ወርቅ የማይገዛው አገልግሎት

photo from (http://www.africaboundadventures.com)

እነሆ ሻንጣዬን እየገፋሁ ወደ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመጓዝ ላይ ነኝ፡፡ ለመንገደኛ መግቢያ ከተዘጋጁት በሮች ሁለቱ ብቻ ይሠሩ ስለነበር የገቢ መንገደኛው ሰልፍ አስፓልቱን አቋርጦ ወደ ሣሩ ደርሷል፡፡ ምስጋና በፍተሻው ላይ ለተሠማሩት ባለሞያዎች ይድረሳቸውና ጥንቃቄው እንደተጠበቀ ሆኖ እንግዶችን በፍጥነት ለማስተናገድ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር፡፡
ተፈተሽንና ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መስኮት ደረስን፡፡ ትኬታችንን አሳየንና ሻንጣዎቻችን አስረከብን፡፡ በመስኮቱ ጀርባ ለምታገለግለው የአየር መንገዱ ባለሞያ ወቅቱ የገና ጾም ወቅት ስለሆነ የጾም ምግብ ማስመዝገባችንን ገለጽንላት፡፡ እርሷም መልከት አለችና ‹‹ምንም ችግር የለውም›› አለችን፡፡ ‹‹የጾም ምግብ አለ ማለትሽ ነው›› ስንል የማረጋገጫ ጥያቄ አቀረብን፡፡ ‹‹ችግር የለውም አታስቡ›› አለችን ፈገግ ብላ፡፡
አንድ የስድስት ኪሎ ወዳጄ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያለን እንዲህ የሚል ግጥም አቅርቦ ነበር
አንድ ችግር አለ የችግር ካንሠር
‹ምንም ችግር የለም› የሚሉት ችግር
አንድ ሌላ ወዳጄም ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ‹ምንም ችግር የለም› በሚለውና ‹ችግር አለ› በሚለው መካከል ያለው ልዩነት የቃላት ብቻ ነው›› ብሎኝ ነበር፡፡ 

የኢሚግሬሽንን መሥመር አልፈን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ የአውሮፕላኑ የመነሻ ሰዓት ደረሰና ወደ ውስጡ ዘለቅን፡፡ እዚያም ተቀምጠን የሚነሣበትን ጊዜ በጉጉት መጠበቅ ጀመርን፡፡ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ይወጣሉ ይገባሉ፡፡ ወዲህ ይመጣሉ ወዲያ ይሄዳሉ፡፡ የመነሻ ሰዓቱ እያለፈ ነው፡፡ ማንም ግን ምን እየሆነ እንደሆነ አይገልጥላችሁም፡፡ ዝም ብላችሁ እንድታስቡ፣ ከቻላችሁም እንድትጠነቁሉ ተፈርዶባችኋል፡፡ ዝርዝር ምክንያታቸውን ባይገልጡልን እንኳን ‹በአንዳንድ ምክንያቶች አውሮፕላኑ ጥቂት ይዘገያል› ማለት የእናት ነበር፡፡ ‹ፓይለቱም ዝም፣ ሆስተሱም ዝም›
ወደ አርባ ደቂቃ ያህል ተቀመጥን፡፡ ለምን እንደተቀመጥን፤ ከዚህ በኋስ ምን እንደሚደረግ የሚነግረን አልነበረም፡፡ በመጨረሻ ‹በመዘግየታችን ይቅርታ› አለና የአውሮፕላን አብራሪው ነገረን፡፡ ‹ዘግይቶ የደረሰን ዜና› አለ የኢትዮጵያ ሬድዮ፡፡
እንደወጉና እንደ ደንቡማ አውሮፕላኑ የሚዘገይ ከሆነ ከወዲያ ማዶ ቤተሰቦቻቸው ለሚጠብቋቸው አካላት መናገር ይቻል ዘንድ ምን ያህል እንደሚዘገይ፣ ለምን እንደሚዘገይና ምን ማድረግም እንደሚገባን አስቀድሞ መናገር ይገባ ነበረ፡፡ ደግሞ ደግነት ከተጨመረበት ሰው ያለ ምክንያት ሲቀመጥ ይጨንቀዋልና ቢያንስ የእግዜር ውኃ እያዞሩ ማደል ይገባ ነበረ፡፡ ‹ጽድቁ ቀርቶ› አለች አክስቴ፡፡
አውሮፕላኑ እንደምንም ተነሣ፡፡ ብዙዎቻችን ከዚያ በኋላ በረራ የምንቀጥልባቸው መሥመሮች ሳይሄዱ ይጠብቁናል? ካልጠበቁን ምን እናደርጋለን? እያልን እንወያይ ነበር፡፡ አንዳንዶች ጠንከር ብለው ጆሃንስበርግ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ ችግሩን እንደሚፈታላቸውና በመዘግየቱ ለሚፈጠረው መሰናክልም አንዳች ነገር እንደሚያደርግ እምነታቸውን በጽናት ይገልጡ ነበር፡፡ ‹ያመኑት ፈረስ ጣለ በደንደስ› እንዳይሆን እንጂ፡፡
ከወደ ኋላችን የበረራ አስተናጋጆቹ ምግብ እያደሉ መጡ፡፡ እኛጋ ሲደርሱ ‹የጾም ምግብ አዝዘን ነበር› አልናቸው፡፡ ቦርዲንግ ፓሳችንን ተቀበሉንና ተጓዙ፡፡ ከዚያም ተመልሰው በኛ ቁጥርና ስም የተመዘገበ ምግብ እንደሌለ ገለጡልን፡፡ ‹ምንም ችግር የለም የሚሉት ችግር› ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ትኬት በቆረጥንበት ቦታ ይህንኑ መግለጣችንን፤ ቦርዲንግ ፓስ ስንወስድም ማሳወቃችንን ሁለቱም ቦታ ምንም ችግር እንደሌለውና እንደተስተካከለ እንደተገለጠልን ነገርናቸው፡፡ ግን እነርሱ ምን ያድርጉ፡፡
ለባለቤቴ በአስተናጋጆቹ ፈቃድ እንደምንም ተፈልጎ የሚበላ ነገር ተገኘ፡፡ እኔ ግን ስምንተኛውን የአየር መንገድ ጾም እንድጾም ተፈረደብኝ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ ነኝ፡፡ ያውም የሼባ ማይልስ የወርቅ አባል፡፡ በአየር መንገዱ ስጓዝ ወርቅ የማይገዛቸው ብዙ ነገሮች ያጋጥሙኛል፡፡ አንዱ የጾም ምግብ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አስመዘ ግባለሁ፡፡ ለምን ቦርዲንግ ፓስ ላይ አትጽፉልኝም? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ መሬት ላይ ያሉት የትኬት ቢሮዎች ግን ሁልጊዜም የሚሉኝ ‹ችግር የለም›› ነው፡፡ በተለይ መነሻዬ አዲስ አበባ ከሆነ፡፡
እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ላይ አሜሪካ ቨርጂንያ ያለው የትኬት ቢሮ የተሻለ ሥራ ሲሠራ አይቼዋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ በታወቁ ታላላቅ አጽዋማት ጊዜ የጾም ምግብ እንዲጫን በማድረግና በተለይም ለሽማግሌዎችና እናቶች በማቅረብ ሲያገለግሉ አይቻለሁ፡፡ አዲስ አበባ ግን ‹ችግር የለም›፡፡
እኔ ና ወዳጆቼ ይህን የአየር መንገድ ጾም ‹ስምንተኛው ጾም› እንለዋለን፡፡ ከኅዳር 15 እስከ ታኅሣሥ 29፣ ከዘወረደ እስከ ፋሲካ የሚጾም አይደለም፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ቀጣዩ የበረራ መዳረሻ የሚጾም ጾም ነው ‹ስምንተኛው ጾም›፡፡ የዐዋጅም የፈቃድም፣ የቀኖናም አይደለም፤ የስንፍና ጾም ነው፡፡
በ2ኛው መክዘ ተነሥቶ የነበረው መርቅያን የተባለው መናፍቅ ቅዳሜ መጾም አለባት የሚል ትምህርት ነበረው፡፡ ታድያ የአንድ የሀገራችን ባለቅኔ ቅዳሜ ቀን የሚበላው እጥቶ በተቀኘው ቅኔ
‹ቅዳሜን እንደ ረቡዕ ቀን አድርጌ ጾምኳት
መርቅያን በዐመጽ ነው እኔ ግን በማጣት›
ብሎ የተቀኘው እንዲህ ያለ ነገር ገጥሞት ነው ለካ፡፡ እነሆ በስምንተኛው የአየር መንገዳችን ጾም በዕለተ እሑድ ጦሜን ዋልኩ እላችኋለሁ፡፡ የሀገሬ ሰው ‹በሰንበት ጦም አይዋልም ቅጠልም ቢሆን መቅመስ ያስፈልጋል› ይላል፡፡ በአየር ላይ ምን ቅጠል ይገኛል፡፡ ቅጠል ቢኖርም ሰላምታ መጽሔት ላይ ብቻ ነው፡፡
የአምስት ሰዓቱ መንገድ አለቀና ጆሀንስበርግ ደረስን፡፡ እዚያ ስንወርድ አንድ ሰዓት ያህል ዘግይተን ነበር፡፡ በመዘግየቱ ሊረዳን የመጣ አንድም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰው አልነበረም፡፡ እኔ ብዙ ጊዜ ወደ አሜሪካ በርሬያለሁ፡፡ የበረራ መዘግየት ሲፈጠር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች እንደ ጉንዳን ሠራዊት በሚያስደንቅ ፍጥነት ችግሩን ለመፍታት ላይና ታች ሲሉ ነው የምታዩዋቸው፡፡ ያውም ምሳ ጋብዘው፣ ዕቃ ተሸክመው፡፡ እዚህ ያሉት ግን ‹በቅተው› ተሠውረዋል፡፡
ዕቃችንን ተቀብለን ወደ ኬፕታውን የሚወስደውን አውሮፕላን ፍለጋ ወደ ብሪትሽ አየር መንገድ መስኮት ሄድን፡፡ ‹መድረስ ከነበረባችሁ ጊዜ እጅግ ዘግይታችኋል፤ ይህን ችግር መፍታት ያለበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነውና ወደ እነርሱ ሂዱ›› የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ መስኮት ያለበትን ቦታ ፍለጋ ያዝን፡፡ በአውሮፕላን ማረፊያው በሚገኙ ሠራተኞች ተባባሪነት የኢትዮጵያ አየር መንገድን መስኮት አገኘነው፡፡
በመስኮቱ ጀርባ አንዲት (ምናልባት ደቡብ አፍሪካዊት) ሠራተኛ ወንበሯ ላይ ለጠጥ ብላ፤ ሌላዋ ደግሞ የሻንጣ መመዘኛው ላይ ተቀምጣ እያወጉ አገኘናቸው፡፡ ያጋጠመንንም ችግር ነገርናቸው፡፡ እነርሱ ምንም ሊረዱን እንደማይችሉ፣ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ ብንሄድ መልካም መሆኑን ምክር ሰጡን፡፡ ‹ወይ ምክር መቀበል፣ ወይ ምክር መስማት› አሉ መንግሥቱ ለማ፡፡ እኛ ምን አማራጭ አለን፤ ቢሮውን ፍልጋ ከመንከራተት በቀር፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቢሮ ከፍለጋ በኋላ ስናገኘው ዝግ ነው፡፡ ምን እናድርግ? አሁን ችግሩን ለመፍታት በመንከራተት ሌላ አንድ ሰዓት ጨምረናል፡፡ በአካባቢው ያሉ ሌሎች ሠራተኞች ‹ብዙ ጊዜ ውስጥ ሆነው ስለሚዘጉት አንኳኩ› አሉንና በመስኮቱ በኩል ማንኳኳት ቀጠልን፡፡ እዚህ ግን ‹አንኳኩ ይከፈትላችኋል› አይሠራም፡፡ ችግሩን የፈጠረው አየር መንገድ ችግሩን ለችግረኞቹ አሸክሞ በሩን ዘግቶ ሄዷል፡፡ አዲስ አበባ አንድ ሽሮ ቤት ውስጥ ‹ቤቷን ዘግታ የምትዘፍን› የሚባል ሽሮ ማየቴን አስታወስኩ፡፡
አሁን የችግሩ ሰለባዎች ከሃያ በላይ ሆነናል፡፡ ሁሉም ፊቱ በንዴት ጦፏል፡፡ ማዘግየታቸው ሳያንስ ቢሯቸውን ቆልፈው መጥፋታቸው፤ ሌሎቹ አየር መንገዶች ችግራችን ለመፍታት ከኛ ጋር ላይ ታች ሲሉ የችግሩ መነሻ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ‹ከመረቁ አውጡልኝ፣ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ›  ማለቱ ያላናደደው አልነበረም፡፡ አንዳንዶች ሰማያዊ፣ ሌሎች ብርማ ሌሎችም ወርቅማ የሆነውን የአየር መንገዱን የደንበኛነት ካርድ ጥቅም በመጠየቅ ላይ ነበሩ፡፡ እንዲያውም አንድ መንገደኛ ‹ ወርቅ ይህን ችግር ያለበት አገልግሎት ከሆነ የሚገዛው፤ ወርቅ ምን ጥቅም አለው?›› ሲል ነበር የጠየቀው፡፡
ተመልሰን ወደ ብሪቲሽ አየር መንገድ ቢሮ መጣን፡፡ እዚያ ያገኘናቸው ኃላፊ ‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከእነርሱ ጋር ይህን መሰሉን ነገር ለመሥራት የነበረው ውል ማለቁን፡፡ ራሳቸው ነገሩን ለማከናወን መወሰናቸውን፤ ነገር ግን ችግሩ በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን› በምሬት ይናገሩ ነበር፡፡ አሁንም አሁንም ከኃላፊዎቻቸውና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ ጋር ይደዋወላሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስልክ ግን ሠራተኞቹ አለመኖራቸውን ነው የሚናገረው፡፡
ለሁለት ሰዓታት ያህል ከተጉላላን በኋላ የብሪቲሽ አየር መንገድ ሰዎች በሦስት በረራ ሊያስተናግዱን ወሰኑ፡፡ በ11 ሰዓት፣ በ12 ሰዓትና በ1 ሰዓት በረራዎች፡፡ ከሃያ የሚበልጡት የበረራ ተስተጓጓዮች እንደ ዕድል ፈንታቸው እየተስተናገዱ ወደ ቦርዲንግ ፓስ መቀበያዎች ማምራት ጀመሩ፡፡
ከሁለት ሰዓት በረራ በኋላ ኬፕታውን ስንደርስ የአየር መንገድ ስምንተኛው ጾም ከ12 ሰዓት በላይ ሆኖት ነበር፡፡ ሊቀበሉን የተዘጋጁት ሄደው፡፡ እንደገና እነርሱን ለመጥራት ወደ አንድ ሰዓት ጠብቀን፤ ለደቡብ አፍሪካውያን የአውቶቡስ ሾፌሮችም ‹የዘገየነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግር ምክንያት ነው› ብለን አየር መንገዳችንን ለማማት አፍረን የቆጥ የባጡን በመቀባጠር ማረፊያችን ደረስን፡፡
እኛ እንደ እሥራኤል ጉዞ ተሰቃይተን ስንደርስ ምናልባትም የጆሃንስበርግ የአየር መንገዱ ቢሮ ‹የዛሬው በረራ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል›› ብሎ ሪፖርቱን እየጻፈ ይሆናል፡፡
ኬፕ ታውን፣ ደቡብ አፍሪካ