ከአዲግራት እስከ ዛላንበሳ፤ ቁርጥራጭ ማስታወሻዎች (ክፍል አንድ)

(መሀመድ ሰልማን)

አዲግራት ነው ያለሁት፡፡ 35 ኪሎ ሜትሮችን ወደ ሰሜን ፈቀቅ ብል ኤርትራ ገባሁ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱ በማይገባኝ መልኩ ጥሎብኝ አሥመራን እናፍቃታለሁ፡፡ አይቻት ግን አላውቅም፡፡ “የማያውቁት አገር እንዴት ይናፍቃል?!” አትበሉኝ፡፡ ተረቱ የማይሰራበት ጊዜ ካለስ? ናፍቆቴን በከፊል ለማስታገስ ወደ ድንበር መጠጋት አማረኝ፡፡ ወደ ዛላንበሳ፡፡ ያን ከማሳካቴ በፊት አዲግራትን ለአጭር ቀናት መቃኘት ይኖርብኛል፡፡

የማትስቀው የተስፋዬ ካሳ አገር

ስለ አዲግራት “አዲግራት ሳንድስቶን” ከሚለው የሰባተኛ ክፍል የኅብረተሰብ ትምህርት የዘለለ እውቀት እንደሌለኝ እረዳለሁ፡፡ አሁን ያን አነስተኛ እውቀት ከቀሰምኩ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በኋላ በዚህች ዝምተኛ ከተማ እገኛለሁ፡፡ የተለየ ስሜት አላደረብኝም፡፡ አዲግራት ምኗ ያስደምማል?

ከጦርነቱ በኋላ አዲግራት ታመመች አሉ፣ ልክ ድሬዳዋ ከባቡሩ መቆም በኋላ እንደሆነችው፡፡ ነግቶ እስኪመሽ ታዛጋለች፡፡ እንደ ጅማ ፍጹም ባታንቀላፋም፤ እንደ አዋሳ ፍጹም ባትነቃም፤ አዲግራት በእኩለቀን እንቅልፍ ሸለብ እያደረገ የሚመልሳት ከተማ ሆነች፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች ቢያንስ ሙዚቃ በስማቸው ስለሚዜምላቸው ለጊዜውም ቢሆን ውብ መስለው በሰው አእምሮ የመሳል እድል አግኝተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ደሴና ጎንደርን የሚስተካከላቸው የለም፡፡ አዲግራት ግን ለዚህም አልታደለችም፡፡ ሟቹ እያሱ በርሄ አንድ የማስተዛዘኛ ሙዚቃ እንዳዜመላት ሰምቻለሁ፡፡ ከዚያ ውጭ ስለእርሷ ያዜመ ያለም አይመስለኝም፤ ምን ብሎስ ያዜማል?

አዲግራት ዜመኞችን አላፈራችም ማለት ግን አይደለም፡፡ “የሰሜኑ ቴዲ አፍሮ” እየተባለ የሚሞካሸው ሰለሞን ሃይለ ትውልዱ አዲግራት ነው፡፡ ከዓመት በፊት “ቆሪበለኹ” የተሰኘው አልበሙ በመላው ትግራይ ብሔራዊ መዝሙር እስኪመስል ከጫፍ ጫፍ ተደምጦለታል፡፡ የአዲስ አበባ ታክሲዎችም በዚህ ሙዚቃ እንደልብ ትርፍ ሰው ጭነዋል፡፡ አዲግራት ደግሞ የጆሮ ታምቡሯ እስኪበጠስ የልጇን ዜማ ደጋግማ ታስደምጣለች፡፡ ልጅ አይጠገብም! በዋና መንገዷ ዳርቻ የተሰየሙ የሙዚቃና የኤሌክትሮኒክስ ሱቆች የላጤ ልብስ ሳጥን የሚያካክል ድምጽ ማጉያዎችን ከደጃቸው አኑረው ይህንኑ የሰለሞን ሀይለን ጥኡም ሙዚቃ ነጋ ጠባ ለከተማዋ ያስተጋባሉ፡፡

በነገራችሁ ላይ በአዲግራት ቆይታዬ የቴዲ አፍሮ ፖለቲካዊ መልእክት አላቸው የሚባሉ ሙዚቃዎችን እንደልብ ሲደመጡ አስተውያለሁ፡፡ ለምሳሌ በከተማዋ እምብርት የሚገኘው “ኢትዮ ሙዚቃ ቤት” “በ 17 መርፌ በጠቀመው ቁምጣ፣ ለለውጥ ያጎፈረው ዙፋን ላይ ሲወጣ…” የሚለውን ዜማ ከፍ ባለ ድምፅ ደጋግሞ ሲያስደምጥ ለመስማት ችያለሁ፡፡ ከዓመታት በፊት ይመስለኛል ከአዲስ አበባ መቀሌ ስጓዝ በአውቶብስ ውስጥ ይኸው ሙዚቃ በመከፈቱ በተጓዦች መሀል ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ በመጨረሻም ሾፌሩ ሙዚቃውን እንዲዘጋው ተገዶ አንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ፖለቲካዊ መቻቻል ነግሶ ይሁን የፖለቲካ ግለቱ ተቀዛቀዞ ብቻ ቴዲ አፍሮ በአዲግራት እንደልብ ይፈነጫል፡፡ እርሱ መድረክ ላይ ለመዝፈን ሳንሱር የሚያደርጋቸው ሙዚቃዎች በአዲግራት አደባባይ እንደልብ እንደሚከፈቱ ቴዲን የምታውቁ ሹክ በሉት፡፡

አዲግራት ሙሉ በሙሉ በተራራ መከበቧ፣ ተስማሚ የአየር ንብረት መጎናፀፏ፣ በበለስና ብርቱካን ምርት መታወቋ፣ በክፉ ከመነሳት ያዳኗት ውስን ውበቶች ናቸው፡፡ በተለይ የአዲግራት ጉንዳጉንዱ ብርቱኳን ጣእሙ ዘላለማዊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ የመድኀኒት ፋብሪካ የሚባለውና “የትእምእት” (ኤፈርት) እህት ኩባንያ የኾነው “አዲስ መድኀኒት ፋብሪካ” ሌላው የአዲግራት ኩራት ነው፡፡ ሻእቢያ በአየር ሊደበድበው ከአንዴም ሁለቴ ሞክሮ ስቶታል፡፡ ብዙዎቹን የከተማዋን ነዋሪዎች ከሥራ አጥነት የታገደው ይኸው ፋብሪካ ነው፡፡
ወልዋሎ

‘ለአዲሳባ “ሸገር” የሚል የዳቦ ስም ከሰጠን ለአዲግራት ምን እንላለን?’ የሚል የሚኒስትሪ ፈተና ጥያቄ ቢመጣ ስንት ተማሪ እንደሚመልሰው አላውቅም። “ወልዋሎ” ካሉ መልሱን አግኝተውታል፡፡ ይህ ስም በከተማዋ ሁሉም ነገር ላይ ተፅፎ ይታያል፡፡ “ወልዋሎ ፀጉር ቤት”፣”ወልዋሎ እንዳ-ባኒ” (ዳቦ ቤት ማለት ነው)፣ “ወልዋሎ ሙዚቃ ቤት”፣ “ወልዋሎ ጥህሎ ቤት”… “ወልዋሎ ከረንቡላ”…የወልዋሎ ነገር ማቆምያ የለውም፡፡ ከ ወልዋሎ የተረፉት አገልግሎት መስጫዎች ደግሞ “አግኣዚ” በሚል ነው የሚጠሩት፡፡ “አግአዚ” በአዲግራት ከተማ ከትምህርት ቤት እስከ ቡና ቤት ያለ ማንኛውም ድርጅት ሊጠራበት የሚችል ስም ነው፡፡ አግአዚ ቡቲክ፣አግአዚ ኢንተርኔት፣ አግኣዚ ትምህርት ቤት፣አግአዚ መሸታ ቤት…ወዘተ

በከተማዋ የሚገኘው ቁጥር አንድ የምሽት ክለብ “ፍሪ -ዞን” ይባላል፡፡ ለመዲናችን አዲስ አበባ እንኳ የሚመጥን ዘመናዊ ክለብ ነበር፡፡ ሆኖም ክለቡ ከከተማዋ በብዙ እርምጃ በመቅደሙ በገበያ እጦት ተዘግቷል፡፡ የዛሬን አያድርገውና አዲግራት የሞቀች-ያበደች፣ አሸሼ ገዳሜ የሚባልባት ከተማ ነበረች አሉ፡፡ የድንበር ጦርነት ጉሮሮዋን ዘጋው፡፡ ብዙዎቹ ነዋሪዎቿም ተሰደዱ፣ ወደ መቀሌ፣ወደ አዲሳባ፡፡
አዲግራት ንጉራጌ

ጉራጌዎችና አዲግራቶች በኢትዮጵያ የሰሜንና የደቡብ ዋልታ ጫፍ የሚገኙ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ሕይወታቸው ግን እንደመገኛቸው አይራራቅም፡፡ “አንድ ትግሬ እሳት የላሰ ነጋዴ ከሆነ ትውልዱ አዲግራት እንደሆነ ትጠረጥራለህ” ሲሉ ነግረውኛል። “በአብዛኛው ግምትህ ልክ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡” እሱ እኮ “ወዲ አዲግራት እዩ” ከተባለ በቢዝነስ እየገሰገሰ እንደሆነ ይገባኻል፡፡ ወልዋሎዎች “የትግሬ ጉራጌዎች” የሚባሉትም ለዚሁ ነው፡፡ አዲሳባ “ሃያ ሁለት” በሚባለው ሰፈር ዞር ዞር ስትል የሚያፈጡብህ ብዙዎቹ መለሎ ሕንፃዎች በትግራይ ተወላጆች የተያዙ ናቸው – ከትግራይም በአዲግራቶች፡፡ የሳትኮን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ተኽላይ የአዲግራትን አፈር ፈጭተው ነው ያደጉት፡፡

በቀድሞ ጊዜ ለኤርትራ ንግድ እንቅስቃሴ የደም ዝውውር መሆን የቻሉትም አዲግራቶች ነበሩ ይባላል፡፡ ኤርትራዎች አዲግራቶችን “አጋመ” ይሏቸዋል፡፡ ስድብ መሆኑ ነው አሉ፡፡ አንድን ጉራጌ “ጉራጌ” ብሎ እንደመሳደብ፡፡ አንድ አዲግራታዊ የ“አጋመ ልጅ ነኝ” ሲልህ ግን በታላቅ ኩራት ነው፡፡ በአዲግራት ምድር “አጋመ” የሚለው ቃል የኩራት ምንጭ ነው፡፡ “ጓል አጋሜ” የሚል ጽሑፍ ለጥፈው የሚንቀሳቀሱ ባጃጆችን በከተማዋ በብዛት አይቻለሁ፡፡ “የአጋሜ ልጅ! የአጋመ ቆንጆ!” እንደማለት ነው፡፡
ጉራጌዎችና አዲግራቶችን የሚያመሳስላቸው ጠንካራ የሥራ መንፈስ ብቻ አይደለም፡፡ የመስቀል በዓልም የጋራ በዓላቸው ነው፡፡አዲግራቶች ልክ እንደ ቤተ ጉራጌዎች ከበዓላት ሁሉ ለመስቀል በዓል ልዩ ግምት ይሰጣሉ፡፡ አዲግራቶች ዓመቱን ሙሉ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ታች ሲሉ ይከርሙና ልክ የመስቀል በዓል ሲደርስ ጓዛቸውን ሸክፈው ወደ አገር ቤት-ከአገርቤትም ወደ አዲግራት ያተማሉ፡፡ ይህ የማይዛነፍ ዓመታዊ መርሀ-ግብራቸው ነው፡፡ ባሳለፍነው ዓመት በሺህ የሚቆጠሩ ትግሬዎች በአዲግራት ደማቅ የመስቀል አከባበር ማድረጋቸው በአገሪቱ ቴሌቪዥን ጭምር ተዘግቧል፡፡

የማትስቀው የተስፋዬ ካሳ አገር

አዲግራት ከግዙፍ ፖለቲከኞች ባሻገር የቀድሞውን ኮሞዲያን ተስፋዬ ካሳን እንዳፈራች ሲነገረኝ ለማመን አንገራገርኩ፡፡ ተስፋዬ ካሳ አዲግራት ተወልዶ፣ አዲግራት አድጎ፣ አዲግራት ጨርቆስ ቤተክርስቲያን አገልግሎ ነው ወደ አዲስ አበባ የሄደው፡፡ አዲስ አበባም “ግቢ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን” አገልግሏል፡፡ ይህን መረጃ ያገኘሁት ተስፋዬ አብሮ አደጌ ነው ከሚል አንድ የአዲግራት ጎልማሳ ነዋሪ ነው፡፡ ይኸው ነዋሪ የነተስፋዬ ካሳ ቤት “ሜዳ አጋሜ” በሚባለው ገበያ /እዳጋ/ ወዲያ ማዶ ነው ሲል በጥቆማ አሳይቶኛል ፡፡ ከተማዋ ግን የምትስቅ አትመስልም፤ በልጇ ተስፋዬ ካሳ ቀልዶችም ቢሆን፡፡

ሓፊሶሞም

የኤርትራ ጦርነት አዲግራትን ያዳከማት በንግድ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ልጆቿን ቀርጥፎ በልቶባታል፡፡ ይህ የድንበር ጦርነት ለአዲግራትና አካባቢዋ የዘውትር ጭንቅ የዘውትር ጣር ነበር፡፡ ከጦርነቱ ቀጠና በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ለተገኘቸው አዲግራት እያንዳንዱ ምሽት የጭንቅ ሌት ሆኖ አልፏል፡፡
መንግሥት በአዲግራትና አካባቢዋ የሚገኙ የትግራይ ቀበሌዎችን እያሰሰ፣ ወጣት እያደነ ለጦርነት መልምሏል፤ ለዚያውም በግዳጅ፡፡ በትግራይ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ገብቶ ሰፊ የማሳመን ሥራ ሠርቷል፡፡ በየክፍሉ እየዞረ ተማሪዎችን ለውትድርና መዝግቧል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ መልማዮች “እናንተ መዋጋት አይጠበቅባችሁም፣ ኮምፒውተር ላይ ቁጭ ብላችሁ ነው የምታዋጉት፤ የተማረ ሰው ስላስፈለገን ነው የምናስቸግራችሁ” እያሉ ያባብሉ ነበር አሉ፡፡

በወቅቱ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ የአዲግራት ወዳጄ እንዳጫወተኝ ከሆነ ይህ ማባበል የኋላ ኋላ ብዙም አዋጪ ሆኖ ስላልተገኘ ወደ ግዳጅ ምልመላ ተገብቷል፡፡ “የአዲሳባ ሕዝብ መጥቶ ሊዋጋላችሁ ትጠብቃላችሁ እንዴ?!” እንባል ነበር ይላል ይኸው ወጣት፡፡ ጦርነቱ እየተራዘመ ሲመጣ ከአንድ ቤተሰብ ቢያንስ አንድ ልጅ መገበር ግዴታ ተደረገ፡፡ ይህን ያላደረጉ ቤተሰቦችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በድንበር ጦርነቱ ወቅት ጥሩ ገቢ የነበራቸው ወጣቶች ልጆቻቸውን በብዛት ወደ አዲስ አበባ ማሸሽ ችለዋል፡፡ የቀበሌ ሹማምንት ሕዝቡ ልጆቹን ወደ ከተሞች እያሸሸ እንደሆነ በመረዳታቸው በመናኸሪያዎች አካባቢ ጥበቃ እንዲኖር ተደርጎ ነበር፡፡ ቆሸሽ ያለ ልብስ የለበሱ ወጣቶች ከጎዳና ታፍሰዋል፡፡ “ሓፊሶሞም!” ከደርግ መውደቅ በኋላ ዳግም ዝነኛ ቃል ሆነች፡፡

የአዲግራቱ ወዳጄ የዚያን ጊዜ ብዙዎቹ ጓደኞቹ እንዳለቁ ነግሮኛል፤ “የተረፉት ግን አሁን መከላከያ ውስጥ ጥሩ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡” ይላል፡፡ ይኸው የአዲግራት ወዳጄ እንዳወራኝ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ ለሟች ቤተሰቦች መርዶ ማርዳት ሲጀመር አዲግራትና አጎራባች የገጠር ሰፈሮቿ ወደ ትልቅ ድንኳንነት ተቀየሩ፡፡ በእያንዳንዱ የሰፈር ጎዳና የለቅሶ ድንኳን መትከል ግድ ነበር፡፡ የድንኳን ተራ ያልደረሳቸው ሜዳ ላይ ለቅሶ ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡ እስካሁንም ትርጉሙ ላልገባን ጦርነት አዲግራትና ዙርያ ገብ የገጠር ቀበሌዎቿ ከሌሎች ከተሞች በበለጠ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡

ቆንጆዎቹ እናቶች

እንደ አዲግራት ብዙ የኔ ቢጤዎች ያየሁበት ከተማ ትዝ አይለኝም፡፡ ፒያሳ በሚባለው የከተማዋ እንብርት “ወልዋሎ ካፌ” በረንዳ ላይ ተሰይሚያለሁ፡፡ ማኪያቶ ፉት እያልኩ ለአመል ያክል ያያዝኩትን የጉዞ መጽሐፍ እያገላበጥኩ፤ በአንድ ዐይኔ ከተማዋን እታዘባለሁ። ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል በዚህ ሁኔታ ተቀመጥኩ፡፡ በቆይታዬ ምፅዋት የሚጠይቁን ለማኞች ቁጥር በአእምሮዬ ለማስላት ሞከርኩ፡፡ ከሰላሳ ይልቃሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል እጅግ የበዙቱ እድሜያቸው የገፉ የትግራይ እናቶች ናቸው፡፡ “ይርደአኹም” የምትለዋን ቁልፍ ቃል ያላወቀ እንግዳ በአያት የኔ ቢጤዎች ያልተቋረጠ ተማፅኖ ስሜቱ ሊረበሽ ይችላል፡፡ መላው ትግራይ እንዲሁ ነው፡፡

በትግራይ ከተሞች በተዘዋወርኩባቸው ግዝያት ሁሉ ቅስም የሚሰብር፣ ስሜት የሚረብሽ ክስተት የሚገጥመኝ ትግራዊ እናቶችን ስመለከት ነው፡፡ በሚሞቀው ፈገግታቸው ውስጥ መከራ ይታያል፡፡ በቆንጆ ፊታቸው ግንባር ላይ ረዥዥም የእድሜ መስመሮች ይጎላሉ፡፡ መስመሮቹ የእድሜ መስመር ብቻ አይመሰሉም፡፡ ዘርፈ ብዙ የዘመናት ችግራቸውን ያሳብቃሉ፡፡ በክልሉ ለዓመታት የተካሄዱ ጦርነቶቹ ልጆቻቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ተስፋቸውን ነጥቀዋቸዋል፡፡ ብዙ ጦርነቶች፣ ብዙ የፍትሕ እጦቶች፣ ብዙ ረሀቦች፣ ብዙ በደሎች የማያልቁ የሚመስሉ፣ እስከአሁንም ያላለቁ፡፡

“ወልዋሎ ካፌ” ደጅ ላይ መሰየሜን አትርሱ፡፡ ከለማኞቹ ጎን ለጎን ከዋናው አስፋልት ላይ ጥቂት የአእምሮ ህመምተኞች ይታዩኛል፡፡ እኔ ከተቀመጥኩባት “ወልዋሎ ካፌ” ትይዩ የከተማዋ ዝነኛ “እብድ” በእንጨት የሰራውን የጦር መሳርያ እያቀባበለ በመተኮሰ ራሱን ያዝናናል፡፡ ስለዚህ “እብድ” ብዙ ማወቅ ፈለኩኝ፡፡ ወታደር እንደነበረና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መካፈሉ ተነገረኝ፡፡ ከዚያ በላይ ስለሱ የሚያውቅ አላገኘሁም፡፡ ወልዋሎ ካፌን ለመልቀቅ ሂሳብ ስከፍል “እብዱ” የእንጨት ጠመንጃውን ወደ እኔ አቀባብሎ እየተኮሰ ነበር።

ወዲ ገሰሰ

ወዲ ገሰሰ አለማያ ዩኒቨርሲቲ አብሮኝ የተማረ ወጣት ነው፡፡ የአራት ዓመት የዲግሪ ትምህርቱን ለመጨረስ 7 ዓመት ፈጅቶበት ነበር፡፡ዩኒቨርሲቲ እንደገባ የአሉላ አባነጋ የቅርብ ዘመድ እንደሆነ በማስወራቱ ስሙ በዩኒቨርሲቲው ገነነ፡፡ ሁለተኛ ዓመት ስንደርስ ደግሞ “አፄ ዮሃንስ አራተኛ የእናቴ የቅርብ ዘመድ ናቸው” ሲል ዘር ቆጥሮ፣ ፍሬሽማን ላይ የወሰደውን የኢትዮጵያን ታሪክ አጣቅሶ ተሟገተ፡፡ በዚህም የብዙ ተማሪዎች መጠቋቆምያ ለመሆን በቃ፡፡ ከተማሪ ዐይን ለመሰወር ግን ሱስ ውስጥ መደበቅ ነበረበት፡፡ወዲ ገሰሰ በከፍተኛ የጫትና የአደገኛ እፅ ሱስ ከመጠቃቱ በፊት ይፈጥራቸው በነበሩ ቀልዶቹ ይታወቅ ነበር፡፡ በእርሱ ስም የተመዘገበች ቀልድ ዛሬም ድረስ አትረሳም፡፡ ላካፍላችሁ፡፡

በአለማያ ዩኒቨርሲቲ አብዝተው ስለ አሳ ሀብትና ስለ አለማያ ሀይቅ ይጨነቁ የነበሩ ዶክተር ነበሩ፡፡ ዶክተር ብሩክ ይባላሉ፡፡ ሌሊት ሌሊት እየተነሡ በአለማያ ሀይቅ ላይ ምርምር ያደርጉ ነበር፡፡ ዘወትር ለአሳ ሀብት እንደተጨነቁ ነው የኖሩት፡፡ ወዲ ገሰሰ ታድያ አንድ ወቅት ላይ በአገሩ የአዲግራት ልጆች “ፈተና እየደረሰ ነው፤ አጥና፤ ኋላ ይቆጭኻል” የሚል ምክር ሲለገሰው እንዲህ አለ አሉ፡፡ “who cares about the dead fish except Dr. Brook.”

ዶክተር ብሩክ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ምክትል ዲን ናቸው፡፡ ወዲ ገሰሰ ግን በአዲግራት ከተማ ቪዲዮ ቤት ቆሞ ፊልም ይተረጉማል፡፡ ዲግሪ ይዘህ እንዴት ይህን ስራ ትሰራለህ አልኩት፡፡ “who cares about the dead fish except Dr. Brook” አለኝ፣ ሲጋራውን ፊቴ ላይ እያቦነነ፡፡ ወዲ ገሰሰ ይህንን አባባሉን እስከዛሬም አልተወውም ማለት ነው፡፡ ወደ “እብደት” ሰፈር እያመራ ለመሆኑ ቅንጣት ታክል አልተጠራጠርኩም፡፡ who cares about….!

የእነ አርከበ ቤት

አዲግራት “ፒያሳ” እያለች የምትጠራው ሰፈሯ በብዙ ለማኞች፣ በብዙ ሙዚቃ ቤቶችና በጥቂት የአእምሮ ህመምተኞች የተሞላ ነው፡፡ በዚህ ሰፈር አንድ ባለአንድ ፎቅ ቀይ ቡኒ ሕንፃ ይታያል፡፡ የቀድሞ የ “አግኣዚ ትምህርት ቤት” ተማሪዎች “አልሙናይ ኅብረት ጽ/ቤት” ነው፡፡ በቀድሞው ዘመን ትግራይ ውስጥ የትምህርት እድል ለማግኘት ሦስት ቦታዎች ብቻ ነበሩ፡፡ አቶ መለስ የተማሩበት የአድዋው ንግሥተ ሳባ፣ እያሱ በርሄ የተማረበት የመቀሌው አፄ ዮሃንስ እና የአዲግራቱ አግኣዚ ናቸው፡፡ የአዲግራቱ “አግኣዚ ትምህርት ቤት” የአሁኖቹን ትላልቅ ባለስልጣናት አስተምሯል፡፡ አቶ ስዩም መስፍን፣ ጄነራል ሀየሎም አርአያ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም /ያልተረጋገጠ/፣ አቶ ታደሰ ሀይለ፣ አቶ አርከበ አቁባይ ወዘተ የዚሁ ትምህርት ቤት ፍሬዎች ናቸው፡፡

የተወዳጁን የቀድሞ የአዲሳባ ከንቲባ የአርከበ እቁባይን ቤት እናሳይህ ሲሉኝ በዙርያው አርከበ ሱቆች አይጠፉም ብዬ ለራሴ ቀለድኩ፡፡ብዙም አልተሳሳትኩም፡፡ የነአርከበ ቤት በዋናው የአዲግራት መንገድ በስተቀኝ “እስላም መቃብር” ፊት ለፊት ይገኛል፡፡ 500ካሬ ላይ ያረፈ በድንጋይ ርብራብ የታጠረ የገጠር ቤት ነው፡፡ ዙርያውን ተሸንሽኖ ለሱቆች ተከራይቷል፡፡ “ጂኤም ፀጉር ቤት”፣ “ፍሰሀ ክሊኒክ”፣ “ቲዜድ መስታወት ስራ”፣ እና አንድ ስም ያልተሰጠው ፑል ቤት የነአርከበን ቤት ተከራይተው ይነግዱበታል፡፡ የአቶ አርከበ ወንድም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቤቱን ይቆጣጠር እንደነበረ ተነግሮኛል፡፡ አቶ አርከበ ልምድ የቀሰሙት ከቤታቸው ኖሯል፡፡

እንደ መቀሌ ሁሉ በአዲግራትም የአቶ መለስ ምስል ያለበትን ነገር መመልከት ቀላል ነው። ብዙ ነዋሪዎች የርሳቸው ምስል ያለበትን ቲሸርት ለብሰው ይታያሉ፤ ምፅዋት ጠያቂዎችን ጨምሮ፡፡ ባጃጆች ላይ “ረዥም እድሜ ለአቶ መለስ” የሚል ጽሑፍ ተመልክቻለሁ፡፡ ፀጉር ቤት ውስጥ የፀጉር ቁርጥ አይነቶችን በሚያሳዩ ፖስተሮች መሀል የአቶ መለስ ግርማ ሞገስ ያለው ፎቶ ተሰቅሎ አስተውያለሁ፡፡

እነአርከበ ቤት ከፊሉ ለፑል ቤት እንደተከራየ ነግርያችሁ ነበር፡፡ በዚሁ ፑል ቤት ጎራ ብዬ ከአዲግራት ልጆች ጋር ፑል በገጠምኩ ጊዜ ያየሁትም ይህንኑ ነው፡፡ በፑል ቤቱ ግድግዳ ዙርያ ብዙ የምእራቡ አለም የራፕና የሂፕሆፕ ዜመኞች ፎቶ ተለጥፏል፡፡ እነ አር ኬሊ፣ብሪትኒ ስፒርስ፣ 50ሴንት፣ ጂ ዩኒት፣ ጃኔት ጃክሰን፣ ጄኔፈር ሎፔዝ፣ ሻኪራ፣ ቢዮንሴ፣ ጄይዚ ወዘተ ሰውነታቸውን ተገላልጠው የተነሷቸው ባለቀለም ፎቶዎች ተሰቅለዋል፡፡ በእነዚህ መሀል የአቶ መለስ ፎቶ ሰርጎ ገብቷል፡፡ ይህ የአቶ መለስ ፎቶ የሚገኘው “ማርያም ጠብቂኝ” የሚል የቅድስት ማርያም ፎቶ ስር መሆኑ ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ አቶ መለስ ካፖርት ለብሰው ሞባይል እያናገሩ ይታያሉ፡፡ “እመቤቴ ጠብቂልኝ” የሚል ትርጉም እንዲኖረው ተደርጎ የተዘጋጀ ነው? የአቶ መለስን ፎቶ ከቅድስት ማርያም ምስል ስር የማስቀመጡን ነገር ኢንተርኔት ለመጠቀም በገባሁባቸው ሁለት ካፌዎች ውስጥም ተመልክቻለሁ፡፡ የተሰጠኝ ማብራርያ እኔው እንደገመትኩት አይነት ነው፡፡ “እመቤቴ እንድትጠብቅልን ነው” ብላኛለች አንዲት በጽሕፈት ሥራ የምትተዳደር ሴት። ነገሩ ሰምና ወርቅ ይሁን አይሁን ግን ለማረጋገጥ አልችልም።

የሃይማኖቶች ፍቅር

አዲግራት ካቶሊክ ካቴድራል

በኢትዮጵያ በዕድሜ አንጋፋው የካቶሊክ ካቴድራል የሚገኘው በአዲግራት ነው፡፡ ለከተማዋ ግርማ ሞገስ ሆኗታል፡፡ አባ ወልደ ሥላሴ ተስፋዬ ይባላሉ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ፡፡ በአክብሮት ተቀብለው አስተናገዱኝ፡፡ ወደ መቅደስ ይዘውኝ ገብተው የሎሬት ሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ድንቅ ስእል አስጎበኙኝ፡፡ ስእሉ በመቅደሱ የፊት ለፊት ግድግዳ በትልቁ ተዘርግቶ ይታያል፡፡/ፎቶውን ይመልከቱ/ አርቲስት አፈወርቅ ይህንን ስእል የሰራው በ1967 ሲሆን ግማሽ ብር ብቻ ተከፍሎት ቀሪውን በበጎ ፍቃደኝነት ነው የሰራው፡፡

አንጋፋው ካቴድራል በ1947 ነው ግንባታው የተጀመረው፤ የሚገርመው ካቴድራሉ በ1960 ሲመረቅ የእስልምናና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በግ አርደው ደግሰዋል፡፡ ያኔ የተጀመረው የሃይማኖቶቹ ወንድማማችነት ዛሬ አድጎና ተመንድጎ በሚያስገርም ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

አዲግራት ጎልጎታ ቤተ ክርስቲያን (ኦርቶዶክስ)

ለምሳሌ አባ ወልደ ሥላሴ ቢሮ ስትገቡ በወርቃማ ቀለም የተጻፈ የምስክር ወረቀት ታያላችሁ፡፡ “አላሁ አክበር” የሚል ቃል በጉልህ ተጽፎበታል፡፡ ትገረማላችሁ፡፡ የአዲግራት ሙስሊሞች አንዋር መስጊድን ሲገነቡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የገንዘብ መዋጮ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረጓ የተሰጣት የምስክር ወረቀት ነው፡፡

የአዲግራት አንዋር መስጊድ

አዲግራት የሚገኘውን የጎልጎታ መድኀኔዓለም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ማን ያሠራው ይመስላችኋል? ከሙስሊምና ከካቶሊክ አማኞች የተውጣጣ ኮሚቴ፡፡ ይህ በዐይኔ ያየሁት ነገር ነው፡፡ “መድኅን ለድኅነት ሕይወት” የተሰኘ ማኅበር በጋራ መሥርተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ አቅም ያጡትን ይደግፋሉ፡፡ ቤተ እምነቶችን ያስገነባሉ፡፡ የተቸገሩ ይጦራሉ፡፡ እኔ በጎበኘኋቻው ጊዜ የደርግ ተጎጂ ቤተሰቦችን በይቅርታው ጉዳይ በማነጋገር ሥራ ተጠምደው ነበር፡፡ አባ ወልደ ሥላሴ ጠረጴዛቸው ላይ አንድ ደብዳቤ አንስተው አሳዩኝ፡፡ ያን ቀን ሙስሊሞች ለምሳ ግበዣ እርሳቸው እንዲገኙላቸው የላኩት ደብዳቤ ነው፡፡

አባ ወልደ ሥላሴ በአዲግራት ካቴድራል ከሎሬት አፈወርቅ ስእል ባሻገር በትንሽ የመስታወት ብልቃጥ የተቀመጠ ነገር አሳዩኝ፡፡ለቤተክርስቲያኑ በረከት ሲባል ከማዘር ቴሬሳ ሰውነት ተወስዶ የተቀመጠ የስጋ ቁራጭ ነበር፡፡ /ፎቶውን ይመልከቱ/ በብዙ ሀገራት ባሉ ካፌድራሎች ይህ የማዘር ቴሬዛ የስጋ ቡራኬ ይገኛል/

ማዘር ቴራዛ

ማዘር ቴሬሳ ሶስት ጊዜ ኢትዮጵያን እንደጎበኙ ተነግሮኛል፡፡ ከዓመት በፊት የመቀሌ ደንቦስኮ የካቶሊክ ማእከልን ስጎበኝ ያገኘኃቸው ህንዳዊት መነኩሲት እንደነገሩኝ ከሆነ ማዘር ቴሬሳ ጋር ሆነው መንግሥቱ ኀ/ማርያምን ጎብኝተውታል፡፡ በሕዝቦቹ ላይ በደል እንዳያደርስ በግልጽ ተማጽነውትም ነበር፡፡ የቅድስት ማርያምን ምስልም በስጦታ መልክ ሲያበረክቱለት “ኀይለማርያም የሚለው የስምህ ትርጉም ‘የማርያም ኃይል’ ማለት ስለሆነ ነው ይህንን የምሰጥህ” ብለውት ነበር፡፡ “መንግሥቱም በስጦታው እጅግ ተደሰተ” ብለውኛል፡፡

አዲግራት መሞካሸት ካለባት በሃይማኖት ተከታዮቿ መልካም የእርስ በርስ ቁርኝት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሙስሊሞች ቤተክርስቲያን ሲሰራ እገዛ አድርገዋል፡፡ ካቶሊኮችና ኦርቶዶክሶች የማህሌት ቅዳሴን ተራ በተራ አንዱ የአንደኛው ቤተ መቅደስ በመሄድ ያካሄዳሉ፡፡ መስጊድ በማሰራት ፍቅራቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህንንም በአዲግራት ቆይታዬ እውነት መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡
አባ ወልደ ሥላሴን ተሰናብቼ ስወጣ “ኢትዮጵያን ወደፊት የሃይማኖት ግጭት ያሰጋታልን?” ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ እያቅማሙ “ይመስለኛል!” ካሉ በኋላ በዝምታ ተዋጡ፡፡

ወደ ዛላንበሳ

የአዲግራቱ ወያላ “ዛላንበሳ! ዛላንበሳ! አሀደ ሰብ ዛላንበሳ!” እያለ ጮኾ ተጣራ፡፡ ስጠጋው ጊዜ “እተው እተው…ቀልጥፍ” አለኝ፡፡ ተሳፈርኩኝ፡፡ ከአዲግራት ወደ ዛላንበሳ ለመሄድ የ10 ብር ታክሲ መያዝ በቂ ነው፡፡ ሚኒባሱ እኔ ከተቀመጥኩበት የኋላ ወንበር ስር ኩልል ያለ ድምፅ የሚያወጣ ሰፒከር ተገጥሞለታል፡፡ በስፒከሩ ኤርትራዊው አብረሃም አፈወርቂ ለብቻው ነግሶበታል፣ ኢሳያስ አፈወርቂ በአሥመራ ብቻቸውን እንደነገሡት አይነት፡፡ “ሰማይ፣ ፊቅረይ፣ ፊሺክ በሊ፣ ሚስጥር ፊቅሪ፣ ሀደራ፣ ሺኮር ….” የተሰኙትን ዜማዎች እያከታተለ ይጫወታል፡፡

የታክሲው መጋረጃ “ይከፈት-አይከፈት” በሚለው ክርክር ውስጥ ከጎኔ ከተቀመጠው ጎልማሳ ሰው ጋር ተግባባሁ፡፡ በትግርኛ የተጀመረው ትውውቃችን እኔ ቋንቋው ላይ ባሳየሁት መደነቃቀፍ ወደ አማርኛ ተሸጋገረልኝ፡፡ ጎልማሳው ሰው ጥርት ያለ አማርኛ ይናገራል፡፡ በጥያቄ አጣደፍኩት፡፡ በግራና ቀኝ የምናልፋቸውን ተራራዎች እያመለከተ ስምና ውለታቸውን ተረከልኝ፡፡ በክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” ቅፆች ብቻ አውቀው የነበረውን የአሲምባ ተራራን በስተቀኛችን በርቀት አመላከተኝ፡፡ የአይጋ ተራራዎችንም እንዲሁ፡፡ ከኤርትራ ጋር ያደረግነውን ውጊያ አነሳሁበት፡፡
“እንደሚባለው ብዙ ሰው ሞቷል እንዴ?” ፈራ ተባ እያልኩ ጠየኩ።

[ቀጣዩን ክፍል ነገ ይጠብቁ]