ይሆን? በዚያኛውም ብንሄድ ያስኬዳል ዝምታ የመስማማት ምልክት ነው ብሎስ እንደሆነ?:: ጥቃትን ወይም በጉልበት መደፈርን ለማስቆም ከተፈለገ ተንጋሎ ማጣጣም ሳይሆን ተነስቶ መታገልን መቃወምንና እምቢተኝነትን ይጠይቃል:: በኢትዮጵያ ህዝብና በሀገሪቱ ላይ መለስ ዜናዊና ጥቂት ግብረ አበሮቹ እያደረሱ ያለውን ጥፋት አፈና ሰቆቃና ጥቃት በቃ ብሎ ለመነሳት ግዜው አሁን ነው::

በብዙ እጅ ከኛ ህዝብ በላቀ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙት የሰሜን አፍሪካ ሀገር ህዝቦችም በላያቸው ላይ ተንሰራፍቶ ያለውን አምባገነን አገዛዝ በህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል እየገረሰሰ ይገኛል::

ይህ ሀገሪቱን ያለ ባህር በር እንድትቀር ትግሉን የጀመረ መንግስት ቀጥሎ ከኤርትራ ጋር ባደረገው ጦርነት ወደሰባ ሺህ ወጣት አስጨፍጭፎ በዓለም የድንበሮች ግጭት ፍርድ ቤት ለኤርትራ እንዲፈረድ ማስረጃ በማቅረብ ለሚመራው ሀገር ሳይሆን ለሌላው የሚሰራ አረመኔ ባለፉት ዓመታት በጎንደር በኩል ያለ የኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት ከህዝብ ደብቆ ለሱዳን መንግስት በገጸ በረከትነት በማቅረብ የውሃውን ጥልቀት ሞክሮ ዛሬ ደግሞ በምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ኢትዮጵያውያንን ከሀገራቸው መሬት በሃይል እያፈናቀለ የቤልጀየምን የቆዳ ስፋት ያክል መሬት እየቆረሰ ለተለያዩ ሀገሮች ሀገራችንን እየሸነሸነ በመሸጥ ላይ ያለ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚሰራ ቡድን ነው::

ይህ የኢትዮጵያ የሆነን ነገር ሁሉ ብዙ ለከፈለ የሚሸጥና የሚለውጥ አፋኝ ወሮበላ መንግስት ኢትዮጵያዊነትን ሸርሽሮ በጎሳ የተከፋፈለ ደካማ ህዝብና ደካማ ሀገር ለማድረግ ይዞ የተነሳውን ዓላማ ሲሰራበት ሃያ አመት ቆየ:: ይህ አፋኝ የኢትዮጵያ ጠላት የህዝቡን የሰውነት መብቱን ገፎ ከመኖር በታች ከሞት በላይ አድርጎት በረሃብ ከሚታመሰው ህዝብ ጉሮሮ እየነጠቀ ከመሬት ሽያጭ ያሚያገኘውን ገንዘብ በተለያዩ የውጭ ባንኮች የሚያሸሸውንና የሚያጉረው አልበቃ ብሎት ዛሬ ደግሞ በአምስት አመት እቅድ ላይ ያልነበረውና ከሰሞኑ የሰሜን አፍሪካው ህዝባዊ አመጽ ጋር አስከትሎ ያመጣው ዜማ አመጹ በኢትዮጵያ እንዳይነሳ የቀየሰው ስትራቴጂ ሃያ አመት አፍኖ ሲዘርፈውና ቁልቁል ሲያየው የከረመውን ህዝብ በብሄራዊ አጀንዳ ስር ለማሰለፍ ወይ ኤርትራን መውረር ወይ አባይን መገደብ ከዚያም ቦንድ ሽጦ በእናት ሀገር ጥሪ መዋጮ የሚሊኒየሙን ግድብ መስራት በሚል ይህን የከፋ ቀን ሸውዶ ሊያልፍ ባለው ዘዴ ሁሉ እየተፍጨረጨረ ነው:: ታድያ ይህን ሁሉ ወንጀል በህዝብ ላይ የሚፈጽመው ኢትዮጵያን የሚጠላ የኢትዮጵያ መሪ ተብዬው መለስ እያለ የአሜሪካ አምባሳደር ንግግር ውሸትና ያልተለመደ ቅጥፈት ላይ ብዙ ሊባል አይገባም ብዙም ከነርሱ መጠበቅ አያስፈልግም:: አለም በሙሉ በተለይ አሜሪካ ፖሊሲዎቿ የሚነደፈውና የሚጠነጠነው ከሀገሪቱ ጥቅም አኳያ እንጅ ከእውነትና ከሀሰት ከሰብአዊነትና ከዴሞክራሲ ጋር በተዛመደ መልክ ስላልሆነ የምታወሩት ሌላ የምታደርጉት ሌላ ብለን ብናሳጣቸው ብንወቅሳቸው ለኛ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም :: መለስ ዜናዊም የሰሜን አፍሪካው የህዝብ አመጽ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይዛመትና እንዳይቀሰቀስ ከፍተኛ ፍርሃት ወርሶት ጋዜጣዊ መግለጫ አብዝቶአል:: ህዝብ ያልኩትን አልሰማ እንደሆነ ብሎም በአዋጅ በነጋሪት ታይቶ በማይታወቀው የስምንት ወር ሪፖርት ለማዳማጥ ለመደገፍና ለማጨብጨብ ብቻ ተጠፍጥፎ የተሰራውን ፓርላማ ሰብስቦ ተቃዋሚዎችን አስፈራርቶ የአባይን ግድብ የቤትስራና ከቻይና በልጦ የተገኘውን የተለመደውን የሁለት አሃዝ እድገት አስረድቶ ህዝቡ በእድገቱ ተደስቶ ግብጽን የቀድሞ ወዳጁንና እሳቸውን መስማት መጽሃፍ ከማንበብ ይበልጣል ብሎ ያሞካሸውን ኢሳያስ አፈወርቂን ከስልጣን ለማውረድ ያለውን ስትራቴጂ ህዝቡም ግብጽን ኤርትራንና ተቃዋሚዎችን በጠላትነት ወግኖ ግድቡ ላይ እንዲያነጣጥር ረጅም የጭንቀት ወሬውን አውርቶአል:: ከዓመት ዓመት በሚሊዮን የሚቆጠር ረሃብተኛና የምግብ ተረጂ ባለባት ሀገራችን የርሻ መሬቱን ለባዕዳን ከበርቴዎች እየሸጠ የዴርቶጋዳን ፕሮጀክት “እውን” ሊያደርግና ሊፈጽመው ከምግብ በፊት ኤሌክትሪክ ማመንጫ ያስፈልገናል ስለዚህ ሱዳን አጠገብ የጣናን ሁለት እጥፍ የሆነ ውሃ ማቆሪያ ይላል ጩሉሌው መለስ ለዚያውም 700 ቢሊዮን ብር ህዝብ እንዲያዋጣ ተደርጎ:: ወደ ዲያስፖራውም የተላኩት መልእክተኞቹ ይህንኑ ልመና ነው:: ብሩን ካገኙት ሊወስዱት ካላገኙትም ዲያስፖራውን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሊያናቁሩት።

እውነት መለስ ለኢትዮጵያ አስቦ???? ለሰለባ የመጣ ልብስ ቢጥሉለት አይመለስ ነው የመለስ ነገር:: ሀገሬና ህዝቤ ያለ ህዝብ በቃ ብሎ ካላስቆመው ይችን ሀገር ሳያፈርሳትና ሳይሸነሽናት ሀብቷንም ሳይበትን አይመለስ ይህ የትውልድ ሁሉ መርገምት;; አሸናፊ የሚወዱት አሜሪካኖችም የህዝብ ብሶት የወለደው አመጽና ምሬት ገፍቶን በቃ ብለን በሰሜን አፍሪካ እንደታየው የህዝብ ማዕበል ከተነሳን አስር ሃያ ሰው እስኪገደል ይጠብቁና ለሌሎች ሸሪኮቻቸው እንዳሉት ሰው አትግደል ስልጣን ልቀቅ ይላሉ እንጅ ምርጫውን ህዝብ ተቀብሎታል ብለው አይሳለቁብንም:: አሜሪካኖች ጥቅማቸው ከሚኖርበት አሸናፊ ከሚመስላቸው ወገን ለመሰለፍ ይሽቀዳደማሉ እንጅ በጎደፈ ታሪክ ሊያስጠይቃቸው በሚችል ሁኔታ ባአስራአንደኛው ሰአት ከአምባገነን መሪዎች ጋር የሙጥኝ ብለው አይወግኑም:: ተሽቀዳድመው እንደ ይሁዳ ይሸጡትና እንደጲላጦስ ከደሙ ንጹህነታቸውን ለማስመዝገብ ሲጋፉ ነው እያየናቸው የኖርነው:: የቱኒዚያ የግብጽ የሊቢያና የየመን መሪዎች የአሜሪካ ቅምጦች የነበሩ ሲሆን ህዝብ ከተነሳ አናውቃችሁም ብለው ወደገደል እንደሚወረወሯቸውና ሲያሻቸው የሚያነበንቡትን ዴሞክራሲ ውዳሴ አንስተው የህዝብ ድምጽ ይከበር ይሉናል በወዲያኛው በር ተሽቀዳድመው ተገኝተው::

ስለዚህ ከደረሰብን አስከፊ ጥቃት ውርደትና ውድቀት ለመውጣት በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ተከምሮ ደሙን የሚመጠውን ጨካኝ አውሬ ለመጣል በቃ ብለን እንነሳ::

ቸር ይግጠመን
ዮሐንስ እ ተመስገን
04-16-2011