የተሰደዱ ስድቦች
በአንድ ወቅት ነፍሷን ይማረውና ፊርማዬ ዓለሙ አንድ ገጠመኟን በኢትዮጵያ ሬዲዮ አስደምጣን ነበር፡፡ ፊርማዬ በመንገድ ላይ ስትጓዝ ከአንድ ጎረምሳ ጋር ትጋጫለች፡፡ ጎረምሳውም በለመደ አፉ በእናቷ ይሰድባታል፡፡ ፊርማዬ ነገሩን በስድብ ብቻ አላየችውም ነበርና ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ትወስደዋለች፡፡ ፖሊስም ልጁን ሕግ ፊት አቅርቦ ያስቀጣዋል፡፡ ይህንን ነበር ፊርማዬ የነገረችን ‹ስድብን ዝም አትበሉ› ብላ፡፡
ይህንን ፊርማዬን እስከ ክስ የወሰዳትን ስድብ ዛሬ ዛሬ በአዲስ አበባ መንገዶች አልሰማውም፡፡ እኔ ስድብ የመስማት ችሎታ ቀንሷል ወይስ ስድቡ ራሱ ሰው ዘንድ የመድረስ ዐቅሙ ተዳክሟል? አንዳንድ ጊዜም ‹ስድቦቻችን የት ሄዱ?› እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ መቼም ነገሮች ከዘመኑና ከቴክኖሎጂው ጋር ይቀየራሉና ስድቦችም መልካቸውን ቀይረው ሊሆን ይችላል፤ አለያም ደግሞ የመሳደብ ፋሽኑ አልፎበት ይሆናል እያልኩ ነበር የማስበው፡፡
በሚገርም ሁኔታ ግን ስድቦቻችን ለካስ እኔ አልሰማሁም እንጂ አድገው ኖሯል፡፡ ለካስ ተራቅቀው ኖሯል፡፡ ለካስ ዘምነው ኖሯል፡፡ ለካስ በአንደበት ብቻ መሳደብ ፋሽኑ አልፎበት ኖሯል፤ ሳልሰማ፡፡
ስድቦቻችን ለካስ ‹ሃይ ቴክ› ሆነውላችኋል፡፡ ለካ ‹አይ ሲ ቲ› ተምረውላችኋል፡፡ ‹ለካስ ጎዳና ተዳዳሪ› መሆናቸውን ትተው ‹ኢንተርኔት ተዳዳሪ› ሆነዋል፡፡
እነዚያን የተሰደዱትን ስድቦቻችንን ዛሬ ኢንተርኔት ላይ ነው የምታገኟቸው፡፡ ብሎግ ላይ፣ ፌስ ቡክ ላይ፣ ድረ ገጽ ላይ፣ ፓልቶክ ላይ፣ ኢሜይል ላይ፣ ዝንጥ ብለው ታገኟቸዋላችሁ፡፡ kkkkk እያሉ በእንግሊዝኛ ሲስቁ፡፡
አንዳንዴ ጭንቅላት ይቀየርና ዘመን ሳይቀየር ይቀራል፡፡ ያኔ እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ መሆን ይመጣል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ጭንቅላታቸው ከዘመኑ ቀደመና ካህኑም፣ ምእመኑም፣ ወታደሩም ሲቪሉም ሊተባበራቸው ቀርቶ ሊከተላቸው አልቻለም፡፡ ብቻቸውን ተቃጥለው፣ የቻሉትንም አቃጥለው ዐረፉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ዘመን ይቀየርና ጭንቅላት ሳይቀየር ሲቀር እንደዚህ ስድቦችን ሁሉ ከሀገር አሰድዶ ‹ሃይ ቴክ› ያደርጋቸዋል፡፡
ኢንተርኔትና ፊስ ቡክ፣ ኢሜይልና ብሎግ፣ ፓል ቶክና ድረ ገጽ ተፈጠሩልን እንጂ በአብዛኛው ፈጣሪያቸው እኛ አይደለንም፡፡ መቼም ይህ ዘመን እምቢ ቢባል እንኳን የመገናኛ ዘዴዎቹ ቤት ድረስ መጥተው የሚያንኳኩበት ዘመን ነውና እነዚህ ዕድሎች እኛው ጋ መጡ፡፡ አንዳንዶቻችን ሳንደርስባቸው ደረሱብን፤ አንዳንዶቻችን ሳንሄድባቸው መጡብን፡፡ ያን ጊዜ የመንገዱንና የመንደሩን ልማዳችንን ይዘን እነርሱ ጋ ወጣን፡፡
በባህላችን ‹የቤት ዐመል ገበያ ይወጣል› ነበር የሚባለው፡፡ አሁን እርሱ መቀየር አለበት፡፡ ‹የቤት ዐመል ኢንተርኔት ይወጣል› ነው መባል ያለበት፡፡ ስንቱ ተሳዳቢ፣ ስንቱ ተራጋሚ፣ ስንቱ ተደባዳቢ፣ ስንቱ ልቡ ያበጠበት የፍየል ወጠጤ ከነ ጠባዩ አንዲትም ሳትነካ ኢንተርኔት ላይ ወጥቶላችኋል፡፡
አሁን ስድብ በኢሜይል ነው፤ ስድብ በብሎግ ነው፤ ስድብ በፌስ ቡክ ነው፤ ስድብ በድረ ገጽ ላይ ነው፤ ስድብ በፓልቶክ ነው፡፡ ስድብ በትዊተር ነው፡፡
አንዳንዱማ እንግሊዝኛ አለማቻሉ የስድብ ሐራራውን እንዳይወጣ እያደረገው እንዴት እንደሚናደድ ታዩበታላችሁኮ፡፡ ‹በእንግልጣር አማርኛ› እንደምንም ብሎ የሚችለውን ያህል ይሳደብና አላረካው ሲል የ‹o› መዓት ወይም ደግሞ የ‹u› መዓት ይደረድርላችኋል፡፡ ሲያንባርቅባችሁ ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ይህ አያረካውም የቡጢ ወይም የስድብ ገጽታ ያለው ፎቶ ወይም ሥዕል ይጨምርላችኋል፡፡ ሌላው ከሁለቱም ያጣ ደግሞ ፊቱ ስድቡን እንዲገልጥለት አድርጎ ፎቶ ይነሣና ይለጥፍላችኋል፡፡
እኔ የምለው፣ መቃወም ወይም መደገፍ ማለት መሳደብ ነው ተብሎ በአራዳ መዝገበ ቃላት ላይ ተተረጎመ እንዴ? ስለምንወደው ሰው፣ አርቲስት፣ ተጫዋች፣ የፖለቲካ ሰው ወይም ድርጅት፣ እምነት፣ አመለካከት ወይም አቋም አንዳች ክፉ የመሰለን ነገር የተሰነዘረ እንደሆን ፍቅራችን በውክልና ስድብ ነው እንዴ የምንገልጠው፡፡ ስለምንጠላው ነገር መልካም ሲነገርስ የተቃውሟችን መገለጫው ስድብ ነው እንዴ? እስኪ በዚህ ጉዳይ በብሎግ፣ በድረ ገጽም ሆነ በፌስ ቡክ የሚደረጉ ውይይቶችን ተመልከቱ፡፡ በሃሳቡ ላይ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ሃሳብ ከሚሰጠው ይልቅ ያንን ሃሳብ ወይም ሰው የተቃወመውን ወይም የደገፈውን ‹ሙልጭ› አድርጎ የሚያጥረገርገው ይበልጣልኮ፡፡ ልክ ልኩን የሚነግረው፡፡
ያውም ደግነቱ ሁለት ነገር እያነቀው፡፡ አንዳንዱ የጊዜ ጥያቄ አለበት፡፡ እንደ መንገዱ ላይ ወይም እንደ ሠፈር ውስጥ እንደልቡ ሰዓት ወስዶ የስድብ መዓት ሊያዘንብ አይችልም፡፡ የመሳደቢያ ሰሌዳውም ውሱን ነው፣ የሚኖረውም ጊዜ ውሱን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለመጻፍ መቻሉ አለ፡፡ በአማርኛ ለመጻፍ የሚችለው፣ በአማርኛ ቢጽፍም ደግሞ ቀልጠፍ ብሎ መጻፍ የሚችለው ጥቂት በመሆኑ፤ በልቡ ያመላለሰውን በኩላሊቱ ያጤሰውን ስድብ ሁሉ ሊያወርድ አልተቻለውምና የኮምፒውተሩን ጠረጴዛ በመደብደብ ወይም ደግሞ በቀይ ወጥ ላይ አጥንት እንደመጨመር፣ በስድቡ ላይ አንዳች የሚያውቃትን እንግሊዝኛ ጣል በማድረግ ግንባር ይመታበታል፡፡
ምንም እንኳን
የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው
በእንግሊዝ አናግሪያቸው
እያልን ስንዘፍን ብንኖርም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታችን ለዐቅመ ስድብ የሚያደርሰን ባለመሆኑ እንዴት ተገላግለናል መሰላችሁ፡፡ በእንግሊዝኛ ተጽፈው በእንግሊዝኛ ውይይት የሚደረግባቸው የፌስ ቡክ ገጾች፣ ድረ ገጾችና ብሎጎች ላይ ሄዳችሁ ›የተማሩ› ተወያዮችን ስታዩኮ ‹ስድብ በእንግሊዝኛ› ምን እንደሚመስል ትማራላችሁ፡፡ አንዳንዱ ወደ ውጭ የወጣ ሰው ሀገሩ አስገድዶት እንግሊዝኛ ተማረ እንጂ ሀሳብ እንዳልተማረ፣ ፕሮናውንሴሽን ቀየረ እንጂ አመለካከት እንዳልቀየረ፣ ከተሰደደበት ሀገር ከገንዘብ በስተቀር ምንም እንዳልወሰደ የሚያጋልጠው የእንግሊዝኛ ስድቡ ነው፡፡
ድሮ እናቶቻችን ልጆቻቸውም ሆኑ ጎረቤቶቻቸው አለያም ደግሞ የመንደር ጋጠ ወጥ ሲያስቸግራቸው ‹ያንተን ነገር እግዜር ያሳየኝ› ብለው ነበር የሚራገሙት፡፡ አሁን ግን ርግማኑ ሳቀየር አይቀርም፡፡ ‹ያንትን ነገር በኢንተርኔት ያሳየኝ› መሆን አለበት፡፡
አፍሪካውያን ‹ከበሮን ሰርቀህ መደበቅ ትችላለህ፣ ከበሮን ሰርቀህ ደብቀህ መምታት ግን አትችልም› ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ከበሮን ሰርቀህ ደብቀህ ብትመታ ትያዛለህና፡፡ ድሮ ድሮ ስድብም እንዲሁ ነበር፡፡ ተደብቆ መሳደብ አይቻልም ነበር፡፡ እዚያው ስትፈልግ ወገብህን፣ ስትፈልግ ጭንቅላትህን ይዘህ ትሳደባታለህ እንጂ፡፡ ቢበዛ ነገር እንዳይከርብህ ሰውዬውን ፊት ለፊት ከምትናገረው በሠፈር ዶሮና ፍየል ወይም ውሻ መስለህ ትሳደባለህ፡፡
እድሜ ለኢንተርኔት፡፡ ‹ሽምቅ ተሳዳቢዎችን› አፍርተናል፡፡ እንደ ሽምቅ ተዋጊዎች የበረሃ ስም የሚጠቀሙ፣ ምሽግ ውስጥ የተደበቁ፣ ሸምቀው አደጋ በማድረስ የተካኑ ሽምቅ ተሳዳቢዎች፡፡ በፌስ ቡክ ሲሆን በውሸት ስምና ፎቶ ተሰውረው፡፡ በድረ ገጽና ብሎግ ሲሆን ደግሞ በስም የለሽነት (anonymous) ተደብቀው የስድብ ናዳ የሚያወርዱ፡፡
ምናልባት እነዚህ ሰዎች ‹ታላላቅ› የሚባሉ ሰዎች ይሆናሉ፡፡ የታወቁም ይሆናሉ፣ ባለ ሥልጣናትም ይሆናሉ፣ የሃይማኖት ሰዎችም ይሆናሉ፣ አስተማሪዎችና መካሪዎችም ይሆናሉ፣ የተከበሩና የተፈሩ ሰዎችም ይሆናሉ፡፡ ግን ሁለት ገጽታ አላቸው፡፡ ‹እንደ ጨዋ በመሬት፣ እንደ ዱርየ በኢንተርኔት›፡፡
እነዚህ ጽሑፍ የሰለቻቸው ወገኖቻችን፣ ሃያ አራት ሰዓት ኢንተርኔትና ስልክ ርካሽ በሆነበት ሀገር የሚኖሩ አምሳያዎቻችንን ደግሞ ፓልቶክ ላይ አግኟቸው፡፡ የፓልቶኩ አስተዳዳሪ እያንዳንዱን ተሰብሳቢ ገሥጾ ገሥጾ እየዘጋ እስከሚያባርራቸው ድረስ መጨፋጨፍ ነው፡፡ እንዲያውም ውይይቱ ከተጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጉዳዩ ይረሳና ‹የተሻለ ስድብ ያለው ማነው?› የሚል ውድድር እየተካሄደ ያለ ይመስላችኋል፡፡ ተው ብሎ የሚከራከረውም ሰው ራሱ እየተሳደበ ነው ተው የሚለው፡፡
አንዳንዴ እኛም በሚገባ እንግሊዝኛ አለመቻላችን፣ ፈረንጆችም አማርኛ አለመቻላቸው እንዴት ጥሩ መሰላችሁ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ለማወቅ ድረ ገጾቻችን ሲጎበኙ ስድብ በየዓይነቱ ነበር የሚኮመኩሙት፡፡ አንዳንዴማ በውጭ የሚወለዱትን ልጆች አማርኛ ካላወቃችሁ እያልን መጨቅጨቃችን ስሕተት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምንድን ነበር የሚያነቡት? ምንስ ነበር የሚሰሙት?
ስድቦቻችን ወደ ኢንተርኔት ሲሰደዱ ብዙ ግፍ ደርሶባቸዋል፡፡ አንቱታ ጠፍቶባቸዋል፡፡ ሽማግሌና ወጣት መለየት አቅቷቸዋል፡፡ ሃሳብና ሰው ተደባልቆባቸዋል፡፡ የሚባልና የማይባልን መለየት አቅቷቸዋል፡፡ የሴትና ወንድ አንቀጽ ተምታቶባቸዋል፡፡
በየፌስ ቡኩ፣ በየብሎጉ፣ ድረ ገጹና ፓልቶኩ ላይ በሚጻፉና በሚነገሩ ስድቦች አንድ ሰው ማን እንደሆነ መለየት ከባድ ነው፡፡ ያ ሰው መቼ ከሀገር እንደወጣ ማወቅ ግን ይቻላል፡፡ በንጉሡ ዘመን በነበሩ፣ በደርግ ዘመን በነበሩ፣ በኢሕአዴግ የመጀመርያዎች ዓመታት በነበሩ ስድቦች አሁንም የሚሳደቡ አሉ፡፡ ያኛው ቀርቶ ሌላ ስድብ መምጣቱን እንኳን ያልሰሙ፡፡ ስድብ መተው ቢያቅታቸው ቢያንስ ስድባቸውን ‹አብዴት› ማድረግ ያቃታቸው ሞልተዋል፡፡
ሊቃውንት ‹መንፈሰ ጽርፈት› የሚሉት አለ፡፡ የስድብ መንፈስ ነው፡፡ ተሳደብ ተሳደብ፣ አጥረግርግ አጥረግርግ የሚል መንፈስ፡፡ ይህ መንፈስ ድሮ በየዐመዱና አተላው ላይ ነበር አሉ የሚገኘው፡፡ በዚህ ዘመን ያልሠለጠን ማን አለ? መንፈሰ ጽርፈትም አተላውንና ዐመዱን ትቶ በየኢንተርኔቱ ሆኗል አሉ የሚዞረው፡፡ ድሮ እናቶቻችን ‹በቀትር አትዙሩ ጋኔን ይመታችኋል› ይሉን ነበር፡፡ ወደፊት ግን ‹ኢንተርኔት ላይ አትውጡ ጋኔን ይመታችኋል› ሳይባል አይቀርም፡፡ እርሱ ነው ስድቦቻችን ሁሉ ከከተማው አሰድዶ ኢንተርኔት ላይ የወሰደብን፡፡ ለመሆኑ እንዴት ይሆን ኢንተርኔትን ጠበል መርጨት የሚቻለው?
ቺካጎ፣ ኤሊኖይስ
©ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በተመሳሳይ ኅትመት ላይ ባለማውጣት ተባበሩ