አንድነት ከደራሼና ከደቡብ ኦሞ ህዝብ ጋር በትግሉ ዙሪያ ተመካከረ
‹‹ኢህአዴግ በቆሎ፣ ሙዝና ቡና መትከል የጀመራችሁት እኔ ከመጣሁ በሁዋላ ነው ሊለን ይፈልጋል›
ተሳታፊዎች
ወደ ደቡብ ክልል በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ዘመቻ ያደረገው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም በደራሼ ልዩ ወረዳ ጊዶሌ እና ሰኔ 24 ቀን 2004 ዓ.ም ደግሞ በደቡብ ኦሞ ጅንካ ከተማ ከህዝቡ ጋር በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር ማድረጉን የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ለፍኖተ-ነፃነት አስታወቀ፡፡
ፓርቲው በመላ ኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ ህዝቡን ማደራጀት፤ ማንቃት፤ በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መመካከር ዋና አላማው ነው የሚለው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ወደ ደቡብ የሀገራችን ክፍል የተንቀሳቀሱት የልዑካን አባላት በፓርቲው ም/ሊቀመንበር በተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉና በፓርቲው ዋና ጸሀፊ አቶ አስራት ጣሴ የተመራ ሲሆን የደቡብ ቀጠና ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፤ የደቡብ ቀጠና አደራጅ አቶ ግርማ አማረና ጋዜጠኛ ዳንኤል ተፈራ ወደ ደቡብ ማምራታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ወደ ደቡብ የተንቀሳቀሰው የልኡካን ቡድን በተለይ በወላይታ ሶዶና በአርባ ምንጭ ካሉ የአንድነት አመራሮች ጋር አጭር ውይይትም አድርጎአል፡፡ በተያዘው መርሃ ግብር መሰረትም ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም ወደ ደራሼ ልዩ ወረዳ ጊዶሌ በማምራት ፒያሳ በሚባለው አደባባይ ላይ ከከተማውና አካባቢው ከመጡ ታዳሚዎች ጋር ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ ውይይት አድርጎአል፡፡
በዕለቱም በጊዶሌ የአንድነት ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ ዳቲኮ ታዬ መንገሻ በደራሼ ፓርቲው ያከናወናቸውን ጠንካራ ጎኖችና ድክመት ነበሩ ያሉዋቸውን የሚዘረዝር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ የመክፈቻ ንግግር አሰምተዋል፡፡ አቶ ግርማ በንግግራቸውም ‹‹የኑሮ ውድነቱ መባባስና የህዝቡ የመኖር ህልውና ፈተና ውስጥ እንደገባ ጠቅሰው ይህን መባባስ የፈጠረው የነፃነት እጦት ነው›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹በፍርሃት የተወጠረና ነፃነት የሌለው ህዝብ አምራች ሊሆን አይችልም ስለዚህ ነፃነታችሁን ለማስመለስ በሰላማዊ ትግል አምባገነን የሆነውን ስርዓት መለወጥ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡
አቶ አስራ ጣሴ በበኩላቸው ‹‹በማሰርና በማንገላታት ትግሉን ማቆም አይቻልም፡፡ መብታችሁን ማስከበር የምትችሉት እናንተ ራሳችሁ ናችሁ፡፡›› የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ማረጋገጥ ችለናል፡፡ በመቀጠልም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ ከተነሱ ሃሳቦችም መካከል የማዳበሪያ አሰጣጡ ፍትሃዊነት እንደሚጎድለው፤ መሬታቸውን ለልማት በሚል ሰበብ እንደሚነጠቁና ዋስትና የሚባል ነገር እንደሌላቸው፤ የኑሮ ውድነቱ ከመክፋቱ የተነሳ ልጆቻቸውን መመገብና ማስተማር እንዳልቻሉ፤ አረጋዊያን በምግብ እጥረትና እርዳታ በማጣት አይናቸው እያየ እየሞቱ እንደሆነ፤ የእርዳታ ስንዴ ክፍፍል ላይ እንኩዋን ፍትሃዊነት እንደሌለ፤ ሙስና እንደሌሎቹ የሃገሪቱ ክፍሎች ጊዶሌንም እንዳጠቃትና ማህበራዊ ህይወታቸው ከመናጋቱ የተነሳ የባልና ሚስት ፍች ከፍተኛ ችግር እንደሆነባቸው ለአንድነት ፓርቲ የአመራር አባላት መግለፃቸውን የህዝብ ግንኙነት መረጃ ያመለክታል፡፡
አመራሩም ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን ዋናው የችግሮች ሁሉ ምንጭ የመልካም አስተዳደር እጦት በመሆኑ መልካም አስተዳደር የሚያሰፍን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አማራጭ የሌለውና አንገብጋቢ ነው ማለታቸውን ለፍኖተ ነጻነት አብራርተዋል፡፡
በተያያዘም የአንድነት የልዑካን ቡድን እሁድ ሰኔ 24 ቀን 2004 ዓ.ም አስራ ስድስት ብሄሮች ወደ ሚገኙባት የደቡብ ኦሞ ዞን ጅንካ ከተማ ያመራ ሲሆን በደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ፅ/ቤት አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ስብሰባውን አከናውኖአል፡፡
የእለቱን የስብሰባ ውሎ ያደረሰን የህዝብ ግንኙነት መረጃ እንደሚለው በአዳራሹ የከተማዋና የደቡብ ኦሞ አካባቢ ኑዋሪዎች ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይም በደቡብ ኦሞ የአንድነት ተጠሪ አቶ ስለሺ ጌታቸው ስብሰባውን መርተዋል፡፡ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ አቶ ግርማ እንዳሉትም፡- ‹‹ለውጥ ማምጣት የምንፈልግ ከሆነ በቅድሚያ ፍርሃታችንን ማስወገድ አለብን፤ ፍርሃትና ነፃነት ዝምድና የላቸውም፤ እኛ የምንፈልገው የነፃነት ቱርፋት ያለምንም ማዳላት ለሁሉም እንዲደርስ ነው›› በማለት ጠቅሰዋል፡፡
ዋና ፀሃፊው አቶ አስራ ጣሴም በበኩላቸው አቶ መለስ ከ20 ዓመት በፊት ቃል የገቡትን እንዳልፈፀሙ ጠቅሰው ‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ነፃ፤ ከፊል ነፃና ነፃ ያልሆኑ ከሚለው ምድብ ውስጥ የኢትዮጵያ የነፃነት ደረጃ ነፃ ካልሆኑት ተርታ ይመደባል፡፡ ከዴሞክራሲያዊ ሀገሮች ውስጥም ኢትዮጵያ የለየላቸው አምባገነኖች ካሉበት ምድብ ውስጥ ትመደባለች፤ የህግ የበላይነት ጠፍቱዋል፤ የስራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር እጦት የሀገራችን መገለጫዎች ሆነዋል፤ እዚች ሀገር ላይ ያለው ዴሞክራሲ አስመሳይ ዴሞክራሲ ስለሆነ ሊለወጥ ይገባዋል፡፡ ህዝብ የመንግስት ተመፅዋች መሆን የለበትም ስለዚህ ተባብረን ለለውጥ መትጋት አለብን›› ብለዋል፡፡
ህዝቡም የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያነሳ ሲሆን ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥም ሙርሲ እየተሰራ ያለው የስኳር ፋብሪካ የሚሰራው መንገድና መጋዘኑ የሚሰራበት ቦታ የአካባቢውን ተወላጆች በቅድሚያ ተጠቃሚ የሚያደርግ አይደለም፤ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ተባብሶአል፤ የጅንካን ከተማ ዋና መንገድ አስፓልት እናደርጋለን ብለው የቀድሞውን ድልድይ ሰብረውት አስፓልቱም በጅምር ቀርቶና ድልድዩም ሳይሰራ ችግር ላይ ወድቀናል፤ ሙስና በልቶ ሊጨርሰን ነው፤ ኢህአዴግ በቆሎ፣ ሙዝና ቡና መትከል የጀመራችሁት እኔ ከመጣሁ በኋላ ነው ሊለን ይፈልጋል፤ የትምህርት ጥራቱ መበላሸት ልጆቻችንን ለፍተን አስተምረን ከንቱ እያደረገብን ነው፤ የኢህአዴግ ካድሬዎች ነፃነታችንን አሳጥተውናልና ሌሎች በርካታ ሀገራዊ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት እንደተደረገባቸው የህዝብ ግንኙነት ገልጦልናል፡፡ በተለይ የትምህርት ፖሊሲውን አስመልክቶ አስተያየት የሰጡት አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዳሉት፡- ‹‹አንድ የህንፃ ዲዛይን ቢሳሳትና ህንፃው ቢደረመስ በወቅቱ ህንፃው ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ አንዲት ሀገር የትምህርት ፖሊሲዋ ከተሳሳተ የሚጠፋው አንድ ትውልድ ነው›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ በደቡብ የተሳካ ስብሰባ ያካሄደው አንድነት ፓርቲ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስና ፓርቲው ያለውን ዕቅድ አብራርቱዋል፡፡ በሃገሪቱ ህዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ማጣት፤ የሙስና መንሰራፋት፤ የፍትህ መጉዋደልና ዜጎችን አሸብሮ በግዳጅ መግዛት ዋና የስርዓቱ ችግሮች መሆናቸውንና ህዝቡን ከተጫነበት እዳ ለመገላገል ከራሱ ከህዝቡ ጋር በመሆን በሰላማዊ መንገድ ኢህአዴግ መወገድ እንዳለበት ተመካክሮ መመለሱን የህዝብ ግንኙነት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡