ይድረስ ለቅድስት ድንግል ማርያም (የመጨረሻ ክፍል)
ድንግል ማርያም ሆይ
ይህ የመጨረሻዬ ደብዳቤ ነው፡፤
አንዳንድ ወዳጆቼ አሁን እንዲህ ያለው ነገር ለድንግል ማርያም ይጻፋል? አሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ እንዲህ ያለው ነገር ለርሷ ያልተጻፈ ለማን ይጻፋል አልኳቸው፡፡ እናቶቻችን የጭንቅ አማላጇ የሚሏትኮ ጭንቅን እርሷም ስላየችው ነው፡፡ ማደርያ አጥቶ መንከራተትን አይታዋለች፡፡ ልጇም ቢሆን ‹‹ለቀበሮዎች ዋሻ ለወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም›› ብሎ ተናግሯል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አሁን የቤት ጉዳይ ይህንን ያህል ደርሶ ነው ለእርሷ አቤት የምትለው? አሉኝ፡፡ ‹‹በግ የሌለው ሰው ቀበሮ አውሬ አትመስለውም›› አለ የሀገሬ ሰው፡፡
‹ምነው ቤት አትገዛም?› ትይኝ ይሆናል፡፡ ላደለውማ ቤት መግዛትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ቢያንስ ልጆቼን የሚቆጣቸው ብቻ ሳይሆን በየቀኑ የሚቆጥራቸው አይኖርም፡፡ በዚህ ሰዓት ግባ፣ በዚህ ሰዓት ውጣ የሚለኝ አይኖርም፡፡ ግንኮ የኛ ሀገር ቤት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጨዋች ሆነብን፡፡ እኛ በልጆቻችን ስም ብቻ የምናውቀውን ‹ሚሊዮን› ዋጋ አድርጎ የሚጠራ ቢኖር ቤት ሻጭ ብቻ ነው፡፡
የሌላው ሀገር ሰው በሚሊዮን ቀርቶ በቢሊዮን ቤት ቢገዛ ከባንክ ተበድሮ ነው፡፡ ዕድሜ እስካለው ያቅሙን እየከፈለ ይኖርበታል፡፡ በኋላ ደግሞ ወይ ዕዳው ያልቃል ወይ ዕድሜው ያልቃል፡፡ እኛጋኮ ‹‹ሚሊዮኗን ቆጥራችሁ አምጧት›› ነው፡፡ እንዴት ሚሊዮን ይቆጠራል? ለመሆኑ ስንት ዓመት ተጠራቅሞ ነው ሚሊዮን የሚቆጠረው፡፡ ትናንትና ከተማዋን ይገዛ የነበረ ብር ዛሬኮ ከተማ ገብቶ ለማደርያም አልሆን እያለ ነው፡፡ ‹ቀን የጎደለበትን ጠገራ አይጥ ይበላዋል›› አለ አበሻ፡፡ ትናንትና የአራተኛ ክፍል ማለፊያና መውደቂያ ቁጥር የነበረው ‹አርባ ስልሳ› ይኼው ዛሬ የቤት ማግኛ ቁጥር ሆነ፡፡ የታደለ ቁጥር፡፡
እነዚህ የድሮ ዘመን ልጆች
ባልንጀሮቼ ቁሙ በተራ
እንጨት ሰብሬ ቤት እስክሠራ
እንኳን ቤትና የለኝም አጥር
እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር
ያሉት ነገር ዘፈን ነው? ትንቢት?
የሀገሬ ሰው ሲያንጎራጉር ‹አልበር እንዳሞራ ሰው አርጎ ፈጥሮኛል› ይላል፡፡ አሁንማኮ ሰውና አሞራ አንድ ሆኗል፡፡ ሰውም በቤት መወደድ ምክንያት ማደርያ አጥቶ ይዞራል፡፡ አሞራም ይኼው ዛፉ ሁሉ ተቆርጦ አልቆበት ጎጆ የሚሠራበት አጥቶ ይዞራል፡፡
አሁን እስኪ ከመሐል አራት ኪሎ ተነሥተን የአዲስ አበባ ጥግ ስንገባ ምን እንደምንመስል አስቢው፡፡ መቼም ሀገር አይደግ፣ ሀገር አይልማ አይባልም፡፡ ነገር ግን አሮጌ ከተማን ማፍረስና አሮጊትን ወጣት ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ለዚህኮ ነው ብዙ ሀገሮች የጥንቱን ከተማ ከማፈራረስ ብለው ሌላ አዲስ ከተማ የሚገነቡት፡፡ እኛስ ሀገር ምናለ አዲስ ከተማ ብንገነባ፡፡ ስንቱን አፍርሰን እንዘልቀዋለን፡፡
አራት ኪሎኮ ለኛ መኖርያ ብቻ አልነበረም፡፡ የ50 ሳንቲም ድንች፣ የስሙኒ ሽንኩርት፤ የ10 ሳንቲም ዘይት፣ የአርባ ሳንቲም እንጀራ ገዝተን የምንጠግብበት ጎተራችንም ነበር፡፡ አራት ኪሎ ላይ ተሸክሞም፣ ጫማ ጠርጎም፣ ተበድሮም ገንዘብ ማግኘት ይቻላል፡፡ አሁን እዚህ የከተማው ጥግ በድኽነት ዐቅም የሀብታም ሠፈር ገብተን፣ እንኳን በስሙኒ በሃያ አምስት ብር ምግብ ማግኘት አልቻልንም፡፡ ያ የመቶ ዓመት ዕድራችንም ፈረሰ፡፡ እዚህ ደግሞ ሁሉ ባለ ፉካ ነው፡፡ እንኳን ዕድር ሳይኖረን የሞትን ዋጋ በዕድርም አልቻልነው፡፡
ይኼው በቀደም ዕለት እዚህ ሠፈር አንድ ሀብታም ሞቶ ልቅሶ ብንሄድ ለካስ የሠፈሩ ዕድር እንደ አራት ኪሎ ዕድር አይደለም፡፡ ቢራ በየዓይነቱ፣ ክትፎ በየመልኩ፣ አትክልት በየ ስሙ፣ ዳቦ በየጋጋሪው፣ እንጀራ በየጠባዩ ተደርድሮ ቡፌ ስናነሳ ነበር፡፡ ድግሱ ድንኳን ውስጥ ባይሆን፣ የሟቹ ፎቶ ተሰቅሎ ባናየው፣ ቤተሰቡም ጥቁር ባይለብስ ኖሮ ባልተጠራንበት ሠርግ በከተፋ የገባን ይመስለን ነበር፡፡
አበሻ ሲተርክ ‹ዓባይ ማደርያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል› ይላል፡፡ ‹ይህንንስ ስለማን ተናግሮታል ቢሉ› አሉ ሊቃውንቱ ‹አንድም ስለ ራሱ ተናግሮታል› ይላሉ፡፡ ‹እንደምን ነው ቢሉ ብዙ የከተማ ሰው ቤት የለውምና፡፡ ግንድስ ያለው ማንን ነው ቢሉ የቤት ዕቃውን፡፡ ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፡፡ ዓባይ ግንዱን ከዛፉ ገንድሶ ከየትም እንዲያመጣው፣ ቤት የሌለው የከተማ ሰውም የቤት ዕቃውን ከየትም ይሰበስባልና፡፡ አንድም ዓባይ ማደርያውን ሳያውቅ ግንዱን ይዞ እንደሚዞረው፡፡ ተከራይም የቤቱን መጠንና ልክ ሳያውቅ ዕቃ እየገዛ ይዞ ሲዞር ይኖራልና›› ብለው ይተነትኑታል፡፡
እንዴው ችግሩን ሲዘረዝሩት ቢኖሩ አያልቅም፡፡ ‹‹ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም›› ይባላልና፡፡ ይልቅ መተሳሰብ፣ መረዳዳትና መገናዘብን እንዲሰጠን ለምኝልን፡፡ አከራይና ተከራይ፣ ሻጭና ገዥ ሁሉም የአንድ ሀገር ዜጎች ናቸውና ምናለ ቢተሳሰቡ፡፡ ተስፋ የቆረጠ ጎረቤት ያለው ሰው በጤና ውሎ መግባት አይችልም፡፡ ሰው ጨዋ የሚሆነው ተስፋ ሲኖረው ነው፡፡ የርሱ ጣራ ወደ ታች እየሄደ የጎረቤቱ ፎቅ እንደ ሸንበቆ ሲያድግ ሰው ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ በጎረቤቶቻችን ሀገሮች እንደምናየው አርዶና ዘርፎ የሚበላ መንጋ እናፈራለን፡፡
እንደው መቼም የአሥራት ሀገርሽ ስለሆነችም እንደሁ እንጃ የኛ ሀገር ሌባኮ አልፎ አልፎ ሰይጣን ሲጣጋው ካልሆነ በቀር በጎረቤቶቻችን እንደምንሰማቸው ያሉ አሰቃቂ ወንጀሎችን አይፈጽምም፡፡ አንዳንድ ሀገርኮ ከነዋሪው ይልቅ ሌባው የተሻለ ነጻነት አለው፡፡ ባለ ድርጅቱና ባለ ቤቱ ሁሉ አምስት ስድስት በር ሠርቶ፣ በሩን በብረት ጠርቅሞ፣ በአራት ቁልፍ ዘግቶ፣ ያም አልበቃው ብሎ ካሜራና ሽቦ አጥሮ እንኳን፣ ግድያና ዝርፊያ አይቀርለትም፡፡ እዚያ ሀገርኮ ዜና የሚሆነው ‹‹ሌባው ሳይገድል ሰረቀ›› ተብሎ ነው፡፡ እኛ ሀገር ግን መግደሉ ነው ዜናው፡፡
ሰው እንደ ዐቅሙ ከመደብ እስከ ቪላ ቤት፣ ከጆንያ እስከ ብርድ ልብስ ካለው ቢያዝንም ሆድ አይብሰውም፤ ቢቸገርም ዐቅሉን አያስተውም፡፡ ይኼ የተሰነጠቀ ዱላ የያዘ ጥበቃ በሚንጎራደድበት ወርቅ ቤት በር ላይ ተቀምጦ የሚለምነውኮ ጨዋነት ይዞት እንጂ መስረቅ አቅቶት አይደለም፡፡ ታድያ ይኼ ሰው ተስፋ እንዳይቆርጥ ነው መስጋት፡፡
ቤታችንን ስናከራየው፣ በሚችለው ዋጋ ስንሸጥለት ንግድ ብቻ አይደለም፡፡ ለራስ የሚከፈል ዋጋም ጭምር ነው፡፡ ሌባና ቀማኛ፣ ማጅራት መችና ኪስ አውላቂ፣ እኅቶቻችንን ደፋሪና ልጆቻችን አማራሪ እንዳይበረክት እያደረግንም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ እኛ ግቢ የሚያድጉ ልጆች ናቸው የነገዎቹ የሀገሪቱ መሪዎች፡፡ እየተማረሩና ጥላቻን እየሰነቁ ካደጉ፣ ነገ የሚያወጡት ፖሊሲ ለሁላችንም አይበጅም፡፡ ገንዘብ ያለውን ሰው እንደ ጨካኝና ቀማኛ፣ ስግብግብና አጥፊ እያዩት ካደጉ በቀል ያረግዛሉ፡፡ ቤታቸውን ያስፈረሰባቸው፣ ከቀያቸው የነቀላቸው፣ ከከተማ ጥግ የወሰዳቸው ያ ባለጠጋ ለእነርሱ የአባታቸው ገዳይ መስሎ ይታያቸዋል፡፡
በዓለም ላይ አምባገነንና ጨፍጫፊ ሆነው ብቅ ያሉ መሪዎች የኋላ ታሪክ ሲታይ በልጅነታቸው ወቅት የደረሰባቸው ነገር በጎ አልነበረም፡፡ ሂትለር ምንም እንኳን ለፈጸመው ጭካኔ የሚበቃ ምክንያት ባይኖረው በልጅነቱ በመንደሩ ከነበሩ አራጣ አበዳሪዎችና ባዕለ ጠጎች በቤተሰቡ ላይ ይደርስ የነበረው ግፍና ጭቆና በለጋነት ስሜቱ ላይ ያሳደረው በቀል ግን ቀላል አልነበረም፡፡
እንዲህ ያለው መተሳሰብ እንዲኖር ደግሞ መንግሥት ቤት ሠርቶና በዕጣ አከፋፍሎ አይዘልቀውም፡፡ ባለ ሀብቱም የሚከራይ ቤት እንዲሠራ መደረግ አለበት፡፡ የኪራይ ቤት ዓይነቶች ደረጃ ወጥቶላቸው መንግሥትም በርካሽ ዋጋ መሬት ሰጥቷቸው እንዲሠሩ መደረግ አለበት፡፡ የኪራዩ ተመን ግን በመንግሥትና በአከራዩ በጋራ ሊተመን ይገባል፡፡ ይኼው አሥር ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ካይሮ የቤትን ተመን አከራይ ብቻውን አያወጣውም፡፡ የተከራየውንም እንደፈለገ ውጣ ማለትም አይችልም፡፡ የኪራዩ ተመን በመንግሥትና በአከራዩ በጋራ ነው የሚወጣው፡፡ መንግሥት የሕዝቡ ወኪል በመሆኑ ተከራዩን ወክሎ ለሕዝቡ የሚበጀውን፣ አከራዩንም የማይጎዳውን ዋጋ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ እንዲህ ሲሆን ሕዝብ ተስማምቶ ይኖራል፡፡
ደግሞም ለሚከራይ ቤት ደረጃም ይውጣለት፡፡ አሁን ሃያ ቤት ለሚያከራይ ግቢ አንዲት የመጸዳጃ ቤት ቀዳዳ በቂ ናት? በተለይ ጠዋትና ማታኮ በአንዳንድ ግቢ የሚታይ የመጸዳጃ ቤት ወረፋ የስኳር ወረፋ ነው የሚመስለው፡፡
አሁን አሁን ሰው ሰፊ ግቢውን ጥግ አስይዞ የሚከራዩ ክፍሎች መሥራት ለምዷል፡፡ ኮንዶሚኒየሙም ቢሆን ጉርብትናን ከአጥር ወደ ግድግዳ አምጥቶታል፡፡ ለመሆኑ ግን የጉርብትና ሕግ አለ እንዴ በሀገራችን፡፡ ለመሆኑ አንድ ሰው ሊጠቀም የሚችለው የድምጽ መጠን ምን ያህል ነው? ከፍተኛ ድምጾችን እስከ ስንት ሰዓት ነው ሊጠቀም የሚችለው? በዚህኛው በኩል ሚስማር ሲመታ በዚያኛው በኩል የተሰቀለ ሰዓት አመድ እንዳይሆን ምን ሕግ ይጠብቀዋል?
አኛ በአብዛኛው የለመድነው በአጥር ተለያይቶ መኖር ነውና ለግድግዳ ጉርብትና ባሕልም ሕግም ያለን አይመስለኝም፡፡ አሁን ግን የአፓርትማና የኮንዶሚኒየም ሰዎች ከሆንን ላይቀር ባሕሉም ሕጉም ሊኖረን የግድ ነው፡፡ አሁን አንዳንድ ኮንዶሚኒየም በረንዳ ላይ ያልተቀመጠ ነገር የለምኮ፡፡ ከሰሉ፣ ማንደጃው፣ ዱካው፣ ባልዲው፣ መጥረጊያና መወልወያው፤ የልጆቹ መጨዋቻ፤ በዚሁ ከቀጠለኮ መጀመርያ በላስቲክ፣ ቀጥሎም በላሜራ ማጠር ይመጣል፡፡
ኧረ ምን እርሱ ብቻ፤ እንዴው ለመሆኑ እያንዳንዱ የኮንዶሚኒየም ወይም የአፓርትማ ነዋሪ የሱሉልታ የሳተላይት መቀበያ ጣቢያን የሚያህል ዲሽ መትከል አለበት? ለሁሉም የሚሆን አንድ ዲሽ መትከል፣ ያም ካልሆነ ደግሞ ውበትንም ቦታንም ሳያበላሽ የሚተከል የዲሽ መጠን ሊኖር አይገባም? ይኼንን በማዳበርያ ያደገ እንጉዳይ መስሎ የበቀለውን ዲሽ ማስቀረት የሚቻልበት መንገድ የለም እንዴ?
ለመሆኑ በጋራ መኖርያ ቦታዎች ላይ የሚቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች ምን ዓይነት መሆን አለባቸው? አንድ ሰው ቤቱን ለፈለገው ሁሉ ማከራየት ይችላል እንዴ? ቤት ማለት ግድግዳና ጣርያው ብቻ አይደለምኮ፤ ሠፈሩም ነው፤ አንድ ሰው ቤቱን የሚከራየው ሠፈሩንም ፈልጎ ነው፡፡ የዚያን ሠፈር መልክዕ የተወሰኑ ግለሰቦች በፈለጉት መንገድ መለወጥ ከቻሉ ለመኖርያ ቤት የተከራየው ወይም የገዛው ሰው የቀለጠው መንደር ውስጥ ሊገባ ነውኮ፡፡
ይኼ የቤት ጉዳይ መቼም ማለቂያ የለውም፡፡ እስኪ ለአከራዩና ለተከራዩ አንጀት፣ ለመንግሥትም ልቡና፣ ለመሐንዲሱም ጥበብ፣ ለሕግ አስከባሪውም ጥብዐት፣ ለደላላውም አእምሮ፣ ለባለ ገንዘቡም ኅሊና ስጭውና ተሳስበን እንድንኖር አድርጊን፡፡
ሰላም ለኪ፡፡
©ይህ ጽሑፍ በሳምንታዊው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በሌላ ፕሬስ ላይ ማውጣት ክልክል ነው