አደንን በመሰሉ ሰው ሠራሽ ችግሮችና በተፈጥሮ ላይ በሚደርሱ አደጋዎች የተነሣ በዓለማችን ላይ የነበሩ አያሌ እንስሳትና ዕጽዋት ጠፍተዋል፡፡
ለእነዚህ ዝርያዎች መጥፋት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው የሚባሉት አራት ናቸው፡፡ የመጀመርያው የሚኖሩበት የአየር ንብረት መለወጥ ነው፡፡ ለኑሯቸው ተስማሚ የሆነውና የሚያስፈልጋቸው የአየር ንብረት መለወጥ ሲጀምር እነርሱም ቀስ በቀስ ቁጥራቸው እየቀነሰ መጥፋት ይጀምራሉ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ልቅ የሆነ አጠቃቀም ነው፡፡ የእነርሱን መብት ሊያስከብር፣ ዝርያቸውንም ከመጥፋት ሊያስጠብቅ የሚችል ኃላፊነት የተሞላው አጠቃቀም ከሌለ እነዚህን ዝርያዎች ማንም እንደፈለገ በማድረግ እስከመጥፋት ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ የሰው ልጆች ያልተገባ ጣልቃ ገብነትና ጫና ነው፡፡ እያንዳንዱ ዝርያ በመኖርያ አካባቢው የራሱን የአኗኗር ዘይቤ ቀይሶና የኑሮ ልማድ መሥርቶ ይኖራል፡፡ የሁሉም የበላይ ነኝ ብሎ የሚያስበው የሰው ልጅ የራሱን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ሲል በሚያደርገው ሁሉንም የመነካካት በሽታው የተነሣ የእነዚህን ዝርያዎች አካባቢ ሲረብሸውና እነርሱም ይህንን የሰው ልጅ ረብሻ መቋቋም ሲያቅታቸው ወይ ቦታቸውን ለቅቀው ለአደጋ ይጋለጣሉ፤ ያለበለዚያም በአካባቢያቸው ሆነው ዝርያቸውን ያጣሉ፡፡ አራተኛው ደግሞ የመኖርያ አካባቢያቸውን ማጣታቸው ነው፡፡ በሕገ ወጥ ሠፈራ፣ በሚገነቡ ካምፖች፣ በጫካዎች መመንጠር፣ በጦርነትና በሌሎችም ምክንያቶች እነዚህ ዝርያዎች ለብዙ ዘመናት የለመዱት አካባቢ መልኩን ይቀይራል፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚህ ዝርያዎችም አብረው ይጠፋሉ ወይም አካባቢውን ለቅቀው ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡
በእነዚህ አራት ምክንያቶች እየጠፉ ካሉት የዓለማችን ዝርያዎች መካከል የኢትዮጵያ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሊካተቱ ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደ ባለሞያዎቹ አገላለጥ አንድ ዝርያ በመጥፋት ላይ ያለ ዝርያ ነው (An endangered species) የሚያሰኘው የዚያ ዝርያ ቁጥሩ እየቀነሰ አለያም ደግሞ በአካባቢያዊ ለውጥ ምክንያት በዓለም ላይ የመቀጠል ዕድሉ እየተመናመነ ሲመጣ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጦችና መጽሔቶችም ቁጥራቸው እየቀነሰና የመጥፋት አደጋም ከፊታቸው እየጠበቃቸው የሚገኙ ዝርያዎች ናቸው፡፡
ከሃያ ዓመታት በፊት ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው ጋዜጦችና መጽሔቶች ሀገሪቱን አጥለቅልቀዋት ነበር፡፡ መንገዱ ሁሉ ንባብ ንባብ ይሸት ነበር፡፡ ያን ጊዜ እስከ ሃምሳ ሳንቲም በሚጠጋ ዋጋ ይሸጡ የነበሩት እነዚህ ጋዜጦችና መጽሔቶች እረኛ ምናለ? የሚለውን ይትበሃል ቀይረው ጋዜጣ ምን አለ? አሰኝተውት ነበር፡፡ ከሰኞ እስከ እሑድ እየተደራረቡ እየወጡ መርጠንና አማርጠን እንድንገዛ አድርገውን ነበር፡፡
ቀስ በቀስ ግን ዝርያቸው እየተመናመነ መጣ፡፡ በአንድ ቀን ሦስትና አራት ጋዜጦችና መጽሔቶች በአናት በአናቱ ይወጡ እንዳልነበር ጋዜጣና መጽሔት የማይወጣባቸው ቀናት እየበዙ ማንበብም ብርቅ እየሆነ መጣ፡፡ የተረፉትም ቢሆኑ የወረቀትና የማሳተሚያ ዋጋ ጭማሬን ተከትለው ቁጥራቸው ወደታች ዋጋቸው ወደ ላይ ወጣ፡፡ አሁን ደግሞ የንባብ ርሃብ የምንቀምስበት ደረጃ ላይ እየደረስን ነው፡፡ ከሳምንት ወደ ሳምንት ከጥቂት ጋዜጦችና መጽሔቶች በቀር ዓይን ይዞ የሚነበብ ነገረ እይጠፋ ነው፡፡ ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ጋዜጦችና መጽሔቶች በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች ናቸው የምለው፡፡ ለዝርያዎች መጥፋት የመጀመርያው ምክንያት የሆነው የምድራችን የአየር ንብረት መለወጥ በጋዜጦቻችንና መጽሔቶቻችንም ላይ እየታየ ነው፡፡ ከ1984 እስከ አሁን ድረስ እጅግ ብዙ አሠራሮች፣ ሕጎችና ሥነ ሥርዓቶች ተለዋውጠዋል፡፡ እነዚህ ለጋዜጦችና መጽሔቶች መኖር አስፈላጊ የሆነውን የአየር ንብረት የሚያጨናንቁ ሕጎችና አሠራሮች መለዋወጥ የጋዜጦቻችንና መጽሔቶታችን ዝርያ እንዲመናመን እያደረገው ነው፡፡
በዓለም ላይ ብዙ ሀገሮች በመጥፋት ላይ የሚገኙ ዝርያዎችን የሚመለከት ሕግ አላቸው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ዝርያዎችንም እያጠና በየደረጃቸው ዝርዝር የሚያወጣና ሕጉንም የሚያስተገብር ተቋምም መሥርተዋል፡፡ ይህ የማይተገበርበት ሁኔታ ሲፈጠር ግን ለእነዚህ ዝርያዎች ሁለተኛው የመጥፋት ምክንያት ይሆናል፡፡ እነዚህ ዝርያዎች በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሮ ምክንያቶች እንዳይጠፉ የመከላከያና የመደገፊያ ሕግና አሠራር ካልወ ጣላቸውና ለዓለማችን ጤንነትና ደኅንነት የሚያስቡ ሁሉ ካልተባበሯቸው በቀር እነርሱ ብቻቸውን ራሳቸውን ከመጥፋት ሊታደጉ አይችሉም፡፡
ጋዜጦቻችንና መጽሔቶቻችንም በዋጋ መናር፣ በአሠራር ዕንቅፋቶች መብዛት፣ በቀላጤና በሥጋት እየተመናመኑና እየጠፉ እንዳይሄዱ እንደ ዝርያዎቹ ሁሉ የሚከላከል ሕግና አሠራር ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፕሬስ ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ እንጂ የጋዜጣ አሳታሚዎችና የጋዜጠኞች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በመጥፋት ላይ የሚገኙ ዝርያዎችን ለመታደግ የተሠማሩ ባለሞያዎች እነዚህን ዝርያዎች ከጥፋት ለምን መታደግ እንዳስፈለገ ሲገልጡ ‹‹ዓለማችን የተመጣጠነች የምትሆነው እነዚህ ሁሉ ዝርያዎች ሲኖሯት ነው፤ ያለበለዚያ የተዛባች ዓለም ትኖረናለች›› ይላሉ፡፡
እነዚህ የሀገራችን ጋዜጦችና መጽሔቶች እየተመናመኑና እየጠፉ በሄዱ ቁጥር አስተሳሰባችንና አመለካከታችን ያልተመዛዘነ (un balanced) ይሆናል፡፡ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻም ያመዝናል፡፡ የካንሰርን መድኃኒት ለመፈለግ የተሠማሩ ሳይንቲስቶች ‹‹ምናልባት ይህንን መድኃኒት ለመሥራት የሚያስፈልገው ነገር ከጠፉት ዝርያዎች ጋር አብሮ ጠፍቶ እንዳይሆን?›› ብለው ይሰጋሉ፡፡ ከእነዚህ ዝርያዎች መጥፋት ጋር ብዙ የኑሮ ብልሃቶችና የችግር መፍትሔዎች አብረው ይጠፋሉና፡፡
እነዚህ የሀገራችን ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲጠፉም አያሌ አስተሳሰቦች መውጫ አጥተው ይጨነግፋሉ፡፡ በአደባባይ ወጥተው ልናያቸው፣ ልንማርባቸው፣ አለያም ልንተቻቸው የሚገቡ ሃሳቦች መድረክ በማጣታቸው ብቻ ሆድ ውስጥ ይቀራሉ፡፡ ግብግባችን የሃሳብ ከመሆን ያልፍና የጉልበት ይሆናል፡፡
ቁሳዊ ዕድገት የሚመነጨው ከሃሳባዊ ዕድገት ነው፡፡ የማኅበረሰብ ንቃተ ኅሊና ሳያድግ የሚከወን ዕድገት ቀጣይነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም ያልነቃ ኅብረተሰብ ዕድገትን የማስቀጠል ዐቅም አይኖረውምና፡፡ በተወሰኑ ኃይሎች ብርታት ለውጥ ወይም ዕድገት ይመጣ ይሆናል፡፡ ይህ ዕድገት እንደ አጥቢያ ኮከብ ታይቶ ብቻ እንዳይጠፋ በነቃ ኅብረተሰብ ኅሊና ላይ መመሥረት አለበት፡፡
ይህንን ኅብረተሰብ ከምንፈጥርባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ሃሳብና መረጃ ነው፡፡ የመረጃና ሃሳብ ማስተላለፊያ መንገዶች የጥበቃና የክብካቤ ሕግና አሠራር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጋዜጦቻችንንና መጽሔቶቻችንን የሚንከባከቡ፣ ዝርያቸው እንዲጨምር፣ አመቺ ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው የሚወተውት ተቋም ያስፈልጋል፡፡ አንድ ፕሬስ ሲጠፋ አንድ አስተሳሰብ ይሠወራልና፡፡
ዝርያዎች ያልተገባ ጫናና ረብሻ የሰው ልጅ ሲያደርስባቸው ለመጥፋት እንደሚዳረጉ ሁሉ የፕሬስ ውጤቶችም ተገቢ ያልሆነ ጫናና ረብሻ ከተፈጠረባቸው በመጥፋት ላይ የሚገኙ ዝርያዎች ይሆናሉ፡፡ ከባለ ሥልጣናት፣ ከደጋፊና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ከፕሬስ ባለቤቶች፣ ያገባናል ከሚሉ አካላት፣ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ከሚያራምዱ ሀገራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ተቋማት፣ የምንፈልገውን ብቻ ጻፉ ከሚሉ አንባብያን፣ ከባለ ገንዘቦችና ከሌሎችም አካላት እነዚህ ጫናዎችና ረብሻዎች ይፈጠራሉ፡፡ እነዚህ አካላት የየራሳቸውን ጥቅም ብቻ ፈልገው የሚጓዙ ከሆነ ይህንን በመጥፋት ላይ ያለ ዝርያ የሚኖርበትን አካባቢ ይረብሹታል፡፡ በምሬት ብዛትም እንዳይኖር ያደርጉታል፡፡
ማሰብና መጻፍ ዘና ያለ ስሜትና ነጻ የሆነ ሚዛናዊ ኅሊና ይፈልጋል፡፡ ደርሰትና ፈጠራ የኃላፊነት ስሜት እንጂ የጫና ስሜት አይስማማቸውም፡፡ ምን በጎ ነገር እንደሠሩ ማሰብን እንጂ ምን ኃጢአት ሠርቼ ይሆን? የሚልን ጭንቀት አይሹም፡፡ በሠራው ነገር ላይ የሚተማመንና ለሚመጣበት ተጠያቂነት የተዘጋጀ ሰውንም ይሻሉ፡፡ ነጻቱን የማያበላሽና በነጻነቱ ውስጥ በኃላፊነት ስሜት የሚሠራን ልቡና የግድ ይላሉ፡፡ ይህን መሰል የመኖርያ ቦታ ካላገኙ ድርሰትና ሃሳብ ሀገር ለቅቀው ይጠፋሉ፡፡ ለዚህ ነው ሁላችንም ለድርሰትና ለፕሬስ የሚሆን የመኖርያ አካባቢ እንፈጥር ዘንድ ግዴታችን የሚሆነው፡፡ ጋዜጦችና መጽሔቶች ብቻ ሳይሆኑ ሃሳብ ራሱ በመጥፋት ላይ የሚገኝ ዝርያ እንዳይሆን፡፡
ውኃ የሚያነሣ፣ ሃሳብን ያዝ የሚያደርግ፣ ኅሊናን የሚሟግት፣ የሚያመራምርና ያልተበላ ዕቁብ የሆነ አንዳች የሚነበብ ነገር እያነሰን የመጣ ይመስለኛል፡፡ በነ አዲስ ዘመንና በነ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ እንኳን እነ አጋረደች ጀማነህ፣ እነ ዳንዴው ሰርቤሎ፣ ሀይለ ዘበቅሎ ቤት፣ እነ አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ፣ እነ ጠንክር ዘካዛንቺስ፣ እነ እሸቴ ዘጃንሜዳ፣ ይጽፏቸው የነበሩትን በሁለት እጅ የማይነሡ ጽሑፎች ሳስብ፤ በእሑድ ጠዋት ፕሮግራም ይቀርቡ የነበሩትን የነ መጽሐፈ ሲራክ ትረካዎች ሳስታውስ፣ ዛሬ ዛሬ በርግጥም ድርሰትና ፕሬስ በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች ናቸው ያሰኘኛል፡፡
በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎችን የሚያጠኑ፣ የሚመዘግቡና የሚከባከቡ ተቋማት እነዚህን ዝርያዎች በሰባት ይከፍሏቸዋል፡፡ እኔም ከቀድሞ ጀምረው ይታተሙ የነበሩትን ጋዜጦችና መጽሔቶች ሳስብ በእነዚህ ሰባት ምድቦች ውስጥ ገብተው ታዩኝ፡፡
- እልም ብለው የጠፉ(Extinct)፡- በምድራችን ላይ የነበሩ፤ አሁን ግን ከምድረ ገጽ የጠፉና ምናቸውም የማይገኝ፡፡
- በዋና መኖርያቸው ውስጥ የጠፉ(Extinct in the wild)፡- በሚኖሩበት ባሕር፣ ውቅያኖስ፣ ጫካና ምድረ በዳ ውስጥ የጠፉ፤ ነገር ግን ዝርያቸው በእንስሳት ማቆያዎች ወይም በምርምር ቦታዎች ብቻ የሚገኝ
- በአደገኛ የመጥፋት ሁኔታ ውስጥ ያሉ(critically endangered)፡- ቁጥራቸው ተመናምኖና አካባ ቢያቸው ተቃውሶ በመጥፋት ላይ ያሉ፡፡ ቁጥራቸው በጣት በመቆጠር ላይ የደረሰ፡፡ ድጋፍና ክብካቤ ካላገኙ ነገ ከነገ ወዲያ የሚሠወሩ፡፡
- በመጥፋት ላይ ያሉ(endangered)፡- እንደ ላይኞቹ አስጊ ደረጃ ባይደርሱም ነገር ግን ኑሮ ያልተ መቻቸው፡፡ አደን፣ የአካባቢ ጥፋትና የሰው ልጅ ወከባ የገጠማቸው፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በአደገኛ ሁኔታ ሊጠፉ ከተቃረቡት ወገን የሚደመሩ፡፡
- ለጥፋት የተጋለጡ(Vulnerable)፡- በመካከለኛ የጊዜ ለጥፋት ይጋለጣሉ ተብለው የሚፈረጁ፡፡ ቁጥራቸው አደገኛ በሆነ ሁኔታ እየቀነሰ ባይሆንም ከሚዋለዱት የሚጠፉት እየጨመሩ መሆናቸው የተረጋገጠ፡፡ በአዳኞች ወይም አካባቢያቸውን በሚፈልጉት አካላት ምክንያት አደጋ እየደረሰባቸው ያሉ፡፡
- በቅርቡ ጎራውን የሚቀላቀሉ(near threatened)፡- በአሁኑ ጊዜ የመጥፋት አደጋ ባይገጥማቸውም ይህ ችግር ከተወሰኑ ዓመታ በኋላ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል መረጃዎች የሚያሳዩ፡፡
- ብዙም ችግር የማይገጥማቸው(list concern)፡- የዚህን ዝርያ ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ምንም ዓይነት ሥጋት የሌለባቸው ናቸው፡፡
እስኪ የኢትዮጵያን ጋዜጦችና መጽሔቶች የትናንቶቹን እያስታወሳችሁ የዛሬዎቹንም እየገመገማችሁ ከሰባቱ በአንዱ መድቧቸውና የት ደረጃ እንዳለን እወቅ?
‹‹የተለያዩ ዓይነት የሕይወት መልኮችና የኑሮ ሥርዓቶች ለሰው ልጅ ዕድገት እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡›› Ishwaram &Erdelery, 2001, p. 179)
©ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በተመሳሳይ ኅትመት ላይ ባለማውጣት ተባበሩ