ገናዧ
ከላስ ቬጋስ ወደ ፊኒክስ አሪዞና በዩ. ኤስ. አየር መንገድ በመጓዝ ላይ ነበርኩ፡፡ የተቀመጥኩት በአውሮፕላኑ ወገብ ላይ ነው፡፡ ከእኔ ቀጥሎ አንዲት ወጣት ሴት፣ ከእርሷም ቀጥሎ አንድ ሽማግሌ በመስኮቱ በኩል ተቀምጧል፡፡ አውሮፕላኑ ተነሥቶ ጥቂት እንደተጓዘ የበረራ አስተናጋጇ ‹አሁን የኤሌክትሮኒክስ መሣርያዎቻችሁን መጠቀም ትችላላችሁ፣ ከስልክ በቀር› ስትል ሁሉም ኮምፒውተሩንና አይ ፓዱን መመዥለጥ ጀመረ፡፡
‹እኔስ የአበሻው ልጅ እንደ አባቶቼ ጎራዴ መመዥለጥ ቢያቅተኝ እንዴት አንድ አሮጌ ላፕ ቶፕ መመዥለጥ ያቅተኛል› ብዬ መዠለጥኩ፡፡ አንድ የማርመው ጽሑፍ ነበርና ያንን ከፍቼ ስሠራ ድንገት ከቀኝ ጎኔ ‹‹ይቅርታ›› የሚል ድምፅ ሰማሁና ዞር አልኩ፡፡ ልጅቱ ናት፡፡ ‹‹የምታነብበት ቋንቋ ምንድን ነው?›› ብላ ጠየቀችኝ፡፡ አማርኛ መሆኑንና የኢትዮጵያ ቋንቋ መሆኑን ነገርኳት፡ ያው እነርሱ ማድነቅ ልማዳቸው ነው ‹‹ዋ……ው›› ብላ አደነቀች፡፡ ከዚያ ደግሞ ስለምጽፈው ነገር ጠየቀችኝ፡፡ እርሱንም ነገርኳት፡፡
‹‹ደራሲ ነህ እንዴ?››አለችኝ፡፡ ምን እንደምሠራ ነገርኳት፡፡
‹‹የሚጽፉ ሰዎች ያስደስቱኛል›› አለች፡፡
‹‹ለምን?››
‹‹ዕውቀትና ሃሳብ ማካፈል በጣም ጥሩ ነዋ››
‹‹አየህ ስለዚህ አውሮፕላን ፍጥነት፣ ጽዳት፣ ውበትና ምቾት ለማሰብኮ አውሮፕላኑ መሥራት አለበት››
ራሴን ነቀነቅኩ፡፡
‹‹አንድ ሰው አእምሮው ካልሠራ በሌሎቹ ነገሮች ብቻ መኖር አይችልምኮ፡፡ አእምሮው እንዲሠራ ደግሞ ማሰብ አለበት፤ እንዲያስብ ደግሞ ዕውቀት የሚያካፍለው ያስፈልጋል፡፡ መብላትና መጠጣት እንድትቆይ እንጂ እንድትኖር አያደርጉህም››
ዛሬ ከፈላስፋ ጋር ነው የተቀመጥኩት አልኩኝና ምን ማለቷ እንደሆነ ጠየቅኳት፡፡
‹‹‹መኖር›ና ‹መቆየት› የሚለያዩ ይመስለኛል፤ መኖር የኅሊና፣ መቆየት ግን የአካል ነው፡፡ እየበላህና እየጠጣህ ሳትሞት ብዙ ዘመን መቆየት ትችል ይሆናል፡፡ በመብላትና በመጠጣት ብቻ ግን መኖር አትችልም፡፡ ለመኖር የኅሊና ምግብም ያስፈልግሃል፡፡ በነገራችን ላይ እኔ በተለያዩ ሀገሮች የሚገኙ ጸሐፊዎችን መብቶች ለመጠበቅ የሚሠሩ ተቋማትን በዐቅሜ በገንዘብ እረዳለሁ፡፡›› አለችኝ፡፡
‹‹ለምን?››
‹‹እንደ እኔ ይህች ዓለም የሰዎች መኖርያ እንጂ መቆያ መሆን የለባትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰዎች እንዲኖሩ ደግሞ የኅሊና ምግቦች ያስፈልጓቸዋል፡፡ የሚነበቡ፣ የሚታዩ፣ የሚጎበኙ፣ የሚሰሙ፣ ነገሮች፡፡ ምግብ ስንበላኮ ምግቡ በቀጥታ ደም ሥራችን ውስጥ አይገባም፡፡ የራሱ ሂደት አለው፡፡ በዚያ ሂደት ብዙ አካላት ይሳተፋሉ፡፡ አእምሮምኮ የሚያላምጠው፣ የሚፈጨው ነገር ይፈልጋል፡፡ ወዲያና ወዲህ የሚያመላልሰው፡፡ ይህንን ከሚሰጡን ሰዎች መካከል ናቸው ጸሐፍት፡፡ ለዚህ ነው የምደግፈው››
ወደ ሀገሬም፣ ወደራሴም እየሄድኩ እየመጣሁ እሰማታለሁ፡፡
‹‹አንቺ ይህንን አስተሳሰብ ከየት አገኘሽው?››
‹‹አጎቴ በጣም ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ያስተምራል፡፡ ከጓደኞቹ ጋር የውይይት ክበብ አላቸው፡፡ ይከራከራሉ፡፡ እኔም አንዳንድ ጊዜ እንድሳተፍ ይጋብዘኛል፡፡ ከእነርሱ ብዙ ተምሬያለሁ፡፡ አንደኛው ጓደኛው ሰውን ‹ለማሰብ የሚበላና›፣ለመብላት የሚያስብ› ብሎ ሲከፍለው ሰምቼዋለሁ፡፡ ››
‹‹አንቺስ ምንድን ነው የምትሠሪው? አልነገርሽኝምኮ›› አልኳት፡፡
ከት ብላ ከልቧ ሳቀች፡፡
ሀገርሽ ወዴት ነው ብዬ ብጠይቃት
ከምከም ብላ ሳቀች ነገሩ ቢደንቃት
የሚለው ሀገራዊ ግጥም ትዝ አለኝ፡፡
‹‹ለምን ሳቅሽ?››
‹‹የኔ ሥራ ከበድ ያለ ነው›› ብላ በድጋሚ ሳቀች፡፡
‹‹እንዴት? ፈላስፋ ነሽ እንዴ?››
አሁን ጭራሽ ከልቧ ሳቀች፡፡
‹‹አጎቴ ያለኝ ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ አሁን የምሠራበትን ሥራ ከብዙ ፍለጋ በኋላ አገኘሁና ኅሊናዬ መቀበል አቃተው፡፡ እንዳልገባ ቀፈፈኝ፤ እንዳልተወው በኢኮኖሚው ምክንያት ሥራ የለም፡፡ ለብዙ ጊዜ ሳወጣ ሳወርድ ቆየሁ፡፡ ኮሌጅ ትምህርቴን ደግሞ መጨረስ ነበረብኝ፡፡ ››
‹‹ሥራው ይህንን ያህል ምን ቢሆን ነው?››
‹‹ሬሳ መገነዝ››
ክው ነው ያልኩላችሁ፡፡ ክው፡፡ እኔን ራሴን እየገነዘችኝ ያለች መሰለኝ፡፡ ለካስ ከገናዧ ጎን ነው ያለሁት፡፡
‹‹ከመጀመርየው ሥራዬ አሰናበቱኝና ለትምህርቴ መደጎሚያ ሌላ ሥራ ስፈልግ በአንዲት ጓደኛዬ አማካኝነት ይህንን ሥራ አገኘሁ፡፡ እኔ በሕይወቴ እንዲህ ያለ ሥራ ይኖራል ብዬም ስላልገመትኩ ከበደኝ፡፡ የበፊቱን ሥራዬን በጣም እወደው ነበር፡፡ ይህንን ግን ለመቀበል ኅሊናዬ አልቻለም፡፡ በመጨረሻ አጎቴ ጋ ሄድኩና አማከርኩት፡፡››
‹‹ለምንድን ነው የከበደሽ›› አለኝ፡፡
‹‹ሥራውን አልወደድኩትም›› አልኩት፡፡
‹‹ለምን?››
‹‹በቃ አልወደድኩትም››
‹‹መልካም፡፡ አንቺ ወደፊት በሕክምና ሞያ ልትሠማሪ አይደለም እንዴ? ታድያ ለምን ጠላሽው? ይህኮ ምንም ማለት አይደለም፡፡ የምትወጅው ሥራ ባታገኚም ያገኘሽውን ሥራ መውደድ ግን ትችያለሽ፡፡ የምትወጅውን ሥራ ብታገኚ መልካም ነው፡፡ እርሱ ግን ባንቺ ብቻ አይወሰንም፡፡ የሚቀጥሩሽም ሰዎች ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ሥራሽን እንድትወጅው ለማድረግ ግን አንቺ ራስሽ ብቻ በቂ ነሽ፡፡ የምትወጅውን ሥራ ለማግኘት ከብዙዎች ጋር መፎካከር አለብሽ፡፡ ያገኘሽውን ሥራ ለመውደድ ግን ከራስሽ ጋር ብቻ ትፎካከርያለሽ፡፡ የምትወጅውን ሥራ ለማግኘት ቀጣሪዎችሽን ማሳመን አለብሽ፤ ሥራሽን ለመውደድ ግን ራስሽን ብቻ ነው የምታሳምኚው፤ የምትወጅውን ሥራ አግኚተሽ ነገ ልትጠይው ትችያለሽ፡፡ ያገኘሽውን ሥራ ከወደድሽው ግን መቼም አትጠዪውም፡፡ ››
‹‹ታድያ ምን ላድርግ?›› አልኩት፡፡
‹‹ ሥራሽን ለመውደድ ሞክሪ፡፡ ተመልከች ሥራሽ ማለት በቀን ቢያንስ ስምንት ሰዓት የምታሳልፊበት ቦታ ነው፡፡ ከቀኑ አንድ ሦስተኛውን፡፡ የሥራሽን ቦታ ከጠላሽው ከሕይወትሽ አንድ ሦስተኛውን ጊዜ ያለ ደስታ አሳለፍሽው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከባድ ጉዳት ነው፡፡ ስለዚህ የግድ መውደድ መቻል አለብሽ›› አለኝ፡፡ እኔን የጨነቀኝ እንዴት አድርጌ? የሚለው ነበር፡፡
‹‹ስለ ሥራሽ ዕወቂ፡፡ ብዙ ጊዜ የማናውቀውን ነገር እንጠላዋለን፣ ወይም እንፈራዋለን፡፡ የሥራውን ጠባይ፣ የሚያስገኘውን ጥቅም፣ በዚህ ሥራ ያሳለፉ ሰዎችን ተሞክሮ፣ ለሀገርና ለወገን የሚሰጠውን ጥቅም፣ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚያስገኘውን ፋይዳ፣ እንደ እምነትሽ ደግሞ ያለውን መንፈሳዊ ቦታ ዕወቂው፡፡ ከዚያም ከደመወዝ ያለፈ ዓላማ ለራስሽ ስጭው፡፡ ምን እያደረግሽ ነው? የአንቺ አስተዋጽዖ ምንድን ነው? ለሕይወትሽ ምን ልምድ ታገኚበታለሽ? ከዚህ ቦታ ብትወጭ እንኳን ምን ጊዜም ልጠቀሚበት የምትችይ ምን ትምህርት ማግኘት ትችያለሽ? ምን አዲስ ዕውቀትስ ትጨምሪያለሽ? እያልሽ ለራስሽ ተጨማሪ እሴት ፍጠሪ፡፡
‹‹የሥራ አካባቢሽን በቀን ለአንድ ሦስተኛ ጊዜ እንደተከራየሽው መኖርያ ቤትሽ ቁጠሪውና አሳምሪው፡፡ ለጽዳት ሠራተኞች ወይም ለሌሎች አትተይው፡፡ ያ ያንቺ ቤት ነው፡፡ ቢያምርና ቢስተካከል፣ ንጹሕና ሳቢ አካባቢ ቢሆን ከኃላፊዎቹም ሆነ ከባለቤቶቹ በላይ የሚጠቅምሽ አንቺን ነው፡፡ ሥራው የተቀላጠፈና የተስተካከለ ቢሆን የአንቺን ደስታ ነው የሚጨምረው፡፡ በነገርሽ ላይ በአንድ የሥራ ቦታ የሚፈጠሩ መልካምም ይሁን ክፉ ነገሮች የሕይወታችን አካል ሆነው ነው የሚቀጥሉት፡፡ ጠባያችንንና አሠራራችንን ይቀርጹታል፡፡ አንቺ ከሥራው ብትለቂም በዚያ ቦታ ያገኘሽው ነገር ግን አንቺን መቼም ቢሆን አይለቅሽም›› አለኝ፡፡
‹‹ለብዙ ቀን አሰብኩበትና ‹ልሞክረው› ብዬ ገባሁ፡፡ ይኼውልህ ሦስት ዓመት ከሰባት ወር ሠራሁ፡፡ አሁን ልለቅቀው አንድ አራት ወር ቀርቶኛል፡፡ ግን ቅር ቅር ይለኝ ጀምሯል፡፡ በሌላ ቦታ የማላገኛቸው ብዙ ነገሮች አግኝቼበታለሁ፡፡ ስለ ሕይወት ያለኝ አስተሳሰብ አሁን ተቀይሯል፡፡ ››
ፊኒክስ አውሮፕላን ማረፊያ ስንደርስ እርሷ ወደ ፍሎሪዳ ነበርና የምትጓዘው ተለያየን፡፡ እኔ ወደ ቺካጎ ለመሣፈር 45 ደቂቃ እዚህ እቆያለሁ፡፡ የነገርችኝ ነገር ግን መቼም ከኅሊናዬ አይጠፋም፡፡
ፊኒክስ፣ አሪዞና
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነውና በተመሳሳይ ኅትመት ባታወጡት ይመረጣል
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነውና በተመሳሳይ ኅትመት ባታወጡት ይመረጣል