ተቃዋሚው ጎራ ያገኘው የስነልቦና ድል በያሬድ አይቼህ
ማንኛውም ትግል በአይምሮ ውስጥ ይጀምራል ፥ በአይምሮ ውስጥ ያበቃል። በስፓርት ፡ በንግድ ፡ በፓለቲካ ፡ በጦርነት ፡ በመንፈሳዊ ትግሎች ሁሉ ፍልሚያው ሚጀምረው በስነልቦና ውስጥ ነው። የስነልቦናን ድል ማግኘት የትግሉ ትልቁ ክፍል ነው። የስነልቦና ሽንፈት የተከናነበ ፡ የትግል ሽንፈቱ የጊዜ ጉዳይ ነው። የስነልቦና ሽንፈት ገጥሟቸው የሚያሸንፉ አጋጣሚያዊ እንጂ ተደጋጋሚ ክስተት አይደለም። ከኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ጋር የሚካሄደው የአገራችን የፓለቲካ ትግልም ወደ አዲስ ምዕራፍ ገብቷል ብዬ አምናለሁ።
ትግሉ የጀመረው ከ40 እስከ 60 ዓመት በፊት ነው። አጼ ኋይለስላሴ የዘመናዊ ትምህርት ለኢትዮጵያ ያለውን አስፈላጊነት ስላመኑበት ኢትዮጵያውያንን ወደ አዉሮፓና አሜሪካ እየላኩ ያስተምሩ ነበር። በተጨማሪም ዘመናዊ ትምህርት በዩኒቨርስቲ ደረጃ በአዲስ አበባ መሰጠት የጀመረውም የዛሬ 62 አመት ነበር።
መማር የጀመረው ትውልድም ጥያቄ መጠየቅ ጀመረ። “ለምን ወደ ኋላ ቀረን?” “ለምን ምዕራባዊያን ሰለጠኑ?” የሚሉትና ሌሎች ማህበራዊ ፥ ፍትሃዊና ፓለቲካዊ ጥያቄዎችም መነሳትና መራባት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነው አሁን ያለንበት የፓለቲካ ትግል የተጠነሰሰው። ምንም እንኳን የደርግ ወታደራዊ መንግስት ትግሉን ለ17 ዓመታት ቢጠልፈውም ፥ እንዲሁም ኢህአዴግ የብሄርን ጉዳይ ከመጠን በላይ አራግቦ ፡ ህወሓት ደርግ ያስወገደውን የአማራውን የገዢ መደብ የበላይነት “ነፍጠኛ አሁንም አለ” የሚል የማስፈራሪያ ፓለቲካ ተጠቅሞ አሁን ያለውን የትግሬ ነፍጠኛ የበላይነትን መስርቷል።
ህዝብን መናቅ
የንግሱም ፥ የወታደራዊውና የኢህዴግም መንግስታት የየራሳቸው ድካም ፥ ጥንካሬ ፥ ወንጀል ፥ ክፋት ፥ ስህተትና ግፍ አላቸው። ለስራዎቻቸውና ትሩፋታቸው ሁሉም አገራዊ ፥ ፓለቲካዊ ፥ ታሪካዊ ፥ አለምአቀፋዊ ምክንያቶች አሏቸው። ነገር ግን ሁሉንም አንድ የሚያረጋቸው ለህዝብ ያላቸው ንቀት ነው።
አጼ ኋይለስላሌ “ህዝብ እንደ ህጻን ልጅ ነው ፥ ሚፈልገውን አያቅም” እንዳሉ ይነገራል። ኮ/ል መንግስቱም “የኢትዮጵያን ህዝብ ከመምራት ዘበኛ መሆን ይሻላል” አይነት ንግግር እንደተናገሩ ይታማሉ። አቶ መለስ ደግሞ “ልማት እንጂ ዴሞራሲ አያስፈልገንም” የሚል ተረት ባገኙት አጋጣሚ ሲተርቱብን ኖረዋል ፤ በጠና መታመማቸውንም የሰማነው ከሴኔጋሉ ፕሬዘደንት እንጂ ከኢትዮጰያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አልነበረም ፤ ይሄም ህዝብን መናቅ ነው።
የህዝብ ልጓም
ህዝብ የሚቆጣጠረው ምንግስት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተከስቶ አያቅም። ህዝብን የሚገዙ ፥ የሚበዘብዙ ፥ የሚያንገላቱ ፥ የሚያስሩና የሚገሉ እንጂ። የህዝብ ልጓም ያልያዛቸው የፓለቲካ ሊህቃን የህዝብ ጠንቅ ናቸው። የህዝብ ልጓም የማይቆጣጠረው መንግስት ይነቅዛል ፥ ይበሰብሳል ፥ ይገረሳሳል።
ኢህአዴግ በመሰረቱ በህዝብ ልጓም ውስጥ መግባት የማይችል ቡድን ነው። የኢህአዴግ ርዮተአለም መሰረታዊ የሆነ ለህዝብ የማይገዛ ፓርቲ እንዲሆን ዋናው ምክንያቱ ቢሆንም ፥ ኢህአዴግ የወረሰው የኢትዮጵያ የፓለቲካ ባህልም ኢህአዴግን ወደ መቃብሩ እንዲገሰግስ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው።
ኢህአዴግ ሁሉንም ነገር ለራሱ ጥቅም በሚመች መንገድ ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። ሁሉንም! መከላከያውን ፥ ፓሊስን ፥ ደህንነትን ፥ ሚዲያዎችን ፥ ማዳበሪያን ፥ የእርዳታ ክፍፍልን ፥ ተማሪዎችን ፥ ፍርድ ቤቶችን ፥ የምርጫ ቦርድን ፥ ስልክ ፥ ኢንተርኔት … ኸረ ምኑ ቅጡ! ሁሉንም ይቆጣጠራል። የመቆጣጠር ፍላጎት ያለመረጋጋትን እና የፍርሃትን መስፈን ያመለክታል። የሚፈራ ድርጅት ሁሉም ያስፈራዋል ፥ ያባንነዋል ፥ ያስደነብረዋል።
ኢህአዴግ አንድ ሊቆጣጠር የማይችለነው ነገር ቢኖር ግለሰቦች ለነጻነት ያላቸውን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። ያንን መቆጣጠር አይቻልም። ሰዎችን ማስፈራራት ፥ መተንኮስ ፥ ማሰርና መግደል ይቻላል ፥ ለነጻነት ያላቸውን ፍላጎት ግን ማስፈራራት ፥ መተንኮስ ፥ ማሰርና መግደል አይቻልም።
የኢህአዴግ ስነልቦናዊ ሽንፈት
ኢህአዴግ ባለፉት 21 ዓመታት ቀስ በቀስ ሲገዘገዝ የኖረ ቡድን ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን አጣብቂኝ ውስጥ በፍጥነት ገብቷል። በ2008 እ.አ.አ የተከሰተው የአለም አቀፉ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ቀውስ የኢህአዴግ ኢኮኖሚ ቀመር መዛነፍ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በተለይም የሚከተሉት ሁኔታዎችና ክስተቶች ኢህአዴግ የስነልቦና ሽንፈት ውስጥ አስገብተውታል፦
1. የገንዘብ በብዛት ማተሙ የፈጠረው የኑሮ ውድነት
2. የአረብ አገሮች ህዝባዊ አመጾች
3. የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ለህዝባዊ አመጾቹ ያሳየው አወንታዊ ድጋፍ
4. የጋዳፊ መገደል ፥ የሙባረክ መታሰር ፥ የየመኑ ሳሌህ መሰደድ ፥ በቅርቡ መውደቁ ማይቀረው የሶሪያው አሳድ
5. የዲያስፓራ ፓርቲዎችና ሲቪክ ድርጅቶች በቅርቡ የተጀመሩት ትብብርና
6. የአቶ መለስ በሞት ከስልጣን መወገድ ናቸው።
መግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት በማንኛውም ትግል የስነልቦና ድል ወሳኙ ድል ነው። ኢህአዴግ በአቶ መለስ መታመም የተነሳ ያሳየው መብረክረክ ፥ የደጋፊዎቹ መራወጥና መደናበር ሁሉም የሚጠቁሙት የድርጅቱን ውስጣዊ የስነልቦና ጽናት መንኮታኮት ነው። አቶ መለስ መሞታቸው እሳቸው ለ21 ዓመታት ያግበሰበሱትን የፓለቲካ ስልጣን አምክኖ ፡ ጥልቀት የሌለውን በአንድ ግለሰብ ዙሪያ የተጎነጎነውን የቁጩ ተቋም ጭንብሉን ገፎ እንርቃኑን አስቀርቶታል። የነ አቶ መለስ ትውልድ ወደ መጨረሻው ተፈጥሯዊ ምዕራፉ ገብቷል። የሳቸውም ጓደኞችና ባላንጣዎች እድሚያቸው እየጨመረ ሳይሆን እየቀነሰ ነው የሚመጣው።
አዲሱ የኢትዮጵያ የፓለቲካ ምዕራፍ ከሚያነሳቸው አንገብጋቢ ጥያቆዎች አንዱ “ከዚህ ወዴት እንሂድ?” የሚለው ነው። ካለፉ ስህተቶች የተማረ ፥ መንግሰትን በህዝብ ልጓም ውስጥ የሚያስገባ ዘለቄታዊ መፍትሄ ማበጀቱ አማራጭ የሌለው አቅጣጫ ነው። በተለይ በገዢው ፓርቲ ሊሂቃንና በተቃዋሚ ፓርቲ ሊሂቃን መካከል ሊፈጠር የሚገባው ከጥላቻ ፓለቲካ የራቀ ፥ ጥገናዊ ለውጥ ውስጥ የሚያስገባ የፓለቲካ ቃና (tone) ብቻ ነው። በዚህ አጋጣሚ ፡ ለአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰብ ፥ ለጓደኞቻቸው ፥ ለወዳጆቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ።
ጸሃፊውን ለማግኘት በዚህ ይጻፉ፦ [email protected]