4 ሚሊዮን

የጡመራችን ተከታታይ 4 ሚሊዮን መድረሱን መረጃችን ገልጦልናል፡፡ ይህ በሁለት ዓመት ከአምስት ወር የተገኘ ስኬት በብዙዎች ጸሎት፣ እገዛና አስተያየት የተገኘ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ በጽሑፎቹ ሃሳቦች ተስማምተው የሚያነቡም ሆኑ ተቃውመው የሚያነቡ፤ የሚያመሰግኑም ሆኑ የሚሳደቡ፣ ለራሳቸው የሚያስቀሩም ሆኑ ለሌሎች የሚያዳርሱ ሁሉ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡

ለጽሑፍ መነሻ የሚሆኑ ነገሮች የሚልኩ፣ ጊዜ ወስደው ከሀገርም ሆነ ከውጭ ደውለውና ጽፈው ሃሳብ የሚሰጡ፤ ያልጣማቸውን ነገር የሚተቹ፤ ለቀጣይ ሥራ ብርታት የሚሆን ድጋፍ የሚሠጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚህ የጡመራ መድረክ የሚወጡ ጽሑፎች በሀገር ውስጥ ከስድስት ከሀገር ውጭ ደግሞ ከአምስት በሚበልጡ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ይወጣሉ፡፡ በልዩ ልዩ ሬዲዮዎችም ይቀርባሉ፡፡ በተለይም አንዱ ዓለም በፋና ሬዲዮ የሚያቀርባቸውን ትረካዎች ብዙዎች እንደሚከታተሉት ነግረውኛል፡፡ 

በዚህ ጦማር የሚወጡትን አንዳንድ ጽሑፎች ለአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፉ ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ ተገቢውን ክፍያና የሥነ ምግባር ደንብ የሚፈጽመው እርሱ ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶች ባይከፍሉም ያስፈቅዳሉ፤ ከዚህ የባሱት ደግሞ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳያገኙ እንዲሁ ያትማሉ፤ እጅግ የባሱትም ከየት እንዳገኙት ምንጭ ሳይጠቅሱ፣ የጸሐፊውንም ስም ሳያሰፍሩ ያወጣሉ፡፡ እጅግ በጣም የከፉት ደግሞ በራሳቸው ስም ያወጡታል፡፡
በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚታተሙ አንዳንድ ጋዜጦችና ድረ ገፆች ስም እንኳን አለማውጣታቸው ካሉበት ሀገር ምንም አልተማሩም እንዴ? ያሰኛል፡፡
በዚያም ሆነ በዚህ ወንጌል ተሰበከ እንዳለው ጳውሎስ፣ በዚህም ተብሎ በዚያ ሃሳቦቹ ብዙ ቦታ እንዲደርሱ ተደርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በኢሜይል የሚያሠራጩ፣ በወረቀት አትመው የሚበትኑ፣ በፌስ ቡክ ላይ የሚያወጡ፣ ማንበብ ለማይችሉ ወላጆቻቸውና ጎረቤቶቻቸው የሚያነቡ አያሌ መሆናቸውን ተረድቻለሁ፡፡ ከባንክ ዓመታዊ በዓል እስከ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በዓል ድረስ ያነበቡም አልጠፉም፡፡ የሃይማትና የፖለቲካ መሪዎች እነዚህን ጽሑፎች እንደሚያገኙዋቸው ርግጠኛ ነኝ፡፡ መጠኘኛ ሃሳብ ያገኙባቸዋል ብዬም አምናለሁ፡፡
አልፎ አልፎ በተገቢው ጊዜ ጽሑፎቹን ለማውጣት ባለመቻሌ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ የክፍለ ሀገርና የውጭ ጉባኤያት ሱበዙ፤ የምሔድበት ቦታ የኔትወርክ ችግር ሲኖረው፤ መብራት ሲጠፋና ኃላፊነቶች ሲደራረቡ እንዲህ ይከሰታል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ የፒዲኤፍ ቅርጹን ለማውጣት የኢንተርኔት መሥመር መጨናነቅ ያጋጥማል፡፡
በተቻለኝ መጠን ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ለሆኑ አገልግሎቶች በቀን እስከ ሰባት ሰዓት መድቤ እንኳን ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡ በየቀኑ ቢያንስ ለሃ አምስት ሰዎች በኢሜይል ጥያቄዎቻቸውን እመልሳለሁ፤ ቢያንስ አምስት ሰው በቢሮ አማክራለሁ፣ ቢያንስ ሁለት ስብሰባ ላይ እገኛለሁ፤ በስልክ ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጭ ካሉት ጋር እንነጋገራለን፤ በገዳማትና በስብከተ ወንጌል ላይ የሚሠሩ ሁለት ኮሚቴዎችን እሰበስባለሁ፤ እነዚህ እንግዲህ ከሌሎች ጋ ሲደመሩ ቀኑ ይጠባል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ግን ላለማቋረጥ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡
እንግዲህ አብረን ተባብረን እዚህ እንደደረስነው ሁሉ ለወደፊትም ጸንተን እንቀጥላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጸሎታችሁ፣ አስተያየታችሁና፣ ሃሳቦቻቸሁ አይለዩን፡፡ ምናልባት በታሪካችን ውስጥ አንድ በጎ አሻራ መተው ብንችል፡፡
በቀጣዩ ዓመት ሚያዝያ ወይም ግንቦት ላይ ዕድሜ ቢሰጠኝ የዚህን ጡመራ ሦስተኛ ዓመት ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኝ አንድ የክልል ከተማ እናከብራለን፡፡ ዋና ዓላማው ከአዲስ አበባ ውጭ ላለው ወገን ስለ ማኅበራዊ ሚዲያ በባለሞያዎችና በሚመለከታቸው አካላት የሚቀርቡትን ዝግጅቶች በቅርቡ እንዲያገኝ ማደረግ ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ እንደዚሁ ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኝ አንድ ከተማ በዚህ ብሎግ ላይ የወጡ ጽሑፎች የተካተቱበት ሦስተኛው መድብል ምረቃ ይኖራል፡፡ ሁሉም ነገር ለምን አዲስ አበባ ብቻ፡፡
ለሁሉም እድሜና ጤና ይስጠን፡፡ አሜን፡፡
ዋሽንግተን፣ ዳላስ ዓለም ዐቀፍ ዐውሮፕላን ማረፊያ