የሸንጎው ራዕይ
ከአገሬ አዲስ
ሃምሌ 24-2004 ዓ.ም.(01-08-2012)
ከሦሥት ወራት በፊት በይፋ የተቋቋመውን ሸንጎ ለመመሥረት ከሁለት ዓመት በፊት ጥሪ ያደረገው የጥቂት ግለሰቦች ስብስብ አገሪቱ የምተገኝበትን በማጤን ወደየት አቅጣጫ እንምትጓዝ፣አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ በቅድሚያ በመገመት መደረግ የሚገባውን ብሔራዊ ተግባር ተንብይቶ ነበር።
ኢትዮጵያን ለገጠማትና ሊገጥማት ለሚችለው ችግር መፍትሔው በጋራ ታግሎ ዴሞክራቲክ ሥርዓት እንዲሰፍን ፣በአገሪቱ ሰማይ ላይ የተንጠለጠለው የመበታተን አደጋ እንዲቀለበስ፣የሕዝቦቿ ልዑላዊነት፣የግዛቷ አንድነትና ሰብዓዊ መብት የተከበረባት፣የሕግ የበላይነት የሰፈነባት አገር መፍጠር ሲቻል እንደሆነ በማመን፣ እነዚህን አብይ ጉዳዮች ዓላማው አድርጎ ለተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣የሲቪክ ማህበራትና ግለሰቦች በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቶ ጥቂቶች ጥሪውን ሰምተውና አክብረው ሸንጎውን ለማቋቋም ችለዋል።
ጥሪው ቡሁሉም ዘንድ ቀና አመለካከትና ሰሚ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ወቅት ጠንካራ የተቃዋሚ ጎራ ተፈጥሮ በተገኘ ነበር፤አሁን በየአቅጣጫው የሚደረገው ጥሪና እሩጫ ባላስፈለገም ነበር።ከጥሪ ወደ ተግባር ተሻግሮ ትግሉን የሚመራ ሃይል ፈጥሮ በሕዝቡ መካከል ተገኝቶ ታግሎ ማታገል በተቻለ ነበር።
አሁንም ቢሆን ምንም እንኳን የዘገዬ ቢመስልም ካለፈው ቸልተኝነት፣ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎት፣የሥልጣን ሽኩቻ እስርቤት ወጥቶ ጠንካራ የጋራ ግንባር ፈጥሮ በአገር አድኑ የትግል ጎራ መሰለፍ አማራጭ የሌለው ብሔራዊ ግዴታ ነው።ከአሁን በዃላ ጨርቄን ማቄን ማለት ጊዜው ያለፈበት ሰበብ ነው።ተቀባይም የለውም።
ለኢትዮጵያ አገራችን አንድነትና እድገት፣የምናስብ ከሆነ፣ለዲሞክራቲክ ሥርዓት መስፈን የቆምን ከሆነ፣ለሕግ የበላይነትና ለሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የምንታገል ከሆነ፣ሸንጎው በቀየሰው ጎዳና ውስጥ ተቀላቅሎ የጋራ ትግሉን በጋራ አመራር መቀጠል ተገቢና ወቅታዊ ሕዝቡም ከተቃዋሚው ጎራ የሚጠብቀው ብሔራዊ ግዳጅ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበውና መልስ ሊሰጥበት ይገባል።
በአሁኑ ወቅት የጠ/ሚኒስትሩ የመለስ ዜናዊን የጤና ሁኔታ ተከትሎ በሚሰማው ወሬ ላይ አተኩሮ መወናበድና የትግሉ መጨረሻ አድርጎ ማየት ስህተት ነው።በገዢው ቡድን ውስጥ አንዳንድ ተለዋዋጭ ነገር መፍጠሩ ባይቀርም መሠረታዊ የሆነ ለውጥ እንደማይመጣ ጠንቅቆ ማወቅ ተገቢ ነው።መለስ ኖረ አልኖረ ትግላችን በአገራችን ዘለቄታ ያለው የሥርዓት ለውጥ እስኪመጣ ድረስ መቀጠል አለበት።አንዱ ወያኔ በሌላው ወያኔ ወይም አጫፋሪ ግለሰብ ቢለወጥ ወይም በጥገና ለውጥ ከተቃዋሚ ጎራ መካከል አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታ ቢፈጠር፣አጃቢ ሆኖ ለመሥራት ይህን ሁኔታ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ሃይሎች ቢኖሩ በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ መታለልና ትጥቅን መፍታት አይገባም።ግራም ነፈሰ ቀኝ ከአጠቃላዩ የትግል መስመርና አቅጣጫ ላለመውጣት ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።በሁኔታዎች መቀያየር ልንገዛና ትግላችንን ማርገብ አይኖርብንም።የዓላማ ጥራትና ጥንካሬ እንዲኖረን ያስፈልጋል። ዓላማችንም ዘረኛና እብሪተኛው የህወሃት/ኢሕአዴግ መንግሥት እንዲወገድና በምትኩ ሕዝባዊ ሥርዓት እንዲመሰረት ነው፤ከቀውስ ተርፎና አገግሞ አገዛዙን እንዲቀጥል መንከባከብና ድጋፍ መስጠት ወይም በተመሳሳይ ሌላ ድርጅት ተተክቶ የግፍና ዘረኛ ስርዓት እንዲቀጥል አይደለም።
በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ስም የሚንቀሳቀሱት የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣ሲቪክ ማህበራት፣የወጣት፣የሴቶች፣የሙያ፣የሃይማኖት ተቋማት እርስ በርሳቸው የሚያደርጉትን ንትርክና ሽኩቻና የተናጠል ጩኸት አቁመው በአገር አድን ትግሉ ለመሳተፍ በአንድነት ግንባር ምስረታው ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ በአደገኛ መንገድ ውስጥ ገብታ በምትዋልለው ኢትዮጵያ አገራችን ስም ጥሪ አደርጋለሁ።
አሁን በሸንጎው አነሳሽነት በመታየትና በመሰማት ላይ ያለው የአንድነት ግንባሩ ምሥረታ ጥረት ፍሬያማ ሆኖ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደርስ በተለይ በውጭ አገር የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ለዚህ ሁሉን አቀፍ ለሆነው ግንባር ምሥረታ ያልተቀላቀሉት ድርጅቶች እንዲቀላቀሉ ጫናና ግፊ እንዲያደርግ፣እምቢ ያሉትንም እንዲያጋልጥና ድጋፍ እንዲነፍጋቸው፣በተጨማሪም ለሚፈጠረው የጋራ ግንባር የሃሳብ፣ የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፉን እንዲያደርግለት በትህትና እጠይቃለሁ።
ምናልባት በአገራችን የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣ ከሆነና የተቃዋሚውን ጎራ የሚጋብዝ ሁኔታ ከተፈጠረ
በቅድሚያ
የዲሞክራቲክ መብቶች ማለትም የመናገር፣የመጻፍ፣የመሰብሰብ፣የመሰለፍ መብቶች ያለምንም ገደብ መከበራቸውን ማረጋገጥ፣የዜና አውታሮች ነጻነትና ለሁሉም እኩል አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣
የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ሁኔታ በነጻ መለቀቅና ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ እንዲያገኙ ማረጋገጥ
የምርጫ ቦርድና ፓርላማ ፈርሶ በአዲስ መልክ በሽግግሩ ቅርጽ እንዲቋቋም የሚያስችል ስምምነት ማድረግ፣
የአገሪቱ ሕገመንግሥት እንደገና እንዲታይና በሕዝቡ ተሳትፎ እንዲረቅ መስማማት፣
የአገሪቱ የጦር ሃይል የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አገልጋይ ከመሆን ተላቆ በብሔራዊ መከላከያ ተግባር ላይ እንዲያተኩር ማደራጀት፣አመራሩንም ሚዛናዊ በሆነ መልክ ማስተካከል፣
የሥርዓቱ ደህንነት ጠባቂ የሆነው የስለላ ተቋም መፍረስና የሕዝቡን ደህንነትና ሰላማዊ ኑሮ በማስከበሩ ተግባር ላይ እንዲሰማራ በሚያስችለው መንገድ ማደራጀት፣
በሕዝቡና በአገሪቱ ላይ በደል የፈጸሙ በቁጥጥር ሥር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያስችል ውል ማድረግ፣ሥልጣንን ተገን አድርገው በዘረፉ ሃብት ያከማቹት እንዲወረሱና ለፈጸሙት ጥፋት ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራርና አስቸኳይ ሕግ የሚወጣበትን ማመቻቸት።
ከዚህ በላይ የተገለጹት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ለውጥ ይመጣል ብሎ ተንደርድሮ ከወያኔ ጉያ መግባት አንገትን ለገመድ አሳልፎ መስጠት ይሆናል።ከቅንጅትና ከሌሎቹ ተመክሮ መቅሰም ተገቢ ነው።
ይህ በግለሰብ ደረጃ ያቀረብኩትን ሃሳብ እንደመንደርደሪያ ወስዶ ለማሻሻልና ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም እንዲረባረብበት እጠይቃለሁ።