ኢትዮጵያ በአለም ላይ የምግብ ዋስትና እጥረት ካለባቸው አስር ዋና አገሮች ውስጥ አንዷ ነች ተባለ

የምግብ ዋስትና እጥረት የከፋ ደረጃ ላይ ካለባቸው አስር የአለም አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነች መባሉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬሽ የተባለው የዜና አውታር ዘግቧል።

የዜና አውታሩ እንደ ምንጭ የጠቀሰው ብሪታንያ በሚገኝ እና ሜፕልክሮፍት በተባለ ድርጅት፣ ከተባበሩት መንግስታት የአለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር፣ የሚዘጋጀውን አመታዊ የምግብ ዋስትና አደጋ መለኪያ ሪፖርት ነው። ሪፖርቱ ወደ ድምዳሜ ከመድረሱ በፊት አስራ ሁለት መመዘኛዎችን እንደሚጠቀም የታወቀ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ የእህል ምርት፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ የግብርና እና የማከፋፈያ መሰረተ ልማት አውታሮች ጥራት፣ ግጭቶች፣ እንዲሁም የመንግስት ብቃት የሚሉት ይገኙበታል። በዚህም አኳኋን በአለም ላይ አደገኛ የምግብ ዋስትና እጥረት ካለባቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ስድስተኛ ደረጃ ላይ አኑሯታል።

በዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር የምትገኘው ኢትዮጵያ በየአመቱ በሚወጡ የተለያዩ የድህነት እና የኑሮ ደረጃ መመዘኛዎች ላይ አሉታዊ ውጤቶች የምታስመዘገብ የአለም ጭራ መሆኗ ይታወቃል። የወያኔ አገዛዝ እድገትን እያስመዘገበ እንዳለ ሁልጊዜ ቢደሰኩርም በአገሪቱ ውስጥ ያለው እውነታ ግን ከዛ የራቀ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚገኙ ሪፖርቶች ማሳየታቸውን ቀጥለዋል።

በቅርቡ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና በተባበሩት መንግስታት ትብብር የተዘጋጀ የድህነት መለኪያ ሪፖርት በኢትዮጵያ ውስጥ ከአስር ሰዎች ዘጠኙ በድህነት ይማቅቃሉ ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል። ኒውስዊክ የተባለው ታዋቂ የአሜሪካ ጋዜጣ ከዛ ወዲህ ባወጣው ሪፖርትም፥ የመቶ አገሮችን የኑሮ ጥራት ደረጃ አነፃጽሮ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ውጤት በማግኘቷ 94ኛ ደረጃ ላይ እንዳኖራት ዘግበናል።