አባ ፊልጶስን ፍለጋ

click here for pdf

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ታላላቅ ሥራ ሠርተው ነገር ግን እጅግም ሳይታወቁ ያለፉ አባቶችና እናቶች አሉ፡፡ ዛሬ ላለንበት መሠረት የሆኑ፣ እምነታችን ሲቀዘቅዝ፣ ሞራላችን ሲናድ፣ ክብራችን ከራሳችን ላይ ሲወርድ፤ ለልባችን ብርሃን፣ ለቀቢጸ ተስፋችን መጽናኛ፣ ለባዶነታችንም መሙያ የሚሆኑ ድንቅ ሰዎች አሉ፡፡ ዐውቀው የሚያምኑ፤ ባመኑበት የሚጸኑ፣ ለጸኑበት የሚያስከፍላቸውን መሥዋዕትነት ሁሉ የሚከፍሉ፣ በጥብዐት የሚጓዙ፡፡ ሥልጣን ገንዘብ፣ ርስት፣ ክብርና ሹመት ያመኑበትንና የጸኑበትን የማያስለውጧቸው፡፡ የስቃይ ዓይነቶች፣ የመከራ ብዛቶች፣ የቅጣት ውርጅብኞች ከአቋማቸው የማያስበረግጓቸው፡፡ በአንድ በኩል መንፈሳውያን ከሚመስሉ ዓለማውያን፤ በሌላ በኩል ኃይልና ሥልጣን ከጨበጡ ነገሥታትና መኳንንት፤ በአንድ በኩል ለሆድ ካደሩ የቤተ መቅደስ ሰዎች፣ በሌላ በኩል ክብራቸውን ሽጠው ካደሩ መለካውያን ባለ ጊዜዎች ጋር የተጋደሉ አባቶችና እናቶች ነበሩን፡፡
አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ ከእነዚህ አንዱ ነበር፡፡ በ1266 ዓም አካባቢ ለት በምትባል ቦታ የተወለደው አቡነ ፊልጶስ ወደ ደብረ አስቦ (ደብረ ሊባኖስ) ገዳም የገባው በ15 ዓመቱ ነበር፡፡ በዚያ መጀመርያ ወደ ደብረ አስቦ ከገቡት 17 የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት አንዱ ነው፡፡ በዚያ ገዳም ቅዱሳት መጻሕፍትንና ምንኩስናዊ ሕይወትን ተምሮ ያደገው አባ ፊልጶስ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዕረፍት በኋላ በ1306 ዓም የደብረ ሊባኖስ ገዳም ሦስተኛው እጨጌ ሆነ፡፡

በእጨጌነት መንበሩ እያገለገለ እያለም አቡነ ያዕቆብ የተባለ ግብጻዊ ጳጳስ ወደ ኢትዮጵያ በ1330 ዓም ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ አቡነ ያዕቆብ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በሰሜንና በደቡብ የነበሩ አባቶችን በአሥራ ሁለት ሀገረ ስብከት እየከፈለ ለስብከተ ወንጌል ሥራ አሠማራቸው፡፡ በዚህም መሠረት የታላቁን ገዳም የደብረ ሊባኖስን ገዳም አባቶች በዚያን ዘመን ሸዋ ይባል በነበረውና በዳሞት ግዛት አሠማራ፡፡ አባ ፊልጶስንም የሁሉም አለቃ አድርጎ ‹‹ኤጲስ ቆጶስ›› ብሎ ሾመው፡፡
በዚህ ዓይነት አገልግሎት ላይ እያሉም ንጉሥ ዓምደ ጽዮን(1307-1337 ዓም) ከክርስቲያን ሕግ ወጥቶ ሦስት ሚስቶችን ማግባቱን ሰሙ፡፡ አቡነ ፊልጶስና ሌሎች አባቶችም ወደ ቤተ መንግሥቱ ሄደው ምክንያቱን ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹አንዳንድ ጥበብ ዐዋቂዎች ይህንን ብታደርግ መንግሥትህ ይጸናል ስላሉኝ ነው›› ሲል መለሰላቸው፡፡ እነርሱም ሌሎቹን ትቶ በአንዲት ሚስት እንዲጸና ነገሩት፡፡ ንጉሡ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በዚህም ምክንያት በአቡነ ፊልጶስ ይመሩ የነበሩት አባቶች አወገዙት፡፡ እርሱም አያሌ የመከራ መዓት በላያቸው ላይ አዝንቦ ወደ ዳር ሀገር እንዲሰደዱ አደረጋቸው፡፡(በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ነገር ከፈለጉ ረዥም ጊዜ በፈጀ ጥናት የተዘጋጀውንና በቅርብ ቀን የሚታተመውን ‹‹አራቱ ኃያላን›› የሚለውን መጽሐፍ ያንብቡ)
አቡነ ፊልጶስ በትግራይ ለሦስት ዓመታት ከተሰደደ በኋላ ዓምደ ጽዮን 1337 ዓም ሲያርፍ አቡነ ያዕቆብ ከዓምደ ጽዮን ቀጥሎ የነገሠውን ልጁን ዐፄ ሠይፈ አርዕድን(1337-1365 ዓም) ነግሮ ከስደት እንዲመለስ አደረገው፡፡ ንጉሡም በአንዲት ሚስት ጸንቶ ለመኖር ቃል ገባ፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ወራት በኋላ የንጉሡን ቀልብ ገዝቶ ርስትና ሹመት ለማግኘት የቋመጠ ‹ዘዐማኑኤል›› የተባለ ሐሳዊ መምህር ‹‹ለንጉሥ ሦስት ሚስት ማግባት በቅዱሳት መጻሕፍት ተፈቅዷል›› ብሎ ሠይፈ አርዕድን አሳሳተው፡፡ እነዚያው ጥቡዐን አባቶችም ይህንን ሲሰሙ ከያሉበት ወደ ቤተ መንግሥቱ ተሰባሰቡ፡፡ ንጉሥ ሠይፈ አርዕድንና ሐሰተኛውን መምህር ዘአማኑኤልንም ተከራከሩት፡፡
ንጉሥ ሠይፈ አርዕድ የአባቶችን ሃሳብ ከመቀበል ይልቅ አቡነ ያዕቆብን ወደ ሀገሩ ግብጽ መለሰው፤ አባቶችንም ደማቸው በከተማው ላይ እንደ ውኃ እስኪወርድ ድረስ አስገርፎ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ዝዋይ ደሴት እንዲጋዙ አደረገ፡፡ 
ከአራት ዓመታት በኋላ በ1341 ዓም አቡነ ሰላማ መተርጉም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የተሰደዱት አባቶች እንዲመለሱ ታወጀ፡፡ አቡነ ፊልጶስ ግን ‹የንጉሥ መሳሳት ሕዝቡንም ያሳስተዋልና ንጉሡ መታረም አለበት፡፡ ንጉሡን ለመገሠጽና ለማረም ካልቻልን እኛ መነኮሳት ሳንሆን ሹመት ፈላጊዎች ነን›› አለ፡፡ ንጉሡም ከስሕተቱ መመለስን እምቢ አለ፡፡ እንዲያውም አባ ፊልጶስን በገንዘብና በሹመት ሊደልለው ፈለገ፡፡ አባ ፊልጶስ ግን አልተቀበለውም፡፡ በመጨረሻም ንጉሡ የሚገዛውን ሀገር ለቅቆ እንዲሄድ ፈረደበት፡፡
አባ ፊልጶስ በ74 ዓመት ዕድሜው በስደትና በተጋድሎ በደቀቀ ጉልበቱ እያዘገመ ወደ ደብረ ሊባኖስ ክረምቱን ሊያሳልፍ መጣ፡፡ በወቅቱ የነበሩት የገዳሙ አባቶችም ‹‹ፊልጶስን ያስጠጋ ይቀጣል›› ተብሎ የወጣውን ዐዋጅ በመፍራት ገዳሙን ለቅቆ እንዲሄድ ነገሩት፡፡ እርሱም የአባቴ ገዳም ከሚበረበር ብሎ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ተሳልሞ ወጣ፡፡ ከዚያም በኋላ በሄደበት ሁሉ ዐዋጁ እየተከተለው የሚያስጠጋው በማጣት እህል እስከመራብ ድረስ ደርሶ ነበር፡፡
በመጨረሻ የንጉሡ ተጽዕኖ ከነበረበት ቦታ ርቆ ጌርጌስ ወደምትባል ቦታ ተጓዘ፡፡ በዚያም አቡነ ሰላማ መተርጉምን አገኘው፡፡ አቡነ ሰላማ ከጌርጌስ ወደ ሐቃሊት ለመጓዝ በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ አባ ፊልጶስም ‹‹ትተኸኝ አትሂድ›› ሲል ለመነው፡፡ አቡነ ሰላማ አባ ፊልጶስን በአልጋ ላይ አድርጎ በሸክም ወደ ደብረ ሐቃሊት ወሰደው፡፡ በዚያም እያለ በተወለደ በ74 ዓመት ከዘጠኝ ወሩ ሐምሌ 28 ቀን ዐረፈና በደብረ ሐቃሊት ተቀበረ፡፡
አብዛኛውን እድሜውን ላመነበት እምነቱና ላመነው አምላኩ ሲል የተንከራተተው፤ ማስፈራራት፣ ግርፋ፣ እሥራት፣ ራቁቱን በገበያ መካከል ታሥሮ መዞር፣ ለውሾች መሰጠት፣ ረሃብና ጥም፣ ስደትና ግዞት፣ ያልበገረው፡፡ ሹመትና ሽልማት፣ ርስትና ጉልት፣ ወርቅና ብር ከአቋሙ የማያዛንፈው ይህ አባት የት ነው የተቀበረው? ጌርጌስ የት ናት? ሐቃሊትስ የት ናት? እንዴት የርሱን ታሪክ ደግመን መሥራት ቢያቅተን ታሪኩን አሟልተን ለትውልድ ማስተላለፍ ያቅተናል? የሚል ጥያቄ ብዙ ጊዜ በውስጤ ነበረ፡፡ በተለይም ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ መዛግብት ስለ እርሱ የተጻፉትን መረጃዎች ሳይ የማወቅ ጉጉቴ ጨመረ፡፡
አንዳንድ ሊቃውንት ጌርጌስና ሐቃሊት በትግራይ ውስጥ እንደሚገኙ ገምተዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በወሎ ውስጥ ሳይሆኑ አይቀሩም ይላሉ፡፡ ገድሉና የደብረ ሊባኖስ መዛግብት ምንም አይነግሩንም፡፡ የመጀመርያው ችግር በወረራና በሕዝቦች ፍልሰት ምክንያት የጥንት የቦታ ስሞች መቀያየራቸውና መዘበራረቃቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊ የቦታ ስሞች ላይ የሠሩ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ሊቃውንት ስለ ጌርጌስና ደብረ ሐቃሊት የሰጡን ፍንጭ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ያለው አማራጭ በተጠረጠሩት ቦታዎች ላይ ፍለጋ ማካሄድ ነው፡፡
የመጀመርያው ፍለጋ የተካሄደው በትግራይ ነው፡፡ አባ በጸሎተ ሚካኤል ተሰድዶበት በነበረው አኩስም አካባቢ በነበረው በጉሎ ማክዳ፣ በኋላም ዐጽሙ አርፎበት በቆየው፣ ሌሎች ደብረ ሊባኖሳውያንም በስደታቸው ወቅት በቆዩበትና ከሕዝቡ ታላቅ አቀባበልን ባገኙበት በተንቤን አካባቢ ፍለጋውን አደረግኩ፡፡ ከሀገር ሽማግሌዎች ጠየቅኩ፡፡ የአካባቢውን መዛግብት አገላበጥኩ፡፡ ምንም ፍንጭ ግን አልነበረም፡፡
ሁለተኛው ፍለጋ የተደረገው በወሎ በተለይም ያን ጊዜ ከጥንቱ ሸዋ ጋር ቅርበት በነበረው በደቡብ ወሎ (የጥንቱ የአምሐራ ግዛት) አካባቢዎች ላይ ተደረገ፡፡ በአማራ ሳይንት፣ በቦረና፣ በአምባሰል ተፈለገ፡፡ ምንም ፍንጭ አልተገኘም፡፡ የጥንቱ የአንጎት ግዛት በነበረው የጁ ገባን፤ የለም፡፡ ላስታና መቄት ወረድን፤ ምንም አልነበረም፡፡ በዋድላና በደላንታ ዞርን አንዳች ፍንጭ ጠፋ፡፡
እንዲያ ደክሞት፣ በሰባ አራት ዓመት እድሜው፣ የንጉሥ ወታደር እያሳደደው፣ በየቦታው የሚቀበለው አጥቶ፣ ‹‹አቤቱ ይህንን በእኔ ላይ ያደረጉትን ግፍ ተመልከት፤ ግማሹ ውኃ፣ ግማሹም እህል ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን አልሰጡኝም፡፡ እነርሱ ግን በደስታ ይበላሉ ይጠጣሉ›› ብሎ ወደ ፈጣሪው እስኪያመለክት ድረስ በረሃብ አለንጋ የተገረፈው አባ ፊልጶስ የት ይሆን የገባው?፡፡
ገድሉን የጻፈለት የደብረ ሊባኖሱ ሰባተኛ እጨጌ ዮሐንስ ከማ ከዛሬ 500 ዓመታ በፊት ይህንኑ ጥያቄ ጠይቆ ነበር፡፡ ‹‹የዚህ ነገር ተመራማሪ እንዲህ አለ፡፡ ይህ ብጹዕ አቡነ ፊልጶስ ከሀገር ወደ ሀገር ሲሰደድ የተቀመጠው ጥቂት ጊዜ በመሆኑ ስለ ገድሉና ስለ ዘመናቱ የሚነግረኝ አጣሁ፡፡ ዜናውንም በማጣት ምክንያትም እያዘንኩና እየተከዝኩ ወደ ማደርያዬ ገባሁ›› ይላል፡፡
ጌርጌስ ሆይ የት ነሽ? የታላቁን ሰማዕት የአቡነ ፊልጶስን ዐጽም የተሸከምሽው ሐቃሊትስ የት ነሽ? በቀጣይ እንመለስበታለን፡፡