የፍትህ ተቋማት ለአገዛዞች እንደማጥቂያ መሳሪያነት በሀገራችን መቼውንም እንዳያገለግሉ፣ ህወሓት/ኢህአዴግን በህጋዊ ትግል ከስልጣን ማስወገድ አማራጭ የለውም! (አንድነት)

የእነ አንዱዓለም አራጌን ክስ ሲከታተል የነበረው ፍድር ቤት ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. በተሰየመው ችሎት፣ ሁሉንም ተከሳሾች ጥፋተኞች በማለት ውስኔ ሰጥቷል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በተለያዩ አጋጣሚዎች የታሳሪዎችን ጥፋተኛነት በአደባባይ የተናገሩትን፣ ፍርድ ቤቱ በጹሁፍ አንብቦታል፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ፍርድ ቤቶች ነጻነት የሚባል ፈጽሞ የሌላቸው ተቋሞች መሆናቸውን ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ በተጨማሪም የፍትህ ተቋማት ህውሓት/ኢህአዴግ በስልጣን እስካለ ድረስ ነጻ ሊሆኑ እንደማይችሉም ዳግም ማረጋገጫ የሰጠ ሆኗል፡፡ ነገም ቢሆን በተመሳሳይ ሁኔታ በሽብርኝነት ሰበብ ተከሰው ውሣኔ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ የመድረክ ፓርቲ አመራር አባላት የሚጠብቃቸው ውሣኔ የተለየ ሊሆን እንደማይችል መገመት አሰቸጋሪ አይሆንም፡፡

አገዛዙ የፍትህ ተቋማትን ያለምንም ማፈርና ይሉኝታ ሠላማዊና ህጋዊ ታጋዮችን ለማጥቅያ መሳሪያነት እየተጠቀመባቸው መሆኑን ዳግም ያረጋገጠ ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ አሳፋሪና ፍርደ-ገምድል ውሳኔ በህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ውስጥ ከተፈጸሙ አስነዋሪና ግፈኛ ውሳኔዎች ውስጥ በታሪክ ሲወሳ ይኖራል፡፡ በክርክሩ ወቅት የቀረቡትን የአቃቢ ህግ ምስክሮችና ማስረጃዎች አንዲሁም የተከሳሾች መከላከያ ምስክሮችና ማስረጃዎች የታሪክ መዘክሮች ናቸው ብሎ አንድነት ያምናል፡፡ ፓርቲያችን የሚታገልለት የመቻቻልና ልዩነት በሰለጠነ መንገድ የማስተናገድ ፖለቲካ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ ፈጽሞ ሊቀበለው እንዳልቻለ ተጨማሪ ማስረጃ ነው፡፡ የፍርድ በቱ ውሣኔ ትንተናም ያረጋገጠው ይሄንኑ ሃቅ ነው፡፡

ህወሓት/ኢህአዴግ የሰላማዊ ታጋዮችን መስከረም 3 ቀን 2ዐዐ4 ዓም ሲያስር ሁለት ዓላማዎች ነበሩት፡፡ አንደኛው ወጣት ታጋዮችን በማሰር ትግሉን ማኮላሸት ሲሆን፣ ሁለተኛው ሰላማዊ ትግሉን ወደፊት ማስፈንጠር አቅም ያላቸውን ወጣቶች ወደ ትግሉ እንዳይቀላቀሉና በፍርሃት ቆፈን እንዲያዙ የተወጠነ ነበር፡፡

በተጨባጭ ስናየው ግን ትግሉ ብዙ ሺ ታጋዮችን እያፈራ ነው፡፡ እነ አንዱዓለም፣ ናትናኤል፣ እስክንድርና ጓዶቻቸው አንግበው የተነሱለትን የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከቀን ወደ ቀን አገዛዙ የሚሄድበት የቁልቁለት ጉዞ እየፈጠነ፣ የለውጥ ኃይሉ እየጐለበተ እየሄደ እንደሚገኝ ግልጽ ነው፡፡ በቅርቡም በሽብርተኝነት ስም የአንድነት ፓርቲ አባላትን ወደዘብጥያ የመወርወር ዕቅድ እንዳለ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ሊረዳው ያልቻለው መራራ ሃቅ ግን በህዝቦች ህሊና የተተከለውን የለውጥ ጥያቄ፣ በአፈናና በእስር ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን ነው፡፡

በዓለም ላይ በርካታ አምባገነን አገዛዞች ነበሩ፤ መጨረሻቸውም አሳፋሪ ውድቀት ነበር፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግም እየተከተለው ያለው አምባገነናዊ መስመር፣ በማይቀረው የጊዜ ሂደት እና የታጋዮች ፅናት የሚሸነፍ መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ የየዕለት ኑሮዋችን እያመሰቃቀለው መሆኑን ተገንዝበን ለለውጥ የሚደረገውን ትግል በስፋት እንዲቀላቀል አንድነት/መድረክ ሀገራዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሀገራችን ያለውን አምባገነናዊ ስርሃት ከስልጣን ለማውረድ በሚደረገው ህጋዊ ትግል ከመቼውም ጊዜ በላይ ከአንድነት/መድረክ ፓርቲ ጐን ቆማችሁ ትግሉን እንድትደግፉ ፓርቲያችን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ የአለም አቀፍ ማሕበረሰብ አገዛዙ የተመሰረተበት ዋንኛው የአምባገነንነት ምርኩዝ መሆናቸውን ተገንዝበው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲና ለነጻነት የሚያደርገውን ትግል ድጋፋቸውን እንዲ ቸሩ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

አንድነት/መድረክ አሁንም ቢሆን በህገ-መንግስቱ የተቀመጡትን መብትና ግዴታዎች በማክበር፣የህገ-መንግስት ድንጋጌዎችን የሚጥሰውን የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በህጋዊና በሰላማዊ ትግል ከስልጣን እንዲወገድ ትግሉን ማፋፋም አማራጭ የለውም ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህ ዓላማ መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት፣ በክብር ለመክፈል የአንድነት ፓርቲ አባላት ሁሌም ዝግጁ ናቸው፡፡

እነ አንዱዓለም የከፈሉት መስዋዕትነት፣ ሁሌም በታሪክ ሲወሳ ይኖራል!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሰኔ 21 ቀን 2004 ዓ.ም.
አዲስ አበባ