የአዲስ አበባ አውራ መንገዶችና አደባባዮች በከፍተኛ የፖሊስ እና ፀጥታ ጥበቃ ሥር መሆኑ ታወቀ

ሰሜን አፍሪካንና መካከለኛውን ምስራቅ እያዳረሰ ያለው ህዝባዊ አብዮት ሊፈነዳ ይችላል የሚል ፍርሃትና ስጋት ሰንጎ የያዘው የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ በአዲስ አበባ ትላልቅ መንገዶችና አደባባዮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የጥበቃ ቡድን እንዳሰማራ የግንቦት 7 ዘጋቢ ከላከልን ዜና ለማወቅ ተችሎአል።

ባለፈው ረቡዕና ሃሙስ በአገራችን መዲና በአዲስ አበባ የተካሄደው አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት ጀምሮ የወታደርና የፖሊስ ልብስ የለበሱ በርካታ አባላት በተለያየ የከተማው መንገዶችና አደባባዮች ላይ በመሠማራት  የእያንዳንዱን ሰው እንቅስቃሴ በቅርብና በሩቅ ሲከታተሉ እንደነበረ የታወቀ ሲሆን ጥበቃው በመዲናችን የተሰባሰቡትን አምባገነኖች ድህንነት ከመጠበቅ ያለፈና ወያኔ ያለበትን ጭንቀት አመልካች እንደሆነ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስገልጹ ስንበተዋል እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት።

ላለፉት 20 አመታት በህዝባችን ላይ የደረሰው ግፍና መከራ በከተማው ውስጥ በተገነቡት ህንጻዎችና በአለም አቀፍ ህብረተሰብ የገንዘብ ድጋፍ በተዘረጉ አስፋልት መንገዶች ውዳሴ እንዲደበሰሰ በፕሮፖጋንዳ ዜጎችን የሚያደነቁረው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በቱንዚያና በግብጽ አምባገነኖችን አከርካሪ የመታ ህዝባዊ አብዮት አይነት በአገራችን ለመነሳት ምንም አይነት ነባራዊ ተጨባጭ ምክንያት የለም ከማለት አልፎ ከሁለቱ አገሮች የተሻለ ፍትህ እና የዜጎች  እኩልነት  የተረጋገጠበት የመንግሥት አስተዳደር በአገራችን አለ፤ የሃብት ክፍፍልም ቢሆን አብዮት ከተቀሰቀሰባቸው አገሮች በተሻለ ሁኔታ በአገራችን ፍትሃዊ ነው በማለት መሳቂያና መሳለቂያ የሆነ ፕሮፖጋንዳ መንዛት ጀምሮአል ተብሎአል።

በምርጫ ህግ ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበትን መድረክ አመቻቻለሁ በማለት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነጻ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ወያኔ በፈቀደበት ምርጫ 97 ከደረሰበት ሽንፈት ያገኘው ልምድ መልካም ስላልሆነ ወያኔ በምንም አይነት ህዝቡን ማመን ስለማይችል የአሁኑ መንገዶችን በፖሊስና በፀጥታ ሃይል ማጠር ምንጩ ያለፈው ልምዱ የፈጠረበት ስጋት ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው። ለዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ ቅድመ ምርጫ 97 የነጻ ካናቴራና የገንዘብ ጉርሻ ተሰጥቶት ሚያዚያ 29 ቀን መስቀል አደባባይ ለወያኔ ድጋፍ ወጥቶ የነበረው የአዲስ አበባ ነዋሪ በማግሥቱ ሚያዚያ 30 ቀን ተቃዋሚዎች ጠርተውት በነበረው ሰልፍ ላይ ያንኑ የወያኔ ካናቴራውን ለብሶ ” ትናንት ለ እንጀራችን ዛሬ ለነፃነታችን ” የሚል መፈክር እያሰማ በመውጣቱ እና በምርጫውም ወቅት ወያኔን ጉድ በማድረጉ ወያኔ ክፉኛ ቆስሎአልና ሰው አያምንም ይላሉ። የምርጫ 97 ን ወጤት ለመስረቅና ሥልጣን ላይ ለመቆየት ወጣቱን አደገኛ ቦዜኔ የሚል ቅጽል ሰጥቶ በአጋዚ ጦር በጠራራ ፀሃት በርካቶችን እንዳስገደለና እንዳቆሰለ የሚታወቅ ነው።