አክሱምና እስልምና በፍቅር ወርቁ
በአክሱማውያን ታሪክ «አልነጃሺ» የተባለ የሰለመ ንጉሥ ነበርን፡- ስለ ነቢዩ መሀመድ፣ የእስልምና ሃይማኖት እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ዙሪያ ታሪክ የሚነግረን ሀቅ ምንድን ነው?
በፍቅር ለይኩን፡፡ [[email protected]/[email protected]]
ከጥቂት ወራት በፊት የመንግሥታቸውን የሥራ ሂደት ሪፖርት ለማሰማትና ከክቡራን የምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በፓርላማ የተገኙት ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ መስመሩን እየሳተ እየሄደ ስላለውና አንዳንድ በሃይማኖት ሽፋን የአክራሪነትና ጽንፈኝነት እንቅስቅስቃሴ ስለሚያራምዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ በሚመስል ንግግራቸው፡- ‹‹እንዲህ ዓይነቱን በሃይማኖት ሽፋን እየተካሄደ ያለውን የአክራሪነትና የጽንፈኝነት እንቅስቃሴ መንግስት ችላ እንደማይለውና በንቃት በመከታተል እርምጃ እንደሚወስድም በግልጽ አስረድተው ነበር፡፡››
ጠቅላይ ሚ/ሩ አክለውም በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ታሪካዊና ጥንታዊ የሆኑት ሁለቱ ሃይማኖቶች ክርስትና እና እስልምና ለረጅም ዘመናት በሀገራችን ተከባብረውና ተዋደው የኖሩና ይህ ልዩ የታሪክ እውነትም የተቀረው ዓለም እስከ አሁንም ድረስ የሚደነቅበትና በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቅሰው መሆኑን አስታውሰው ይህን እውነታ የሚያስረግጥ አንድ ገጠመኛቸውን ለፓርላማው ክቡር አባላት እንዲህ አቅርበው ነበር ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር መለስ፡-
በቅርቡ አሉ ጠቅላይ ሚ/ሩ አንድ ከወሎ ክ/ሀገር የገጠር ቀበሌ የመጣ ሰው/ወደጃቸው በዛ ቀበሌ ዝናብ በመጥፋቱ ምክንያት ድርቅ ስላጠቃቸው በቀበሌው ያሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ክርስቲያኖች ታቦታቸውን ነቅለው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ መቁረጣቸውን የሰሙ የእስልምና እምነት ተከታዮችና የዕድሜ ባለጸጋ አባቶች ክርስቲያን ወገኖቻቸውን ይህ ታቦት የእናንተ ብቻ እኮ አይደለም የሁላችንም ነው፡፡ በዚህ ቦታ ለብዙ ዘመን ቆይቷል እናም እባካችሁ ከዚህ ቦታ አትንቀሉት እኛም አላህን እንለማመናለን እናንተም እግዜርን ተማጠኑ በማለት ክርስቲያኖቹ ታቦታቸውን ነቅለው እንዳይሄዱ እንዳገላገሉ ለፓርላማው አባላት ተናገረው ነበር፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚ/ሩ በዚህ ንግግራቸው ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልእክት ለብዙዎቻችን ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በታሪካችን የቆየውና እንደ ምሳሌ የምንጠቀስበት በሃይማኖቶች መካከል ያለው መከባበርና መቻቻል በዚህ ዘመን እንዴት እየጠፋና ከመስመር እየለቀቀ እንዳለ ያሳሰቡበት መልእክት ይመስለኛል፡፡
በዛሬው ጹሑፌ ይሄንኑ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀውን የመከባበር ባሕል እያጠፉና ወደ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እየመሩ ካሉት ምክንያቶች አንዱ በሃይማኖቶች መካከል ያለውንና የነበረውን ታሪክ ከማጣመምና አንዳንዴም ደግሞ ያለ በቂ መረጃ በአፈ ታሪክ የሚነገሩ ትውፊቶችና ታሪኮች በአማኞች መካከል የተጋነነ ስሜትና የተሳሳተ አቋም እየፈጠሩ በሃይማኖቶች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነቶች ሲያሻክሩት እየታዘብን ነው፡፡ ከነዚህም መካከል በብዙዎች የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እየተነገረና በሰፊው እየተጻፈለት ያለው የአክሱም ንጉስ «አልነጃሺ» እና አክሱማውያንም መስለማቸውንና ከዚህም የተነሳ አንዳንዶች አክሱም ቅዱስ የሙስሊም ከተማ ናት እስከማለት የደረሱበትን አጋጣሚዎችንም እየታዘብን ነው፡፡ እናም እስቲ በዚህና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ በትምህርትና በሥራ አጋጣሚ በእጆቼ ከገቡ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት በማጣቀስ ጥቂት ነገሮችን ልበል፡፡
በ፳፻ ወርኃ ክረምት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያለሁ በእስልምና ሃይማኖትና በአክሱማውያን ስረወ መንግሥት መካከል የነበረውን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ግንኙነት ለማጥናትና በዚህም ላይ ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የሚሆነውን መመርቂያ የጥናት ጹሑፍ ለማዘጋጀት ከአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት ከሚገኝ ዩኒቨርስቲ ከመጣ አንድ ጎልማሳ ምሁር አሜሪካዊ ጋር ወደ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ አክሱም ከተማ ለመስክ የምርምር ጥናት አቅንተን ነበረ፡፡ በቆይታችንም ከአዲግራት ፳፭ ኪ.ሜ ርቀት ከሚገኘው የሙስሊሞች ቤተ አምልኮ ከሆነው «አል ነጃሺ» መስጊድ ተገኝተን ነበር፡፡
በዚሁ የመስክ ጉዞ ቆይታችንም በዛ ከሚገኙ በዕድሜ ባለጸጋ ከሆኑ የእምነቱ አባቶችና ሸህዎች ጋር ለጥቂት ሰዓታት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ቆይታን አድርገን ነበር፡፡ እስካሁን ልረሳው ባልቻልኩት በልቤ ጽላት ውስጥ በማይደበዝዝ ቀለም በታተመ እጅግ በሚመስጥ ትህትና፣ ጨዋነትና የኢትዮጵያዊነት እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ነበር አቀባበል ያደረጉልን እነዚህ የሃይማኖቱ አባቶች፡፡
እነዚህ የዕድሜ ባለጸጋዎች የመጀመሪያዎቹ የነቢዩ መሀመድ ተከታዮች በነቢዩ ምክርና ትዕዛዝ ወደ አክሱም ግዛት እንዴት እንደመጡና በአክሱም ስለተደረገላቸው አቀባበል፣ በዛም እስልምናን ለማሳፋፋት ስላደረጉት እንቅስቃሴና ይህም እንቅስቃሴያቸው በወቅቱ የአክሱምን ንጉሥ እንደ እነዚህ ሰዎች እምነት «አል ነጃሺን» ጭምር ሳይቀር የእስልምናን እምነት በገዛ ፈቃዱ እንዲቀበል እንዳደረጉትና በአክሱም ግዛት የሚኖሩ ሰዎችና አንዳንድ መነኮሳትም ጭምር ሳይቀሩ እስልምናን መቀበላቸውን፣ ስለ እስልምና ሃይማኖትና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት ጭምር በአፈ ታሪክ ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን ትውፊት ከቅዱስ ቁርአንና እንዲሁም ከአረቡ ምድር ታሪክ አዋቂዎች የታሪክ ሰነድና አፈ ታሪኮች በማጣቀስ ጭምር ያስረዱን በራስ መተማመን ፍጹም የተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር፡፡
ከዛም ባሻገር ከመጀመሪያዎቹ ወደ አክሱም ከመጡት የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የነቢዩ ሙሀመድ ልጅ የሆነቸው ሩቂያ፣ ባለቤቷ በኋላም ሦስተኛ ካሊፋ የሆነው ኡስማን አቡበከር፣ ጃፋር አቡጣሊብና የሌሎችንም የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች በአክሱም በሰላም መቆየታቸውንና ከእነዚህም ስደተኞች መካከል አስራ አምስት የሚሆኑት በዚሁ በአልነጃሺ መስጊድ ቅጥር መቀበራቸውን የሚያረጋግጥ መካነ መቃብራቸውንም በእነዚህ የእምነቱ አባቶችና ዕድሜ ባለጸጎች ልብን ከሚመስጥ ትረካቸው ጋር ለመጎብኘት ችለን ነበር፡፡ እነዚህ የእምነቱ አባቶች በገለጻቸው መጨረሻም በነቢዩ መሀመድም ሆነ ከእርሱ በኋላ በተነሱ የእስልምና ታላላቅ አባቶች ዘንድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሙስሊም ሃይማኖት አማኞችና በአረቡ ዓለም ያላቸውን ታላቅ ተቀባይነት፣ መፈራትና ክብር የነገሩን ታላቅ በሆነ ሀበሻዊ ኩራትና ደስታ ውስጥ ሆነው ነው፡፡
ለሰዓታት ባደረግነው ቆይታችን ይህ አሜሪካዊ ተመራማሪ ለመመረቂያ ጹሑፉና ለምርምር ጥናቱ የሚጠቅሙትን መረጃዎች በድምጽ በምስልና በጹሑፍ ከከከተበ በኋላ በሰጡን ሰፊ መረጃዎችና ትንታኔዎች ላይ ሞቅ ያለ ውይይትና ክርክር እያደረግን ወደ ጥንታዊቷ አክሱም ከተማ ተመለስን፡፡ ጉዞአችን እጅግ አስደሳችና ውጤታማ በመሆኑ በወቅቱ የተሰማን ስሜት እጅግ ልዩ ነበር፡፡ እስቲ የጉዞአችንን ማስታወሻ ትረካ በዚሁ ልግታውና አንድ ጥያቄ እናንሳ፡-
ለመሆኑ አክሱማውያን/ኢትዮጵያውያን ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የነበራቸው ታሪካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ግንኙነት አንዳንዶች እንደሚሉት የአክሱምን ንጉሥና አክሱማውያን ከክርስትና ወደ እስልምና እስኪያፈልስ ድረስ ጉልበት ነበረውን? ስለ ‹‹አልነጃሺ›› እና ስለ አክሱማውያን መስለም የሚተረከው ታሪክ ምን ያህል እውነት ነው? የታሪክ ድርሳናትና መዛግብት እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ምሁራንስ ምን ይላሉ፣ ምንስ ጻፉ…፡፡
በእርግጥስ በኢትዮጵያውያኑ፣ በምዕራባውያኑና በአርብ ሀገራት የታሪክ ተማራማሪዎች፣ ሊቃውንትና ጸሐፍት የታሪክ ድርሳናት ዘንድ በእርግጥ የአክሱም ንጉሥና አክሱማውያን ስለመስለማቸው ነው የሚነግሩን ወይስ በተቃራኒው፡፡ በእኛስ ዘመን «ኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ደሴት» የሚለው የቆየው ብሂልና አገላለጽ በአንዳንድ ሙስሊሞች ዘንድ ለምን ቅር ከማሰኘት አልፎ ከቃላት ውርጅብኝ ወደ ቁጣና ወደ ግጭት እና ጥቃት ለመሻገር እንዲበቃ ያደረገው የዘመናችን ጽንፈኞችና አክራሪዎች «የአልነጃሺ ሰልሟል» እና «አክሱም የመጀመሪያዋ የእስልምና እምብርት ከተማ ናት» መፈክርና ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው ትረካ ከሃይማኖቱ ባለፈ ግብ ያደረገውና የተቀመመበት ታሪካዊ መነሻና ዳራው ውሉ ከየት እስከ የት ሊመዘዝ ይችላል፡፡ በአንዳንድ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከመካ፣ ከመዲናና ከሶሪያዋ ደማስቆ ቀጥሎ አክሱም አራተኛዋ የእስልምና ቅዱስ ከተማ ተደርጋ መጠቀሷስ ውስጠ-መልእክቱ ምንድን ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ የታሪክ ሽሚያ ወይም ዝርፊያና ሃይማኖትን ማስፋፋት ዘመቻ ባሻገር በሀገራችን በሁለቱ ሃይማኖቶች ዘንድ በአንጻሩም ቢሆን ለዘመናት የቆየው ተከባብሮና ተዋዶ እስከ ጋብቻ መጣመር ድረስ የዘለቀውና ለተቀረው ዓለም ሁሉ ምሳሌ እስከመሆን የዘለቀው በሰላም የመኖር ባሕል በእኛ ዘመን በተዛባ ታሪክና በጓዳው ውስጥ ተረት ተረት/አፈ ታሪክ በተወለደ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት መንፈስ እንዴት እንዲህ ያለው አደጋ ሊጋረጥበትና እንዲህ ዓይነቱ አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ ቻለ፡፡ ከዚሁ ሁሉ ሁነቶች ጀርባና ስለ ‹‹አል ነጃሺ›› አክሱምና አክሱማውያን ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የነበራቸውስ ግንኙነት ምን ድረስ ነው በሚሉት ጉዳዮች ላይ የታሪክ መዛግብትና ሰነዶች ምን ይላሉ የሚለውን በጣም በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዓለማችን ተወዳዳሪና አቻ ካልተገኘለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምሮ በእስልምና ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ ቁርአን፣ ዓለማችን አሁን ለደረሰችበት ስልጣኔና እድገት ትልቁን ድርሻ በሚሰውዱት በግሪካውያኑ ታላላቅ የጥበብ፣ የፍልስፍና እና የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ስሟ ተደጋግሞ በአድናቆት የተጠቀሰ በመካከለኛው ክፍለ ዘመንም ለአውሮፓውያን አሳሾችና ተጘዦች የልብ ትርታ ሆና የቆየችና «የታላቁ የቅዱስ ዮሐንስ ክርስቲያን ሀገር» በመባል ትልቅ ስምና ዝናን ያተረፈች ሀገር መሆኗን በርካታ አሳሾችና የታሪክ ድርሳናት የመሰከሩላት ሀገር ናት፡፡
ከዚህም ባሻገር በጥበብ ፍቅር አቅሏን ለሳተችው በቅዱስ ወንጌል በጌታችን አንደበት ‹‹የጥበብን ሀሰሳ ረጅም ጉዞዋ›› በአድናቆት የተተረከላት የንግሥተ ሳባ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ይህች ንግሥታችንም በሩቅ ሆና በሰለሞን የጥበብ ዝና መንፈስዋ ሸፍቶባት ይህን ታላቅ ጥበብ በጆሮዋ ሰምታ በዓይኗ አይታ ለማረጋገጥ ከምድር ዳርቻ እስከ ዛሬ ድርስም ሆነ ወደፊትም አንድ ሴት ለአንድ ወንድ ልሰጠው ከምትችለው ስጦታ ወደር ያልተገኘለትና እንደ ሁለቱ እንግሊዛውያን የታሪክ ምሁራንና ጸሐፍት ኖርማን ፐርን እና ቨርኖን ባርሎው Quest for Sheba በተባለው መጽሐፋቸው በአድናቆት እንደገለጹት፡-
በንጉሡ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሲተመን ከሃያ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሚገመት ስጦታን ይዛ፣ (ይህ የስጦታ መጠን ስንሰማ ዛሬ በድህነት ቀንበር ስር ወድቀን በቀን ሦስቴ እንዃን እንደ ነገሩ በልቶ ለማደር የመጽዋቾችን በር ነጋ አልነጋም ብለን ደጅ ለመጥናት ለተገደደን ኢትዮጵያውያን ወይ ነዶ… እንዲህ ካለው የታሪክ ሰገነት ተሸንቀጥረን ነው ለዚህ የበቃነው አያሰኝም ትላለችሁ አንባቢዎቼ) በሺህ ግመሎችና የጋማ ከብቶች የተጫኑ ውድ የሆኑ ማዕድናትን አስጭና የተጓዘች የጥበብ ምርኮኛ ንግሥት የሳባ ሀገር ኢትዮጵያ የዓለማችን የእግዚአብሔር ምስጢር ምድር እንደሆነች በብዙዎች የተጻፈላትና የሚደመሙባት ሀገር ናት፡፡ ይህች እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና ብዙ የአርኪዮሎጂና የታሪክ ምርምር ጥናት የሚያስፈልጋት ባለ ብዙ ምስጢርና ባለ ብዙ ኅብር ባለታሪክ ምድር ናት፡፡
ሀገረ ኢትዮጵያ እስከዛሬም ድረስ ዓለም ምስጢርና እንቆቅልሽ የሆነበት የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኘው በእኔ ምድር ነው ኢትዮጵያውያንም የዚህ ታላቅ የእግዚአብሔር ምስጢር ጠባቂና ባለአደራ ናቸው የምትል ብቸኛዋ የዓለማችን ሀገር ናት፡፡ ከዚህም የተነሳ የብዙዎችን ጎብኚዎች አሳሾችና ታሪክ ተመራማሪዎች ቀልብ የሳበች ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በአንድ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የሽያጥ ጣራን ለመቆናጠጥ የበቃው በእንግሊዛዊው ግራሃም ሀንኩክ የተጻፈው The Sign and the Seal የተባለው መጽሐፍ ኢትዮጵያን ከጥንት ጀምሮ በመንፈሳዊ ኩራት ስለሚናገሩለት ስለእዚሁ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሀሰሳ/ፍለጋ የተጻፈ ክርስቲያኑን ዓለም በሰፊው ያነጋገረ መጽሐፍ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
አስገራሚው ገጠመኝ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዓለማችን ሀገራት በተለየ መልኩ በመካከለኛው ምስራቅ ለተገኙት ለሦስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ለአይሁድ፣ ለክርስትና እና እስልምና ቀዳሚ ማእክል መሆኗ ነው፡፡ ይህን እውነት የመካከለኛው ምስራቅና የዐረብ ሀገራት እውቅ የታሪክ ተመራማሪ፣ የእስልምና ሃይማኖት ምሁር፣ የእስራኤልና የአረቡ ዓለም/የፍልስጤም ግጭት ታሪክ ከፍተኛ ተንታኝና በአንድ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ መምህሬ የነበሩት አሁን በሕይወት የሌሉት በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ Department of History and Heritage Management ባልደረባ የነበሩት ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ Aksum in Muslim Historical Traditions በሚል ጥናታዊ ጹሑፋቸው አክሱምን ሁለቱን የመካከለኛው ምስራቅ ሃይማኖቶች በሰላም ያስተናገደች ከተማ መሆኗን ሲገልጹ፡-
Aksum possesses the unique distinction of being at once the cradle of both Christianity and Islam in Ethiopia, and perhaps represents perhaps the earliest example of a geographical setting favorable for a peaceful encounter and harmonious coexistence between two great monotheistic religions: Christianity and Islam.
በተጨማሪም ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ al-Tiraz al-Manqush fi Mahasin al-Habush (The Colored Brocade on the Good Qualities of the Ethiopian) በሚል ርእስ መሀመድ አብዱል ባኪ አል ቡከሃሪ አል ማቅዚ (በዚህ የዐረቢኛ ስም የአማርኛ ትርጉም ላይ ሰህተት አድርጌ ከሆነ አስቀድሜ አንባቢያንን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡) እ.ኤ.አ በ1583 ዓ.ም የጻፉትን ታሪካዊ ሰነድ ዋቢ አድርገው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በነቢዩ መሀመድና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ያላቸውን ተወዳጅነት እና ክብርም እንዲህ ገልጸውታል፡-
«Who brings an Ethiopian man or woman into his house brings the blessings of God there.»
በሀገራችንም ሆነ በዐረብ ታሪክ ጸሐፊዎችና የእስልምና እምነት ሊቃውንቶች ዘንድ የተጻፉት የታሪክ ድርሳናት አክሱማውያን የነቢዩ መሀመድን ተከታዮችን በሞቀ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዳስተናገዷቸውና በአክሱም ግዛት በነጻነት የመኖር መብት እንደተሰጣቸው በግልጽ ያስረዳሉ፡፡ በአክሱማውያን ግዛት እነዚህ በእምነታቸው ምክንያት የተሰደዱ ሰዎች በሰላም መስተናገዳቸውና በነጻነት መንቀሳቀስ መቻላቸው ቁጭትና እልህ ውስጥ የከተታቸው የመካ ሹማምንት በብዙ ስጦታና አጀብ ወደ አክሱም በላኳቸው መልእክተኞቻቸው እነዚህ በስደት ወደ ግዛትህ የገቡ ሰዎች የእኛንም ሆነ የአንተን እምነት የማይከተሉ ከሃዲያንና አረመኔዎች ናቸውና አሳልፈህ እንደሰጠን አደራ ጭምር የታከለበት መልእክት በዘመኑ ወደነበረው የአክሱም ንጉሥ ልከው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
አክሱማዊው ንጉሥ ግን እነዚህን ሰዎች አስቀርቦ ስለተሰደዱበትና አሁን ደግሞ በጥብቅ ስለሚፈለጉበትና ስለተከሰሱበት እምነታቸው ከጠየቃቸው በኋላ ወደ መካ ሹማምንት በላከው መልእክት እነዚህ ሰዎች ምንም ክፉ ነገር አላገኘሁባቸውምና አሳልፌ ልሰጥህ አልችልም በሚል መልእክተኞቹም ያመጡትን ስጦታና መደለያ ይዛችሁ በሰላም ወደመጣችሁበት ወደ መካ መሄድ ትችላላችሁ በማለት ቁርጣቸውን ነግሮ እንዳሰናበታቸው በተለያዩ የአረብ ሀገራት ታሪክ ጸሐፍት ሰነዶች ውስጥ በግልጽ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ የአረብ ጸሐፊዎችና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሰለመው የአክሱም ንጉሥ «አልነጃሺ» ለነቢዩ መሀመድ ተከታዮች ባደረገው ውለታና እንክብካቤ የተነሳ ከነቢዩ ጋር ልዩ የሆነ ወዳጅነት መስረተው እንደነበርና ይህ መልካም የሆነ ግንኙነታቸውም አድጎ ይኸው የአክሱም ንጉሥ ነቢዩ መሀመድን ለመጎብኘት ሲጓዝ በመንገድ ላይ ማረፉንና በወቅቱም በዚህ መጥፎ አጋጣሚ ልባቸው የተነካ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሐዘናቸውን የገለጹበት ግጥም እሰከ አሁንም ድረስ በትውፊት ደረጃ በኢትዮጵያውያን ሙስሊም እንደሚታወስ ፕ/ር ሁሴን በጥናታቸው እንዲህ ያወሱታል፡-
ወዳንቱ ሲመጣ ወዳንቱ ሲሸሽ፣
ትግሬ ላይ የቀረው «አህመድ አል ነጋሽ/አልነጃሺ፡፡»
አልነጃሺ ከነቢዩ መሀመድ ጋር የወዳጅነት የደብዳቤ ልውውጥ ማድረጋቸውንና እስከአሁንም ድረስ ብዙዎችን እያከራከረ ስላለውና የአክሱም ንጉስ ሰልሟል የሚለው አገላለጽና በክሱማውያን ንጉስና በነቢዩ መሀመድ መካከል ተደርገዋል የተባሉት የወዳጅነት የደብዳቤ ልውውጦችም ከአፈ ታሪክ በዘለለ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የሌላቸውና እንዲሁም የአክሱም ንጉስ ስለመስለሙ የሚነገሩ አፈ ታሪኮችና በአንዳንድ ጸሐፍት ዘንድ በዋቢነት የሚቀርቡ ደብዳቤዎችም ሆኑ ክርክሮች በቂ የሆኑ ታሪካዊ መረጃዎች የሌላቸው መሆኑን ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ በጥናታቸው ሲገልጹም፡-
የሃይማኖት ጉዳይ ዋንኛ አጀንዳና የአክሱማውያን መለያ በሆነበት ሁኔታ የአክሱም ንጉሥና አክሱማውያን ሰልመው ቢሆን ኖሮ እንዴት ያን ሊገልጹ የሚችሉ በአርኪዮሎጂ ቁፋሮም ሆነ በሌሎች የታሪክ ድርሳናት የተቀመጡ ይህን እውነት ሊያረጋግጡና ፍንጭ ሊሰጡ የሚችሉ ጥቂት እንኳን መረጃዎች እንዴት ሊገኙ እንዳልቻሉ በመጠየቅ… አሳባቸውን ሲያጠናክሩም በቅድመ ክርስትና ዘመን የግሪክን አማልክት ሲያመልኩ የነበሩ አክሱማውያን ክርስትናን በተቀበሉ ማግስት በወርቅ ሳንቲሞቻቸው ላይ የክርስትና ሃይማኖት መቀበላቸውን በግልጽ በሚያረጋግጥ መልኩ በሳንቲሞቻቸው ላይ የነበሩትን ምልክቶች በመስቀል ቅርጽ መተካታቸውንና አክሱማውያን በዘመኑ ከነበሩት ነገሥታት ጋር ባደርጓቸው የደብዳቤ ልውውጦችም ሆነ በአውደ ግንባር ስለተጎናጸፉት ድሎቻቸው ወደ ክርስትና ሃይማኖት መግባታቸውን የሚያረጋግጡ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በግልጽ መጠቀሳቸውን በአክሱምና በአዶሊስ አካባቢ በሚገኙ በአርኪዮሎጂ ቁፋሮና የታሪክ ምርምር የተገኙ የድንጋይ ላይ ጹሑፎች በግልጽ እንደሚያስረዱና በትክክልም የአክሱም ንጉስ «አልነጃሺ» ወደ እስልምና ገብቶ ቢሆን ኖር ተመሳሳይ የሆኑ እንዴት እንዲህ ዓይነት ቢያንስ እንኳን ጥቂት መረጃዎች ሳይገኙ ቀሩ በማለት በአግራሞት ይጠይቃሉ…፡፡
በሂብሪው ዩኒቨርስቲ የመካከለኛው ምስራቅ እውቅ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤልሪችም Ethiopia and the Middle East በሚለው መጽሐፋቸው የፕሮፌሰር ሁሴን አህመድን አሳብ እንደሚጋሩ በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ ምናልባትም ይላሉ እነዚህ የመካከለኛው ምስራቅና የአረብ ሀገራት ታሪክ አጥኚዎች፣ ከፍተኛ ተመራማሪዎችና እንዲሁም የእስልምና ሃይማኖት ከአክሱምና አክሱማውያን ጋር ስለነበረው ታሪካዊ ግንኙነት ሰፋ ያለ ጥናት ያደረጉት ሁለቱ ምሁራን፡-
«በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እምነቱን ለማስፋፋትና ብዙዎችን ወደ እምነቱ ለመሳብ ሲሉ በጊዜው እጅግ ገናና እና ታላቅ ስልጣኔ የነበረውንና በግዛቱም በሰላም የተቀበላቸውን የአክሱምን ንጉሥ እስልምናን እንደተቀበለ አድርጎ ወሬ መስፋፋቱ በአረቢያን ምድር ሃይማኖቱ ሰፊ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲሉ የመጀመሪያዎቹ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የተፈጠረ መላና ዘዴ ሊሆን እንደሚችል እነዚሁ ምሁራን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡»
በእስከ አሁኑ አጠር ባለ መልኩ ዳሰሳ ያደረግንባቸው ታሪካዊ ሰነዶችም ሆኑ በዚህ ጹሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት የታሪክ ምሁራንና የመካከለኛው ምስራቅ ሃይማኖቶች ታሪክ አጥኚዎች ኢትዮጵያዊው ምሁር ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድና አይሁዳዊው ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤልሪች የአክሱም ንጉሥም ሆነ አክሱማውያን ስለመስለማቸው የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ሰነድም ሆነ ማረጋገጭ እንደሌለ ነው በጥናታቸው ግልጽ ያደረጉት፡፡ ታዲያ ታሪካዊው እውነታው ይህ ከሆነ በዘመናችን የሌለ ታሪክን በመፍጠርና ታሪክን በመበረዝና ተጋነው የሚነገሩት አክሱማውያንና እስልምናን በተመለከተ የሚነገሩ ታሪኮች ትክክለኛ ምንጫቸው ከየት ነው፣ ዓላማቸውስ ምን ሊሆን ይችላል ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡
እንዴትስ በእነዚህ ሁለት እምነቶች መካከል ለብዙዎች ምሳሌ እስኪሆን ድረስ የቆየውን አብሮ በሰላም ተከባብሮና ተዋዶ የመኖር ባሕል በሌለ ታሪክና ተጨባጭነት በሌለው ተረት ተረት ለመናድስ ለምን አስፈለገ፡፡ እንዴትስ እንዲህ በግብታዊነትና በማን አለብኝነት አንዳንድ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን የሚያራምዱ ሰዎች በእንዲህ ዓይነቱ ታሪክን የመበረዝና የማጣመም ዘመቻ ውስጥ ለመግባት ደፈሩ፡፡
በዓለማችን በሚገኙ አብዛኛው ሃይማኖቶች ዘንድ ያሉ አስተምህሮዎች ከሰዎች ሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር ተከባብረንና ተስማምተን እንድንኖር የሚሰብኩና የሚያተጉን ትምህርቶችና ትዕዛዛቶች የሚያስተላልፉ ሆነው ሳሉ በምን ምክንያት በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ የቆዩ የክርስትና የእስልምና ሃይማኖቶች በመካከላቸው ጠብና ግጭት ይፈጠር ዘንድ ሌተ ተቀን እየተጉ ያሉ ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን የሚሰብኩ ሰዎችን ወዴየት እየደሄዱ እንደሆነ ቆም ብለው እንዲያስቡ ልንነግራቸውና ተው ልንላቸው ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡
እንዴትስ ከአክሱማውያን በኋላ በሺህ ዘመናት የጊዜ ርዝማኔ የምንገኝ ትውልዶች እንደ አክሱማውያን አባቶቻችን የሌሎችን አሳብ፣ እምነትና ፍልስፍና ለማከበር ያልቻልንበትንና ልዩነቶቻችንን በኃይልና በጉልበት ለመፍታት በተጠንቀቅ የቆምንበት የታሪክ ዝቅጠት ውስጥ ልንገኝ እንደቻልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል… ‹‹ሀገር የጋራ ነው ሃይማኖት/እምነት ግን የልብ ምስጢር/ጉዳይ ነው›› የሚለው የቆየውና ዘመናትን የተሻገረው ብሂላችን የሚነግረን ተግባራዊው እውነታ ምን እንደሆነ ቆም ብለን ልናስተውል የሚገባን ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል… የዛሬን አበቃሁ… ሌሎች የምትሉን ነገር ካላችሁ እባካችሁ አሳባችሁን በፍቅር፣ በቅንነትና በጨዋ መንፈስ ጀባ በሉን አደራችሁን…!!!
ሰላም! ሻሎም!