ጃንደረባ ሎሌ በጌታው ብልት ይፎክራል

ከቴዎድሮስ ሐይሌ

ገንዘብን መውደድ የጥፋት ሁሉ ስር ነው አንዳንዶች ይህን ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ስቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (2 ጢሞ. 6፡6)

AESAONE is a legally registered non-profit organization based on a non-political, non-ethnic and non-religious platform. We remain sports and culturally focused. Our mission is to embrace ALL Ethiopians using sports and culture as a vehicle. We have organized concerts and cultural events throughout the week. We, again, invite each and every one of you to join us at the annual AESAONE soccer tournament.

በሃገራችን መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ አበው እንዲሉ ባህልና ወጋችን ሆኖ ፈሪውን ደምመላሽ በታኙን አንዳርጋቸው ክፉውን ለገሰ አስቀያሚዋን ዉቢት የሚቀመስ ጥሬ በሌለበት የተወለደውን ሐብታሙ አለያም ሺህበሺ እያልን ብቻ የባህሪ የተፈጥሮና የሃብት ጉድለታችንን በስም እየጠገንን በተስፈኝነት የስም ስንቅ ችግራችንን እያቀለልን ዘመናት ተሻግረናል በእርግጥ እንደህብረተሰብ ጠቀሜታው የጎላ እንጂ ጉዳት ያለው ነው ሊባል የሚያስችል አይመስለኝም።ይህን አይነቱ ባህል ሌሎች ሕዝቦች የሚጋሩት እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ በከሃዲነቱ ስሙ ጎልቶ የሚታወቀው ይሁዳ የስሙ ትርጓሜ በእብራይስጥ ቋንቋ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደሆነ የሚስጥርና አንድምታ ሊቃውንት ያስተምራሉ ። እንግዲህ የዚህ መልካም ስም ባለቤት የሆነው ይሁዳ የእጁን ታምራት የቃሉን ትምህርት የሰማይ መና የተመገበውን አዳፋ እግሩን በቅዱስ እጁ ያጠበውን የጌታውን እጅ ሊነክስ የበላበትን ወጭት ሊሰብር ያነሳሳው የዚህ ዓለም የጥፋት ስር የተባለው ገንዘብ በመውደዱ ለሰላሳ ዲናር አምላኩን ለሞት አሳልፎ እንደሰጠ ስንማረው ያደግነውና የምናውቀው ቢሆንም ባለማስተዋል ዛሬም በይሁዳ መንገድ የሚጓዙትን የገዛ ወንድሞቻችንን አይተን እንዳንስት ለማስታወስና አንዳንዶቻችንም ጥቂት ለጥቅም ብለው ወገን ሲከዱ ሃገር ሲያዋርዱ በምናያቸው ይሁዳውያን የተነሳ ራሳችንን እስክንጠላ ከአንድ ሃገር ማሕፀን በመፈጠራችን ራሳችንን ስንረግም ለምንገኘው ጥሩ ምሳሌ ይሆናል።

ተገንጣዩ AESAONE ነኝ የሚለው ከበርቴ ሰራሽ የአድርባይ መንጋ ወጉ እንዳይቀርበት አላማዬ በሚለው ከላይ በእንግሊዝኛው የቀረበውን አይነት በልኩ ያልተሰፋ ቀሚስ አጥልቆ ሠው ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን የአደባባይ ሚስጥር አይታወቅ ይመስል ከፖለቲካ ገለልተኝነቱን ከጎሳ አመለካከት መጽዳቱን ሊያሳምን ይሞክራል ፤ ለመሆኑ የስፖንሰሩ ፖለቲካዊ አቋም ከፖለቲካ ያለፈና የኢትዮጽያን ሕዝብ ደም የሚመጡትን እንደ በረከት ስምዖን ያሉትን እንደማንቆርቆሪያ እያንጠለጠለ ውጭ ወስዶ የሚያሳክምና ከመሸታ ቤት ቱማታነት ያላለፈውን የባልቴቶች ወግ የሆነውን መጽሃፍ ሲያሳትም የንብ ባንዲራ ለብሶ አራዊቱንና ሰው በላውን የወያኔ ቡድን ሲያስተዋውቅ አዲሱ የኳስ ቡድን አያውቅምን ከዘበኛው እስከ ዋና አማካሪው በአንድ ጎሳ ሰዎች የተከበበ የኢትዮጽያን ሕዝብ አፈናቅሎ በሚያርሰው መሬት ወገን እየተራበ ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ የሃገሪቱን ሃብት ያለ ገደብ እየተጠቀመ ያለ ግለሰብ በለገሰው ገንዘብ ገለልተኛ ነኝ ብሎ መዋሸት ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው።

እኔ በእውነቱ የሼኩም ሁኔታ ያሳዝነኛል አላህ በረከት ያበዛለት በህይወት ዘመኑ በልቶት አይደለም ቆጥሮ የማይጨርሰው ሐብት እያለው ከበረከቱ መረገሙ እየተረፈን እንኳ ከዓለም ሃብታሞች መካከል በባለጸጋነቱ የሃገራችን ተወላጅ ወንድማችን በመሆኑ እኛም ስንኮራበት ምን አለ ውሎውን ከጭፍራና ከምስለኔ ጋር ባያደርግ ለሃገር ፍቅር ከሆነ ያለ ምንም የወሽካታ መንጋ ሚሊዮኖችን ከጎኑ በተሰለፍን ነበር። ጥቂት ወንድሞቹን በጥቅም ቢያንበረክክም ቆሎ በልቶ እስቴኪኒ የሚይዝ ኩራት እራት ከሚል ጅንን ማህበረሰብ የፈለቅን ታሪካችንን ያልዘነጋን ዜጎች እልፍ አእለፍ በመሆናችን ይህን አይነቱ የአደግዳጊነት ባህል ለመቀበል አንችልም ።ቅዱስ ቁራን “ስታጣ ታጋሽ ስታገኝ ለጋስ ሁን!” ሲል ይመክራል ስለዚህም ያለው ይሰጣል የሌለው ይቀበላል ይህ ደግሞ የነበረ ያለና የሚኖር መንፈሳዊና ሰብዓዊ ዑደት ነው። ያለው የአመለካከት ባሪያዎችን ሊያሰማራ ቢችልም ይህን ማድረግ ለጌታውም ሆነ ለሎሌው የሞራል ክስረት እንጂ ክብርም ትርፍም የለውም ስለዚህም የተከበሩ ሼክ አላሙዲ የኔ ብጤው በሃገሩ የመኖር ነጻነት አጥቶ የኮበለለ ዜጋ ብርጭቆ አጥቦ በሚያገኘው ገንዘብ ፈጣሪውን አመስግኖ በሰላምና በነጻነት በመኖሩ ተረጋግቶ የሰው እጅ ሳያይ በሚኖርበት ሃገር ያውም የተሻለ ኑሮ እያላቸው ክብራቸውንን አድፋፍተው ወገናቸውን ክደው የተፉትን ልሰው ጫማዎት ስር የሚርመጠመጡት ጃንደረባ ሎሌዎች ከትቢያ ያላነሱ ከህዝብ ጋር እንዳይታረቁ እንቅፋት የሚሆኑ ከወዳጆ ከወያኔም የባሱ በመሆናቸው ከዚህ አፍራሽ ድርጊት ቢቆጠቡ መልካም ነው መጽሃፉም የቆመ የሚመስለው ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ ይላልና ሰልፎን ከሽፍቶች ሳይሆን ከህዝብ ያድርጉት!

አበው ሠይጣን ገንዘቡን ያስቀድምና ገመዱን ሲያሰስከትል አይታይም ይላሉ ነገሩንም ሲያጠናክሩ ይሁዳ ጌታውን በሰላሳ ዲናር አሳልፎ ከሰጠ በኋላ የተከፈለው ገንዘብ እርካታና ደስታ ሊገዛበት ይቅርና እጁ ገብቶ ሳይውል ሳያድር የፀፀት ማቅ አልብሶት ዕምነቱን ያሰጣው ፀጋውን ያስገፈፈው ያ የጓጓለት ገንዘብ ለባለቤቶቹ መልሶ ማቆና ታንቆ ራሱን እንደገደለና በጣለውም ገንዘብ መታሰቢ ይሆን ዘንድ ፈሪሳውያን የደም መሬት አኬል ዳማ የሚባል ርስት እንደገዙለት ታሪኩ ያትታል። ይሁዳ የዛሬ ሁለት ሺህ አመት ይህን ታሪክ ፈጽሞ ቢያልፍም ዛሬ አለመታደል ሆኖ ሃዋረያቶች ከተሰውላት ጻድቃንና ሰማዕታት የተጋደሉላት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሳይቀር በውስጧ የመሸጉ በጥቅመ ሰናዖር የናወዙ ንዋይ አሳዳጆችና መንጋቸውን ለገንዘብ የሚሸጡ አደራ በላ ካህናት ሳይቀር ( እንደ አባ መላኩ ፤ አባ ምላጭ) አይነቱ ጭምር በክፉ አርዓያነት ትውልዱ የምግባር መስመሩን እንዲስት በተናገሩበት ጸንተው መገኘት በዋሉበት ማደርን ትተው በአደባባይ የተናገሩትን ዘንግተው በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ይዘው ሲገኙ ታዲያ እንዴት ትውልድ ለእውነት ዘብ ይቁም ማን ተምሳሌት ይሁነው አንዳንዴ በእውነት በተራው ዜጋ መፍረድ ይቸግረኛል።

ያም ሆኖ በሃገሩ የመኖር ነጻነት አጥቶ የተሰደደ ማህበረሰብ ቢችል ሃገሩና ወገኑ የተጫነውን የድህነትና የጭቆና ቀንበር አራግፎ የተሻለ ስረዓት ሊፈጥር የበኩሉን አስተዋጽዖ ሊያበረክት ባይችል ከገዳዮቿ ላያብር ዝምታን ሊመርጥ በተገባ ነበር። አለመታደል ሆኖ በተለይ በአሜሪካ የሚኖረው የኛው ወገን እነ ማርቲን ሉተርና የጥቁር መብት ታጋዮች ምስጋና ይድረሳቸውና በነሱ ሞት በመጣው ነጻነት ተጠቃሚ ሆኖ ያጣውን የሆድና የነጻነት በረከት በሌሎች መቃብር ላይ የሚያጣጥመው የኑሮ በረከት አንሶት በልቶ ማደር የህይወት ሸክም በሆነበት እናት ሃገር ባለው የአካላችን ቁራጭ የአጥንታችን ፍላጭ በሆነው በገዛ ወገናችን መከራ ላይ ለመዘበት በመከራው ልናተርፍ በስቃዩ ልንነግድ ምን መንፈስ አነሳሳን በእርግጥ ሰው ሰርቶ በሚበለጽግበት ሃገር ሆነን እንደ ምንዱባን ቀን ካነሳው ከበርቴ ሽርፍራፊ ሳንቲም ይመረን አረ ጎበዝ ቆም ብለን እናስብ ፤ ቢቸግረን እንኳ በፉድ እስታንፕ ማርና ወተት የሚቀልበን የአሜሪካ መንግስት እያለ እንዴት የደም ገንዘብ እንፈልጋለን።

ከላይ ከመግቢያው እንደሰፈረው የሃሰት የአላማ ሽፋን በአንድ የዋህ ከበርቴ ገንዘብ ተቋቁሞ አባታችን አዳምንና እናታችን ሔዋንን ከገነት እንዲባረሩ መልዕክተኛ የሆነውን ጥንት ጠላታችን እባብን በባህሪ የሚመሳሰው የወያኔው የጥፋት ሃይል በህዝብ መሃል ፍቅር እንዳይነግስ አንድነት እንዳይበረታ ሴራ በመጎንጎን መንድም መንድሙን እንዲጠላ ቅራኔን በማስፋፋት በጋብቻ በጉርብትና በፍቅርና በአንድነት የኖረውን ህዝብ ለመበታተን በተዘዋዋሪ የእርጉም ኣለማው ማስፈጸሚያ ለማድረግ ራሳቸውን የከበርቴ ጃንደረባ ባደረጉ የአመለካከት ስልቦችን በማስፎከር በተንበርካኪዎችና በነጉርሻ ብርቁ ምስለኔዎች ጀርባ ተረማምዶ የጥፋት ነጋሪቱን ለመጎሰም የተደረገው ሰጣናዊ ውጥን ከመነሻው የከሸፈ ቢሆንም የወያኔ ተፈጥሮው የእባብ ነውና እንደለመደው አቧራውን ቅሞ በሌላ ዙር የጥፋት ተግባር እንዳይሰማራ የተነቃቃው ሕዝባዊ ሃይል ትግሉን በበለጠ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።