በውግዘት በተለያዩት አባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማኅበረ ቅዱሳን ጠየቀ
ድረ ገጹ (Link) የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲ/ን
ሙሉጌታ ኀይለ ማርያምን ጠቅሶ እንዳለው “በአገር ውስጥና በውጪ አገር በሚገኙ አባቶች መካከል የተጀመረው ውይይት ከሁሉም ጉዳዮች በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሠራና እንዲፈጸም የማኅበሩ ፍላጎት” መሆኑ ተገልጿል።
ዋና ጸሐፊው ለመካነ ድሩ በሰጡት መግለጫ “የማኅበሩ አባላትም ሆኑ ሌሎቹም ምእመናን የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት በጥሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ተግተው መጸለይ ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የሰላሙንና የዕርቁን ሁኔታ ሊያደናቅፉ የሚችሉ ጉዳዮችን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱም
አንድነቷ ተመልሶ የምትሠራበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ማኅበሩ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመፈጸም ዝግጁ ነው፡፡ ስለሆነም የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መምህራን ጭምር የማኅበሩን አቋም የማስታወቅ ሓላፊነት አለባቸው” ብለዋል፡፡
እርቁ እንዴት ይሁን? እንዴት ይፈጸም የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጣቸው በሁለቱም ቦታዎች በሚገኙ አባቶችና በአስታሪቂ ሽማግሌዎች መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት መተው እንደሚገባ ዲ/ን ሙሉጌታ ማስታወቃቸውን
የጠቀሰው ድረ ገጹ “የተጀመረው እርቅ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግና እግዚአብሔርንም በጸሎት እንዲማጸን አሳስበዋል” ብሏል።
ዋና ጸሐፊው በማጠቃለያ መልእክታቸው “ፍቅር ሰላምና አንድነት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ስምረት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ሁል ጊዜ ለፍቅር ለመግባባትና አብሮ ለመሥራት በሰላም ለመኖር ሁሉም መጣር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ከዚህ የሚያደናቅፍ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ አንድነትን የሚጠላ ፍቅርን የሚጠላ ሁሉ ከእግዚአብሔር
አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ለዚህ ጉዳይ መትጋት ይኖርባቸዋል” ማለታቸውን ዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜና ይህንን የአባቶችን እርቅ አስመልክቶ ማኅበረ
ቅዱሳን ካሉት የውጪ አገር ማዕከላት አንዱ የሆነው የአሜሪካ ማዕከል ያዘጋጀው የቴሌኮንፍረንስ ውይይት ባለፈው እሑድ መካሄዱ ታውቋል።
ዕርቀ ሰላሙን በተመለከተ የተለያየ ሐሳብ ያላቸው ክርስቲያኖች ከተለያዩ የአሜሪካ እና የካናድ ከተሞች በተሳተፉበት በተባለው በዚህ
ውይይት የተለያዩ ሐሳቦች የተንሸራሸሩ ሲሆን በሚቀጥለው እሑድ ጥቅምት 4/2005 ዓ.ም/ ኦክቶበር 14/2012 ከሰዓት በኋላ እንዲቀጥል
ቀጠሮ ተይዞለታል።
አዘጋጅ ክፍሉ እንዳለው ውይይቱን ለመሳተፍ የሚፈልጉ በሙሉ በሚከተለው መግለጫ መሠረት መጠቀም ይችላሉ።
የኮንፈረንስ ቁጥር፦ 1-559-726-1200/ መግቢያ ኮድ፦ 24-81-12
ቀን፦ እሑድ ጥቅምት 4 ቀን
2005 ዓ/ም (October 14, 2012 )
ሰዓት፦ 6:00 PM - 8:00 pm በዲሲ ሰዓት
(EST) / 3:00 pm - 5:00 PM ካሊፎርኒያ ሰዓት (PST)
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
