ወያኔ በስዊድን ያለውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መዝጋቱ ጸረ-ኢትዮጵያዊ አቋሙን የሚገልጽ ነው ተባለ
ዘረኛውና አምባገነናዊው መለስ ዜናዊ ረቡእ ነሐሴ 5 ቀን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ በስዊድን የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደሚዘጋ መናገሩ ይታወሳል። ጉዳዩን በሚመለከት አርብ እለት ለዝግጅት ክፍላችን መልክት የላኩ የፖለቲካ ተንታኝ ይህ የመለስ ውሳኔ ጸረ-ኢትዮጵያ አቋሙን የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል።
መለስ ዜናዊ ኤምባሲውን ለመዝጋት የወሰነበትን ምክንያት ሲገልጽ በስዊድን እና በኢትዮጵያ መካከል የልማት ትብብር እና ኢትዮጵያን የሚጠቅም ንግድ እንደሌለ ተናግሯል። ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን የላኩት የፖለቲካ ተንታኝ ስዊድን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ከመቶ አመት ያለፈ ግንኙነት ለአገራችን ከፍተኛ ውለታን መዋሏን አስታውሰው፤ መለስ በሁለቱ አገራት መካከል የልማት ትብብር የለም ማለቱን “ነጭ ውሸት” ብለውታል። አምባገነኑ እንደ ስዊድን ካለች የረዥም ዘመን ወዳጅ ጋር አገራችንን ለማቆራረጥ የወሰነው ውሳኔ የጸረ-ኢትዮጵያ አቋሙ መገለጫ ነው ብለዋል።
ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የኢትዮጵያውያን ድረ-ገፆች ላይ የወጡ ትንታኔዎች መለስ ዜናዊ ኤምባሲውን ለመዝጋት የተነሳሳበት እውነተኛው ምክንያት ስዊድን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ፣ በተለይም የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እስር በሚመለከት፣ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ጫና ማድረግ በመቀጠሏ ነው የሚል አመለካከት አዝለዋል።