ኢትዮጵያ በግብጽ ታየች ብሥራት ደረሰ

የግብጹ ሙስሊም ብራዘርሁድ በጠባብ ልዩነት አሸነፈ፡፡ እንኳን ደስ ያለው፡፡ ማሸነፍ ደስ ይላል፡፡ እንደማሸነፍ የሚያስደስት የለም፡፡
ይህ እስላማዊ ቡድን በአፄ ሙባረክ ዘመነ መንግሥት ከሕዝቡ 20 በመቶ ብቻ ይደግፈው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ዛሬ ግን ሕዝብ ተገልብጦ 53 በመቶ አካባቢ በሚሆን የመራጮች ድምፅ ይሄው እስላማዊ ቡድን አሸነፈ ተብሏል፡፡ ዓለም ዘወርዋራ ስለሆነች ይህ ክስተት አይደንቅም፡፡
የግብጽ ነገረ ሥራ ከኛዋ ከርታታ ኢትዮጵያ ጋር በብዙ የሚመሳሰል እንደሆነ ታዘብኩ፡፡

ቅንጅት በ97ዓ.ም ማሸነፉ ሲሰማ ወያኔ ተደናግጦ በቅጽበት ብዙ ሕጎችን በአንድ አዳር ለዋወጠ – በተለይ አዲስ አበባን በሚመለከት፡፡ ቀስ ብሎ ግን በመፈንቅለ መንግሥት ሁሉንም ሥልጣንና ይዞታውን እንደጠቀለለ ዕድሜ ልኩን ለመቀጠል በመፈለጉ ምርጫውን ያሸነፉ ተቃዋሚዎችን የእንጭብጭቢት ብሎ የገደለውን ገድሎ ያሠረውንም አሥሮ ያሰደደውንም አሰድዶ ሀገሪቱን በወለድ አገድ በመያዝ እንዳሻው እያደረጋት ይገኛል፡፡

የግብጾቹ ወታደሮችም ከወያኔ ባልተናነሰ መልኩ – ከወያኔም የተማሩ ይመስላል – በእናቴ መቀነት አሰናከለኝ ዓይነት ማቄን ጨርቄን እያሉ ሕዝቡን እያምታቱ ናቸው – በዚያውም የጌቶቻቸውን ፍላጎትና ትዕዛዝ ለማስከበር፡፡ በስንት ደጅ ጥናት በተገለጠው የምርጫ አሸናፊ ውጤት የእስላማዊ አክራሪው ቡድን አባል ሞሃመድ ሞርሲ – ኢንጂኔር ዶክተር – እንዳሸነፈ ዛሬ ተገልጧል – ሕዝቡም ደስታውን በታህሪር አደባባይ በርችትና በዳንኪራ እየገለጠ ነው፡፡ ነገር ግን የውጤቱ መገለጥ እውን እስኪሆን ድረስ በነበረው ጊዜ ወታደራዊው ጁንታ ብዙ ሸፍጦችን እንደሠራ ሰምተናል – እንደወያኔ የ97 ምርጫ ተብዬ ዓይነት ማንንም ሊያታልል የማይችል የቁጭ በሉ ሸፍጥ፡፡ ስለዚህም የዚህን አሁን ሕዝብን እያስፈነደቀ ያለ ‹ድል› እውነተኛ ውጤት የምናየው ገና ወደፊት ይሆናል፡፡

ይህ ውጤት የእልህ ውጤት ነው፡፡ አምናና ታቻምና ከግብጽ ሕዝብ 20 በመቶው ብቻ እንደሚደግፈው ይነገርለት የነበረና ሴት ሙስሊሞችን እንኳን በስያሜው የማያካትት ጽንፈኛ ሃይማኖታዊ ቡድን ዛሬ በለስ ሊቀናው የቻለው በበጎ ምግባሩና በፖለቲካ ፕሮግራሙ ሳይሆን በአጋጣሚ ይሁን በሌላ በማናውቀው ምክንያት ተፎካካሪ ሆኖ የገጠመው ሞሃመድ ሻፊቅ የሚባለው ሰው የቀድሞውና በሕዝቡ ዐመጽ ተንኮታኩቶ የወደቀው የሙባረክ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበረ በመሆኑ ነው፡፡ እናም ሁኔታው ለዚህ ሃይማኖታዊ ጠባብ ቡድን አመቺ ሆነ፡፡ በረከት ስምዖን ‹ንፋስ የሰጣቸው ድል ነው› ብሎ ነበር የቅንጅቶችን ድል – እውነቱን በመደበቅ፡፡ ይሄኛው ግን እውነትም ንፋስ አውጀምጅሞ የጣለላቸው ያላሰቡት ድል ነው፡፡

‹የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይቀላውጡ› ይባላል፡፡ ግብጽ እነአልባራዳይንና እነአምር ሙሳን የመሳሰሉ ድንቅ ሰዎች አሏት፡፡ ነገር ግን ግብጽም እንደኢትዮጵያ ሁሉ ‹የሸክላ ሠሪ ልጅ በገል ትበላ› ዓይነት ሆኖባት – እንደኛው ተረግማም ሊሆን ይችላል – ይሄውና ወታደርና አክራሪ ሙስሊም ይጫወትባት ይዟል፡፡ በሃይማኖት ስም የሚመጣ የሀገር መሪ ደግሞ ለማንም ለምንም አይበጅም፡፡ ሀገርና ሃይማኖት ካልተለዩ አደጋ ነው፡፡ ግብጽ 10 በመቶው ክርስቲያን ነው፡፡ በግብጻዊነቱ ከማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ጋር እኩል መታየትና መብቱ እኩል ሊከበር ይገባዋል፡፡ ‹እስላማዊ ብራዘርሁድ› ብሎ የሀገር ሥልጣን ያዥ ለኔ አይታየኝም፡፡ ለኔ ክርስቲያን ሲስተርሁድም ይባል ፋዘርሁድ ወይም ብራዘርሁድ ያው ነው፡፡ በዘርና በሃይማኖት የሚቋቋም የፖለቲካ ቡድን መርዝ ነው – ከመርዝም በላይ እንዲያውም፡፡ መርዝ ማርከሻ አለው፡፡ የሃይማኖት ጽንፈኝነት ግን ካለምፅዓት አንድም መፍትሔ የለውም፡፡ ከሔሮይንና ከኦፒየም የበለጠ አእምሮን የሚያዝግና በሰው አምሳል የሚንቀሳቀስ ጨካኝ ደም የጠማው አውሬ የሚያደርግ አደገኛ ዕፅ ነው፤ የስሜት ሕዋሳትን ያደነዝዛል፤ ከሰውነት ተራ ያወጣል፤ እናትንና ልጅን ሳይቀር በክብር ግድያና ሞት ሳይቀር ለሰይጣናዊ ጭዳነት ይዳርጋል – ምን እማያደርገው ነገር አለ – ኅሊናችንን ካልዋሸነው እውነቱን እናውቀዋለን፡፡ ቋንቋና አመክንዮ ላንቃቸው እሚዘጋበት፣ ምክንያትና ሎጂክ እንደተወረረ ከተማ ጸጥ እረጭ እሚሉበት፤ ማመንና ማሳመን ጉልበታቸው ቀጤማ እሚሆንበት፣ የምትታዘዘውን ከማድረግ በስተቀር ያንተ አእምሮ ከትቢያና አመድ አንድ እሚሆንበት የየትኛውም አክራሪነት ሰለባ ስትሆን ነው፡፡ በግብጽ ይህ ሁኔታ አስቸግሯቸው ይመስለኛል ሻጥር ቢጤ ለመሥራት ከወሳኞቹ የመማክርትና የረድኤት ሀገራት ጋር የስካፍ ወታደሮች እየተመሰጣጠሩ ተንኮል እየጎነጎኑ የሚገኙት፡፡ ነገር ግና ነገሮችን ይበልጥ መንግገው አሰፉና የፈሩት አልቀረም የሆነው ሆነ – የውጤቱ መዘዝ ገና በቅርብ ርቀት የሚታይ ቢሆንም፡፡ የትኛውም ዓይነት አክራሪነት ደግሞ ዳኛ የሌለበት ኳስ ሜዳ ማለት ነው፡፡ የመጽሐፍ አንድ ገጽ ቀደደ ወይም አቃጠለ የተባለን ዜጋ በ‹ብላስፌሚ› የስቅሎ ስቅሎ ያረጀ ያፈጀ ሀሙራቢያዊ ክስ አንገት ለመቁረጥ ያሰፈሰፈሰ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ‹ሥልጡን ዜጋ› በሞላባት ዓለማችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት መጠሪያ ይዞ ወደ ሥልጣን ማማ መውጣት አደጋው የከፋ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙ ግብጻዊ ጤናማ እስላሞችና ክርስቲያኖች በዛሬው ውጤት አብደውና ሰክረው የታዘብናቸው – ሻፊቅ እንዴት አላሸነፈም ከሚል፡፡ መራጮቹም ቢሆኑ ወደው አይመስለኝም፡፡ እንዳልኩት ምርጫ ከማጣትና ሙባረክን ከመጥላት አኳያ ይመስለኛል፡፡

በ97 ምርጫ አቶ አርከበ ዕቁባይ በአዲስ አበባ ሲሸነፍ መለስ እንዲህ ብሎታል ይባላል፡- ‹የተሸነፈው ኢሕአዲግ እንጂ አንተ እኮ አይደለህም፡፡(አትዘን ከሚል የማፅናናት ስሜት መሆኑ ነው)› አሁንም ያሸነፈው ሙስሊም ብራዘርሁድ ሳይሆን የተሸነፈው ከመቃብሩ ወጥቶ በተለያዩ ሽፋኖች ለውድድር የቀረበው የሙባረክ መንግሥት ነው፡፡ ሕዝቡ ይህንን ቡድን በማፍቀሩ ሳይሆን ሞርሲን ‹የመረጠው› የፊተኛውና በጭራቅነት የፈረጀው የሆሲኒ ሙባረክ መንግሥት በምዕራፍ ሁለት የዲሚክራሲ ጭምብል እንዳይመለስበት በመሥጋት ነው – ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሻፊቅ ጥሩ ሰው ሊሆን ይችላል – ዐርከበ ጥሩ ነበር ይባልለት እንደነበረው፡፡ ነገር ግን አንዴ የተበላሸ ስም በቀላሉ አይቃናምና ኢሕአዲግም የሙባረክ መንግሥትም በግለሰብ ደረጃም ይሁን በቡድን ሰው ሊወጣላቸው አይችልም፡፡ በቃኝ፡፡