የአዲስ አበባው ሸራተን ሆቴል በድህነት ኑሮ በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ማፈናቀሉን ቀጠለ

ካፒታል የዜና ምንጭ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው፤ ከዘረኛው የወያኔ ቆንጮ ባለስልጣናት ጋር ልዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ትስስር አለው የሚባለው የሸህ አላሙድን ንብረት የሆነው ሸራተን አዲስ በሆቴሉ አካባቢ ይኖሩ ከነበሩት ነዋሪዎች ጋር ለረዥም ጊዜ ሲካሰስበት የነበረውን 42 ሄክታር መሬት አሸንፎ የግንባታ ሥራውን እንደሚጀምር ታውቆአል። እንደ ካፒታል ዘገባ ከሆነ ስምምነቱ የተደረሰው ያካባቢው ነዋሪዎች ከፍላጎታቸው ውጭ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ወደተገነቡት ኮንዶሚኒየም ቤቶችና ወደተዘጋጁላቸው መሬቶች እንደሚሄዱ ቃል ከተገባላቸው በሗላ ነው። ያካባቢውን ነዋሪዎች ያናገረው ዘጋቢያችን እንደገለጸው ከዚህ ቀደም ሸራተን አዲስ በተገነባበት ወቅት የተፈናቀሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በድህነት አቅማቸው የፈለጉትን ሊያገኙና ልጆቻቸውን ለማስተማር አቅማቸው ወደማይችልበት የሲኤምሲ አካባቢ በመስፈራቸው እስከአሁን ድረስ ከነሙሉ ቤተሰባቸው እየተሰቃዩ መሆናቸውን ለሚየስታውስ ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ምን ያህል ለድሃው ህብረተሰባችን ደንታ እንደሌለው ያሳያል ብለዋል።

የሚፈናቀሉት ያካባቢው ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገባላቸው ማካካሻ በቂ አይደለም በማለት እሮሮ ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን የሚመለከታቸው የአራዳ እና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሃላፊዎች በየቀበሌው ጊዜያዊ መኖሪያ እናዘጋጃለን፣ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን እንድታገኙም ቅድሚያ እድል እንሰጣለን ካሉ በሗላ ጊዜያዊ ስምምነት ተደርሶ ነበር.፡ ይሁን እንጂ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለመግዛት የቤቶቹን 20 በመቶ ዋጋ ቅድሚያ መክፈል እንዳለባቸው ሲታሰብ ከአብዛኛዎቹ ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ አንፃር የማይታሰብ ከመሆኑም በላይ ባለፉት ሃያ አመታት ተመሳሳይ ቃል ተገብቶላቸው የተፈናቀሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የከተማይቱ ነዋሪዎች እስከዛሬም ድረስ ከዝናብም ሆነ ከብርድ ሊያስጥሉ በማይችሉ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እስከነ ህጻን ልጆቻቸውና ጧሪ የሌላቸው አዛውንት ቤተሰቦቻቸው ጋር ተጥለው የቁም ስቃይ ህይወት እየገፉ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ተችሎአል።

ከተፈናቃዮቹ አብዛኞቹ አሁን ለመልቀቅ በተገደዱበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ተወልደው ያደጉ እና የኑሮ መሠረታቸውንም እዚያው ያደረጉ እንደሚገኙ ሲታወቅ ለንብረታቸው ዋጋ በአሁኑ ሰአት ባለው የገበያ ሂሳብ እንዲገመትላቸው ቢጠይቁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግን ከዋጋ በታች እጅግ ያነሰ ካሳ እንዲቀበሉ ስለፈረደባቸው በምትኩ በተሰጣቸው ሌላ መሬት ላይ አዲስ ቤት ለመገንባት የማያስችላቸው መሆኑ ታውቋል። ከቦታው ከህሊና ግምት የበዛ ትርፍ ለማትረፍ ድሆችን እያባረረ ያለውና በአፍቃሪ ወያኔነቱ አንቱታን ያተረፈው የሸራተን አዲስ ሆቴል ባለቤት ሙሃመድ አላሙዲ ለቦታው ተገቢ የሆነውን ማካካሻ መክፈል እንዳለበት ህሊናው ያስገድደዋል ተብሎ የሚገመት ባይሆንም ለድሃው ቆሜያለሁ እያለ በቁጥጥሩ ስር ባሉት ሚዲያዎች ሌት ከቀን እየወተወተ ያለው የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ ተባባሪ በመሆን ካቅም በታች እንዲገመትና እንዳይሆን ማድረጉ የሚያሳየው ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፆች መሆናቸውን ነው ሲሉ ዘጋቢያችን አስተያየት የጠየቃቸው ነዋሪ ገልጸዋል።