አቶ ስዬ አብረሃ በሲያትል ያደረጉት ንግግር

ክቡራትና ክቡራን
ጤና ይስጥልኝ
በዛሬው ስብሰባ ከአቶ መለስ ሕልፈት በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በማተኮር አንዳንዳ ሃሳቦችን ለማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
የአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት ይፋ ሆኖ አስከሬኑ ቦሌ ደረሰ ሲባል የአዲስ አበባ ሕዝብ በድንጋጤና በሓዘን፤ የክረምቱ ዶፍ እየወረደበት አሰከሬኑን ቤተ መንግስቱ ድረስ አድርሶታል፡፡ አስከሬኑ ከገባ ከአስራ ሁለት ቀን በኋላ ስርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብም እርሙን አውጥቷል፡፡ በአቶ መለስ ሕልፈተ ሞት የተሰማኝን ሓዘን ቀደም ብየ የገለጽኩ ቢሆንም አሁንም ለቤተሰቡ መጽናናትን እመኛለሁ፤ ፈጣሪ ነብሱን በይቅርታ እንዲቀበለውንም እመኝለታለሁ፡፡

እንግዲህ ከኢህአዴግ መሪዎች የሚጠበቀው ላልተመለሱት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነው፡፡ ከእነዚህ አነዱ የሕልፈቱን ምክንያት ግልጽ ማድረግ ይሆናል፡፡
የኢህአዴግ መንግስት የገዛ መሪው መታመምን ይፋ ያደረገው በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሴኔጋሉ ፕረዚዳነት ለአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በመጡ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ከተናገሩ መሆኑ ይታወሳል፤ ያም ሆኖ ሕክምናው የሚሰጥበት አገርና ሆስፒታል ሳይቀር አንገልጽም ማለታቸው ያስታውሷል፡፡ አየተሻለው ነው በቅርብ ይመለሳል እየተባለ ለበርካታ ሳምንታት ሲነገር ከቆየ በድንገት ለዚያውም በኢንፌክሽን አረፈ ተባለ፡፡

የአቶ ሕመም ምን መሆኑ አለመታወቁና ደህና ነው ሲባል አረፈ መባሉ ነገሩን ለብዙ መላምቶች ክፍት አድርጎታል፡፡ ለሕዝብ በግልጽ ባልተቀመጠ ሁኔታ የአንድ አገር መሪ አረፈ፤ለዝያውም በሌላ አገር አረፈ ሲባል ብዙ ጥያቄዎች ሊያጭር እንደሚችል መሆኑን በመገንዘብ የኢህአዴግ መሪዎች እውነታውን ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በ 2002 በተካሄደው ህወሓት/ኢህአዴግ ጉባኤ ለተተኪ አስረክቦ እርሱ ገለል ይላል ሲባል ነበር፡፡ እርሱ እለቃለሁ እያለ ቀሪዎቹ የኢህአዴግ መሪዎች አይሆንም በለው ጫና በመፍጠራችው ምክንያት እንዲቆይ መገደዱ ተነግሮናል፡፡ አቶ መለስ መታመሙን ካወቀ ብዙ እንደቆየና ረጅም እረፍት እንደሚያስፈልገው ሰሞኑ ይሰጡ ከነበሩት መግለጫዎች ለመገንዘብ ተችለዋል፡፡ መድከሙንና መታመሙን እያወቁ፤አንተ እረፍ ከዚህ በኋላ ያለውን እኛ ማስቀጠል እንችላለን ማለት ባለመቻላቸው እስከመጨረሻ ሰዓት እንዲቆይ አድርገውታል፡፡

ይህ እየታወቀ የአቶ መለስ ሕልፈተ ሞት ተከትሎ ነገር በነበረበት መልኩ ይቀጥላል የሚለወጥ ነገር አይኖርም ተበሏል፡፡ እርሱ በሕይወት እያለ የእርሱ ምክር ከጎናቸው እያለ ‹‹እኛ እንሞክረው›› ማለቱን ያልተቻላቸው ሰዎች አሁን እርሱ በሌለበት ነገሮችን እንደድሮው እናስቀጥላለን ማለታቸው ያስገርማል፡፡ ከጥንት ከጥዋቱ ጀምሮ ‹‹የራእዩ አመንጪ›› ‹‹ቀያሹ ዋና አስፈጻሚው›› እሱ እንደነበረ ከገለጹልና እውነቱ ይህ መኖሩን ካመኑ ዘንዳ እርሱ በሌለበት እኛ እንችለዋለን ነገሮች በነበሩበት ይቀጥላሉ መለታቸው ተኣማኒነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይልቁንስ የተጀመሩትን በጎ ጅማሮዎች አጎልብቶ ዳር ለማድረስ የሚያስችል፤ የጎደሉትን የሚያሟላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ልቦና የሚደብስ መንገድ ማቀየስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የአሜሪካ ሬድዮ ጣብያ እንኳን እንዳይሰማ የሚከለከለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ መሆኑን የታላቅ ወግና ስርዓት ባለቤት መሆኑን በአቶ መለስ ሕልፈተ ሕይወት አሳይቶአል፡፡ ይህን ያደረገው ለሕይትና ለሕልፈተ ሕይወት ትልቅ ስፍራ የመስጠትን፤ በሃዘን ወቅት በጎውን እንጂ መጥፎውን ማውሳት ያለመፈለግን የመሰለ ታላቅ ወግና ስርዓት ያለው ሕዝብ ስለሆነ እንጂ በኢህአዴግና በአቶ መለስ አገዛዝ በደል ስላልተፈጸመበት ወይም ረስቶት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ቀሪዎቹ የኢህአዴግ መሪዎች መፈክሮች እንዲወጡ በማድረግ፤ በየቀበሌው ድንኳን እንዲተከልና ሰዉ ጥቁር ልብስ እንዲለብስ መመርያ በማሰራጨት የሕዝቡን ሃዘንና ድንጋጤ እና ታላቁን የኢትዮጵያውያን ወግና ስርዓት ወደ የተደራጀና የተራዘመ የፖለቲካ ዘመቻ ለመለወጥ ሞክረዋል፡፡
በአቶ መለስ ዜና ዕረፍት የታየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሓዘንና ድንጋጤ ኢትዮጵያውያን በአደጋና በፈተና ጊዜ በአንድነት እንደሚቆሙ ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው፡፡ እስካሁን የተሰራው በጎውም ክፉውንም ስራ እንደ የጋራ ታሪካችን ተቀብለን ወደፊት በጋራ ቆመን የአገራችንን የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ግንባታ እንድናጠናክር መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን ያመለክት እንደሆነ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንድ ፓርቲ አገዛዝ ይሁንታ እንደሰጠ ተደርጎ መተርጎም አይችልም፡፡ የኢትየጵያ ሕዝብ ኢህአዴግ ይግዛኝ ብሎ የ99 % ድጋፍ አልሰጠም፡፡ ጋዜጠኞችና የኢህአዴግን አገዛዝ የተቃወሙ ፖለቲከኞች በሽብርተኝነት እንዲታሰሩ ይሁንታ አልሰጠም አይሰጥምም፡፡ የኢህአዴግ መሪዎችነ የኢትዮጵያውያንን ሓዘን በዚህ መተርጎማቸውና ነገሩን ለመጪው አገዛዛቸው ማጠናከርያ ለመጠቀም መሞከራቸው፤ ለዚህ ታላቅ ሕዝብ ያላቸውን ሚዛን ምን እንደሚመስል ያመለክታል፡፡ ይህ ደግሞ ጤነኛ አመራርን አያመለክትም፡፡

የአቶ መለስ ማለፍ ሲታወቅ መወሰድ የነበረበት የመጀመርያ እርምጃ ተተኪውን ሰው መሰየምና ማስቀመጥ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የቀብሩን ዝግጅት አያስተጓጉልም ማድረጉን ድግሞ የአገሬውን ስነልቦና ያረጋጋል፡፡ ኢኮኖሚውን ያረጋጋል፤ ለአለምአቀፉ ማሕበረሰብም መረጋጋትን ያመለክታል፡፡ ሆኖመ አቶ መለስ ካለፈ ከሳምንታት በኋላም ይህንን ማድረግ አልተቻላቸውም፡፡ ይህም ጤነኛ አመራርን አያመለክትም፡፡

ነብሱን ይማረውን ከእንግዴህ አቶ መለስ አርፏል፤አልፏል፡፡ ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ የሚያቋቋመው መንግስት የአቶ ሃይለማርያም ወይም ከሌሎቹ የአንዱ ሊሆን ይችላል የአቶ መለስ ግን ሊሆን አይችልም፡፡ ኢህአዴግ ማንንም ቢሾምም የአቶ መለስን ስፍራ ሊተካ አይችልም፡፡ ለመለስ አገዛዝ የሰራው ለእነርሱም አይሰራም፡፡ ተወደደም ተጠላም የምናውቀው ኢህአዴግ አይኖርም፡፡ ሁኔታ ተቀይሮአል፤ “ሰታተስኮው” ላይ አይደለንም፡፡ ፡ለውጥ እንዳለና አንደምታው ግዙፍ እንደሆነ ኢህአዴግ ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሃያ ዓመት ያገኘውን ተነጻጻሪ ሰላምና ይብዛም ይነስ በዚህ ወቅት ያፈራቸውን ቁሳዊ እሴቶች ሊያጣ አይፈልግም፡፡ በማያሻማ መልኩ ሁኔታዎች ለሰላማዊ ዴሞክራስያዊ ሽግግር እንዲመቻቹለት ይፈልጋል፡፡ ለውጥ በመጣ ቁጥር ትርምስና መናጋትን አይቶአልና አሁንስ ምን ይመጣብን ይሆን የሚል ስጋት እንዳለበት መገንዘብ ይገባል፡፡ ኢህአዴግ ለዚህ ሁኔታ ከተለመደው የእኛ እናውቅልሃልን ፖለቲካ የተለየ መንገድ ማሰብ አለበት፡፡ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎችም እውነታውን በጥሞና መመርመር ይገባቸዋል፡፡ አለ የሚሉትን የአቶ መለስን ሌጋሲ መፈክር አና ፎቶ በማንጠልጠል ወይም ዜማ በማዜም ሊያስጠብቁት አይቻላቸውም፡፡ ሁሉን እናስቀጣላለን ብሎ መሞከር ሁሉንም ማጣት ሊያስከትል ይቻላል፡፡ ነገሩ የቁጭትና የእልህ ሳይሆን የብልህነትና የአስተዋይነት ጉዳይ ነው፡፡ ለውጥ መኖሩን መገንዘብና ይህንን የተገነዘብ ሁሉንም የሚያሳትፍ መንገድ መቀየስ አጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡

እንደአያያዛችን ይህ ሁኔታ መጥፎም ጥሩም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢህአዴግ እርስ በርስ መስማማት አቅቶት ትርምስ ውስጥ ቢገባ ወይም ለአዲሱ ሁኔታ ተገቢውን መላሽ መስጠት ቢያቅተው ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ መጠቀምዋንና መጠናከርዋን የሚያሰጋቸው ሃይሎች አጋጣሚው አገኘን ቢለው በውስጣዊ ድክመቶቻችን ውስጥ መጫወት ቢጀምሩ አገራችን ሕዝቡን እያሳሰበው ካለው ችግር ውስጥ ልትገባ እንደምትችል መገመትም ይገባል፡ የኢትዮጵያ መናጋት ከኢትዮጵያ ድንበር የዘለለ አካባቢውን በጠቅላላ ሊነካ እንደሚችልም መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህን ማስቀረት የሚቻለው ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች በመውሰድ በአገራችን ውስጥ ሲጠራቀም የቆየውን ውጥረትን ማርገብ ሲቻል ብቻ ነው፡፡
ለውጡንና የአንደምታው ግዙፍነት መገንዘብ ያለባቸው ተቃዋሚዎችም ዲያስፖራውም ጭምር ናቸው፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ብቅ ያለው የለውጥ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ የተፈጠረ አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ለውጡን በዚህ እይታ እንቀበለው ካልን መንገዱ የይቅርታ፤ የመመካከር፤ የፍቅርና የአንድነት መንገድ ብቻ ነው፡፡ የኢህአዴግ ደጋፊ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ፤ የዚህና የዚያ ብሄር ተወላጅ ወይም የዚያና የዚህ ሃይማኖት ተከታይ ሳንባባል ሁላችንም ለሁላችን እና ለአገራችን ድል በጋራ መስራትን ስንቀበል ነው፡፡

በአንዳንደ ወገኖች ከታላቁ የሕዝባችንና የአገራችን ወግና ስርዓት ወጣ ባለ ሁኔታ በሰው ሞት መደሰት ታይቶባቸዋል፡፡ የተፈጸሙ በደሎች እንዳሉ ሆኖ ለውጡን የምንቀበለው በዚህ መንፈስ አይገባም፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ጥቂት ቢሆኑም በኢትዮጵያውያን መካከል ሊፈጠር የሚችለውን የአንድነት የእርቅና የፍቅር መንፈስ በመበረዝ ረገድ ከቁጥራቸው የገዘፈ አጥፊ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ የኢህአዴግን ስህተቶች እንደምንተች ሁሉ አነዚህንም ስሕተታቸውን ማሳየት የሁሉም ወገን ሃላፊነት መሆን አለበት፡፡

ከዚህ አኳያ በተቃዋሚዎችና በዲያስፖራው በኩል ትኩረት ሊሰጣቸው የሚላቸውን አምስት ነጥቦችን ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡

1.አሁንም በውይይትና በምክክር ሁሉንም ወገን ሊያስማሙ የሚችሉ የጨዋታ ሜዳ ሕግጋት እንዲኖሩ ጠንክሮ መስራት ከኢህአዴግ ጋር የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረንም እኛም የአገራችን ኢኮኖምያዊ እድገት በጠንካራ መደላደል እንዲቆምና ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ እንፈልጋለን፤ የሃያ አንደ ዓመቱ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አገራችን በክፍለአህጉራችንና በአህጉራችን ሰላም የምትጫወተው ገንቢ ሚና ቀጣይና አስተማማኝ እንዲሆን እንሻለን፤ ሃገራችን በተፈጥሮ ሃብቷ ተጠቃሚ ትሆን ዘንድ የተጀመሩት ጅማሮዎች ቀጣይነትና ጥልቀት እንዲኖራቸውና ለዚሁ ስኬት ከአካባቢው አገሮች በምክክር መስራትዋን እንድትቀጥልበት እንፈልጋለን፡፡

የፖለቲካ ልዩነት ጠላትነት እንዳልሆነ እናምናለን፤በመንጋራቸው እምነቶች አብረን አየቆምን ልዩነቶቻችን በሰለጠነ መንገድ የሚስተናገዱበት ስርዓት ሊመቻች ይገባል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን እንጠይቃለን እንታገላለን፡፡ ይህንን በሰላማዊ መንገድ ዳር ማድረስ እንደሚቻልም እናምናለን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ይበልጥ የምትጠቀመው በውይይትና በምክክር ሁሉንም ወገን ሊያስማሙ የሚችሉ የጨዋታ ሜዳ ሕግጋት ቢኖሩ እንደሆነ ካለን ፅኑ እምነት ለዚህ እውን መሆን ከኢህአዴግ ጋራ ለመወያየት ዝግጁነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡

2. የመደራጀት መብትን፤ ሃሳብ የመግለጽ መብትን፤ የመቃወም እና የመተቸት መብትን፤ እንዲሁም ስልጣን በነፃ ምርጫ የመያዝ መብትን የሚገድቡት ሕጎች እንዲነሱና አንዲሰተካከሉ በእነዚህ ሕጎች የታሰሩት ወገኖቻችን እንዲፈቱ መጠየቅ የሐገራችን ሕገ መንግስት ችግሮች እንዳሉት እንገነዘባለን፤ ከአቶ መለስ ሕልፈት በተያያዘ የተፈጠረው ሁኔታ የዚሁ ክፍተት አንድ ማሳያ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከሌለ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩም ሆነ የፕረዚዳንቱ መኖር ወይም አለመኖር የሚፈጠረውን ክፍተት ከመሙላት አንጻር ምንም ሕገ መንግስታዊ ፋይዳ እንደሌላቸው አሳይቶናል፡፡

ሕገ መንግስታችን ጠንካራ ገጽታዎች አሉት፡፡ የመደራጀት መብትን፤ ሃሳብ የመግለጽ መብትን፤ የመቃወም እና የመተቸት መብትን፤ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንዲሁም ስልጣን በነፃ ምርጫ የመያዝ መብትን ይደነግጋል፡፡ እነዚህ የማይነኩ የሕዝብ መብቶች መሆናቸውንና ይህ ታላቅ ሕዝብ ለዚህ ብቁ እንደሆነ እናምናለን ይሁን እንጂ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነዚህ መብቶች ተጠቃሚነቱ ተገድበዋል፡፡ አነዚህን መብቶች ትርጉም አልባ የሚያደርጉ በርካታ ሕጎችና በሕግ ያልሰፈሩ አሰራሮች ስራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ የዳኝነት ስርዓቱ ነጻነቱን በማጣቱ የሕዝብ ከበሬታን አጥቶአል፡፡ ከዚህ በተያያዘ በረካታ ወገኖቻችን ለሞት፤ ለእስር ለስደትና ለኑሮ መመሰቃቀል እንደተዳረጉና እየተዳረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እነዚህ የሕዝብ መብቶች ናቸው፡፡ ሉኣላዊነቱ የሚያረጋግጥባቸው አገሩን የሚያለማባቸው የአገሩን ሰላምና አንድነት የሚያስጠብቅባቸው ወሳኝ እሴቶቹ ናቸው፡፡ ሊመለሱለት ይገባል፡፡ ኢህአዴግ ለዚህ ሕዝብ አክብሮትና እምነት መሳያ ጊዜው ከረፈደ ቆይቶአል፡፡ ከገዛ አገሬው ጋር ለመተቃቀፍ ያለው የመጨረሻ እድል ይህ ሊኖን ይችላል፡፡

3. የከረሩ ጫፎችን በመተው ወደ አማካይ ስፍራው ጋር መሰባሰብ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈለግን መከተል፡፡

ጫፍ ላይ የቆመና የተካረረ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ሲያደማት ቆይቶአል፡፡ ክስተቱ የስድሳዎቹ ክስተት ብቻ ሳይሆን አሁንም ያለ ችግራችን ነው፡፡ አሁንም በገዢው ፓርቲ፤ በተቃዋሚዎችና በዲያስፖራውም ያለ ችግር ነው፡፡

የከረረ ቃል መጠቀምን፤ የጥላቻ፤ የጭካኔና የ ‹‹እኛ እነሱ›› ቃላት የበለጠ ያስጨበጭባሉ፡፡ ነገሮችን ስለ ማለዘብ ስለፍቅር ስለእርቅና ስለሰላም መናገር እንደደካማነት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ የሚናገሩት ትችትና መነጠል ሰለሚያሰጋቸው አለማለቱን ይመርጣሉ፡፡ ከዚያም ባሻገር ከመድረክና ከፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን ያገላሉ፡፡
ይህ ችግር ትልቁን ስእል ለማየት አሰቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ቡዙሃኑን የሚያሳትፍ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያስተናግድ ፖለቲካና መድረክ መፍጠሩን ከባድ አድርጎታል፡፡
ከማንኛውም ወገን የሚመጡትን ለእርቅና ለመግባባት የማያመቹትን ድርጊቶችና ንግግሮችን መቃወም በዚያው ልክ ደግሞ ከማንኛውም ወገን ለሚመጡ ገንቢ ሃሳቦችና ፍንጮች ዋጋ መስጠትና አጸፋውን በገንቢ ተግባርና ቃላት እያስደገፉ የተፈጠረውን መራራቅ ጥረት ማድረግ፤ በዚሁ መንገድ በሕዝባችን የታየውን የአንድነትና የይቅርታ መንፈስ ማጠናከር ይጠበቃል፡፡

4. አገር ውስጥ ለሚሰራው ስራ ድጋፍ መስጠት፡፡

በአገራችን ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ምኀዳር እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቶአል፡፡ በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓረቲ አባልና ደጋፊ መሆንን፤ ሃሳብን በነፃነት መግለጽና ተቺ ጋዜጠኛ መሆን እጅግ አደገኛ ሥራ ሆኖአል፡፡ ይህ ብቻ በራሱ ወንጀል ሆኖ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ደጋፊዎች፤ ጋዜጠኖችና ብሎገሮች ታስረው መከራ እያዩ ነው፡፡
አስቸጋሪና አደገኛ ቢሆንም በአገር ውስጥ መቆየትና ቦታውን አለመልቀቅ እጅግ አስፈላጊ የፖለቲካ ኢነቨስትመንት ነው እናምናለን፡፡
በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች አመራሮች አገር ውስጥ ባለው ሕዝባችን ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጪ ካለው ኢትዮጵያዊም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ለትግል የሚያስፈልገውን ዓቅም በአዝጋሚና አስቸጋሪ ሁኔታም ተሁኖ በሚገባ መገንባት ካልተቻለ ሁኔታዎች ለለውጥ ምቹ ቢሆኑም የተገለገው ውጤት ጋር ለመድረስ አይቻልም፡፡
ከአራት ዓመታት ቀደም ብሎ በመክክር የተጀመረው የመድረክ ስራ ከቅንጅት አልፎ ወደ ግምባር ተሸጋግሮአል፡፡ አዚህ ለመድረስ የተሰራው ስራ ቀላል አልነበረም፡፡ በአገራችን ሕዝብና በዲያስፖራው ለዚህ ፕሮጀክት የተሠጠው ድጋፍ የሚመሰገን ሆኖ አሁነ በተለይ በተጠናከረ መልኩ ድጋፉን ማስቀጠል በትግሉ ላይ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

4. ከፍተኛ ሕዝባዊ ዲፖሎማሲ

ሁለት ነገሮችን በምሳሌነት መጥቀስ ይህንን ጉዳይ የሚያብራራው ይመስለኛል፡፡ የአርመንያውያን የሕዝብ ዲፕሎማሲና ሰሞኑን በወ/ሮ ሱዛን ራይስ በአቶ መለስ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ያደረጉትን ንግግር ላይ በአንዳንደ የዲያስፖራ ሚድያ በኩል የተሰጠው ትችት፡፡ የመጀመርያው የሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ስኬትን ያሳያል ሁለተኛ ድክመትን ያመለክታል፡፡

አርመንያ ትንሽ አገር ነች፤ ከአሜሪካ ስትራተጂ አንጻር ይህ ሊባል የሚችል ስፍራም የላትም፡፡ የአርመንያውያን ሎቢ ግን በአሜሪካ ውስጥ እጅግ ውጤታማ ከሚባሉት ሶስት ሎቢዎች አንዱ ነው፡፡ የአመሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አርመንያን በሚጠቅም መልኩ እንዲቃኝ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

ወ/ሮ ሱዝን ራይስ በአቶ መለስ ቀብር ላይ ሰውየውን በማድነቅ የሰጡት ዲስኩር የተጋነነ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ተኩረት ሊሰጠው ይገባ የነበረው ግን ከአቶ መለስ በኋላ ከሚኖረው መንግስት ጋር አሜሪካ ሊኖራት የሚገባው ግንኙነትን አስመልክቶ ምን አሉ የሚለው መሆን ነበረበት፡፡ ዴሞከራሲ ሰብአዊ መብትና ነጻ ፕሬስ ላይ መሻሻል እንዲኖር አሜሪካ የምትጠብቅ መሆኑዋን የመለከተ መልእክታቸውን መዞ በማውጣትና በዚሁ አስታኮ መደረግ ያለበትን መጠቆም ላይ ማተኮር በተገባ ነበር፡፡ በአንዳንዳ የዲያስፖራው ሚድያ በኩል ይበልጥ የተተኮረበት ግን አቶ መለስን በማድነቅ የተናገሩት ላይ ነው፡፡ ተኩረት ሊሰጠው የሚገባው ላይ ከማተኮር ይልቅ ዘለፋ አዘል አጸፋ መሰጠቱ ራስን ከማስገመት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

ዲያስፖራው መጀመርያ ከቤቱ ደጃፍ ያለውን ስራ ማሳካት አለበት፡፡ ብዛቱን ወደ ሚቆጠር ድምጽና ወደ ሚሰማ ድምጽ መቀየር መቻል አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ መጀመርያ ዲያስፖራውን ራሱን ይጠቅመዋል ቀጥሎ ኢትዮጵያን ይጠቅማል፡፡

አንዳንድ ወገኖች አጋጣሚውን እንጠቀምበት፤ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊት ለማድረግ መጣ የሚሉት ሌላ አጋጣሚ ሊያመልጠን አይገባም ይላሉ፡፡ አባባሉ ትክክል ነው፡፡
እንዳያመልጠን ማለት ግን እሽቅድድም አይደለም፡፡ ካለፉት ስሕተቶች ተምሮ አካሄድ ማስተካከል እንጂ፡፡

5. የአገራችን የዴሞክራሲ እውን መሆኑ አይቀሬ ነው ለስኬቱ በጽናት በሕብረትና በብቃት እንስራ
አገራችን በታሪክም በአካባቢያችንም ታላቅ ስፍራ ያላት፤ ተስፋዋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየለመለመ ያለ ሃገር ናት፡፡
ይህንን ስፍራዋን ሳትለቅ በሰላማዊ መንገድ የእድገትና የዴሞክራሲ መንገድዋን ይበልጥ ለማጠናከር የምንችልበት ሰፊ እድል አለ
በአለፉት ሰላሳና አርባ የፖለቲካ ታሪካችን የደረሱ ጉዳቶች ያደረሱብንን ጉዳት በዚሁ ይብቃ ማለት ይኖርብናል፡፡ እነሱን አየመዘዝን በወደፊት የጋራ ጉዞአችን እንቅፋት እንዳይሆኑ ሁላችንም በሃላፊነት ከሰራን ተሰፋውን ከተስፋ የዘለለ ተጨባጭ ነገር እንዲሆን ማድረግ ይቻላል
ታላቁ የኢትዮጵያ ለዚህ ብቃት ያለው ሕዝብ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቶአል፡፡ ይህንን ሕዝብ አክብረንና አምነን እርሱን የአገሩ ጉዳይ ባለቤት ይሆን ዘንድ በጋራ እንስራ፡፡