ወርቅ እንዲህ ሲገዛ
ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ ወደ ጆሃንስበርግ በሚሄደው ኢትዮጵያ አየር መንገድ የደረሰብኝን መጉላላት ዘርዝሬ በዚህ ጦማር ላይ ጽፌ ነበር፡፡ ያንን ሳደርግ ዋናው ዓላማዬ የኢትዮጵያ አንዱ መለያ የሆነው አየር መንገዳችን እንዲሻሻል በማሰብ ነው፡፡ ‹ጠላት ያማል ወዳጅ ይወቅሳል› እንዲሉ፡፡ ታላቁን መርከብ የአንዲት ብሎን መውለቅ ለአደጋ እንደሚ ዳርገው ሁሉ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ታላላቅ ተቋማትንም በየአካባቢው የሚፈጠሩ ትናንሽ የሚመስሉ ስሕተቶች ዋጋ ያስከፍሏቸዋል፡፡
ዛሬ ከጆሃንስበርግ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአካባቢ ሥራ አስኪያጅ በተፈጠረው ጉዳይ ላይ አነጋግረውን ነበር፡፡ ባለፈው ለተፈጠረው መጉላላት ይቅርታ ጠይቀው፣ በቀጣይ ተመሳሳይ ስሕተቶች እንዳይፈጠሩ አሠራራቸውን ማረማቸውን ገልጠውልናል፡፡ ያለፈውንምንም ለመካስ በቢዝነስ ክላስ ወደ አዲስ አበባ እንድንመለስ አድርገዋል፡፡
በመጀመርያ ቅሬታችንን በመስማታቸው፤ ቆይቶም ቢሆን ይቅርታ በመጠየቃቸውና ስሕተቱን ለማረም አሠራር መዘርጋታቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ ችግሮች መቼምና የትም ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ሁለት ነገሮችን ግን ይፈልጋሉ፡፤ አንድ ሲፈጠሩ በቅርብ ተገኝቶ ሳይብሱ የሚፈታ አመራርና፣ ችግሮቹ ዘላቂ ሆነው እንዳይቀጥሉ የሚያደርግ አሠራር ናቸው፡፡ ያኔ ያጣነው ይሄንን ነበር፡፡
ደንበኞች ቅሬታቸውን የሚሰማና የሚፈታ ካገኙ ከአየር መንገዱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይቀጥላሉ፡፡ ቅሬታቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ከተደረገ ግን በዚህ የውድድር ዘመን ፊታቸውን ወደ ሌሎች ያዞራሉ፡፡
በመሆኑም አየር መንገዳችን ቅሬታውን ተቀብሎ ለማረምና ይቅርታ ለመጠየቅ ያደረገው አሠራር አስደስቶኛል፡፡ ወርቅ እንዲህ ሲገዛ ያምርበታል፡፡ ነገም እንዲሁ እየተሰማማን እንደምንቀጥልም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጥበቡን በልቡናችሁ፣ መልካሙን መስተንግዶ በአውሮፕላናችን ላይ ያሳድርብን፡፡ አሜን፡፡
ከጆሃንስበርግ ወደ አዲስ አበባ በረራ ላይ
