የብሔራዊ ቡድናችን/የዋልያዎቹ ድል ዳግም የኢትዮጵያዊነት ኩራት ፍቅርንና አንድነት ቃል ኪዳን ውል ሲያድሰው በፍቅር ለይኩን

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ባንኪሙን በስዊዝርላንድ ጄኔቫ እ.ኤ.አ ግንቦት 11/2011 ዓ.ም ስፖርት ለሰላምና ለልማት ያለው አስተዋእፆ በሚል ባደረጉት ንግግራቸው ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራትን ድንበር ተሻግሮ፣ የዘር የጎሳና ሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድበው፣ የዓለም አቀፍ መግባቢያ ቋንቋ መሆን እንደቻለና ስፖርት ለሰው ልጆች ሰላም፣ አንድነትና እድገት ቁልፍ እየተጫወተ ያለውን ትልቅ ሚና እንዲህ በማለት ነበር የገለጹት፡-

“Sport has become a world language, a common denominator that breaks down all the walls, all the barriers. It is a worldwide industry whose practices can have a widespread impact. Most of all, it is a powerful tool for progress and development.”

አገራችን ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ማለፏ በሕዝቡ መካከል የፈጠረው ደስታና ፈንጠዚያ እጅግ ልዩ ነው፤ እስካሁንም ስሜቱ አልበረደም፡፡ ይህ ከሦስት አስረት ዓመታት በኋላ የእግር ኳስ አፍቃሪ ኢትዮጵያንን ልብ በሐሴትና በደስታ የሞላው የኢትዮጵያና የሱዳን ብሔራዊ ቡድኖች ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲዮም፣ በየአደባባዩ በተሰቀሉ ሶኒ ስክሪኖች፣ በየቤቱና በየመዝናኛው ስፍራ ጨዋታውን የተከታተለው ሕዝብ ብሔራዊ ቡድናችን/ዋልያዎቹ ማሸናፋቸውን የሚያረጋግጠውን ፊሽካ በሰማበት ቅጽበት በመላው ኢትዮጵያ ደስታውን የገለጸበት ሁኔታ እጅግ መሳጭና ብዙ መልክ የነበረው ነው፡፡

ብዙዎች በደስታ ዘለዋል ጨፍረዋል፣ አንዳንዶችም በደስታ እንባ ተራጭተዋል፡፡ ይህ ደስታ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ሴት፣ ወንድ፣ ዕድሜ… ወዘተ የለየ አልነበረም፡፡ ሁላችንንም በአንድ የደስታ፣ የብሔራዊ ኩራትና ስሜት ያስተሳሰረ ልዩና አንጸባራቂ ድል ነበር፡፡ በቀደመው ዘመናችን ኢትዮጵያ ሀገራችን በእግር ኳስ ታሪክ እንደ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ባሉ የሀገራችን ስፖርት ፈርጥ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራችን ልዩ ታሪክና ክብር ያስመዘገበች ሀገር ለመሆን ችላ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በተለይ በእግር ኳሱ መስክ የነበራት አንጸባራቂ ስምና በአፍሪካ እግር ኳስ መድረክ ከመስራችነት እስከ ተሳታፊነት የነበራት ትልቅ ሚና እየደበዘዘ መጥቶ ከነጭራሹ ከእግር ኳሱ ዓለም የተገለለንበትና ውራ የሆንበትን አሳፋሪ ታሪክ ተሸክመን ለበርካታ ዓመታት ተጉዘናል፡፡ ይህን የትናንት አኩሪ ታሪካችንን ለመድገም የአንድ ትውልድ ዘመን ትግል ወኔያችንን ተፈታትኖት ነበር፡፡ እናም በእልህ መቼ ይሆን ዳግም በአፍሪካ እግር ኳስ መድርክ ተርታ አገራችን ስሟ የሚገባው፣ ሰንደቀ ዓላማችን ከፍ ብሎ የሚታየው በሚል ምኞትና ቁጭት ያሳለፍነው የሀገራችን እግር ኳስ የጨለማ ዘመን ታሪክ ዛሬ በዋልያዎቹ ደማቅ ድል የብሩህ ዘመን ጮራ ፈንጥቆበት አይተናል፡፡ ጀግኖቻችን/ዋልያዎቹ በደቡብ አፍሪካ አዲስ ታሪክና ድል እንደሚያስመዘግቡም ተስፋ እናደርጋለን፡፡

በብሔራዊ ቡድናችን አንጸባራቂ ድል ኢትዮጵያዊነት ዜማ ከዳር እስከ ዳር ከፍ ብሎ ተሰምቷል፤ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቀ ዓላማችን በሀገራችን ሰማይ ላይ ከፍ ብሎ ተውለብልቧል፡፡ የኢትዮጵያዊነት የአንድነት፣ የፍቅርና የአብሮነት ውብ የዘመናት ታሪካችን ዳግም በብሔራዊ ቡድናችን ድል ታድሶ ወኔያችንን ከፍ አድርጎታል፡፡ ድሉ የአንድነታችንን ቃል ኪዳን የፍቅርችንና የአብሮነታችንን ውል ዳግም አድሶታል፡፡ በብሔራዊ ቡድናችን የሰሞኑ ድል በመላ ሀገራችን የተሰማው የድል፣ የአንድነትንና የኢትዮጵያዊነት ልዩ ስሜትና ክብርን የሚያንጸባርቁ መዝሙሮቻችን፣ ዘፈኖቻችንና ጭፈራዎቻችን የብዙዎችን በደስታ ባህር ውስጥ በሐሴት እንድንዋኝ ያደረገና የኢትዮጵያዊነታችን የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌነትን ሰንደቅ በሀገራችን ሰማይ ላይ ከፍ አድርጎ ያሳየ ትልቅ ትእይንት ነበር፡፡

አትነሳም ወይ… አትነሳም ወይ… ይሄ ባንዲራ የአንተ አይደለም ወይ…፣ አያ ሆ ሆ ማታ ነው ድሌ፣ ኢትዮጵያ ሀገሬ መመኪያዬ… ምኒልክ ጥቁር ሰው… የሚሉት ዜማዎች… ዓባይ ይገደባል… የሚሉት ከድሉ ጋር የተያያዙ መፍክሮችና ጭፈራዎች ትናንት በዓለም መድረክ የምንታወቅበትን የራብ የጦርነትና የኋላ ቀርነት መጥፎ ታሪካችንን ማብቂያ ማብሰሪያ ፊሽካ ሆነው የታዩበት ነበር የእሁዱ የብሔራዊ ድላችን ድልና የሕዝባችን ሆታና ጭፈራ፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ በብርቅዬ አትሌቶቻችን ተደጋጋሚ ድል ከሮም እስከ ቶኪዮ፣ ከሞስኮ እስከ ሜክሲኮ፣ ከአቴንስ እስከ አትላንታ፣ ከባርሴሎና እስከ ኦስሎና ለንደን… በዓለም ዙሪያ ሰንደቀ ዓላማችን ክፍ ብሎ በተውልበለበበትና ብሔራዊ መዝሙራችን በተሰማበት መድረክ ሁሉ ኢትዮጵያውያን በደስታ ሲቃ አንብተዋል፣ አንብተናል፡፡ ሁሌም በድርቅ፣ በራብና በጦርነት የሚነሳው ስማችን በጀግኖቻችን ድል የተነሳ በዓለም መድረክ ስማችንና ክብራችን ከፍ ሲል የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ኩራትና ስሜት በአንድነት ሆነው ስሜታችንን ሲንጡት የተሰማንን ደስታ ለመግለጽ ቃል እና ቋንቋ የተቸገርንበትን አጋጣሚዎችን አሳልፈናል፡፡ ከጀግኖቻችን ከደራርቱ ቱሉና ከኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጋር በድላቸው በኢትዮጵያዊነት ታላቅ ኩራትና ስሜት አብረን ያነባንበትን ጊዜ በታሪካችን ማህደር ምስክር ሆኖ አለ፡፡

እንደ አትሌቲክሱ ተደጋጋሚ ድሎቻችን ሁሉ በእግር ኳሱ መስክም ከ31 ዓመታት በኋላ ታሪካችንን ለማደስ በድል የተቀላቀልነው በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ለኢትዮጵያዊነታችን ታሪክ፣ ታላቅ ኩራትና አንድነታችን ልዩ መገለጫ ሆኖ ሰንብቷል፣ ስሜቱ ዛሬም አልበረደም፡፡ የልዩነታችንን ድንበር በፍቅር አንድ አድርጎ ልዩነታችን በአንድነታችን ህብር ውበት ገኖና ደምቆ በሀገራችን ሰማይ ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡ ለዚህ ክብርና ብሔራዊ ኩራት ላበቁን ጀግኖቻችን በእርግጥም ምስጋናና አድናቆት ይገባቸዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድ/ት ዋና ጸሐፊ የባንኪሙን ስፖርት ለዓለም አቀፍ ልማትና ሰላም ልዩ አማካሪ የሆኑት ሚ/ር ዋይልፍራይድ ስፖርት ለብሔራዊ አንድነት፣ ለሀገራት መልካም ግንኙነት፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለልማትና ለሰላም ያለውን በጎ የሆነ አስተዋእፆ በ2011 ባቀረቡት ሪፖርታቸው ሲገልጹ እንዲህ ነበር ያሉት፡-
The United Nations considers Sport to be a powerful tool to promote education, health, development and peace. Sport unites people of all social classes, cultures, religions and backgrounds in a positive and educational way.
በተጨማሪም እኚሁ በተባበሩት መንግሥታት የዋና ጸሐፊው አማካሪ የሆኑት ሰው ስፖርት ከሰሀራ በታችና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል ለሰላምና ለእድገት ውይይትና እርስ በርስ መቀራረብ ያደረገውን አስተዋእፆ በዚሁ ሪፖርታቸው አጽንኦት ሰጥተው በሰፊው ገልጸውታል፡፡

በእርግጥም በሰሞኑ የብሔራዊ ቡድናችን ድል ከዳር እስከ ዳር ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያለ ምንም ልዩነት ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ዘር ሳይለያቸው ወንድ፣ ሴት፣ ሕጻን አረጋዊ ሳይል ሁላችንም በአንድ መንፈስ ደስታችንን የገለጽንበት ስሜት ለሀገራችን ሰላም እድገትና ብልጽግና እጅ ለእጅ የምንያያዝብትን የፍቅር ውል ኪዳን እንድናድስ ልዩ አጋጣሚን የፈጠረልን ነበር፡፡ ዛሬ ሀገራት በዓለም መድረክ ታሪካቸውን፣ ባሕላቸውን፣ ቅርሳቸውንና ብሔራዊ የቱሪስት መስህቦቻቸውንና ፖለቲካዊ ጥንካሬያቸውን በዓለም አቀፉ መድረክ የሚያሳዩበት እየሆነ እንዳለ በግልፅ እያስተዋልን ነው፡፡
The Grand Coalition Government in Kenya: A Recipe for Sports Development በሚል በኬንያ ናይሮቢ ዩኒቨርስቲ የስፖርት መምህራንና አማካሪ የሆኑ ዶ/ር ኤልያስ ሙያኒ እና ይስሐቅ ሙያንጊ በጋራ ባቀረቡት የጥናት ጹሑፋቸው በዘመናችን ስፖርት ለሀገራት አንድነት፣ ሰላም፣ ለፖለቲካ ምርጫ ዘመቻ እና ግጭቶችን ለመፍታት እንዲሁም በሕዝቦች መካከል መቀራረብን፣ አንድነትንና መተሳሰርን ለማጎለብት ያለውን ፋይዳ በጥናታቸው በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡

እነዚሁ ምሁራን እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም የኬንያውን አትሌቲክስ ቡድን በአቴንስ ኦሎምፒክ ያስመዘገበው አንጸባራቂ ድል በሀገሪቱ በዚሁ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ከ1200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በተገደሉበትና ከ350 000 በላይ ሰዎች ከቀዬቸው በተፈናቀሉበትና በተሰደዱበት 2008ቱ የምርጫ ቀውስ ምክንያት በሀገሪቱ ሰማይ ላይ ያጠላውን ጥቁር ደመናን የገፈፈ እንደነበርና ኬንያውያን አንድነታቸውንና ብሔራዊ ኩራታቸውን በዓለም ፊት ዳግም በአንድነት ሆነው እንዲግልጹ ያደረገ ድል እንደነበር ዶ/ር ኤልያስ በጥናታቸው ያወሳሉ፡፡

ከዚህ አሰቃቂ እልቂትና የኬንያውያን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ በኋላ በኮፊ አናን አደራዳሪነት የጥምር መንግሥት ያቋቋሙት ሁለቱ የሀገሪቱ አንጋፋና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ‹‹ፓርቲ ኦፍ ናሽናል ዩኒቲ›› እና ‹‹ኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንት›› መሪ የሆኑት ፕሬዝዳንት ሞአይ ኪባኪ እና ጠቅላይ ሚ/ር ራላይ ኦዲንጋ በፓርቲዎቻቸው ፕሮግራምና ፖሊሲዎቻቸው ውስጥ በሀገሪቱ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ቱሪዝምና ማህበራዊ እድገት ውስጥ ስፖርት ያለውን ትልቅ ስፍራ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በምርጫ ዘመቻው ወቅት በንቃት ይንቀሳቀሱ እንደነበር ምሁራኑ በጥናታቸው ገልጸውታል፡፡

ዶ/ር ኤልያስ በጥናታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደጠቀሱት፡- … the sport has continued to play an invaluable role of enhancing political tranquility in Kenya and has been a neutral toll of minimizing political tension and differences thereby paving the way for collective effort toward the development of various sectors of the country.

በሀገራችን በዘመናዊው ሆነ በባሕላዊ ስፖርቶቻችንን ልዬ ትኩረት በመስጠት ገዢው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚዎች ወጣቱን በማስተባበር ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለአብሮነትና እና ለሰላመዊ ፖለቲካ ትግል ማካሄጃ ስፖርቱን በበቂ ሁኔታ ሲጠቀሙበት አይታይም፡፡ ስለዚህም እንደ ጎረቤታችን ኬንያ ፓርቲዎች ስፖርታዊ ጨዋታዎችንና ድሎቻችንን ለሀገራችን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማምጣት ያለውን አዎንታዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማገባት ሊንቀሳቀሱ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡

በውድድር ጊዜ ብቻና ድል በቀናን ሰሞን ብቻ ሽር ጉድ ጭፈራና ሆታ፣ ሽልማቶችና ተስፋዎች የሚዥጎደጎዱለት ስፖርታችን ዘላቂና ቋሚ የሆነ ትኩረት እስካልተሰጠው ድረስ በስፖርቱ መስክ የምናደርገው ጉዞ ነገም ተመልሶ ወደኋላ የማይንደረደርበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እምብዛም ትኩረት ያልተሠጠውና በርካታ ችግሮች ያሉበት የስፖርቱ መስክ የሀገራችንን አኩሪ ታሪክ፣ ባሕል፣ ቅርስ፣ ስልጣኔና በጎ ገጽታችንን ለማስተዋወቅ ያለውን በጎ አስተዋእፆ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡

በተለያየ አጋጣሚ በሀገራችን የሚመጡ የውጭ ሰዎችና ወደ ሀገራቸው በስደት፣ በትምህርትና በሥራ አጋጣሚዎች በምንሄድባቸው ሀገራት ኢትዮጵያችንን አብዝተው የሚያውቋት በድርቅ፣ በራብና በጦርነት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ከትላንት አኩሪ ታሪካችንና ስልጣኔያችን ባሻገር በእኛ ዘመን ውጪዎቹ ኢትዮጵያችንን የሚያውቋት ወይም ስለ ኢትዮጵያዊነታችን ስንነግራቸው ኦ… በባዶ እግሩ ሩጦ ኦሎምፒክን ያሸነፈው የአበበ በቂላ ሀገር፣ የእነ ኃይለ ገብረ ሥላሴ… የእን ደራርቱ ቱሉ… የጀግና ሯጮች ሀገር በሚል ነው የሚያውቁን ወይም የሚያስታውሱን፡፡

ይህ በዓለም መድረክ በራብና በጦርነት የሚነሳው ስማችን በስፖርቱ መድረክ ጀግኖቻችን ባስመዘገቡት ድል በይበልጥ እንዲለወጥና በስፖርቱ መስክ ሀገራችን ማግኘት የሚገባትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስከበር ስፖርቱ ሊኖረው የሚችለውን በጎና ሰፊ አስተዋእፆ በሰሞኑ ድላችን ያሳየን እውነታ አለ፡፡ ድሉ ብሔራዊ ኩራታችንን አድነታችንን በኢትዮጵያዊ ኩሩ ስሜት እንድንገልጽና ልዩነቶቻችንን በፍቅር አንድ አድርገን ያሳየንበት ስለሆነ ብሔራዊ ወኔያችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ አድርጎታል ብል ብዙም የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡

ይህ የስፖርቱ ድል ያደሰው የፍቅር፣ የአንድነትና የመቀባበል ስሜት በሀገራችን ፖለቲካ ሰማይ ላይም ሊታይ የሚገባውና ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቀዋሚ ፓርቲዎች ተቀራርቦ ለመወያየት፣ ለሰላምና ለእድገት መፋጠን እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት የሚያስችል ድል እንደሆነ በጽኑ አምናለሁ፡፡ የመንግሥታቱ ዋና ጸሐፊ ባንኪሙን በጄኔቫው ንግግራቸው እንዳሉት ስፖርት ለሀገራት ሰላምና እድገት ዋና ቁልፍ ነውና፡፡ በደቡብ አፍሪካው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መልካም ዕድል ለብሔራዊ ቡድናችን በመመኘት ልሰናበት!!!
ሰላም! ሻሎም!