የአቶ ኃይለማርያም ሥልጣን ከእግዚአብሔር ወይስ … ? ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
“ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና። በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። ለኢየሱስም መልሰው አናውቅም አሉት እርሱም ደግሞ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።”
ለጽሑፌ መነሻ የሆነኝ የኢሳት “የዜና” ማሰራጫ ማዕከል ባለደረቦች የሆኑት ሦስት ጋዜጠኞች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀመጠው በሳምንቱ ዓበይት ርዕሰ ጉዳያትን በሚዳሱሱበት የእሁድ ወግ በመባል የሚታወቀው ፕሮግራም ላይ የአቶ ሃይለማርያም ሹመትን በተመለከተ በሰፊው የተደረገውን ውይይት ነው። ሙሉውን የውይይቱ ይዘት ለማዳመጥ የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ሊያገኙት ይችላሉ። (ESAT Yehud Weg 23 September 2012 http://www.youtube.com/watch?v=d_MqXGNdMtU&feature=plcp)
ሌላውን የውይይቱ ይዘት እንደተጠበቀ ሆኖ የውይይቱን እቅጣጫ ካስቀየሰ የጋዜጠኛ ሲሳይ አስተያየት ልነሳ:: “ኢትዮጵያ ላለፉት አርባ ምናምን ዓመታት እምነት የሌለው ሰው ነው ሲመራት የኖረው ሀገራችንን:: ምንም እምነት የሌለው:: ምንም ይሁን ምን እምነት የሌለው ሰው ፈሪሐ እግዚአብሔር ሲያድርበት ከሱ በላይ የሆነ ሃይል ሲኖር ያንን እያሰበ የሚሰራ ትልቅ ነገር ነው:: በኮሬኔል መንግስቱም በአቶ መለስ ጊዜም እምነት የሚባል አልነበረም::”1እዚህ ላይ ከሌሎች የውይይቱ ተካፋዮች የተነሱ ጥያቄዎች በቀላሉ የማይታለፉና የላቀ አንድምታ ያላቸው ጥያቄዎች ተነስተዋል:: ከዚህ ቀደም ሀገሪትዋ የመሩ ግለሰቦች እምነት አልነበራቸውም ለሚለው ድምዳሜ “አይ መስቀል ሲሳለሙ ታይተው የለም ወይ? የተቀበሩትም ስላሴ ነው::” የሚል የሚል አንጻራዊ አመለካከት ሲንጸባረቅም “ለስታቲክ ነው” የሚል ምላሽ ተሰጥቶታል:: በነገራችን ላይ በእውቀትም ሆነ በስህተት ስማቸው ሳይጣራ የታለፉት ሃይማኖተኛ ነበሩ ተብለው የሚነገርላቸው የባእድ እምነት ተከታይ የሆኑትን ጃንሆይ በአጠቃላይ በሀገሪትዋ ያደረሱትን ውድመት ለሚመለከታቸው በመተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያንን እንዴት ገድለዋትና መዝብረዋት እንዳለፉ ለማወቅ ከተፈለገ ግን አሁንም በህይወት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ ሙሁራንና የመጻህፍት ሊቃውንት እነ መ/ም ሉሌና መጋቤ ብሉይ መዘመር በር ማንኳኳት ነው::
የጃንሆይ የእምነት ሰው መምሰል የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ከራሳቸው አልፈው ለዘመድ አዝማዶቻቸው እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ከመጠቀም ጋር የተየያዘም ነበር:: ስማቸው ሳይጠራ የታለፈውም የሃይማኖት መልክ ስለተላበሱ ነው፡፡ እውነቱ ግን ጃንሆይ በተግባራቸው የእምነት ሰው ነበሩ ወይ? ያልን እንደሆነ ጋዜጠኛ ደረጀ “ግን እንዴት እናውቃለን እምነታቸውን?” ሲል ባነሳው ማለፍያ ጥያቄ የተመዘኑ እንደሆነ ጃንሆይ በተለይ በቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ጉዳይ ላይ ቤተ–ክርስቲያን እየጠቀሙ እንዳሉ በማስመሰል ዘመድ አዝማዶቻቸውን (ምንም ክህነት የሌላቸው ተራ ምእመናን) በቁልፍ ቁልፍ ቦታቸውን በማስቀመጥ የፈጸምዋቸውንና ያደረስዋቸውን ግፎች መዘርዘር ሊያስፈልግ ነው:: በአጭሩ ግን እንደ ጃንሆይ ካባ ለብሰው ከሊቅነ ጳጳሳቱ እኩል እየቆሙ እያስቀደሱና እየቆረቡም የቤተ ክርስቲያን ካዝና የሚያራቁቱ መሪዎችም እንዳሉ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት በተጋባ ነበር።
ወደ ርእሰ ነገራችን ስንመለስ አንድ ፖዘቲቭ ነገር አድርጌ የማይላቸው የእምነት ሰው መሆናቸውን ነው እያለ ሲያስረዳ የመጣ ሲሳይ አሁን ይህን እምነቴ የሚሸረሽር ነገር ተከስተዋል በማለት ሲያስረዳ እንደሚከተለው ነበር ያለው “ይህንን እንኳን ፈተና ላይ የጣሉት ነው የሚመስለኝ:: ንግግር ሲያደርጉ ሁለት ጊዜ አይተናል እስከ አሁን እና ከምንም በላይ ይህንን ቦታ በርሳቸው ትግል በርሳቸው እንትን አይደለም ያገኙት እግዚአብሔር ስለ ፈቀደ ጭምር ነው ያገኙትና የሚያምን ሰው ደግሞ በተለያየ መንገድ እንደምናውቀው ያነበብነው የወጡ የሰጡአቸው ኢንተርቭዎች በሃይማኖት መጽሔት ላይ አንብበናል:: እና እዛ ላይ ደጋግሞ እግዚአብሔር የሚያነሳ ሰው እንዲህ ያለ ትልቅ መድረክ ላይ ሰማኒያ ሚልዮን ሕዝብ ትወክላለ ተብሎ አደባባይ ላይ ወጥቶ ሲናገር እግዚአብሔርን አንድን ቦታ ላይ አልጠቀሱም:: ከአንድ ሁለት ጊዜ ነው የምለው:: የማምነው ይሄ ምንድነው; የሚያደርጉት አንደኛ እንደዚህ በማለት ሰው ታሸንፋለህ ሰው ልብ ቀልብ መግዛት ትችላለህ ያንን የማያደርጉት አቶ መለስን ማሳጣት ሆኖ ስለታያቸው ነው:: እኔ እንደማምነው:: አቶ መልስ በስህተት እግዚአብሔርን ጠርተው አያውቁም::”
በመጀመሪያ “ከምንም በላይ ይህንን ቦታ በርሳቸው ትግል በርሳቸው እንትን አይደለም ያገኙት እግዚአብሔር ስለ ፈቀደ ጭምር ነው ያገኙት … ” የሚለውን የጋዜጠኛ ሲሳይ አባባል ምንም እንካ “በኢትዮጵያ ውስጥ ስርዓት ሊለውጥ የሚችለው በህወሐት መልካም ፈቃደኝነት ወይንም ህወሐት በሌላ ሃይል አስገዳጅነት ነው::“2እንዲሁም በተለይ“እዚህ ላይ ያለ ህወሐት ፈቃድ ምንም የሚሆን ነገር የለም። ቅድም ያልነው ነገር ነው ያለ ህወሐት ካልፈቀደ ምክንያቱ ስርዓቱ ስርዓት አድርጎ ያቆመው ህወሐት ነው እዚህ ላይ ምንም ብዥታ አያስፈልግም።“3የሚል ከቅድሞ አባባሎችና እምነት ፈጽሞ የሚጣረስና የሚያፈርስ እርስ በርሱም የሚጋጭ ወጥነት የማይታይበት አመላካከት ሲንጸባረቅ ብንሰማም ቀዳሚው አባባል በግልጽ የሚያስተላልፈው መልዕክትቢኖርየሲሳይ እምነትየአቶ ሃይለማርያም ስልጣን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ የሚያስረግጥ ሲሆን ሁለተኛና ሶስተኛው አነጋገሮች ደግሞ የአቶ ሃይለማሪያም ስልጣን ያለፈቃዱ አንዳች ነገር የማትከናወን ከህወሐት ዘንድ እንደሆነ በግልጽ ያስረዳሉ። እነዚህ ሁለት ጽንፍ የያዙ አስተሳሰቦች ለማስማማት የተሞከረ እንደሆነም ህወሐት ከመቼ ወዲህ ነው ፈጣሪ የሆነ የሚል ጥያቄ ሲሳይ መልስ መስጠት ሊጠበቅበት ነው።
“የሚያምን ሰው ደግሞ በተለያየ መንገድ እንደምናውቀው ያነበብነው የወጡ የሰጡአቸው ኢንተርቭዎች በሃይማኖት መጽሔት ላይ አንብበናል:: እና እዛ ላይ ደጋግሞ እግዚአብሔር የሚያነሳ ሰው እንዲህ ያለ ትልቅ መድረክ ላይ ሰማኒያ ሚልዮን ሕዝብ ትወክላለ ተብሎ አደባባይ ላይ ወጥቶ ሲናገር እግዚአብሔርን አንድን ቦታ ላይ አልጠቀሱም:: ከአንድም ሁለት ጊዜ ነው የምለው። እንዲህ ላለ አስተሳሰብ መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። ኢየሱስ እንዲህ አለ“ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። እርሱም መልሶ፦ አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ፦ እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። (ማቴ፣ 21፣ 28)።
አንደኛ፤ አንድም ስፍራ የእግዚአብሔር ስም አልጠሩምና … ተብሎ እንደ ምክንያት ለቀረበው የቅድሳት መጻህፍት ይዘትም ሆነ የክርስትና እምነት አስተምህሮ ግንዛቤ ከማጣት የተነሳ ነው:: ምን ነው ቢሉ በመጽሐፈ አስቴር የእግዚአብሔር ስም አልተጠራምና መፅሐፈ አስቴር ከቅድሳት መጻሕፍት ጋር ምንም ክፍል የለውም የማለት ያክል ነው:: ይህ ደግሞ እውቀት ሳይሆን በሀገርኛ አባባል አዲስ አፍላነት ይባላል:: ስለዚህ የአቶ ሃይለማርያም መንግስታዊ ቃል/ስልጣን ለአማኝ ብቻም ሳይሆን ከሃይማኖት ውጭ ለሚመላለሱ ኢትዮጵያውያን እስከሆነ ድረስ ያደረጉት ንግግር ተገቢና ከግል እምነታቸውም ምንም የሚያገናኝ ነጥብ እንደሌለው ሊሰመርበት ይገባል::
ሁለት፤ በዬ መጽሔቱ በተደጋጋሚ የእግዚአብሔር ስም ሲያነሱ የመጡ ሰው አሁን ባድረጉት ንግግር ግን አንድንስ ጊዜ እንኳ የእግዚአብሔር ስም አልጠሩም ተብሎ ገና ወንበራቸውን ባላደላደሉ ሰው የረባና ያልረባ ነገር ተይዞ ለትችት መሽቀዳደሙና አካኪ ዘራፍ ማለቱ በእውነቱ ነገር የሚያስገመግም ነው:: ለትችት ከመታጠቅም በፊት እኚህ ሰው በመጽሔት ያደረጉት ቃለ ምልልስም ሆነ የሰጡትን ቃል ለማን ነው? የመልእክቱ ተቀባይ/ተደረሲ ማን ነው? በመዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ፈንታ በተረከቡት ስልጣን ምክንያት ያደረጉት ንግግርም ሆነ የሰጡትን መግለጫስ ተቀባዩ ማን ነው? ንግግሩን ያደረጉት ማንን ወክለው ነው? እንደ አንድ የሀገር መሪ ምንስ ይሉ ዘንድ ይጠበቃል? የሚለውን በቀላሉ ሊነሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች እንኳ ግምት ውስጥ አልገቡም:: ለነገሩ የውውይቱ መሪ ከፍተኛ የሆነ የሃስብ ልዩነትና አለመግባባት እየታየ ሲመጣ “በመጀመሪያ እኛ ጋዜጠኞች እንጂ ኤክስፐርቶች/ባለሞያዎች አይደለንም “4ሲሉ በግልጽ እንዳስቀመጡት የዚህ ሁሉ ሕጸጽና ስህተትም መንስኤ ከዚህ አልፎ ሌላ ሊሆን አይችለም ባይ ነኝ::
ሶስተኛ፤ በመሰረቱ ሲሳይ “በአንድ በኩል አከብራቸዋለሁ” ሲል ክብሩን የለገለሰላቸው መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መከበርም ካለባቸው መከበር የሚገባቸው የእግዚአብሔር ስም ለማስመሰል ባለ መጥራታቸው ሳይሆን የት ቦታ ለማን ምን መናገር እንደሚገባቸው በሚገባ በማወቅ በዚህ በኩል የተጣለባቸው ሀገርን የመምራት ሃላፊነት በብቃት ተወጥተዋል በማለት ሊያከብራቸው በተገባ/መሆን ይገባዋል፡፡
የማምነው ይህን ለምንድ ነው ይህን የሚያደርጉት አንደኛ እንደዚህ በማለት ሰው ታሸንፋለህ የብዙ ሰው ልብ ቀልብ መግዛት ትችላለህ ያንን የማያደርጉት አቶ መለስን ማሰጣት መስሎ ስለታያቸው ነው። እኔ እንደማምነው። አቶ መለስ በስህተትም እግዚአብሔር ጠርተው አያውቁም። በአንድ በኩል እናከብራቸዋለን ለማስመሰል ባለመጥራታቸው።”5በመሰረቱ ሲሳይ ከጅምሩ የሳትከው ቁምነገር ቢኖር አቶ ሃይለማርያም የተሰጣቸው መድረክ ዓላማ ስተኸዋል በተጨማሪም እኚህ ባለ ስልጣን መድረኩን በመጠቀም ምን አይነት መንፈሳዊ ቋንቋ ይናገሩ ዘንድ ጠብቀህ እንደነበርክ ግልጽ ያደረግከው ነገር የለም።
“አቶ መለስ በስህተት እግዚአብሔር ጠርተው አያውቁም“የሚለውን አንድ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የፍልስፍናና የስነ ምግባር መምህር የሆኑትን የቅርብ ወዳጄ መምህር ተሾመን ነበር ያስታወሰኝ። በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራኖቻችንን ወደ መማሪያ በሚገቡበት ሰዓት ከመቀመጫችን ተነስተን አክብረን የመቀበል ልማድ ነበረን። ታድያ እኚህ መምህራችን አንዲህ ዓይነቱ ውዳሴ ብዙም አይደላቸውምና ከዕለታት አንድ ቀን ለእኛ ለተማሪዎችቻቸው ያላቸውን የላቀ ክብር በመግለጽ አንዲህ አሉን “በእውነቱ ነገር ወደ ክፍል በገባሁ ቁጥር ከመቀመጫቹ እየተነሳችሁ ለምን ትቸገራላችሁ። ስለ ቆማችሁ ሳይሆን ተቀምጣችሁም ክብር መስጠት አለ እየቀፈፋችሁ ከምትነሱ“ሲሉ እንደዋዛ የክብር ትርጉም አስተምረው ማለፋቸውን አስተውሳለሁ። አሁንም ቢሆን ግን ማወቅ የሚገባን ነጥብ ቢኖር አቶ ሃይለማሪያም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያን ባለ ስልጣን እንደ የመንግስት ሹሞችና የሀገር መሪዎች መድረኩ ይሰብኩ ዘንድ እስካልተሰጣቸው ደርስ የግል እምነታቸውን በ አደባባይ ማንጸባረቅ አይጠበቅባቸውም። በመሰረቱ እግዚአብሔር ማምለክ ማለት የእግዚአብሔር ስም ከመጥራትና ካለመጥራት የሚያገናኝ ምንም ነገር የለውም። እግዚአብሔር ማምለክ ህይወት እንጂ ድስኩርም አይደለም።
እኔ ሲሳይ የየትኛው እምነት ተከታይ እምነት እንደሆንክ አላውቅም ቢሆንም ግን በነጋ በጠባ ቁጥር የሌለውን አቅምና ሃይል እየሰጠህ “ህወሐት፣ ህወሐት” ከማለት ውጭ እንደ አማኝነትህ/ክርስቲያን (ይቅርታ ከሆንክ ነው) የሌላ እምነት ተከታይም እንደሆንክ እንደ አማኝነትህ የምታመልከውን አምላክ ስም በመጥራት የኢትዮጵያ ምድር ችግር የሚፈታ መንፈሳዊ ህይወታችን ሲስተካከል ነው፣ ፊታችን ወደ “እግዚአብሔር” ስንመለስ ነውና ወደ “እግዚአብሔር” እንመለስ ስትል መንፈሳዊ መፍትሔ ስትሰጥ ሰምቼህ አላውቅም። ይህ አለማድረግህ ግን ሲሳይ ከሃዲ/አምላክ የለሽ ነህ ማለት አይደለም። አንደ አንድ ሰራተኛ የምትሰራበት የዜና ማሰራጫ ማዕከል የአንድ የእምነት ተቃም መገልገያ እስካልሆነ ድረስም ይህ አለማድረግህ ለኩነኔ የሚፈጥን ሰው ካለ ተሳስተዋል። እንግዲህ የአቶ ሃይለማርያም መድረክም እንዲሁ ነው። እውነቱ ለመናገር ሲሳይ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን እምነት ተከታይ ከሆንክ አማትበህ ፕሮግራምህ ስትከፍትና አስጀምሮ ያስጨረሰን … በማለትም በተመሳሳይ ፕሮግራምህ ስትዘጋ ገጥሞኝ አያውቅም። ይሄማ እንዴት ይሆናል ስራዬን እየሰራሁ አይደለ እንዴ? ትል ይሆናል። እንግዲህ አቶ ሃይለማሪያምም ስራቸውን እየሰሩ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ አንድ ተራ ዜጋ የማይስተው እውነት ነው። እንደ ጋዜጠኛነትህ ሞያህ ይህን ታደርግ ዘንድ እንደማይፈቅድለህ እንዲሁ አቶ ሃይለማርያም በሃይማኖታዊ መንግስት የምትመራ ሀገር መሪ እስካልሆኑ ድረስ የተሰነዘረውን ትችት በየትኛውም ፖለቲካዊ ትንተና ሚዛን የማይደፋ ተራ አባባል ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ብዙ አርቀን ሳንሄድ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ልጨምር ይኸውም ጋዜጠኛ አበበ ገላው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በስያትል ቅዱስ ገብርኤል አጥቢ ተገኝቶ የሰጠውን የህይወት ምስክርነቱን እንመልከት።6 አበበ በዚህች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ተገኝንቶ ካደረገው ንግግር መካከል አንድ እንዴት ወደ ፖለቲካው ዓለም እንደተቀላቀለና በሚገባም ሊገፋበት እንደቻለ ይገኝበታል። ይኸውም አበበ ሲሲያረዳ እንደተናገረው “መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል” እንደ ተገለጠለት ተናግረዋል። እዚህ ላይ በግሌ ምንም ዓይነት ተቃውሞም ሆነ ቅራኔ የለኝም። ቢሆንም ግን አንደ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና ሰው ግን የተሰጠው ምስክርነትና የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎችን በመንተራስ አበበ በህልሙ ያየው ወይም በድምፅ የሰማውን ነገር በእርግተኝነት ከእግዚአብሔር ለመሆኑ ይረዳው ዘንድ ግን በርካታ ወሳኝ ጥያቄዎች ማንሳኔ አይቀርም። ይህ በእንዲህ አንዳለ በየደቂቃው ከስክሪ የማይጠፋው አበበ ይህን የህይወት ምስክርነቱ ለምን በኢሳት አልተናገረም? የሚል አይጠፋም። ይህንስ ያላደረገበት ምክንያት እውነት የተባለውን “መልአከ ቅዱስ ገብርኤል” ስላልተገለጠለት ይሆን? በማለት ስጋታቸውን የሚገልፁ ወገኖችም አንዳሉ ሆነው። በሌላ በኩልም እኔን ጨምሮ (የህይወት ምስክርነቱ እንደ ምስክርነት የሚጠብቁ ማለት ነው) አበበ የህይወት ምስክርነቱ በቤተ ክርስቲያን አከባቢ ብቻ ተወስኖ አንዲቀር ያደረገበት ምክንያት የት ስፍራ ለማን ምን መናገር እንደሚገባው ከማወቅ የተነሳ እንጂ በኢሳት እስክሬን ምስክርነቱ ደግሞ አለመናገሩ ስለሚያፍርበት ነው የሚል እምነት የለኝም። በመሰረቱ የሚናገረውን የሚያውቅ ሰው አስቀድሞ ለማን ምን መናገር እንዳለበት የማያውቅ ሰው ነው። ሲሳይ አንተም አንደሆንክ ፕሮግራምህ ይዘህ ለቀረጻ ከመውጣህ በፊት የምትዘጋጅበት ርዕስ አድማጭህን ማእከል ያፈረገ እንደሆነ ትስተዋለህ የሚል እምነት የለኝም።
አሁንም ቢሆን የአቶ ሃይለማርያም ጉዳይ እንዲሁ ነው። ሰማንያ ሚሊዮን ሲባል የተጠቀሰውን ሕዝብ በመላ የአቶ ሃይለማርያም ቡራኬ ለመቀበል ሳይሆን የሚጠባበቀው መንግስታዊ ቃላቸውን ለመስማት ነው። ሲሳይ በአንጻሩ ጠብቀህ ኖረክ እንደሆንክ ግን የአቶ ሃይለማርያም የእግዚአብሔር ስም አለመጥራት ሳይሆን ስህተቱ ጥፋቱ ያንተው ነው። የተጠቀሰውን አሃዝ ቁጥር ያለው ሕዝብ እንደሆነም የየትኛውም ቤተ እምነት ተከታይ ቢሆኑም ዳሩ የአቶ ሃይለማርያም እምነት የሚጋራ ሕዝብ አይደለም። ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ መንግስትም አይደለችም ባለ ስልጣንዋ ሃይማኖታዊ ቋንቋ እንዲናገርም አይጠበቅበትም። ለወደፊቱም እንዳትጠብቅ!!
በአንድ ወቅት መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በመቀሌ ከተማ ተገኝተው ያደረጉትን ንግግር በዛሬ አጉሊ መነጸር እየታየ እንዴት ኢትዮጵያን ከሚመራ መሪ ይህን ይነገራል እየተባለ የሚሰነዘሩ ትችቶችን ሰምተን ጠግበነዋል። አቶ ሃይለማሪያም ንግግራቸውን ሲከፍቱ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እጸለያለሁ …” በንግግራቸው መኸልም “እያጣቀሱ ኢየሱስ ጌታ! … አሜን!” በንግግራቸው መዝጊያም “ጌታ ኢየሱስ ይባርካችሁ” በማለት ወርደው ቢሆኑ ኖሮ በመንግስታዊ ንግግራቸው ማኸል የግል እምነታቸውን ቢያጸባርቁ ኖሮ ቀደም ስል እንደገለፅኩት አንድም ጊዜ ቢሆን በስህተት “ጌታ ይባርካችሁ” ቢሉ ኖሮ አቤት የፈጣሪ ያለህ ከየአቅጣጭው ሊያስነሳው የሚችለው አቧራ እንግዲህ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው:: “እንዴት እንዲህ ይላሉ ኢትዮጵያ እኮ የሙስሊሙም; የኦርቶዶክሱም; የባህዩም የሁሉም ናት” እየተባለ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ የሚዘልቅ ምድር ትሸከመው ዘንድ ያማይቻላት ስድብና ውርጅብኝ በከናነቡ ነበር።
እንግዲህ “የአቶ ኃይለማርያም ሥልጣን ከእግዚአብሔር ወይስ … ?”ለሚለው ጥያቄ እያንዳንዳችን በጅምላ ሳይሆን በየግላችን ሃላፊነት በመውሰድ የምንመልሰው መልስ ይሆናል። እዚህ ላይ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ እንደማይወጣ: በተምታታ አስተሳሰብም ህይወት እንደማይመራ በመገንዘብ አንዱን ላይ ራሳችንን እናሳርፍ። ከእግዚአብሔር ነው ተብሎ መታመኑ ብቻ ሳይሆን የአቶ ሃይለማሪያም ስልጣን ምንጭ ከሌላ ወገን/ሃይል ነው ብሎ ማመን በራሱ ራሱ የቻለ ጥቅምና ጠንካራ ጉን ሊኖረው ስለሚችል አንዱ ላይ መርገጥ ይጠበቅብናል።
የአቶ ሃይለማርያም ስልጣን በእርግጥም ከእግዚአብሔር ነው በማለት ይሁንታችንን የሰጠን እንደሆን የዚህ ዓይነቱ እምነት አንድ የተገለጠ ጥቅሙ ከእንካ ሰላምታ ዓይነቱ ህይወት ወጥተን በቀላሉ ከጎናቸው በመቆም ለለውጥ ያለንን ተነሳሽነት በማሳየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደሚፈለገው የእድገት ደረጃ ሊያደርሰን ይችላል ይሆናል አንድነት ሃይል ነውና። የለም! የስልጣናቸው ምንጭ ሌላ ሃይል ነው ከተባለም ታጋዩ በሚፈልገውና በሚያመቸው የትግል መስመር ነድፎ የሚፈልገውን ነጥብ ማስመዝገብ ይቻለው ዘንድ ያግዛል።
ለነገሩ ከሰው ነው የተባለ እንደሆነ የቀድሞ ህወሐት የለም፣ ተንኮታኩተዋል፣ ተዳክመዋል: እክትሞለታል: ግባ በለው! እየተባለ የሚሰጠውን ደመ ነፍሳዊ “ትንተና” እሳት ሊበላው ነው። ከእግዚአብሔር ነው የተባለ እንደሆነም በአቶ ሃይለማርያም ላይ አፍህን መክፍት ማለት የሚያስሸልምና አፈወርቅ እየተባለ የሚያስሞግስ መሆኑ ይቀርና ቀደሞውኑ በድፍረት የተነሱት በቅባቱ ባለቤት በሆነው በእግዚአብሔር ነውና አፈ ወርቁ ወደ አፈ ለምጽ ተለውጦ በሃፍረትና በቁዘማ ቀሪ ዘመን መግፋትም ያስከትላል ማለት ነው:: (ይህ የምለው ግን ለሚያምኑ ፈሪሃ እግዚአብሔር ላላቸው ነው)::በመጨረሻ አስፈላጊ ከሆነም ስመ ክርስቲያን ሳይሆን አንድ አማኝ በፖለቲካ ቦታ ላይ ምንም ዓይነት ስብእና ሊኖረው እንደሚገባና ምን እንደሚመስል በሰፊው የምለው ነገር ይኖረኛል ለዛሬ ግን የወጣውን ሁሉ በሆነ ባልሆነ በረባ ባልረባ ለመቀጥቀጥ ከመትጋት ይልቅ አንደበቶቻችን በመጠበቅ ህይወታችንን እንለውጥ ለማለት እወዳለሁ::
ጥብቅ ማሳሰቢያ፡
የጽሑፉ ይዘት ክርስቲያን በፓለቲካ ተሳትፎው ከማንጸባረቅ አልፎ ጽሑፍ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑትን ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጥብቅና የተጻፈ እንዳይደለ ጸሐፊው በእክብሮት ለመግለጽ ይወዳሉ።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E-mail [email protected]
United States of America
September 30, 2012