ከፊታችን ያለው መንገድ

click here for pdf

በትግራይ ክልል ዐድዋ ውስጥ ልዩ ስሙ እንዳ አቡነ ገሪማ በተባለው ቦታ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓም የተወለዱት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማረፋቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱ በይፋ ገልጣለች፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ከተሰየሙት ፓትርያርኮች መካከል በመንበራቸው ላይ ብዙ ጊዜ የቆዩት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡ ለሃያ ዓመታት፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ውስጥ ካለፉት አምስት ፓትርያርኮች መካከል አንደኛው በደርግ ተገድለዋል፤ አንደኛው ተሰድደው ወጥተዋል፤ ሦስቱ ደግሞ በአገልግሎት እያሉ ዐርፈዋል፡፡ ምንጊዜም ቢሆን አንዲትን ቤተ ክርስቲያን ይመራ የነበረ አባት ሲያርፍ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ዘንድ በአንድ በኩል ያረፉት አባት እንዴት ነበር ያገለገሉት የሚል ጥያቄ ሲነሣ በሌላ በኩል ደግሞ ቀጣዩስ ማን ይሆናሉ የሚል ጥያቄ ይፈጠራል፡፡
በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቀኖናና ትውፊት መሠረት አንድ ፓትርያርክ ሲያርፉ የሚከናወኑ ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህም በስድስት ይከፈላሉ፡፡

  1. ሁኔታውን ማወጅ
ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ አባት ሲያርፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ በይፋ ማወጅ አለባት፡፡ ይህ አባት በመንግሥት ወይም በአላውያን ተይዞ የደረሰበት ካልታወቀም ሲኖዶሱ የመጨረሻውን እስኪያውቅ ድረስ በቦታው ሰው ሳይተካ ሥራውን እየሠራ ይቆያል እንጂ በይፋ ሳያውጅ ሌላ አባት ወደ መምረጥ አይሄድም፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በተመለከተ በታሪካችን የተሠራው ስሕተት ይህ ነበር፡፡ እርሳቸው ማረፋቸውን በይፋ ቤተ ክርስ ቲያኒቱ ሳታውጅ ወደ ሌላ ምርጫ ገባች፡፡ ይህም ከሌሎች እኅት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በቀኖና ከማለያየቱም በላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክም ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ አልፏል፡፡
  1. የኀዘን ጊዜ መወሰን
የቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ የአዲሱ ፓትርያርክ ምርጫ የሚከናወነው ነባሩ አባት ካረፈ ከዐርባ ቀን በኋላ መሆኑን ይገልጣል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ዐርባ የኀዘን ቀናት ስለሚታወጁ ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ለዐረፉት አባት የፍትሐት ጸሎት ይደረጋል፡፡ ታሪካቸው በቤተ ክርስቲያን ደረጃ በይፋ ይወጣል፡፡ ስለነበሩበት የአገልግሎት ዘመን ይነገራል፡፡ በየቤተ ክርስቲያኑም ጸሎት ይደረግላቸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ይፋዊ የኀዘን ጊዜ አላወጀም፡፡ ይህ ግን የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
  1. ዐቃቤ መንበር መሠየም
የቅዱስ ሲኖዶሳችን ደንብ በምእራፍ 3 በቁጥር አንድ ላይ ዐቃቤ መንበር ዕለቱኑ መሰየም እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይሄ ሁኔታ ግን የብጹዐን አባቶችን መሰብሰብ የሚጠይቅ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ዕለቱን ለማከናወን ያስቸግራል፡፡ ዐቃቤ መንበሩ ቀጣ አባት ተመርጦ መንበሩን እስኪረከብ ድረስ መንበሩን በመጠበቅና የቤተ ክርስቲያኒቱን የዕለት ተዕለት ተግባር በማከናወን ይቆያል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱ ደንብ ‹‹በማዕረገ ጵጵስና ቅድሚያ ካላቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል›› እንደሚመረጥ ይደነግጋል፡፡ ዐቃቤ መንበሩ ‹‹ፓትርያርክ እስኪሾም ድረስ የነበረውን ጠብቆ ማቆየት እንጂ መሾም፣ መሻር፣ መጨመር፣ መቀነስ፤ አዲስ ሥርዓት እና ደንብ ማውጣት አይችልም፡፡››
  1. የቀብሩን ሥነ ሥርዓት ማከናወን
የአንድ ፓትርያርክ የቀብር ሥነ ሥርዓት የቤተ ክርስቲያኒቱን ታላቅነት፣ ቀኖና እና ጥንታዊ ትውፊት የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡ ይህንንም ነገር ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ለማከናወን ራሱን የቻለ መርሐ ግብር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የቅዱስ ፓትርያርኩ ቀብር በአስቸኳይ የማይከናወነው፡፡ የሚቀበሩበት ቀን፣ የሚቀበሩበት ቦታ እና የቀብሩም ሥነ ሥርዓት አስቀድሞ ደንብና ሥርዓት የወጣለት መሆን አለበት፡፡ ያረፉትን አባት ሕዝቡ የሚሰናበትበት ሥርዓት፣ በቀብሩ ቀን የሚነገሩትና የሚዝሙት ነገሮች፣ የአካሄድና የቀብር ሥርዓቱ ሁሉ ዝርዝር የሚያስፈልገው ነው፡፡
አሁን በቤተ ክርስቲያናችን በአስቸኳይ የሚያስፈልጉት ከላይ የተጠቀሱት አራት ነገሮች ናቸው፡፡ ስለ አቡነ ጳውሎስ የቱንም ዓይነት አመለካከት ቢኖረንም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርና እርሳቸውም በሕይወት ዘመናቸው በነበሩ ጊዜ ስለ ፈጸሟቸው በጎ ተግባራት ሲባል ነገሮች የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪካዊነት፣ ጥንታዊነትና ሰላማዊነት በሚያሟሉ ደረጃ መፈጸም አለባቸው፡፡
የአንድ ፓትርያርክ ዕረፍት የአንዲት ቤተ ክርስቲያን የአንደኛው የታሪክ ምዕራፏ ማጠናቀቂያ ነው፡፡ ሌላኛውን ምዕራፍ በተገቢው መንገድ ለመጀመር ያለፈውን ምዕራፍ በተገቢው መንገድ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ይቅር ባይነትና ርኅራኄ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም ማሰብና ለምጣዱ ሲባል አይጧን ማለፍ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡
አሁን ከምንም ጊዜ በላይ ነገሮችን በሰከነና መንፈሳዊ በሆነ መልኩ ለማስኬድ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብዙ ይጠበቃል፡፡ ቢያንስ እነዚህ ዐርባ የኀዘን ቀናት ትውፊታችንን፣ ቀኖናችንን፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችንንም በጠበቀ መልኩ መከናወን አለባቸው፡፡ ስለ ሌላው ነገር ለማሰብ ጊዜ አለን፡፡
  1. የምርጫውን ሂደት ማከናወን
እኔ እስከማውቀው ድረስ በቅዱስ ሲኖዶሱ ደንብ ላይ ከተገለጠው በቀር የአዲስ ፓትርያርክን አመራረጥ በተመለከተ የተዘጋጀ ዝርዝር ደንብ የለንም፡፡ በግብፅ ቤተ ክርስቲያን እንዳየነው ከሆነ ራሱን የቻለ ዝርዝር ሕግ አለ፡፡ አስመራጩ ከየት ይዋቀራል? ምርጫው ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? ጥቆማ ከየት ይመጣል? የጠቋሚና የተጠቋሚ መመዘኛ ? የምርጫው ሥነ ሥርዓት? የጸሎቱና የዕጣ ማውጣቱን ሂደት በተመለከተ ይደነግጋል፡፡ እያንዳንዱ ተግባር ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድም ያትታል፡፡
ቢቻል ቅዱስ ሲኖዶስ አስቀድሞ ቋሞ የሆነ ተመሳሳይ ሕግ ቢኖረው፡፡ ካልተቻለም ቢያንስ ለዚህኛው ምርጫ የሚያገለገል መመርያ ቢያወጣ፡፡ ቀጣ ምርጫ በተቻለው መጠን በቻል የሁሉንም ባይቻል ደግሞ የአብዛኛውን ምእመን ይሁንታ እንዲያገኝ፤ ምርጫው በድምጽና በቆጠራ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነትና ትውፊታዊነትን በተላበሰ መልኩ በጸሎትና በዕጣም እንዲከናወን ቢደረግ፡፡ ዕጩዎቹ ቀድመው ታውቀው ሕዝቡ የሚጸልይበት የጸሎት ጊዜ ቢኖር፡፡ የምእመናን ተሳትፎ ተጠናክሮ የሚታይበትና አባቶችና ልጆች አንድ ሆነው የሚመሰክሩበት ጊዜ እንዲሆን ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
  1. መምረጥ
ይህ ማለት ቀጣ ፓትርያርክ የሚታወቅበትና የመጨረሻው የምርጫው ዕለት ማለት ነው፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሕግ ከመጨረሻዎቹ ሦስት አበው መካከል ስማቸው በመንበሩ ላይ ተደርጎ ከጸሎት በኋላ ዕጣ የሚወጣበት ዕለት ማለት ነው፡፡ በኛ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ድምጹ ተቆጥሮ አብላጫውን ያገኘው በቅዱስ ሲኖዶሱ ጸድቆ ቃለ መሐላ የሚፈጽምበት ጊዜ ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ወደፊት በዝርዝር እንነጋገርበታለን፡፡