አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ ጋዜጠኞች ፎቶግራፍ እንዳያነሡ ከለከለ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊታችን ሰኔ 30 እና ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. በሚያካሂደው የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የሕትመት ፎቶ ጋዜጠኞች አዳራሽ ተገኝተው ፎቶ ማንሣት እንደማይችሉ አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሪፖርተር በላከው ደብዳቤ ‹‹የሕትመት ሚዲያ ጋዜጠኞች የፎቶግራፍ ካሜራ ማስገባት አይችሉም፡፡ አስፈላጊውን ፎቶግራፍ ከቢሮአችን መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፤›› በማለት አዳራሽ ገብተው ፎቶ እንዳያነሱ ከልክሏል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ራሱ አስተምሮ ዕውቀት ያስጨበጣቸውን ፎቶ ጋዜጠኞች ወደ አዳራሽ እንዳይገቡ የከለከለበትን ምክንያት እንዲያብራሩልን የጠየቅናቸው የዩኒቨርሲቲው የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ነፃነት ይልማ እንደገለጹት፣ ከፀጥታ (ሴኩሪቲ) አንፃር ከምረቃው አዳራሽ ተማሪም፣ ወላጅም ሆነ የሕትመት ጋዜጠኛ የፎቶግራፍ ካሜራ ይዘው እንዳይገቡ ተወስኗል፡፡ ሁለተኛው ምክንያትም ሥነ ሥርዓቱን በፎቶግራፍ እንዲያስቀሩ ከተስማማቸው ድርጅቶች ጋር ሌላ ካሜራ እንዳይገባ ስምምነት ላይ በመድረሱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያስተላለፈውን ውሳኔ በሚመለከት ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ፎቶ ጋዜጠኞች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በሰጡት አስተያየት፣ ውሳኔው የተሳሳተና አግባብነት የሌለው መሆኑን ተናግረው፣ ‹‹ፎቶ ጋዜጠኛ ከሌሎቹ ታዳሚዎች ተለይቶ የፀጥታ ችግር ያስከትላል የሚለው እሳቤ እንዴት ሊመጣ እንደቻለ የሚያጠያይቅ ከመሆኑም በላይ፣ ራሱ አሠልጥኖ ለሙያው ብቁ ያደረጋቸውን ጋዜጠኞች መከልከሉ ተቋሙን የሚያስተች ነው፤›› ብለዋል፡፡

ብቁ ጋዜጠኞችን ለማፍራት ከሚሰጣቸው ኮርሶች አንዱ ፎቶ ጆርናሊዝም መሆኑ እየታወቀ፣ ለዓመታት አስተምሮ ያስመረቃቸውንና ብቃት ያላቸውን ፎቶ ጋዜጠኞች ‹‹አዳራሽ ገብታችሁ ታዳሚዎችን ፎቶ አታነሡም፤›› ብሎ መከልከሉ አስቂኝም አስገራሚም መሆኑን አባሉ ተናግረዋል፡፡ ማንነታቸውን ካልገለጻቸው ፎቶግራፍ አንሺዎች ጋር ውል ፈጽሞ፣ ‹‹እነሱ ያነሡትን ፎቶ ውሰዱ›› ማለቱ በተቋሙና በፎቶ አንሺዎቹ መካከል ያለው ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት መሆኑንም አክለዋል፡፡

በሙያው ሲያሠለጥናቸው ከነበሩት ፎቶ ጋዜጠኞችን የሚያሳዝንና የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር የሚያስተች መሆኑንም በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ፎቶ ጋዜጠኝነት ማለት በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በመገኘት ፎቶ አንሥቶ ለታሪክ የሚያስተላልፍና በሰነድ የሚያስቀምጥ እንጂ፣ በችርቻሮ ሥራ ላይ የሚሰለፍ ባለሙያ ማለት አይደለም፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ የሕትመት ፎቶ ጋዜጠኞች ለተቋማቸው ለሚያሳትሙት የሕትመት ውጤት ያላቸውን ጥበብ ተጠቅመው የሚወስዱትን ፎቶግራፍ፣ ከሚጽፉት ዜና ሐተታ ጋር በማዋሐድ ብቃታቸውን ለአንባብያን ማድረስ ሲገባቸው፣ ‹‹እኔ ያነሣሁትን ፎቶ ግዙኝ›› መባሉ ከ60 ዓመታት በላይ ካስቆጠረ ተቋም የማይጠበቅና ዕውቀት የማስገብየት አቅሙ ወዴት እያመራ መሆኑን እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡