የማያረጅ ፈረሰኛ ዛር!
የጽሑፉ ዓላማ፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ወንድ ሴት፣ ወጣት ሽማግሌ፣ “የተማረ” ያልተማረ፣ ከግለሰብ እስከ የፖለቲካ ድርጅት፣ እንዲሁም በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኘውን ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ ሁሉ “ሀገሬ!” ሲል የሚጠራትን ኢትዮጵያ ለመታደግ በአጠቃላይ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ፖለቲካ ድርጅት የምንከተለውና፣ የምናምነውንም የመፍትሔ ሃሳብ እንዲሁም የቆምንበትን የትግል መስመር ዳግም ቆም ብለን እንመረም ዘንድ በተጨማሪም መጽሐፍ ራዕይ የሌለው ሕዝብ መረን ነው እንዲል የፈውስም ሁሉ መጀመሪያ ራስህን በማወቅ ውስጥ ነውና ለውጥ የምትፈልግ ነፍስ ሁሉ ራስዋ፣ ስራዎችዋንና ድርጊትዎችዋን ትመረምር ዘንድ ተፃፈ።
የነበረውን አንደ ዋዛ አልፎ በታጋይ ፈንታ መምህር በትረ ሥልጣኑን ተረክበው ሀገርና ሕዝብ የማስተዳደር ሥራቸው ከጀመሩ እነሆ ሳምንታት ገፍተዋል። በእርግጥ “ሳምንታት ገፍተዋል” የሚለው አገላለፅ የነበረውን አልፎ አዲስ ሰው ስለ መተካቱን ለማሳየት እንጅ ለረጅም ዓመታት የዘለቁ ከመዋቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ግላዊና መንግሥታዊ ስብእናዎች ጋር የተያያዙ “ተቃውሞአችን የምንገልፅባቸው” መንገዶች መጨረሻው የት እንደሚያድርሰን አብረን የምናየው ይሆናል እንጂ አሁንም በነበርበት ፍጥነት እንደቀጠለ ነው። እዚህ ላይ ወደ ሰፊው ሐተዬ ከመዝለቄ በፊት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ (መልካም ምኞቴን በመግለጼ መቼም የሚያኮርፍ ባለ አእምሮ አይኖርም) ጥቂትዋ እርሾ ባልቦካ ሊጥ ውስጥ ገብታ ሊጡን እንደምታስነሳ ሁሉ በዚህ አጋጣሚ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገርን የሚጠቅም ሕዝብንም የሚረባና የሚያሳርፍ ለመጪውም ትውልድ መልካም አሸራ ጥለው ማለፍ ይሆንላቸውና ይቻላቸው ዘንድ ከልብ የሆነ መልካም ምኞቴን ለመግለፅ እወዳለሁ።
በጽሑፉ መግቢያ በግርድፉ ለመግለጽ እንደ ተሞከረ በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ የምንገኝ ዜጎች በሥልጣን ያለውን መንግሥት ኢ–ፍትሐዊ ድርጊቶቹን የምንቀወምበት መንገድና ይዘነው የመጣነው እንዲሁም ወቅቱንና ሰዓቱን ያለገናዘበ አሰላለፍ አሳሳቢነቱ ከምን ጊዜ በበለጠ እጅግ ገዝፎ እየታየ ነው። ይኸውም ሀገር ገድለዋል ትውልድ አጥፍተዋል በማለት የምንከሳቸው አውራዎች ከእንግዲህ ወዲህ ተስለንም ቢሆን ዳግም ፈጽመን ላናያቸው ተሰናብተውን ሲያበቁ በአንጻሩ እኛ ደግሞ ህያዋን ሆነን ሳለን ከማያይና ከማይሰማ በድን ተሽለን መታየት እያቃተን ነው። በነገራችን ላይ ሁላችን “መዋቾች” እንደ መሆናችን ሃይማኖት ኖረንም አልኖረንም የየትኛውም ርዕዮት ተከታዮችም ብንሆን ሰው ከሞተ በኋላ “አፈሩ ያቅልልለት” በማለት መልካም ምኞት መመኘትና የመዋች ቤተ ዘመድ ማጽናናት ሰብአዊነት ነው። ከዚህ በተረፈ ግን ግለሰቡ የሚያድነውም የሚያጠፋውም በመዋእለ ዘመኑ የነበረው እምነትንና ሥራ እንጅ ሰው የወደደ እንደሆነ ፊቱ እየቧጨረ ደረቱም እየደቃ ስለ አለቀሰ፣ የሀገር ሰው ጠርተን ደግሰን ስላበላንና ስላጠጣን፤ የጠላም እንደሆነ በሚያወርደው የእግርማን መዓትና ጸያፍ ቃላቶች የተነሳ ወደ ሲዖል የምትወርድ ሆነ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምትገባ ነፍስ እንደሌለች በዚህ አጋጣሚ አጽንዖት ሰጥቼ ጠቆም አድርጌ ለማለፍ እወዳለሁ።
ከኢትዮጵያ ውጭ ለከተመ ሕዝብ:
ጠቢቡ፡ “ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤
ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤
ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤
ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤
ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤
ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤
ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤
ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤
ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤
ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤
ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው እንዲል። በአጭር ቋንቋ ወቅቱን ያልጠበቀ አለጊዜው የሚሆንና የሚደረግ ማንኛውም ነገር ትርፉ ከንቱ ልፋትና ድካም ከመሆኑ በላይ ውበትም የለውና ሁሉን በጥቁር መነጽር የማየትና በጠላትነት የመፈረጅ በሽታ ነጥብ በነጥብ እየዘረዘርኩ እንደሚከተለው ያርጅልን ለማለት እወዳለሁ።
አንደኛ: ህያዋን ከሙውታን ጋር ምንም ዓይነት ክፍል እንደ ሌላቸውና የሞተውን ሰው በማሳደድ፣ በመርገምና፣ እያነሳንም በመጣል ለምን ጊዜአችንን እንገድላለን? ለምንስ ራሳችን አናደክማለን? በማለት ላነቃችሁ እወዳለሁ። ምንነው? ቢሉ አንድም የሞተውን አካል እያነሳ የሚያፈርጥና የሚፈጠፍጥ ሌላ ማንም ሳይሆን አፈር ያልለበሰ የሞተ ህሊና የተሸከመ ደካማ ፍጥረት ነውና። ለመሆኑ ከሞተ ጋር የሚያሯሩጠን ምስጢሩ ምንድ‘ነው? አሁን እኮ እኛ ኢትዮጵያውያን የሞተውን ለመውቀስ ዶክመንተሪ ፊልም እየሰራን የምንፅናናበት ጊዜ ሳይሆን እልፍ በማለት በስራ ራሳችን የምንለውጥበት ጊዜ ነው። ወይስ ይህ ሁሉ ጋጋታ ሰውዬው አልሞቱም ማለታችን ይሆን እንዴ? ታድያ በህልሙም በውኑም “አባይን የደፈረ መሪ አልሞተም!” እያለ … ደክሞ የሚያደክም ፍርፋሬ ለቃሚው ካድሬ ሳይሆን የተሳሳተው ያበድነው “እኛው” መሆናችን ነው።
ሁለተኛ: በህይወት የሌለውን ሰው እያነሳን ቡራ ከረዬ ማለቱ ምንድ ነው ጥቅሙ? አገር በድለዋል አልበደሉም? በድለዋል። ታድያ የሚሻለው በደልን በሞቁጠር በበደል ላይ በደል ለመፈጸም ማድባቱን ነው ወይስ ስህተትን ላለመድገም ካለፈው ስህተት ትምህርት በመውሰድ ለለውጥ እግርህን ማንሳትን ነው የሚበጀው? በአሁን ሰዓት በሙውት መቃብር ላይ ተቀምጠህ ወሬ መፍተልና ማቅጠንስ ለእኛ ለኢትዮጵያውን የሚሰጠው ትርጉም/ፋይዳው ምንድ ነው? እንዲህ ያለ ክፉ አመል ከቀድሞ ስህተት ይልቅ የከፋ ነውርና ስህተት እየፈፀምን እንደሆንስ ልብ ማለት ተስኖን ይሆን?
ሦስተኛ: ለመሆኑ በአዲስ ምዕራፍ በቀደመ አመላችን የሚያመላልሰን ምንድ ነው? መቼ ነው በሰከነ አስተሳሰብ ፖለቲካዊ ልዩነቶቻችንና አስተሳሰባችንን በማቻቻል ለአንዲት አገር የምንቆመውና ተግባብተንም የምንሰራው? ጎበዝ ተው እንጂ ሰው እንሁን እንደ ሰውም እናስብ:: በሆነ ባልሆነ ማጉረምረም ማንን ጠቀመ ነውና ገና ምን ከምኑ ባላየነው ወንበር ላይ እንዲህ የሚያንገራግረን? ለመሆኑ አዲስን ሰው በአዲስ አስተሳሰብ/መንፈስ መቀበል ያቃተን ምን ቢሆን ነው ችግራችን? ስለ አንድ ሰው ክፉም ደጉም ለማለትም‘ኮ ጥቂትም ቢሆን ጊዜ መውሰድና መረጋጋት ያስፈልጋል:: በእርግጥ በአዲሱ ባለ ስልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አይመጣም ብሎ ገና ለገና ከወዲሁ ልቡ የዘጋ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ቢኖር ይህ ሰው/ድርጅት ራሱ ካልመራና ካልነገሰ በስተቀር እግዚሃሩም ቢወርድ አሜን ብሎ በደስታ ይቀበላል ብሎ ማመን በራሱ የዋህነት ነው:: ክፉ ዓመል ከወዳጅ ዘመድ ያጣላል ይለያያልምና ይህም ያርጅልን!!
አራተኛ: በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ የምንገኝ ወገኖች ከውጭ ተቀምጠን በምናደርገው ትግል በኢትዮጵያ የለውጥ ፖለቲካ ልናበረከተው የምንችለው ድርሻችን በጣም ውሱን መሆኑን በመገንዝብ፣ በማወቅና በመረዳት ባልሆነ ነገር ጉልበታችንን ከመጨረስ ይልቅ ድርሻንን ለይተን በማወቅ ሀገር ውስጥ መሰረት ያደረገ የሀገሪቱ ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ ባማከለ መልኩ በተቀናጀና ወጥነት ባለው ሰላማዊ የሆነ የትግል መስመር ልንከተልና ልናበረታታ ይገባል። ይህ ለማለት የተገደድኩበት ዋና ምክንያትም ገንዘብ መሳሪያ ይገዛ እንደሆነ እንጂ ታጋይ ሊገዛ/የሰው ሃይል ሊሆን እንማይችል ማናችንም እንደማንስተው ስለማምን ነው። ባለ ሀብቱ ጠመንጃ ገዝቶ ራሱንም አስታጥቆ ሀገር ቤት ወርዶ ለመታገል እስካልገባ ድረስ ሐቁ ይሄ ነውና ማንም ለገዛ ግሉ ፍላጎትና ጥም በቀረጸው አጀንዳ ላይ መነገጃ አንሁን። ራሳችንን ችለን እንቁም! መነዳት፣ ባልገባንና በማናውቀው ፖለቲካ ውስጥም እየገባን ማዳመቅና ድምጽ ማጉሊያ መሆን ያርጅልን!! የምናደርገውን ከማድረጋችን በፊት ለምን? በማለት ጥያቄ መጠየቅን ይልመድብን።
በአጠቃላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር እናይበት በነበረው መነጽር እኚህ አዲሱን ባለ ሥልጣን ማየቱ ተገቢ አይደለም። ይቅር በእያንዳንዱ ዜጋ ጓዳ ጉዳይ ያለው ሰው ሲመጣ ቀርቶ አሮጌና አዲስ የሌለው ዓመት እንኳን አዲስ ዓመት ገባ/መጣ እየተባለ ሰው ራሱንና ቤቱን አፀዳድቶ ይጠብቅ የለም ወይ? አማርኛን እንደ ዓረብኛ ከቀኝ ወደ ግራ መፃፍ ካልተጀመረ በስተቀር ተቃውሞ እንደሆነ የትም አይሄድብንም። ደግሞ ለተቃውሞ አንደርስበታለን!! ነገር ግን ሰማንያ ቋንቋ የሚናገር: ከሰማኒያ እናቶች የሚወለድ ሰማንያ መልክ ያለው አንድ ሰው ተጠፍጥፎ ካልመጣ ከሆነም የቀረን ፌርማ የማሰባሰብ ስራ ነውና እንሞክረው። በተረፈ ወቅቱ ተረጋግተን ማረጋጋት የሚጠበቅብን ወቅት ነው። ተረጋግተን የማረጋጋት ግዴታ አለብን። ይህን ግዴታ በመወጣት ፈንታ ግን የተገላቢጦሽ ሆነን መገኘቱና በተለወጠ ከተማ እየኖርን ለራሳችን ሳንለወጥ ስለለውጥ ለመናገር መድፈራችን በእውነቱ ነገር በጣም የሚያሳፍር ነው። እንደባለ አእምሮ ማሰብ፣ ማውጣና ማውረድም እንደሆነ‘ኮ ከምንም በላይ ለራስ ጥቅም ነው። ብትበርም ጥንቸል ናት ዓይነቱ አካሄድ ግን ማንንም የማይጠቅም ፍሬ አልባ ዘር ነው የሚሆንብንና በከንቱ አንድከም።
ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች!
ፕሮፌሰር፣ ዶክተር፣ ተጋዳላይ፣ አንጋፋው … የሚሉትን ያልተማረውን ማኅበረስብ ማስደንገጫ ተቀጽላዎች ትተን ግልጹን እንነጋገር ከተባለ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓለቲካ ድርጅት መሪዎች ያለፉት ሃያ ዓመታት የፖለቲካ አመራር፣ ብስለትና ብቃት ለመገምገም ብዙ ማለቱ ሳያስፈልገኝ ዘና ብሎ ትክሻውን አደላድሎ ቤተ መንግሥት ጎብኝቶ የወጣውን ጎበዝ ላየች ዓይን ትቸዋለሁ። ይህን እጅን በአፍ የሚያስጭን ትእይት ያየች ነፍስ ከስም በዘለለ ከራሱ አልፎ ኢትዮጵያን የምታክል ግዙፍ አገር የመምራት ብቃት ያለው ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት/መሪ አለ ለማለት የምትደፍር ከሆነች ፊደል የማስቆጠር ያክል ወደኃላ ተመልሰን መነጋገር የሚኖሩብን ርዕሶች መነሳታቸው አይቀሬ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆፎው እንደተነካ ንብ የሞተውን ለመቅበር ግር ብሎ ሲወጣ መዋቹ ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱንም ጨምሮ አብሮ እዛው ግብዓተ ምድር ፈጽሞ/ቀብሮ በሰላም ወደ ቤቱ መግባት ይጠበቅበት ነበር። የታየው ግን በአንፃሩ አንዳንዶች እንደሚሉት “ተከፍሎትም” ሆነ “ተገዶ” የገደለውን ርዕሰ መንግሥት ሕዝብ በታላቅ ዋይታና ጭኾት መሪውን በክብር ሲሸኝ ነው። (አሁንም ይህ ሐቅ የሚክድ ግለሰብ ካለ ጨርቁን ሳይጥል የህክምና ባለሞያዎች ማየት ይጠበቅበታል።) ፍጥረት ዝር በማይልበት ስፍራ ጎበዝ እየተገለባበጠ ለእይታ በሚያመቸው መልኩ ዓይኖቹ እያወራጨ፣ አካሉ ያለ ከልካይ እግሩም መንገድ ወደ ወሰደው እያመራ ቤተ መንግስት ጎብኝቶ ሲወጣ ዛሬም እንደ ትናንት ቀረርቶ ማሰማት፣ በመግለጫና በስብሰባ ብዛት ሕዝብን ማድከም ከእናንተ አይጠበቅም ነበር። ዳሩ ግን “ዋናው ቀድሞ መገኘት ነው!” ሆነና የኢትዮጵያ ፖለቲካ መርህ ቀድማችሁ የያዛችሁትን የመሪነት ስፍራ ያሳየን ፍሬ ቢኖር መሪው ሞቶ ሥርዓቱ ግን እንደ ሥርዓት ራሱን አደላድሎ መቀጠሉ ነው። አሁንም ቢሆን ግን ወዴት እየሄደ እንዳለ በውል ያልተገነዘበ እናንተ የሚሰማና የሚከተል ግራ ቀኙን የማይውቅ ሕዝብ እስካለ ድረስ በተግባር አገር እየመራ ያለውን የኢህዴግ መንግሥት የለም! ብሎ በቃል የመናገር መብታችሁ የተጠበቀ ነው።።
እኔ የምለው ግን ይህ ሁሉ ፖለቲካዊ ኪሳራ ራሳችሁን መለስ ብላችሁ እንድታዩ የትግል አሰላለፋችሁ ድጋሜ እንድትመረምሩ ካልረዳችሁና ካላደረጋችሁ፤ ሰው ታጥቶ ሀገሪትዋን የመምራት ዕድል ብታገኙ እንኳን ያለውን ሥርዓት ካጠፋው ጥፋት ይልቅ መቶ እጥፍ ይህችን ሀገር ገድላችኃት እንደምታልፉ ለአፍታ እንዳትጠራጠሩ። ካለፈው ስህተቱ የማይማር፣ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቹንና ክንውኖቹን የማያይና የማይገመግም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ይቅር ሀገርና ሕዝብ የሚያክ ነገር ሊታደግና ሊያተርፍ ለራሱ ታዳጊ ያስፈልገዋልና።
ስለ እግዚአብሔር ንቁ! የምትመሩት ሕዝብ አይቅደማችሁ። ሕዝብ ከመሪው የተሻለ ነገር ይጠብቃል እንጂ እናንተ ተመልሳችሁ ሕዝብ አቅጣጫ እንዲያስይዛችሁ፣ እንዲመራችሁና፣ እንዲጠቁማችሁ ቆማችሁ አትጠብቁት። ከተራ አሉባልታና የጥላቻ ፖለቲካ በጸዳ በአዲስ መንፈስና በአዲስ ስልት ራሳችሁን መንቃት ካልቻላችሁ ግን ጊዜው ሲደርስ በሚነሱ ሃያላን የሚመሆነውን መሆኑ አይቀርምና የእናንተ የአሁኑ ወዲህ ወዲያ ማለት በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ኑሮአችሁን ትዶግሙ እንደሆነ እንጅ የዚህ ሕዝብ የድሉ ተካፋዮች ልትሆኑ እንደማትችሉ የተቀመጣችሁበት ወንበር እንደ በልዓም አህያ አፍ አውጥቶ እንዲናገራችሁ/እስኪናገራችሁ ድረስ አትጠብቁ።
በተረፈ ይሄ ዝም ብሎ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ዳህፀ ልሳን እየጠበቅህ በዬ ጋዜጣውና ደረ ገጹ ያዙኝ ሉቀቁኝ ማለትና ዲስኩር መንፋትም እንደሆነ ከቡና ወሬ የዘለለ ሀገራዊ ፋይዳ የሌለው ቀልድ/ድርጊት መሆኑን ተገንዝባችሁ የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ ወደ ሚችል ምዕራፍ ትሸጋገሩ ዘንድ እንዲሁም ሃያ ዓመት ዓመት ሙሉ የደከማችሁበት ብቸኛ ግለሰብ አልፈዋና እናንተም ገለሰብ ላይ ያነጣጠረ ፖሊሲያችሁን ቀርቶ ሥርዓቱን ታግላችሁ መጣል ይሆንላችሁ ዘንድ አእምሮን የሚሰጥ እግዚአብሔር ይርዳችሁ።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E-mail [email protected]
United States of America
October 06, 2012