በታሪክ መርካት

click here for pdf

(ፎቶ -በአሜሪካ የኢትዮጵያ  ኢምባሲ ድረ ገጽ)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመመለሱ ፌሽታ ሕዝቡን አልለቀቀውም፡፡ ተጨዋቾቹና ፌዴሬሽኑም በዚሁ ደስታ ውስጥ ናቸው፡፡ ስለ እሑዱ ድል እንጂ ስለ ቀጣዩ ውድድር የሚያስብ ግን ያለ አይመስልም፡፡ ሌሎቹ ቡድኖች እስከ ጥር ወር ድረስ ምን እንደሚሠሩ በሚናገሩበት ጊዜ እንኳን የኛው ቡድን እስከ ጥር ወር ድረስ ምን እየሠራ እንደሚቆይ አይታወቅም፡፡
እንዴውም እንደምንሰማው ከሆነ አንዳንድ ተጫዋቾቻችን በየመጠጥ ቤቱ እየተጋበዙ በሸክም ሆኗል አሉ የሚወጡት፡፡ ምነው ሲባሉ ‹ድል አድርገናልኮ› ነው መልሱ፡፡
ይኼ በትናንት ድል እየረኩ ነገን የመርሳት አባዜ የቆየ በሽታችን ነው፡፡ በአድዋ ጦርነት ጣልያንን ወኔያችንን ተጠቅመን፣ ጀግንነታችንን ተኩሰን ፈጣሪም ረድቶን ድል አደረግናት፡፡ በጥቁር አፍሪካ ምድር ቅኝ ገዥዎችን ድል ያደረገ ጥቁር ሕዝብ መሆናችንን አስመሰከርን፡፡ ታሪክ ሠርተን ታሪክ አየን፡፡

ጣልያንን የአድዋው ውርደቷ ሲቆጫት ነው የኖረው፤ ያንን ውርደቷን እንዴት እንደምታራግፈው ስትመክር፣ ስትሠራና ስትፈጥር ኖረች፡፡ እኛ ደግሞ የአድዋን ድል ስናከብር፣ በድሉ ፌሽታ ስንጥለቀለቅ ከረምን፡፡ እኛ ዐርባ ዓመት ስለ አድዋ ስንዘፍን፣ እነርሱ ዐርባ ዓመት ውርደታቸውን ለማራገፍ ሲሠሩ ከረምን፡፡ ለኛ ጣልያንን ተወግዞ እንደወጣ ሰይጣን ተመልሳ የማትመጣ አድርገን ቆጠርናት፡፡

ከዐርባ ዓመት በኋላ በ1928 ዓም ጣልያን ካለፈው ስሕተቷ ተምራ አውሮፕላንና መርዝ ሠርታ፣ ዘመናዊ ወታደር ትጥቅ አሟልታ፣ እስከ አፍንጫዋም ታጥቃ መጣች፡፡ እኛ ግን እነዚያኑ አድዋ የወሰድናቸውን መሣርያዎችና አጋሠሶች ይዘን ማይጨው ዘመትን፡፡ እናም በማይጨው የሆንነውን እናውቀዋለን፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ረሃብ፣ ወረርሽኝና ተስቦ እየደጋገመ ሀገሪቱን ሲመታና ሲያደቅቅ እናገኛለን፡፡ እያንዳንዱን የመከራ ጊዜ በጸሎትም፣ በእሳትም፣ በሞትም ስናሸንፈው ሌላ መከራ የማይመጣ ይመስል ያኛውንና ያለፈውን እንዴት እንደተወጣነው ብቻ በመተረክና በመዝፈን ጊዜውን እንጨርሰዋለን፡፡ ያም የመከራ ዘመን ጊዜውን ጠብቆ እንደገና ይመጣል፡፡
ጅርመኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሀገራቸው እንዳልነበረች መሆንዋ፣ ከናዚ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ ስሟ መጥፋቱ፣ ጀርመናዊ ነኝ ማለት እስኪያሳፍር ድረስ መድረሱ አስቆጭቷቸው ለአርባ ዓመታት ሠሩ፡፡ በዐርባ ዓመት ጊዜ ውስጥ ጀርመን የዓለምን አራተኛ ኢኮኖሚ የምታስተዳድር ሀገር ሆና ወጣች፡፡ እኛ ግን የአፍሪካን ዋንጫ እንኳን ለመሳተፍ 31 ዓመታት ፈጀብን፤ ለምን? ቢባል በታክ የሚዝናና እንጂ በቁጭት የሚሠራ ስላላገኘን፡፡
አሁንም በእግር ኳስ ቡድኑ ላይ የምናየው ይኼንኑ ነው፡፡ ትናንት አሸነፍን፤ መልካም፡፡ ነገር ግን የኛ ደስታ እንደ ሄሊኮሜት በዘመናት አንድ ጊዜ ብቻ ነው እንዴ መምጣት ያለበት? ያለፈ ድል ለቀጣዩ መነሻ ይሆናል እንጂ ስንቅ ይሆናል እንዴ? አሁን መጠየቅ ያለብን ከነማን ጋር ደረሰን? የሚለውኮ አልነበረም፡፡ አሠልጣኝ ሰውነት እንዳሉት ‹ከማንም ጋር ይድረሰን፣ ከተዘጋጀንና ከሠራን እናሸንፋለን፤› ካልሠራን ግን ከራሳችንም ጋር ተጫውተን አናሸንፍም፡፡
ለምን እንረሳለን፤ እኛኮ በአፍሪካ ዋንጫ ከሁሉም ቡድኖች የበለጡ ጎሎችን ያስተናገድን ነን፤ በአፍሪካ ዋንጫ ከሚሳተፉ ቡድኖች በፊፋ ደረጃ ዝቅተኛ ደረጃ ካላቸው መካከል የምንመደብ ነን፤ ሌሎቹኮ ተጨዋቾቻቸውን  ከአውሮፓ እየጠሩ ነው፣ አራትና አምስት የወዳጅነት ጨዋታ ከአውሮፓ ቡድኖች ጋር ለማድረግ ዕቅዳቸውን ይፋ አድርገዋልኮ፡፡

     ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋናጫ ያሸነፈው ቡድን
           ( ፎቶ -ከሪፖርትር)

እኛ ሱዳንን ስላሸነፍን ተዘጋጅቶ የሚጠብቀን እንጂ ፈርቶን የሚሸሽኮ የለም፡፡ እንዴት አሸነፉ? ምን ዓይነት ስልት አላቸው? ጠንካራና ደካማ ጎናቸው ምንድን ነው? እያለ ተንትኖ የሚጠብቀን እንጂ አርድ አንቀጥቅጥ የለበስን ይመስል ማንም አይደነግጥልንም፤ ያለፈው ድላችን ተጋጣሚዎቻችንን ይበልጥ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁን ያደርጋቸዋል እንጂ ‹እንደ ሰም አቅልጦ፣ እንደ ገል ቀጥቅጦ› አይጥላቸውም፡፡
ባለፉት 31 ዓመታት የዛሬ ሠላሳ አንድ ዓመት ማን በጭንቅላት በገጫት ኳስ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዳለፍን ስንተርክ ሰነበትን፡፡ ለመሆኑ ቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫስ? ‹ሳላዲን ሰይድና አዳነ ግርማ እንዲህና እንዲያ አድርገው ባገቡት ግብ ነበር ያለፍነው› እያልን ለምን ያህል ዓመት ይሆን የምንተርከው?
ይህ ሀገሩ ከፍ ስትል የሚወድ ሕዝብ ደስታው ምንያህል እንደነበረኮ አይተነዋል? ኢትዮጵያ ቡድን እንጂ ሕዝብ አላጣችም፤ ፌዴሬሽን እንጂ ሕዝብ አላጣችም፡፡ ይልቅስ አሁን መነጋገር ያለብን ይህንን ደስታ እንዴት ዘላቂ ማድረግ እንደምንችል ነው፤ እንዴት ነው የአፍሪካ ዋንጫ ብርቅ የምይሆንብን ደረጃ የምንደርሰው? እንዴት ነው የዓለም ዋንጫን በቴሌቭዥን ብቻ ከማየት የምንላቀቀው? እንዴት ነው በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረተ እግር ኳስ የምናደራጀው? እንዴት ነው የባለሃብቶችን ድጋፍ ከሽልማት ወደ ቀድሞ መደገፍ የምንቀይረው?
ብዙ ሥራ አለብን፡፡ ደስታው ይብቃ፤ ፌሽታውም ልክ ይኑረው፤ እርሱ የኛ ሆኗልና ማንም አይነጥቅብንም፤ አሁን የኛ ስላልሆነው የአፍሪካ ዋንጫ እናስብ፡፡ ታሪክ ላይ መተኛት ብዙ ጊዜ ጎድቶናልና ይብቃን፡፡