አሳዛኙ ዜና
እየሰማሁት ያለሁትን ነገር ለማመን ረዥም ሰዓት ፈጅቶብኛል፡፡ ቆይቼ ደግሞ ምናለ ውሸት በሆነ እላለሁ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን በዚህ ሁኔታ ማጣት አልነበረብንም፡፡ እንደ ሰው የተሳሳቷቸውን ራሳቸው አርመዋቸው፤ የጀመሯቸውን ነገሮች ውጤታቸውን አይተው፡፡ በሕይወት እያሉ ሌላ ሰው በሥልጣናቸው ተቀመምጦ፤ እርሳቸው እንደማንኛውም ሰው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሲራመዱ ለማየት ነበር ምኞቴ፡፡በተለያዩ ሚዲያዎች ስለ ሕመማቸው፣ ከዚያም ዐልፎ ስለ መሞታቸው አስቀድሞ ሲነገር ነገሩ እጅግ ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ ከሕመማቸው ተሽሏቸው ያለፉትን ሃያ ዓመታት ስሕተቶችን ራሳቸው ያርሙታል፤ ያለፉትን ሃያ ዓመታት ጥንካሬዎችም በግለሰብ ላይ ሳይሆን በሥርዓት ላይ ይስኬዱታል ብዬ አምን ነበር፡፡
ግን አልሆነም፡፡ ሰው መሆን አይቀርም፡፡ አሁን ራሱ ለማመን እየከበደኝም ቢሆን አቶ መለስ ዜናዊ ዐርፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ መሪዎቿ በሕይወት እያሉ ሥልጣን ሲቀያየሩ ሳያይ፣ የመሪዎች ለውጥ የሚመጣው አንድም በሞት አንድም በስደት ብቻ እንደሆነ ልንቀጥል ነው ማለት ነው፡፡
በአንድ ሰሞን ፓትርያርኩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያጣንበት ምክንያት ምን ይሆን? የእግዚአብሔርስ መልእክቱ ምንድን ነው? ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኀዘን ቦታ ላይ ‹‹ሞት ታላቅ መጽሐፍ ነው፤ ነገርግን የሚያነበው የለም›› እንዳሉት ከሰሞኑ ሁኔታ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ሌሎቻችንስ ምን እንማራለን?
ለሁላችንም መጽናናቱን ይስጠን፡፡
እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር