ሰው የሚያጣምመው መሬት
ሰኞ ሰኔ አሥራ አንድ ቀን2004 ዓም ከቀኑ በሰባት ሰዓት ላይ ከካሊፎርኒያዋ ኦክላንድ ወደ ሳንታ ክሩዝ በመጓዝ ላይ እንገኛለን፡፡ አብረውኝ አስጎብኚዎቼ ኢሳይያስና ቅዱስ አሉ፡፡ ዓለማችን መቼም ዕንቆቅልሻቸው ያልተፈታ አስገራሚ ድንቅ ነገሮች አሏት፡፡ ልክ እንደ ቤርሙዳ ትሪያንግል ከመላምት በስተቀር እቅጩን ነገር ሊናገሩላቸው የማይቻሉ፡፡ ዛሬም የምንጓዘው አሜሪካኖቹ «ብታምኑም ባታምኑ ም» በሚለው የቴሌቭዥን ፕሮግራማቸው ከሚያቀርቧቸው የዓለማችን ድንቅ ነገሮችና ቦታዎች አንዱን ለማየት ነው፡፡
የሀገሬ ሰው ላሊበላ ሲሄድ
እንግዲህ ዲያብሎስ ምን ትበላ?
ትንሹም ትልቁም ሄደ ላሊበላ
የሚለው መዝሙር አሁን ነው ትዝ ያለኝ፡፡ እኔም በተራዬ
እንግዲህ ፊዚክስ ምን ትመልስ
ትንሹም ትልቁም ሄደ ሳንታ ክሩዝ
ለአንድ ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ የገባንበት የሳንታ ክሩዝ ደን እንዴት ያምራል፡፡ ከጂማ ወደ ቴፒ ስጓዝ ግራና ቀኝ ጉሬዛ ከዛፍ ወደ ዛፍ እየተንጠላጠለ ሲዘል እያየሁ የሄድኩበትን መንገድ አስታወሰኝ፡፡ ቀና ቢሉ ሰማዩን በማያሳይ የከተማ ደን ወስጥ ነው የምንጓዘው፡፡ አካባቢው የካሊፎርንያ ባዕለ ጸጎች የበጋ ቤት የሠሩበትና እንዲህ የልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሲዘጋ ወጣ ብለው በአካባቢው በሚገኘው ሐይቅ ዳርና በዚህ መንፈስ በሚመስጠው ጫካ ውስጥ የሚዝናኑበት ነው፡፡የሀገሬ መናኝ ዛፉ አልቆበታል፡፡ የአሜሪካ ደን ደግሞ መናኝ አላገኘም፡፡ የሀገሬ መናኝና የአሜሪካ ጫካ ቢገናኙ ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እያሰብኩ ሁለት መኪና ብቻ ግራና ቀኝ በምታስኬደው እንደ ግሼን መንገድ በቀጠነችው መንገድ ተፈተለክን፡፡ በጫካው ውስጥ ከአራት ኪሎ ሜትር በላይ እንደነዳን የሳንታ ክሩዝን ምሥጢራዊ ፓርክ ምልክት አገኘነው፡፡
የመንገዱ መንገጫገጭና ግራና ቀኙ አቧራ መሆን ወደ አንዳች ልዩ የሆነ ሥፍራ እየሄዳችሁ መሆኑን እንድትረዱት ያደርጋል፡፡ መንገዱ አንድ ይሆናል፣ እንደገና ደግሞ በሁለት ዛፎች ተከፍሎ መሄጃና መምጫ ይሆናል፡፡ መልሶ ደግሞ አንድ መንገድ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ከመንገዱ ጥበት የተነሣ ተያይቶ መተላለፍ የግድ ይላል፡፡ በጫካው ወስጥ ስታቋርጡ አስፓልቱ እንደ ዲሲ መንገድ ያንገጫግጫችኋል፡፡ መቼም እኔ ከሀገሬ የገጠር መንገድ የማይተናነስ ጎርበጥባጣ መንገድ በምዕራቡ ዓለም ያየሁት ዋሺንግተን ዲሲ ነው፡፡
ደረስን፡፡
የስጦታ መሸጫው ሱቅ ሄዳችሁ ነው ትኬት የምትቆርጡት፡፡ በየአሥራ አምስት ደቂቃው ጎብኚዎች ወደ ጉብኝት ሥፍራው ይገባሉ፡፡ እስከዚያው ትኬታችሁ ላይ ያለውን ሰዓት እያያችሁ መጠበቅ ነው፡፡ በሀገሩ አቆጣጠር አራት ሰዓት ተኩል፣ በኛ ደግሞ አሥር ሰዓት ተኩል ላይ ተራችን ደርሶ ገባን፡፡ «እንኳን ደኅና መጣችሁ» ብላ የተቀበለችን አስጎብኚ ጉብኚቱ 45 ደቂቃ እንደሚወስድ ነገረችን፡፡
«ከሰባ ዓመታት በፊት በ1939 ዓም እኤአ ሚስተር ፓራተር የተባለ ሰው በዚህ አካባቢ የበጋ ቤት የሚሠራበት መሬት ለመግዛት ይመጣል፡፡ ሚስተር ፓራተር በአካባቢው በሁለት ተራሮች መካከል ያለውን ረባዳ መሬት ለመግዛት የመሬቱን ባለቤት ይጠይቀዋል፡፡ ባለቤቱ ለመሸጥ ዝግጁ መሆኑን ለሚስተር ፓራተር ይገልጥለታል፡፡ ነገር ግን ረባዳውን መሬት ሲገዛ ሁለቱን ግራና ቀኝ የሚገኙ ተራሮችንም አብሮ መግዛት እንዳለበት ይነግረዋል፡፡
መጀመርያ ሚስተር ፓራተር ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ በኋላ ግን በአካባቢው በነበረው መልክዐ ምድር በመማረክ ሊገዛው ተስማማ፡፡ ከዚያም በስተግራ በሚገኘው ኮረብታ ላይ አነስተኛ ቤት ለመገንባት የመሬቱን አቀማመጥ የሚያጠናለት ሰው ቀጠረ፡፡ የተቀጠረው ሰው ወደ ኮረብታው ወገብ ላይ ወጥቶ በኮምፓስ አቀማመጡን ለማየት ሲሞክር ኮምፓሱ እየቀባዠረ ተቸገረ፡፡ ትንሽ ራቅ ሲል ግን ኮምፓሱ ይሠራል፡፡ ሚስተር ፓራተር የፈለገበት ቦታ ላይ ግን ኮምፓሱ ሊሠራ አልቻለም፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ወደዚያ ቦታ ለመሄድ ሲነሡ ከላይ የሚመጣ ኃይል ወደታች ይገፋቸው ነበር፡፡ ጫን ጫን እየተነፈሱ ነበር ወደዚያ ቦታ የሚደርሱት፡፡ በቦታው ላይ እንደምንም ሲደርሱ ያዞራቸዋል፣ ያጥወለውላቸዋል፣ የድካምና የመዛል ስሜት ይሰማቸዋል፣ አንዳንዴም ዕንቅዕፍ ዕንቅልፍ ይላቸዋል፡፡ ነገሩ ባለሞያውንና ሚስተር ፓራተርን ግራ አጋባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ነገሩ የተከሰተው በአንዲት ጠባብ ቦታ ላይ ብቻ መሆኑ ዕንቆቅልሽ ሆነባቸው፡፡
ይህንን ጉዳይ ለመሬቱ ባለቤት ሲነግሩት እርሱም ተመሳሳይ ነገር እንደገጠመው አወራላቸው፡፡ እንዲያውም ቤት ሲሠራ ቤቱ እንደሚንሸራተት ነገራቸው፡፡ አላመኑም፡፡ እነርሱም አንዲት ትንሽ ቤት በእንጨት ሠርተው ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ በማግሥቱ ግን ቤቱ ተንሸራትቶና በአፍጢሙ ሊደፋ ደርሶ አገኙት፡፡ ቤቱ ወደ ተራራው ግርጌ እንዳይደርስ የሚያግደው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ በአካባቢው የነበሩት ዛፎች ተቆርጠው ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ቦታ ላይ ቆሟል፡፡
እነ ሚስተር ፓራተር ሌሎች ባለሞያዎችን ይዘው ለአንድ ዓመት ያህል ጥናት ሲደረግ ያ ቦታ እጅግ በሚገርም ምሥጢር የተሞላ ልዩ ቦታ መሆኑ ተደረሰበት፡፡ ከ1940 ዓም እኤአ ጀምሮም ለሕዝብ ክፍት ሆነ፡፡
ይህ ነው እንግዲህ «የሳንታ ክሩዙ ሚስትሪ ፓርክ» እየተባለ የሚጠራው ሥፍራ፡፡ በተራራው ወገብ ላይ የሚገኝ አንድ መቶ ሃምሳ ጫማ ዲያሜትር ስፋት ያለው አስደናቂ ቦታ፡፡
ወደ ቦታው ስትዘልቁ የዛሬ ሰባ ዓመት ሚስተር ፓራተር ቦታው ላይ ሲደርስ ያጋጠመውን ነገር አስመልክቶ የጻፈው ማስታወሻ በትልቅ ቢል ቦርድ ላይ ተለጥፎ ታገኛላችሁ፡፡ አስጎብኛችን አንድ ነገር ከብበን እንድንቆም ነገረችን፡፡ ሁለት እንጨቶች ግራና ቀኝ ሆነው፣ በመካከላቸው ውኃ ልክ ተቀምጧል፡፡ የእንጨቶቹ ከፊል አካል ከሚስትሪ ፕሎቱ ክልል ውጭ፣ ከፊል አካሉ ደግሞ ውስጥ ነበረ፡፡ ውኃ ልኩን እንድናይ ጋበዘችን፡፡ ውኃ ልኩ ልክ ነው፡፡ ሁለት ሰዎችን ጋበዘች፡፡ ተመሳሳይ ቁመት ያላቸውን ሰዎች፡፡ ሁለቱ ሰዎች አንደኛው በወዲህ ሌላኛውም በወዲያ ሁለቱን እንጨቶች ጫፍና ጫፍ ረግጠው እንዲቆሙ አዘዘቻቸው፡፡እኛን ደግሞ እነርሱን እንድናይ ነገረችን፡፡ ሁለቱም ተመሳሳይ ቁመት አላቸው፡፡ እንጨቶቹ ላይ ወጥተው ስናያቸው ግን ከሚስትሪ ፓርኩ ውጭ ያለው ሰው ረዝሞ፣ ከሚስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያለው ሰው ያጥራል፡፡ ተቀያየሩላችሁ፡፡ ያጠረው ረዝሞ፣ የረዘመው ደግሞ አጠረ፡፡ ግራ ተጋባንና ሁላችንም እየወጣን ሞከርነው፡፡ ከውስጠኛው ክፍል ስትሆኑ ታጥራላችሁ፣ ከውጨኛው ክፍል ስትሆኑ ደግሞ ትረዝማላችሁ፡፡ ለምንድን ነው? ብትሉ መልስ የለውም፡፡
ወደ ሚስትሪ ፕሎት ቤት ለመግባት ሠላሳ ሜትር የማይሞላ ዳገት አለው፡፡ ያንን ዳገት ከመውጣት በአንድ ፊት የግሼንን ዳገት መውጣት ይሻላል፡፡ አንዳች ነገር ወደ ኋላ ይገፋችኋል፡፡ ገባን እንደምንም፡፡
ፊዚክስ ደኅና ሰንብች፣ የመሬት ስበት ደኅና ሁኚ ማለት እዚህ ነው፡፡
ኦክላንድ፣ ካሊፎርንያ

