ለኢትዮጵያውያን የፕሬስ ውጤቶች

ይህ የጡመራ መድረክ አገልግሎቱን ከጀመረ በቅርቡ ሦስተኛ ዓመቱን ያከብራል፡፡ በዚህ የሦስት ዓመት ጉዞ ውስጥ ከገጠሙት ችግሮች አንዱ የብሎጉ ጽሑፎች ባለቤትነታቸው እንደ ሥነ ቃል የሁሉም እየሆኑ መምጣታቸው ነው፡፡
በዚህ የጡመራ መድረክ የሚወጡት ጽሑፎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚታተሙ ልዩ ልዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ ይወጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ አንድ ወይም ሁለት ጽሑፍ ለማውጣት አስፈቅደው በዚያው ማውጣት የቀጠሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ማንንም ሳያስፈቅዱና ሳያናግሩ በራሳቸው ሥልጣን የሚያወጡ ናቸው፡፡
ይህንን ሁኔታ ለተወሰኑ ዓመታት በዝምታ ያለፍኩበት ምክንያት ነበረኝ፡፡ የመጀመርያው እነዚህ ፕሬሶች እየቆዩና እየተደራጁ ሲሄዱ እነርሱ ራሳቸው ሥነ ምግባሩን ወደጠበቀ አሠራር ይገባሉ፡፡ ራሳቸው ከሂደት ይማራሉ በሚል ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እየወደቀ እየተነሣ በሚሄደው የሀገሪቱ የግል ፕሬስ ላይ ጫና ላለማብዛትና ነገሩን በመነጋገር ብቻ ይፈታ ይሆናል በማለት ነበር፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት በዚህ መንገድ ነበር የቀጠልነው፡፡

አሁን አሁን ግን አራት ችግሮች በመከሰት ላይ ናቸው፡፡ አንዳንድ የፕሬስ ውጤቶች ጽሑፉን ከየት እንዳገኙ ምንጭ ሳይጠቅሱ ልክ ለዚያ ፕሬስ እንደተጻፈ አድርገውና ዓምድ ሰጥተው በተከታታይ እያተሙ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ እኔ ራሴ የትኛው ጽሑፌ በየትኛው ፕሬስ እንደታተመ ወደማላውቅበት ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል፡፡ በሁሉም የፕሬስ ውጤቶች ላይ ገንዘብ ተከፍሎኝ እየሠራሁ የሚመስላቸውን ሰዎችንም አበራክቷቸዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የትኛው ጽሑፌ በየትኛው ጋዜጣና መጽሔት (ከአዲስ ጉዳይ በቀር) እንደወጣ የማውቀው እንደሌላው አንባቢ ከታተመ በኋላ ነው፡፡

ሁለተኛው ችግር ደግሞ የኔ ያልሆነውን ጽሑፍ በእኔ ፎቶና ስም የሚያትሙ ጋዜጦችና መጽሔቶችም እየመጡ ነው፡፡ ይህ በዚሁ እንዲቀጥል ከተደረገ ደግሞ ሃይማኖትን፣ ሥነ ምግባርንና ሕግን የሚጥሱ ጽሑፎችንም በስሜ ሊወጡበት የሚችሉበትን ዕድል ይከፍታል፡፡ አንድ እግረኛ ያበላሸውን ደግሞ ሃምሳ ፈረሰኛ አይመልሰውም፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በብሎጉ ላይ የወጡትን ጽሑፎች አሳጥረው፣ አሻሽለው፣ ቀይረውና አዘባርቀው የሚያትሙ ፕሬሶችም እየመጡ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አንድን ጽሑፍ ሁለትና ሦስት ዓይነት ቅጅ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡
አራተኛው ችግር ደግሞ ከዚህ ብሎግ የተገለበጡ ጽሑፎችን የራሳቸውን ስምና ፎቶ ለጥፈው በስርቆት የሚያትሙ፤ ምንጭም ሳይጠቅሱ ስምም ሳይጠቅሱ በጋዜጣቸውና በመጽሔታቸው የሚያወጡ፤ ከሌሎች ሰዎች ጽሑፍ ጋር አዳብለው የሚያወጡ ፕሬሶችም አሉ፡፡  
እንደ እውነቱ ከሆነ በሀገሪቱ ሕግ የተቋቋመ ፕሬስ ሕጉን የማክበር ግዴታ ብቻ ሳይሆን ለሰዎች መብቶችም የመቆም ግዴታም አለበት፡፡ ራሱ መብት የሚጥስ ፕሬስ ግን ለሌሎች መብቶች ጠበቃ ለመሆን አይችልም፡፡ በአንድ ሰው ስምና ፎቶ ለመጠቀም፣ የአንድን ሰው የጥበብ ሥራዎችንም ለማተም የባለቤቱ ፈቃድ መገኘት አለበት፡፡ ከዚህ ውጭ የሚሠሩ ነገሮች ዶክተር ላጲሶ እንዳሉት በሃይማኖት ኃጢአት፣ በባሕል ነውር፣ በሕግም ወንጀል ይሆናሉ፡፡
ስለሆነም ከዚህ ብሎግ ጽሑፎችን እየወሰዳችሁ የምታትሙ የፕሬስ ውጤቶች ከእኔ በጽሑፍ ፈቃድ ካላገኛችሁ በቀር እንዳታትሙ አሳስባችኋለሁ፡፡
የዚህን ብሎግ ጽሑፎችን የምታነብቡ አንባቢዎችም እኔ በቋሚነት የምጽፈው አስቀድሞ በአዲስ ነገር ጋዜጣ በኋላም በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ብቻ መሆኑን እንድታውቁ፡፡ ከዚህ ውጭ የሚታተሙት ጽሑፎች ሁሉ ከዚህ ብሎግ እየተገለበጡ እንጂ ለመጽሔቶቹ ወይም ለጋዜጦቹ እየተጻፉ አለመሆኑን እንድትገነዘቡ አሳስባለሁ፡፡
እንደእኔ እምነት እነዚህ ችግሮች በመነጋገርና በመግባባት ይፈታሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ ወደባሰ ነገርም እንገባለን ብዬ አላምን፡፡ ነገር ግን መግባባቱና መተራራሙ ብሎም ጨዋነት በተሞላበት የፕሬስ ሥነ ምግባር ችግሩን መፍታት ካልተቻለ የመጨረሻው አማራጭ ወደ ሕግ አደባባይ መጓዝ ሊሆን ነው፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እዚያ አንደርስም፡፡