ሞያ ከጎረቤት

ባለፈው እሑድ ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓም አዋሳ ላይ ሆኜ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን 118ኛ ፓትርያርኳን ስትመርጥ እያየሁ ነበር፡፡ እጅግ ደስ የሚለው ሥነ ሥርዓቱን ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሽፋን ሰጥተውት ነበር፡፡ በረከታቸው ይደርብንና ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ በዘመናቸው ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከሠሯቸው ሥራዎች አንዱ ዘመናዊ የሆነ የኦዲዮ ቪዡዋል ማዕከል ባለቤት ማድረጋቸው ነው፡፡ በእርሳቸው ዘመን ታላቅ የሆነ የቴሌቭዥን ስቱዲዮ ተገንብቷል፡፡ ኮፕቲክ ቴሌቭዥን፣ አጋፒያና ክርስቲያን ቲቪ የተሰኙ የቤተ ክርስቲያኒቱን የዕለት ተዕለት ጉዳዮች የሚዘግቡ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተቋቁመዋል፡፡
በዕለቱ የነበረውን ዝግጅት ከዋዜማው ጀምሮ ታላላቅ ባለ ክሬን ካሜራዎችን በመትከልና የትኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መቀረጽ እንዳለበት በመለየት የኮፕቲክ ቴሌቭዥን ጣቢያ ከኮፕቲክ የኦዲዮቪዡዋል ማዕከል ጋር በመሆን ተዘጋጁ፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥና ውጭ ከ16 በላይ ባለ ክሬን ካሜራዎች ተተክለው ነበር፡፡
ከመላው ዓለም የተገኙ ከ230 በላይ ጋዜጠኞች በተዘጋጀላቸው ልዩ ቦታ ላይ ሆነው ከጠዋቱ ጸሎት አንሥቶ እስከ ምርጫው ፍጻሜ የነበረውን ሥነ ሥርዓት ለመላው ዓለም በቴሌ ቭዥን፣ በሬዲዮ፣ በዌብ ሳይትና በብሎግ ያስተላልፉ ነበር፡፡ ከአሥር ሺ ሕዝብ በላይ የሚይዘው የአባስያ የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በተመረጡ ገዳማውያን፣ ካህናት፣ ምእመናን እና ተጋባዥ እንግዶች መሞላት የጀመረው ገና ከጠዋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነበር፡፡ 

ይህ መንበረ ፕትርክና የተገነባበት ቦታ ጥንት የግብጻውያን ክርሰቲያኖች መቃብር የነበረበት ቦታ ነው፡፡ ቦታው ለቤተ ክርስቲያኒቱ የተሰጠው 969 ዓም ለቤተ መንግሥቱ መሥሪያ ተብሎ በተወሰደባት ቦታ ምትክ ነው፡፡ በቦታው ላይ ጥንታዊው የአባ ሮዩስ ቤተ ክርስቲያን ነበረበት፡፡

12ኛው መክዘ በአካባቢው 12 አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ 1280 ዓም አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ተነሥተው አብያተ ክርስቲያናቱን አቃጠሏቸው፡፡ ከዚያም በቦታው ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩ፡፡
አሁን ያለውን የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ያሠሩት ፖፕ ቄርሎስ 6 ሲሆኑ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውም 1968 ዓም ነው፡፡ በዚህ ቤተ ክርስቲያን ሥር ነው የታላቁ ሐዋርያዊ አባት የቅዱስ አትናቴዎስ ዐጽም ያረፈው፡፡
ለወትሮው ከባድ ጥበቃ የማይለየው መንበረ ፓትርያርኩ በዚያ ቀን የፖሊሶችም ሆኑ የወታደራዊ ጥበቃዎች ቁጥር ጨምሮ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኒቱ በኩል የተሠማሩ ክርስቲያን የጸጥታ አስከባሪዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚከናወነውን እያንዳንዱን ንቅናቄ በንሥር ዓይን እየተከታተሉት ነበር፡፡ ከ300 በላይ ወጣት የሰንበት ተማሪዎች እንግዶቹን ለማስተናገድና ሥነ ሥርዓት ለማስከበር ተሰልፈዋል፡፡ ‹‹የሚያለቅሱ፣ እጆቻቸውን ወደላይ ሰቅለው የሚማጸኑ፣ አንገታቸውን ደፍተው ከልብ የሚጸልዩ፣ የሚሆነውን ለማየት ጓጉተው አገጮቻቸውን በመዳፋቸው ይዘው መቅደስ መቅደሱን የሚያዩ ብዙዎች ነበሩ›› ብሏል አንድ በፌስ ቡክ ሁኔታውን ያስተላለፈ የካይሮ ነዋሪ፡፡

ባለፈው ሳምንት በተደረገው ምርጫ ከፍተኛውን ድምጽ ያገኙት ሦስት አባቶች ስሞች ከመስተዋት በተሠራና ፋኖስ በሚመስል ዕቃ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጎ በሕዝብ ፊት ነበር በሰም የታሸገው፡፡ ይህ የመስተዋት ሙዳይ በአባስያ የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል መንበር ላይ ተቀምጦ ለአንድ ሳምንት ያህል ጸሎት ሲደረግበት ነበር፡፡
ጸሎቱ የተጀመረው ከማለዳው 12 ሰዓት ሲሆን ቅዳሴው የተጀመረው ዘግየት ብሎ ነው፡፡ በቅዳሴው ላይ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳሳት ተሳትፈዋል፡፡ ሁሉም አብረው ቆርበዋል፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ለማጠንከርና ሥራውን ለእግዚአብሔር ለማስረከብ ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ በምርጫው ሂደት የተወቀሱ፣ ከዕጩነት የተለዩ፣ የተከፉና ያዘኑ ይኖራሉ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ማብቃት አለበት፡፡ እናም ከጸሎቱ በፊት በሚደረገው የዕርቅና የይቅርታ ሥነ ሥርዓት ይህ ሁሉ ይጠናቀቅና ሁሉም ወደ ቅዳሴ ይገባሉ፡፡ አሁን የሰው ሥራ አብቅቷል ቀሪውን የሚመርጠው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ ወደ ሦስት ሰዓት የፈጀው ቅዳሴ መጀመርያ ጳጳሳት ከዚያም ካህናት በመጨረሻም የተወሰኑ ምእመናንን በማቁረብ ተጠናቀቀ፡፡ 

በዚህ ቅዳሴ ልዩ ዕድል ያገኙ 12 ሕጻናት ዲያቆናት ነበሩ፡፡ እነዚህ ዐሥራ ሁለት ሕጻናት ከመላዋ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሕጻናት ተመርጠው የመጡ ናቸው፡፡ ጳጳሳቱን በማገልገል በቅዳሴው ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ከሦስቱ አባቶች አንዱን ለፕትርክና ዕጣ የሚያወጣው ከእነዚህ ሕጻናት አንዱ ነው፡፡
ቅዳሴው እንዳበቃ ዐቃቤ መንበሩ አቡነ ጳኩሚስ ያንን የመስተዋት ሙዳይ ከመንበሩ አንሥተው ወደ መድረኩ ሲያወጡት ዕልልታው ቀለጠ፡፡ አሁን የፕትርክና ምርጫው ወደ መጨረሻው ደረጃ በመጓዝ ላይ ነው፡፡ አስቀድመው የዐሥራ ሁለቱ ሕጻናት ስም በወረቀት ተጽፎ እየተጠቀለለ በአንድ የመስተዋት ሙዳይ ውስጥ ገባ፡፡ ከዚያም ጸሎት ተደረገ፡፡ ከጸሎቱ በኋላ ዕጣው ወጣ፡፡ ዕጣውም ዕድለኛ ለሆነው ለቢሾይ ጊርጊስ ማሳድ ወጣ፡፡
ዕድለኛው ሕጻን ቢሾይ ጊርጊስ ማሳድ ወደ ላይኛው መድረክ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ ዓይኑን በመስቀሎች በተሞላ ጥቁር መሐረብ ተሸፈነ፡፡ አቡነ ጳኩሚስ ለሁሉም ሰው እያሳዩ ከሳምንት በፊት የታሸገውን የመስተዋት ሙዳይ ከፈቱት፡፡ ሕዝቡ በጸሎት ላይ ነበር፡፡ እንኳን የግብጽ ሕዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ብዙዎች በጸሎት አብረዋቸው ነበሩ፡፡ ከመላዋ ኢትዮጵያ ሥነ ሥርዓቱን እየተከታተሉት መሆኑን የሚገልጡ ከ133 በላይ የስልክ አጭር መልእክቶች ይደርሱኝ ነበር፡፡ ብዙዎች ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና የቤተ ክህነት ሰዎች ሥነ ሥርዓቱን እንዲከታተሉ በስልክ ሲጋብዙ ነበር፡፡ 

እኩል በሆኑ የመስተዋት ዕንቁላሎች ውስጥ ስማቸው እንዳይለይ ተደርገው የተጠቀለሉት ወረቀቶች አሉ፡፡ የተመረጠውና ዓይኑን የታሠረው ሕጻን እጁን ሰደደና አንደኛውን አወጣ፡፡ ግብጻውያን ይህንን ‹የእግዚአብሔር እጅ›› ይሉታል፡፡ ዐቃቤ መንበር ጳኩሚስ ከልጁ ተቀብለው እግዚአብሔር አቡነ ታዋድሮስን ለመንበረ ማርቆስ 118ኛ ፓትርያርክነት መምረጡን አበሠሩ፡፡ ካቴድራሉ በደስታ ተሞላ፡፡ ዕንባዎች ይታዩ ዕልልታዎችም ይሰሙ ነበር፡፡ ወዲያውኑ ዜናውን እነ ሲኤን ኤን፣ ቢቢሲ፣ አልጄዚራ፣ ፕሬስ ቲቪና ሌሎችም ተቀባብለው ናኙት፡፡

አቡነ ታዋድሮስ የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ረዳት የነበሩ ናቸው፡፡ እድሜያቸው ወደ ስድሳ የሚጠጋው አቡነ ታዋድሮስ በእንግሊዝና ሲንጋፖር የፋርማሲ ትምህርት የተከታተሉ፣ ሰፊ ልምድና የአስተዳደር ችሎታ ያላቸው አባት መሆናቸውን ለቢቢሲ ዜናውን የዘገበው ጆን ሊየን ተናግሯል፡፡ አቡነ ታዋድሮስ ከተመረጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በዋዲ ኤል ናትሩን ገዳም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ይህ ሥልጣን ሳይሆን ኃላፊነት ነው፡፡ ዋናዋ ነገር እኔ ሳልሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ናት›› ብለዋል፡፡ የግብጽ ብሔራዊ የዜና አገልግሎት ‹‹ሜና›› እንደተናገረውም አቡነ ታዋድሮስ ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት በስድሳኛው የልደት ቀናቸው ነው፡፡ በ1986 ዓም በዋዲ ኤል ናትሩን ገዳም የመነኮሱት አቡነ ታዋድሮስ ቅስናንም የተቀበሉት ከሦስት ዓመት በኋላ በ1989 እኤአ ነበር፡፡ በቀጣዩ ኅዳር 9 ቀን በሚደረገው በዓለ ሲመት 118ኛው የግብጽ ፓትርያርክ ሆነው በመንበረ ማርቆስ ይቀመጣሉ፡፡  

ግብጻውያን ከዚህች ቀን ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረድ አይተዋል፡፡ በቆራጥነትና በጸሎት ሊያሰናክሏቸው የነበሩትን ሁሉ ታግለዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ጋር ሆነው አሸንፈዋል፡፡ ግልጽ የሆነ የምርጫ ሕግ፣ ለሕጉ በቆራጥነት መቆም፣ ሥራውንም ከጸሎት ጋር መሥራት ለዚህ አድርሷቸዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የፓትርያርክነት መምረጫና መመዘኛ ዝርዝርና ግልጽ ሕግ ያስፈልጋታል፡፡ የግለሰቦችን ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ፍላጎት የሚያሟላ፡፡ ሁላችንም የምናውቀው፤ የምንጠብቀው፡፡ ከዚያ ቀጥሎም ግልጽ የሆነ የምርጫ ሂደት መርሐ ግብር ያስፈልጋል፡፡ ምን መቼ ይደረጋል? በማን? የሚለውን በግልጽ ማስቀመጥ ያሻል፡፡ ከዚያም ደግሞ ምርጫውን የሚያስፈጽም ከአባቶች፣ ከሊቃውንትና ከምእመናን የተዋቀረ ገለልተኛና ታማኝነት ያለው አስመራጭ አካል ያስፈልጋል፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የምርጫ ሂደት ከሕግ ውጭ ለመመረጥ የሞከሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ገዳማውያን አባቶችና ምእመናን በወሰዱት ቆራጥ አቋም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጥንካሬ የሚለካው ባጋጠማት ችግር መጠን አይደለም፡፡ በወሰደችው መንፈሳዊ ቆራጥነት የተሞላው መፍትሔ እንጂ፡፡ ችግሩን ተቋቁማና አሸንፋ ለማለፍ በመቻሏ እንጂ፡፡ የኛ ቤተ ክርስቲያንም እየተሰሙ ያሉትን ችግሮች ተቋቁማና አሸንፋ ለማለፍ የሚያስችላት ሕግ፣ አሠራርና ቆራጥነት ያስፈልጋታል፡፡

የምንከተለው የምርጫ ሕግ፣ ሥነ ሥርዓትና መርሐ ግብር እንኳን ክርስቲያኑ ሌላውም ተመልክቶ የሚማረክበት፣ የሚያደንቀውና የሚመሰክርለት መሆን አለበት፡፡ ዕጣውን የሚያወጣውን ሕጻን እንኳን በዕጣ የወሰኑት ሐሜትን ለመከላከል ሲባል ነው፡፡ ግብጻውያን እንደዚያ የዓለም ጋዜጠኞችን ሁሉ ጠርተው ‹ኑ እዩን› ያሉት የሚያሳዩት ነገር የማያሳፍር መሆኑን ስለተማመኑ ነው፡፡ የኛስ?
በቴሌቭዥን የተላለፈው ቅዳሴና የምርጫ ሥነ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያኒቱን በዓለም ፊት ከፍ አድርጎ ያሳያት ነው፡፡ የመራወጡ፣ የሚያወሩ፣ የሚንሾካሾኩ አልነበሩም፡፡ አንዳንዴ እኛ ጋ ሆኖ ቢሆን ብዬ ሳስበው ወዲያና ወዲህ እያሉ የሚራወጡ፣ ጋቢያቸውን አፋቸው ላይ ደግነው የሚያወሩ፣ ሞባይል አውጥተው የሚነጋገሩ፣ በሥነ ሥርዓቱ አካሄድ ላይ በሃሳብ እየተለያዩ ‹ተው ተው› የሚባባሉትን ሁሉ ዓለም ሲያይ ይታየኝ ነበር፡፡
ሌላው ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን የምንማረው የመራጮችን ቁጥርና ተዋጽዖ መወሰን ነው፡፡ በእነርሱ ዘንድ የመራጮቹ ቁጥር 2411 ነበር፡፡ በኛ ዘንድስ ስንት ነው? ከምን ከምን የተውጣጡስ ናቸው? የትኞቹ ገዳማት፣ አድባራትና አህጉረ ስብከት ስንት ተወካይ ይኖራቸዋል? የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ተሳትፎስ? ምን ያህል ምእመናን ይሳተፋሉ? እንዴትስ ይመረጣሉ? የታዋቂ ሰዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፎስ እንዴት ነው? በመጨረሻስ የሚወሰነው እንዴት ነው? እነዚህ ሁሉ ቀድመው ሊወሰንባቸው የሚገቡ ናቸው፡፡

አሁን ያለው ምእመን ያንን የመሰለውን የግብጻውያን የምርጫ ሥነ ሥርዓት ያየ ነው፡፡ የዛሬ 21 ዓመት እንደነበረው አይደለም፡፡ አሁን ያለችው ኢትዮጵያም የዛሬ 21 ዓመት እንደነበረችው አይደለችም፡፡ ዛሬ እንኳን የተነገረውና የተሠራው፣ የታሰበውም የሚሰማበት ዘመን ነው፡፡ ስለዚህም ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት፣ ለምእመናንም መንፈሳዊ ጥንካሬ አባቶች ዋናውን ትኩረት ይሰጡ ዘንድ አደራ አለባቸው፡፡
መልክ ከፈጣሪ ተሰጥቶናል፤ ሞያን ደግሞ ከጎረቤት እንማር፡፡