ሥጋ፣ ኅሊናና ልቡና

በአሜሪካዋ ኮኔክቲከት ግዛት በሳንዲ ሁክ ትምህርት ቤት ሕጻናትና መምህራን ላይ የተፈጸመው ኢ ሰብአዊ ግድያ ሰሞኑን የዓለም መነጋገርያ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ጉዳዩን አሳዛኝና አሰቃቂ ያደረገው ደግሞ ምንም በማያውቁ ሕጻናትና በሥራ ላይ በነበሩ መምህራን ላይ የተፈጸመ መሆኑ ነበር፡፡ እነዚህ አካላት ከገዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ‹ጠብ ወይም ዝምድና› የሌላቸው፣ ለዚህ ቀርቶ ለቁጣ እንኳን የሚያበቃ ጥፋት በአጥፊው ላይ ያልፈጸሙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሕይወታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከማጣት አልታደጋቸውም፡፡
ምንም በማያውቁና በራሳቸው ዓላማ ምክንያት ተሰባስበው በሚገኙ ወገኖች ላይ የተኩስ እሩምታ እየከፈቱ ሕይወትን መቅጠፍ አሁን አሁን በዓለማችን እየተለመደ የመጣ ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኖርዌይ ሀገሪቱን ጸጥ ያሰኘ ግድያ በአንዲት ደሴት ተሰባስበው በነበሩ ተማሪዎች ላይ ተፈጽሞ ነበር፡፡ እምብዛም ይህን መሰል ወንጀል በማይሰማባት ቻይና እንኳን ሳይቀር በትምህርት ቤት ሕጻናት ላይ እሩምታ መክፈት እየተለመደ መምጣቱን የሚያሳዩ ድርጊቶች ብቅ እያሉ ነው፡፡ 

ምናልባት በጦር መሣርያ ላይ ያላቸው ሕግ መላላት ለዚህ መሰሉ አውሬያዊ ተግባር ጊዜያዊ መነሻ ይሆን እንደሁ እንጂ የሥር ምክንያቱ ግን አይመስለኝም፡፡ አሜሪካኖቹ የጦር መሣርያን በተመለከተ ያላቸው ባህልና ሕግ አዲስ አይደለም፡፡ ለብዙ ዘመን አብሯቸው የቆየ ነው፡፡ ይህ ባሕላቸውም የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የፊልሞቻቸውም ባህል ሆኖ አብዛኞቹ የአሜሪካ ፊልሞች መሣርያን እንደ ዋና ቅመም ይጠቀሙበታል፡፡
ባለፉት ሠላሳና ዐርባ ዓመታት ግን በአሜሪካ የጦር መሣርያን በመያዝ የሚፈጸሙ ጭፍጨፋዎች እየተባባሱ መምጣታቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ እነዚህ በጦር መሣርያ የሚደረጉ ግድያዎች ደግሞ ጠላትነትን ወይም የጥቅም ግጭትን መሠረት ያደረጉ አይደሉም፡፡ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች፣ የተደራጁ ወንጀለኞች አለያም ደግሞ ዘራፊዎች የሚፈጽሟቸው ዓይነቶችም አይደሉም፡፡ ከዚህ መሰሉ ተግባር ጋር ግንኙነት የሌላቸው ድንገት የሚነሡ ግለሰቦች ከውስጥ በሚመጣ ግፊት ተገፋፍተው የሚፈጽሟቸው ጭካኔዎች ናቸው፡፡
ነገሩን ዕንቆቅልሽ የሚያደርገውም ይኼው ነው፡፡
እዚህ ላይ እንደ ሰው ቆም ብለን መመርመር ያለብን ይመስለኛል፡፡ ዓለም አሁን በየትኛው የአስተሳሰብ ጎዳና ላይ ናት? የሚለውን፡፡ እንደ እኔ ዓለም አሁን ለቁሳዊ ነገርና ለቁሳዊ ዕድገት ታላቅ ቦታ የሰጠችበት ጊዜ ላይ ናት፡፡ የሰው ልጅን ሞራላዊና መንፈሳዊ እሴቶች የቀረጹት፣ ከሰው ጋር ተዋሕደው ህልው እንዲሆኑም ያደረጉት ተቋማት፣ ግለሰቦችና አስተሳሰቦች እየቀሩ፣ እየተረሱ፣ እየፈራረሱና፣ ቅርጻቸውንና ማንነታቸውንም እየቀየሩ፣ የሰውን ልጅ ቁስ ብቻ እንዲሆን አጋልጠው የሰጡት ይመስላል፡፡
የሰው ነባር ባህል፣ ማኅበራዊው መስተጋብር፣ እምነት፣ ሞራልና ሥነ ምግባር አሁን ባለው ዓለም ውስጥ የሚቃለሉ፣ የሚናቁ፣ የሚተቹ፣ የሚጥላሉ ብሎም ‹በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች እየሆኑ› ነው፡፡ ዕድገትና ሥልጣኔ ማለት መንፈሳዊና ሞራላዊ፣ ባህላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን የዘነጋ፤ በሚታይና በሚዳሰስ ነገር ላይ ብቻ የተመሠረተ ዕድገት እየሆነ ነው፡፡ የፎቆች ብዛት፣ የመንገዶች ርዝመት፣ የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የመገናኛ መንገዶች መወሳሰብ፣ የጤናና ማኅበራዊ ተቋማት መስፋፋት፣ ሀብት መፍጠርና ማካበት ብቻቸውን የዕድገት ማሳያዎች እየሆኑ ነው፡፡
‹እንበለ ሥጋ ኢትቀውም ነፍስ› ይባላልና ለሰው ልጅ ምቾትና ድሎት፣ ደኅንነትና ጤንነት የሚሆኑ ነገሮች መፈጠራቸው፣ መስፋፋታቸውና ማደጋቸው አይጠላም፡፡ ነገር ግን የሚያድገውም ሰው፤ የሚሠራውም ለሰው ነውና የሰውን ማንነት የዘነጋ መሆን የለበትም፡፡ ሰው ኅሊና፣ ልቡናና ሥጋ ያለው ፍጡር ነውና፡፡
ሥጋው በመብላትና በመጠጣት፣ በመልበስና በመዋብ፣ በመተኛትና በመንቃት፣ ጤናውን በመጠበቅና በስፖርት፣ በመወለድና በመሞት ይረካል፡፡ ይህ ግን በአብዛኛው ከእንስሳትና ዕጽዋት ጋር የሚጋራውና የእነርሱ ዘውግ መሆኑንም የሚያውቅበት ነው፡፡ በአብዛኛውም እነዚህን ለማድረግ ሰው መሆን ላያስፈልገው ይችላል፡፡
ኅሊናው በፍልስፍና፣ በጥበብ፣ በኪነ ጥበብ፣ በሰብአዊ ተግባራት፣ በማኅበራዊ ክዋኔዎች፣ ኃላፊነትን በመወጣት፣ ለሀገርና ለወገን በሚደረጉ ተግባራትና በፈጠራ ሥራዎች ይረካል፡፡ ከእንስሳት የሚለይበት፣ ከመላእክትም የሚለይበት ይህ ነው፡፡ መላእክት ልቡና እንጂ ኅሊና የላቸውም፡፡ ስለዚህም ውበትና፣ ሰብአዊነት፣ የፈጠራ ሥራና ክህሎት፣ ፍልስፍናና ርእዮተ ዓለም እነርሱ ጋር የለም፡፡ እነርሱ አካልና ልቡና ብቻ ነው ያላቸው፡፡ ያውም አካላቸውም ከእኛ የተለየ፣ ልቡናቸው ግን ከእኛ የሚመሳስል ነው፡፡
እዚህ ላይ ሰው በኅሊናው የሚደርስበት አንድ ነገር አለ፡፡ ዕውቀት፡፡ ዕውቀት ሲባል ደግሞ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን መኳተን፣ መፈተን፣ ማረጋገጥ፣ መተንተን፣ ችግርን በዕውቀት መፍታት፣ አዳዲስ ነገሮችን ለማግኘት መትጋትና መጣር፡፡ መሻሻልና ማሻሻል፡፡ ይህ ዕውቀት በልቡና ከሚገኘው ዕውቀት ይለያል፡፡ የልቡና ዕውቀት የመኳተን ዕውቀት ሳይሆን የተገልጦ ዕውቀት ነው፡፡ የአብርሖት ዕውቀት ነው፡፡ አንዴ የሚገኝ፣ ከዚያም የማይጠፋ፣ መርሳትም የሌለበት፣ ጊዜና ቦታም የማይወስነው ዕውቀት ነው፡፡  
የሰው ልጅ ልቡናው በአምልኮና በአብርሖት ዕውቀት ብቻ ነው የሚሞላውና የሚሠራው፡፡ የሚረካውም፡፡  ሰው ማንንም ያምልክ፣ ምንንም ይከተል ግን አምላኪ ፍጡር ነው፡፡ አምልኮቱም የተገዥነት አይደለም፡፡ የተገዥነት አምልኮት የእንስሳት ነው፡፡ የሰው ልጅ አምልኮ የመስተጋብር አምልኮ ነው፡፡ ከሚያመልከው ጋር መገናኘት፣ የሚያመልከውን መጠየቅ፣ መመርመርና ማወቅ፣ መረዳትና ማግኘት ይሻል፡፡ ከእርሱም ጋር መኖር ይፈልጋል፡፡
እንግዲህ ሰው ማለት እነዚህ ሦስቱ ያሉት ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልጉትም ፍጡር ነው፡፡ አሁን አሁን ግን በዓለም ላይ የሚነፍሱ አስተሳሰቦች ሰውን ቁሳዊ ወይም ሥጋዊ ብቻ እያደረጉት ነው፡፡ ለቁስ የሚኖር፣ በቁስ የሚመራ፣ በቁስ የተከበበና ቁስን ብቻ የሚከተል፡፡
ዓለምን ያስደመሙት የፈጠራ ሥራዎችኮ እየቀሩ ነው፡፡ መኪና፣ አውሮፕላን፣ ኮምፒውተር፣ ባቡር፣ ጨረቃ ላይ መውጣት፣ ስልክ፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቭዥን፣ አዳዲስ ዓለማትን ማግኘት፣ የተፈጠሩበትና ሰውን ጉደኛ ፍጡር ያሰኙበት ዘመናትኮ አለፉ፡፡ አሁን ፈጠራውም ‹ግብር እም ግብር ነው›፡፡ በሰዓት አሥር የሚጓዘውን መቶ ማስኬድ ነው፡፡ ያለውን መቀባባት፡፡ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች እኔ ባይ የሆኑ፣ ለሰው ልጆች በጎ መሆን የሚጨነቁ፣ ከግላዊ ጥቅም ባሻገር የሚያዩና ሕይወታቸውንም ለበጎ ሥራ የሚሠው ሰዎችን ይፈልጉ ነበር፡፡ ለዚህም ነው እነዚህን ነገሮች ያስገኟቸው ሰዎች አብዛኞቹ ‹ምኑን ሊቃውንት› የሆኑት፡፡ እነዚህ ኅሊና የነበራቸው ፣ ሥጋቸውንም ለኅሊናቸው ያስገዙ ሰዎች ነበሩ፡፡
ኅሊና ሥራውን እያቆመ ሲሄድ ግን ለምን እለፋለሁ? የሚል ትውልድ መጣ፡፡ አንድን ሳይንሳዊ ግኝት ለማግኘት አርባና ሃምሣ ዓመት ለምን ይለፋል? ሃያ አራት ሰዓትስ እንቅልፍ አጥቶ ለምን በሙከራ ክፍል ሲታትር ይውላል? በቀላሉ ሊደሰት፣ በቀላሉስ ገንዘብ ሊያገኝ፣ በቀላሉስ ሊኖር ሲችል፡፡ እነዚያ በዘጠና ደቂቃ በኢንተቬ፣ ካርቱም ሄዶ ቀረ፣ የኛ ሰው በደማስቆ፣ የስድስቱ ቀን ጦርነት በሚሉት መጻሕፍት ያነበብናቸው ለሀገራቸው የሚብከነከኑ እሥራኤላውያንኮ ዛሬ የሉም፡፡ ‹ለምን ከፊሊፒን ወታደር አንቀጥርም› የሚሉ እሥራኤላውያን ትውልዶችኮ መጥተዋል፡፡
ሰው መኖርን ከቁስ ነገር ጋር ብቻ ስላያያዘው የሚኖረው በዕድሜው ልክ ብቻ ሆኗል፡፡ ሰው ኅሊና ካለው ግን ከዕድሜው በላይ ይኖራል፡፡ ከዕድሜ በላይ ለመኖር ደግሞ ከዕድሜ በላይ ማሰብ ይገባል፡፡
የእምነት ተቋማት እምነትን ወደ ኩባንያ በመለወጣቸው፤ አርአያና አይከን የሚሆኑ የእምነት ሰዎች በመጥፋታቸው፣ በሌሎች የሚታዩት የሞራልና የሥነ ምግባር ድቀቶች በእምነት ተቋማቱም በመታየታቸው፣ ለብዙ ዘመንም በሂስና በጥላቻ በመብጠልጠላቸው ሰውን ልብ አልባ ፍጡር እያደረጉት ነው፡፡ በእምነት ሰዎችና ተቋማት ዘንድ ተከታይነት እንጂ መንፈሳዊነት በመጥፋቱ፤ ሩጫቸውንም ሰው ከማዳን ይልቅ የገበያ ውድድር ስላደረጉት፤ የሰው ልቡናና ሞራል ባለቤት አጡ፡፡
መንግሥትም ቢሆን ሕግ ያወጣል፣ ያስከብራል እንጂ የሰውን አእምሮ ሊቆጣጠርና ሊከታተል አይችልም፡፡ መንግሥት ከኅሊናና ከልቡና ውጭ ነው፡፡ ያማ ባይሆን የታሠሩ እሥረኞች ኅሊናቸውንም ማሠር በተቻለ ነበር፡፡ አካላቸው ወኅኒ ሲቀመጥ ኅሊናቸው ግን ‹በንፋስ ትከሻ ተጭኖ አየረ አየራቱን ይዋኛል›፤ ልቡናቸውም ወደላይ ወደ ፈጣሪ ይደርሳል፡፡ አንድን ሰው አካሉን እንጂ ኅሊናና ልቡን ማሠር አይቻልም፡፡ አካልን እንጂ ኅሊናና ልቡን መቅጣትም አይቻልም፡፡
እስካሁን በምድር ላይ ሰዎች የፈጠሯቸው ሥርዓቶችም ሆኑ ቴክኖሎጂዎች ሥጋን እንጂ ኅሊናን የሚገዙ አይደሉም፡፡ ሰውን በመድኃኒት እንዲወፍርና እንዲከሳ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሰውን በምንም ቁሳዊ ነገር ሃሳቡን እንዲለውጥ ማድረግ ግን አይቻልም፡፡ እንዲያውም ሰው አምባገነኖችንና በሃሳብ ልዕልና የማያምኑትን እንዲሸውድ ያደረገው ይህ ችሎታው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰው ውስጡን ውጩ እንዳይገልጠው ማድረግ ይችላልና፡፡ በመሪና በገዥ መካከል ያለውን ልዩነት የፈጠረውም ይህ ነው፡፡ መሪ ኅሊናን፣ ገዥ ሥጋን ብቻ ይገዛሉ፡፡
አሁን እየታየ ያለው ነገር ዓለም ከፍተኛ የኅሊናና የልቡና ኪሣራ ላይ መሆንዋን ያሳየናል፡፡ ቁሳዊ ዕድገቷ እስካሁን የነበረውን ኅሊናና ልቡና ተጠቅሞ እዚህ ደረጃ ደረሰ፡፡ ቁሳዊ ዕድገቱ ሲመነጠቅ ግን ኅሊናዊና ልቡናዊ ዕድገቱ ባለበት በመቆሙ፣ እንዲያውም ወደ እንስሳነት እንዲወርድ በመደረጉ አሁን ዓለምን ከኪሣራዋ ማዳን አልተ ቻለም፡፡ ቁሳዊም ዕድገቷ አሁን ባላት ኅሊናና ልቡና ከዚህ በላይ አይሄድላትም፡፡ ለዚህም ነው የዓለምን የኢኮኖሚ ቀውስ መፍታት ያልተቻለው፡፡ የኢኮኖሚ ቀውሱ በኢኮኖሚ አስተሳሰቦች ብቻ ሳይሆን ኅሊናዊና ልቡናዊ ብርሃን ባላቸው አስተሳሰቦች ጭምር ሊፈታ ስለሚገባው፡፡
ከሰው ልጅ ሕይወት ኅሊናና ልቡና በመራቃቸው በመግደል የሚደሰቱ፣ ያለ ተፈጥሯቸው በሚኖር ተራክቦ የሚረኩ፣ የሰውን አካል በመቸብቸብ የሚከብሩ፣ የጥፋት ነጋዴዎች እንዲበረክቱ አድርጓቸዋል፡፡ ዓለም ከዘመናት በፊት በኋላ ቀርነት ውስጥ ሥልጣኔን ትታትር ነበር፡፡ እናም ሥልጣኔ ረትቶ ኋላ ቀርነት ተሸነፈ፡፡ አሁን ግን በሥልጣኔ ውስጥ የሚታትር ድብቅ ኋላ ቀርነት እየታየ ነው፡፡ ምንጊዜም ደግሞ የተደበቀ ያሸንፋል፡፡
በእኛ ሀገር እንኳን በልጆችና በእኅቶች ላይ የሚፈጸሙት አደጋዎች መብዛት የኛም ማኅበረሰብ ከልቡናዊነትና ከኅሊናዊነት እየወረደ መሆኑን እያመላከተን ነው፡፡ ሰዎች በጎ ሠሩ የሚለውን የእምነት ሰዎች ታሪክ ንቆና አቃልሎ የተወው ትውልድ፣ ሰዎች ሲጋደሉና ‹መግደል ያባቴ ነው› ብለው ሲፎልሉ የሚያሳየውን የመገዳደል ፊልም ያደንቃል፡፡ ለእርሱም ጀግኖቹ እነዚያ በፊልሙ ላይ ያያቸው የእሩምታ ተኩስ የሚነሠንሱት ናቸውና እርሱም ‹እኔም እንዳይዬ› ብሎ እየወጣ በሕጻናቱ ላይ ቢነሰንሰው ምን ይገርማል?
በተለይ ደግሞ ‹ከለማበት የተጋባበት› ይብሳልና ምዕራባዊውን የኑሮ ዘይቤ እንዳለ በሚገለብጥ ማኅበረሰብና፣ እርሱንም እንደዘመናዊነት በሚቆጥር ሕዝብ መካከል ችግሩ ከዚያኛውም የባሰ ይሆናል፡፡ እናም ዓለም ከወረደችበት ሥጋዊ ጠባይ ከፍ ብላ ኅሊናዊና ልቡናዊ ጠባዮቿንም እንደገና ገንዘብ ካላደረገች ማንም ነሽጦት የተነሣ ሁሉ ዛሬ ጥይት እንዳርከፈከፈው ሁሉ፤ ነገ የነሸጠው መሪ ኑክሌርን ቢያርከፈክፍብን የማን ያለህ እንላለን፡፡
ማስተዋሻ
ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው