‹ሁሉም ወደየበኣቱ ይመለስ›
click here for pdf
በአንድ ገዳም የነበሩ አበው አንድ ጉዳይ ይገጥማቸውና ከየበኣታቸው ወጥተው በገዳሙ ዐውደ ምሕረት ላይ ይከራከራሉ፡፡ ክርክሩ ወደ መጋጋል ይሄድና ኃይለ ቃል መውጣት ይጀምራል፡፡ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ አረጋውያን አባቶች ወጡና በየወገኑ የነበሩ ተከራካሪዎችን ሊያስማሟቸው ሞከሩ፡፡ ነገር ግን የሚያስማማ ሃሳብ ማምጣት አልቻሉም፡፡ በዚህ ጊዜ በገዳማውያኑ ዘንድ በብቃታቸው የሚታወቁ አንድ አባት ከበኣታቸው በር ላይ ቆሙና ‹በሉ ሁላችሁም ወደየበኣታችሁ ግቡ፤ ከዚያ በኋላ ለክርክራችሁ መፍትሔ ታገኛላችሁ› ሲሉ ተናገሩ፡፡
እርሳቸው እንዳሉትም ሁሉም ገዳማውያን ወደየበኣታቸው ገቡ፡፡ ወደ ዋሻው የሚገባም ገባ፤ ወደ መቅደስ የሚሄድም ሄደ፤ ወደ ምርፋቅ የሚሄድም ሄደ፤ ወደ ተግባር ቤት የሚሠማራም ተሠማራ፤ ወደ እርሻም የሚሄድ ሄደ፡፡ ያን ጊዜም ማዕበሉ ጸጥ አለ፡፡ ዐውደ ምሕረቱም ዐውደ ምሕረት ሆነ፡፡ ሁሉም ገዳማዊ ወደ በኣቱ ተመልሶ በረጋ ኅሊናና ነገሩን ማሰላሰል ጀመረ፡፡ አንዳንዱ በማያውቀው፣ አንዳንዱ በማያገባው፣ አንዳንዱ መልካም የሠራ መስሎት፣ አንዳንዱ ለሌላው ሰው ደጋፊ በመሆን፣ አንዳንዱ ያለ ችሎታው ነበር በነገሩ የገባው፡፡
ሁለትና ሦስት የጸጥታ ቀናት አለፉ፡፡ ሁሉም ሰው ወደ ልቡ ተመለሰ፡፡ እኒያ አባትም ሁሉም ከሄደ በኋላ የሚገባቸውንና የሚያገባቸውን የገዳሙን ሰዎች ጋበዙ፡፡ የገዳሙን አበ ምኔት፣ ሊቀ አርድዕቱን፣ መጋቢውን፣ ገበዙንና የአብነት መምህሩን ጠርተው በተነሣው ጉዳይ ላይ ተነጋገሩበት፡፡ መነጋገርም ብቻ ሳይሆን ተግባቡ፡፡ ገዳሙም ከነ ሰላሙ ቀጠለ፡፡
‹ሁሉም ወደየበኣቱ ይመለስ›
በቤተ ክርስቲያን ሞገድና ማዕበል ሲነሣ የሚያዋጣው ‹ሁሉም ወደየበኣቱ ይመለስ› ብሎ መጮህ ነው፡፡ አሁን የዕርቀ ሰላ ጉዳይ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል በቅዱስ ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አይደለም ውይይቱ እየተደረገ ያለው፡፡ በሕዝብ አደባባይ ነው፡፡ አቡነ እገሌም፣ እነ እገሌም፣ የሚናገሩት በዚህ ወይም በዚያ ሬዲዮ፣ በዚህ ወይም በዚያ ብሎግ፣ በዚህ ወይም በዚያ መግለጫ ሆኗል፡፡
አሁን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ወደ በኣታቸው ይግቡ፡፡ የመግለጫውን ጋጋታ ትተው ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ገብተው ይወያዩ፤ ሃሳባቸውን ያቅርቡ፣ ይከራከሩ፡፡ እዚህ ወይም እዚያ መግለጫ ማውጣቱ ነጥብ ከማስቆጠር ውጭ ችግሩን አይፈታም፡፡ ችግሩን የሚፈታው ወደ በኣት ገብቶ መጀመርያ የጸጥታ ጊዜ ከወሰዱ በኋላ ነገሩን በምልዐተ ጉባኤ ማየት ነው፡፡
ከፊታችን የታላቁ የቅዱስ ገብርኤል በዓል ይከበራል፡፡ ይህ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ይህንን ጊዜ የጸሎትና የመረጋጋት ጊዜ አድርጎ መጠቀም ነው፡፡ ከዚያም ሁሉም አባቶች ወደ በኣታቸው ገብተው ይወያዩ፡፡ የአባቶች የመወሰኛ መድረክ የቅዱስ ሲኖዶስ አዳራሽ እንጂ ሚዲያዎቹ አይደሉም፡፡
አሁንም ሌሎቹ ሁሉ ወደየበኣታቸው ይግቡና ቅዱስ ሲኖዶስ ከልዑካኑ ጋር በጋራ የሚሠሩ ሊቃውንትን ይመድብ፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ከቤተ ክርስቲያን ሕግና ታሪክ፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ልምድ፣ ከሀገሪቱ ሕጎች፣ ያኔ ችግሩ ሲነሣ ከተፈጠሩት ክስተቶች አንጻር አማራጭ ሃሳቦችን የሚያቀርቡ፣ ልዑካኑን በቴክኒክ የሚያግዙ፣ የልዩነት ጉዳዮችን ቀድመው አውቀው መፍጥሔ የሚጠቁሙ መሆን አለባቸው፡፡
ከእነዚህ ሊቃውንት መካከል ሂደቱን ለታሪክና ለሪፖርት የሚመዘግቡ፣ ለሚመለከታቸው አካላት ወጥ የሆነ መግለጫ የሚሰጡ፣ የልዑካኑን መዛግብት የሚይዙ፤ ቦታውንና ሂደቱን አስቀድመው አይተው መንገድ የሚጠርጉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አስታራቂ ኮሚቴውም ወደ በኣቱ ይግባ፡፡ በባህሉም ሆነ በእምነታችን ለማስታረቅም ሆነ ለማግባባት ልምድና ችሎታ፣ ብቃትና ታማኝነት፣ ገለልተኛነትና ብስለት ይጠይቃል፡፡ ምንም እንኳን በጎ ዓላማ ቢኖር በጎውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ግን ለዓላማው ብቁ የሆነ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ዘሩ መልካም መሆኑ ብቻ እንዲያፈራ እንዳላደረገው ወንጌል ነግሮናል፡፡ መሬቱ መልካም ባለመሆኑ ምክንያት ከተዘሩት አራቱ ዘሮች ሦስቱ 75% ሳያፈራ ቀርቷል፡፡ የዕርቁም ሃሳብና ዓላማ ምንም መልካም ቢሆን የአስታራቂዎቹ ብቁና መልካም መሆን አለመሆን ግን ለፍሬያማነቱ ወሳኘ ነው፡፡
ሲሆን ሲሆን ምንም አስታራቂ አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን አመቻማች (facilitator) ካስፈለገ ሁለቱም አካላት በጋራ ሊሰይሙ ይችላሉ፡፡ አሁን ያለው አስታራቂ አካል ገለልተኛነቱ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡ የተለያዩትን አንድ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ ጭራሽ አንድ የሆኑትን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከፊሎቹን ‹ጥቂት የቅ/ሲኖዶስ አባላት› እያለ ‹የመንጋው እንባና ጩኸት የማይገዳቸው ጥቂት የሲኖዶስ አባላት› ብሎ ሲዘልፋቸው ሌሎቹን እያሞገሰ ይከፋፍላቸዋል፡፡
ለአንድ አመቻማች ወይም አስታራቂ አካል ደግሞ ትልቁ መመዘኛ ገለልተኛነቱ ነው፡፡ ሰሞኑን አስታራቂው ራሱ ያወጣውን የቅዱስ ሲኖዶስን አባላት የዘለፈበትና የከፋፈለበት መግለጫ እንደሚያሳየው ይህ አካል አመቻማች ሳይሆን እንደ ጸጥታው ምክር ቤት የበላይ አካል ሆኖ የሚቆጣጠርና የሚያዝ ሆኗል፡፡ ‹በዚህ ቀን ተሰብሰቡ፣ በዚህ ቀን አትሰብሰቡ፣ እኔ ሳልመጣ አትሰብሰቡ፣ እነ እገሌ እረፉ፣ ተጠንቀቁ› የሚል አካል ሆኗል፡፡ ሂደቱንም በሀገር ቤትና ከአሜሪካ ውጭ ካሉት አባቶችና ምእመናን ዕውቅናና ሱታፌ ውጭ አድርጎታል፡፡
ስለዚህም ወደ በኣትህ ተመለስ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የዕርቁን ሂደትም ሆነ የአስታራቂዎቹን ማንነት፣ የዕርቁንም ቦታ ቅዱስ ሲኖዶስ በድጋሚ ቢያየው፣ ቢመረምረውና ቢያርመው መልካም ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ ካለችበት አጣብቂኝ አንጻር የተለያዩ ሃሳቦች ሊሠነዘሩ ይችላሉ፡፡ ይህ በትክክለኛው መንገድ ከመጣ፣ የራስን ሐሳብ በኃይልና በሥልጣን በሌላው ላይ ለመጫን የሚደረግ ነገር ከሌለ፤ የሃሳቦች ከየቦታው መሰጠት ቤተ ክርስቲያኒቱን ይጠቅማታል እንጂ አይጎዳትም፡፡ እንዲያውም ቅዱስ ሲኖዶስ እነዚህ ሃሳቦች እንዲፋጩ አድርጎ የተሻለውን ለመምረጥ ያስችለዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን በሚከሰቱ ፈተናዎች በአባቶችና በሊቃውንት ዘንድ ሃሳቦች ሲለያዩ ይህ የመጀመርያው አይደለም፡፡ በ13ኛውና በ14ኛው መክዘ በቤተ ክርስቲያን የሰንበትን አከባበር በተመለከተ በአባቶች መካከል የሐሳብ ልዩነቶች ነበሩ፡፡ ቤተ ኤዎስጣቴዎሳውያን የሚባሉት አበው የሁለት ሰናብትን መከበር ሲደግፉ ቤተ ተክለ ሃይማኖታውያን ደግሞ የአንድ ሰንበትን መከበር ይደግፉ ነበር፡፡
ይህ ሃሳብ በአባቶች መካከል ሲንሸራሸር መልካም ነው ያሉትን ሐሳብ ከመከተል ባለፈ እገሌ ስለሚያዝንና ስለሚቆጣ፣ እገሌም ስለሚደሰት ብለው የሚቀይሩት ሐሳብ አልነበራቸውም፡፡ በቤተ ተክለ ሃይማኖት ሥር ከነበሩት ገዳማት አንዱ ደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ በቦታ ለደብረ ሊባኖስ ቢቀርብም በአቋም ግን በኤርትራና በትግራይ እንደ ነበሩት ገዳማት የሁለት ሰንበትን መከበር ይደግፍ ነበር፡፡ የአንድ ሰንበትን መከበር ያስተምሩ ከነበሩት ከሐይቅ እስጢፋኖስ መምህራን የተማረው አባ ጊዮርጊስ በአቋም ግን ከእነርሱ ተለይቶ የሁለት ሰንበትን መከበር ይደግፍ ነበር፡፡ የሁለት ሰንበትን መከበር በመደገፋቸው የደብረ ቢዘኑን አቡነ ፊልጶስን በሐይቅ እስጢፋኖስ በግዞት ያስቀመጣቸው የዐፄ ዳዊት ባለቤት ዕሌኒ ግን የአቡነ ፊልጶስን ትምህርት ትቀበል ነበር፡፡
የተለያዩ ሐሳቦችን ይዞ መከራከርና በመጨረሻ ግን ለሚወሰነው ውሳኔ ተገዥ መሆን ያለና የነበረ የቤተ ክርስቲያን ባህል ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሐሳቦች በደብረ ምጥማቁ ጉባኤ በተወሰነው ውሳኔ ነው ወደ አንድ አቋም የመጡት፡፡
ዛሬም ቢሆን የተለያዩ ሐሳቦች መነሣታቸውና መንሸራሸራቸው ክፋት የለውም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዐት ተሰብስቦ አንድ አቋም ሲይዝና ያም የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም ሲሆን ሁላችንም ለዚያ ተገዥ እንሆናለን፡፡
ስለዚህም ‹ይህንን ወይም ያንን ሐሳብ ለምን ትሰጣላችሁ፤ እኛ የምንላችሁን ብቻ አራምዱ የሚሉ አካላትም ወደ በኣታቸው ሊመለሱ ይገባቸዋል፡፡ ‹ጴጥሮስ ሆይ ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ› ሊባሉም ይገባል፡፡ የተለየ ሐሳብ ያለውን ሁሉ ማውገዝ ፍቅርን ከማሻከርና የቤት ሥራ ከመጨመር በላይ ጥቅም እንደሌለው በቅርብ ጊዜ ታሪካችን የተማርን ይመስለኛል፡፡
እናም ‹ሁሉም ወደየበኣቱ ይመለስ›
