የወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር የሚገኙ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን የሚፈበርኩት ውሸት

በዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የሚፈበርኩት ውሸት ከአሳፋሪነት እያለፈ ነው ሲሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አወገዙ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ድረ-ገጽ በአፋር ክልል በመጪው አመት ትምህርት ቤት የሚገቡ ህፃናትን አስመልክቶ ያወጣው ዜና አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ድረ-ገጹ በመጪው አመት በአፋር ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህፃናት ትምህርት ቤት እንደሚገቡ እና ይህም በክልሉ ያለውን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ወደ ሃምሳ በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው ዘግቧል።

በራሱ በአገዛዙ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ባወጣው ቁጥር መሰረት የአፋር ክልል አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር አንድ ሚሊዮን አራት መቶ አስራ አንድ ሺህ ዘጠና ሁለት ነው። በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዘገባ መሰረት ግን በክልሉ ውስጥ ያሉት ህፃናት ቁጥር ብቻ ከሶስት እጥፍ በላይ የአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሩን ይበልጣል።

በተጨማሪም፥ እንደ ዜና አውታር ተብዬው ዘገባ፥ በመጪው አመት ትምህርት ቤት ሊገቡ የተዘጋጁት አምስት ሚሊዮን ህፃናት የክልሉን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ከፍ የሚያደርጉት ከ46 በመቶ ወደ 50 በመቶ፤ በአራት በመቶ ብቻ ነው። ይህ ማለት በአፋር ክልል ለትምህርት እድሜ የደረሱ ህፃናት ቁጥር 125 ሚሊዮን ነው ማለት ነው። ያ ደግሞ አሁን ካለው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እራሱ በአስርተ ሚሊዮን ይበልጣል።

ጉዳዩን በሚመለከት ለዝግጅት ክፍላችን ጥቆማን የላኩ ግለሰብ፥ በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ጉዳይ ከአሳፋሪነት አልፎ አስቂኝ ሆኗል ብለዋል። ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ከዚህ ቀደም የአንድ ክልል ቢሮ ሃላፊ በክልሉ ክትባት ወስደዋል የተባሉ ህፃናት ቁጥር ከክልሉ ህዝብ ቁጥር የበለጠ እንደሆነ የሚያሳይ ሪፖርት ቀርቦለት እንደፈረመው መስማታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህ የሃሰት ዘገባ ኢትዮጵያን ሪቪው በተባለ ድረ-ገጽ ላይ ከተጋለጠ የተወሰኑ ሰዓታት በኋላ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ምንም ማስተካከያ ሳያውጅ እና ይቅርታ ሳይጠይቅ ዘገባውን ከድረ-ገጹ እንዳስወገደ ለማወቅ ችለናል።