እንዴ! ወያኔዎች ማበዳቸውን ለማሳየት ይህን ያህል ርቀት መጓዝ ነበረባቸው? ታረቀኝ ሙጬ

ሰሞኑን በአርምሞ ሰነበትኩ፡፡ በሀገር ቤትም ሆነ በውጪው አሳዛኝና አስገራሚ ዜናዎችና ሀተታዎች ግን እየተደነቅሁ፣እየቆዘምኩና እየተሳቀቅሁ ከርሜያለሁ፡፡ በተለይ በተለይ በሁለቱ ጉዶች – መለስና አሳድ፡፡

እንደነዚህ ሁለትና ሦስት ቀናት ግን በሰው ልጆች ከንቱነት ተደምሜ አላውቅም፡፡ በመሠረቱ የኢትዮጵያን ጉዳይ ሸለል ካላሉት በእርግጠኝነት ሊያሳብድ ይችላል፤ ወያኔዎቹ ግን ይህን ይፈልጉታል – ጠቅልለን ጨርቃችንን እንድንጥልና ብቻቸውን ካለገልማጭና ካለቆንጣጭ ካለአሳባቂም ሥልጣንና ሀብት ላይ ፊጥ እንዳሉ ዝንታለማቸውን ሲምበሸበሹ ለመቆየት – በዚያች የመተካካት ቻይናዊ ፈሊጣቸው፡፡ ምኞት አይከለከልም መቼም፡፡

በጥንቱ አማርኛ ያንዠቴን ነው የምላችሁ ወያኔ እንደሰሞኑ አሳዝኖኝም አበሳጭቶኝም የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ እንዴ – ከ85 ሚሊዮን ሕዝብ መሀል ተመስገን ደሳለኝ የምንለውን የፍትህ ጋዜጣ መሥራችና ዋና አዘጋጅና ቆፍጣና የብዕር ወታደር በአልሻባብ ተባባሪነትና የኮንትራት ተቀጣሪነተ ፈርጆ እንዲህ እንደማሽላዋ በምፀት ሣቅ ሆዳችንን ያንፍረው እንዴ? ምን ዓይነት ቀውስ ውስጥ ቢገቡ ይሆን ጃል እንዲህ የተጃጃሉት? በውነት ምን ነካቸው? አንድ ሺህ ከመቶ(1000 ፐርሰንት) ቢታበድ እንዲህ ዓይነት የለዬለት የዕብድ ሥራ ይሠራል እንዴ? በኢሜይል አድራሻየ ቢጠይቁኝ ከዚህ የተሻለ የመወንጀያም ሆነ የማሳደጃ ዘዴ ልነግራቸው እችላለሁ፡፡ የኢትዮጵያን ሥልጣን ይዘው በሀገራችን ስም ይህን መሰል አሳፋሪ ነገር ከሚሰሩና በዓለም ፊት ከሚያዋርዱን ለተወሰነ ጊዜ እምነትና አቋሜን ‹ሰስፔንድ› አድርጌ በነጻ ልተባበራቸው ዝግጁ ነኝ፡፡

እንደውነቱ ከሆነ የማስመሰል ውንጀላ ዓይነትና ልክ አለው፡፡ ማስመሰል ማለት ነጭ ውሸት ማለት አይደለም፡፡ ይሄ ውንጀላ እኮ ሌላ ስያሜ ካልወጣለት በስተቀር የዓለም ቋንቋዎች ሁሉ በጋራ ቢመካከሩ አንድም ገላጭ ቃል ሊያገኙለት አይችሉም፤ ወያኔዎች ለካንስ እንደዚህ ዓይነት ወራዳና ተራ ጩልሌ ኖረዋል? እኔ ይህን ያህል ይወርዳሉ ብዬ በውኔም በልሜም አልጠበቅሁም፡፡ አህያዋ ‹አያ ጅባጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ› ያለችው ወዳ አይደለም፡፡ ከዚህ ከዚህስ ‹ተሜ! በይ እስካሁን አየንሽ፤ ጥሩ ትጽፊያለሽ፤ ሀገሬና ሕዝቤ ለምትያቸው ጥሩ የምትቆረቆሪ መሆንሽን ተረድተንልሻል፡፡ ነገር ግን መቼስ ማል ጎደኔ ይባል የለም? አዎ፣ እኛም መኖር አለብን፡፡ 17 ዓመት ታግለንና ተከታይ ጭፍሮቻችንን አታግለን ያገኘነውን ድል በብዕርና በዴሞክራሲ ሰበብ ልናጣው አንፈልግም፡፡ ስለዚህ አደብ ግዢና እንደሌላው ሕዝብ አርፈሽ ተቀመጪ፡፡ አለበለዚያ እንደ አሰፋ ማሩና እንደፕሮፌሰር አሥራት ሮጠሽ ሳትጠግቢ በለጋነት ዕድሜሽ እናጠፋሻለን፡፡ አለዚያም አንዳችም ምክንያት ሳያስፈልገን እንደነ እስክንድርና አንዷለም ዘብጥያ እናወርድሻለን፡፡…› ቢሉ ባማረባቸው ነበር፤ ይህኛው መቶ ዕጥፍ የተሻለና የመሰል አምባገነኖችንም ራሮት የሚያስገኝ ተግባር ነው ፡፡ የአሥመራው ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋዜጣ የለ፣ ፓርላማ የለ፣ ምርጫ ብሎ ነገር የለ፣… የለየለት ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ሆኖ ሕዝቡን እንደከብት ሲነዳ ማን ነካው? የምን ማስመሰል ነው? በነገራችን ላይ በድረ ገፆቻችን ላይ ዛሬ ስለውሸት ያነበብኩት የበላይነህ አባተ መጣጥፍ እንዴት ግሩም ነው?

በርማ እንኳን ከኛ በኋላ ተነስታ በዴሞክራሲ ረገድ የትና የት ስትደርስ እኛ እንደግመል ሽንት የኋሊት እንቅር? ያቺው የነበረችን ብቸኛ የብሶት መተንፈሻ ጋዜጣም እንደሌሎች ጓደኞቿ ልትዘጋ ይሆን? ምን ዓይነት ጉድ ነው? ምን ዓይነትስ ዕድል ነው ያለን? ጨለማው በረታሳ – ሊነጋ ይሆን እንዴ? እኔ ጠርጥሬያለሁ – እናንተስ?

የለየላቸው አምንዣኪ ከብቶች ከሆንን ይሄውና ሰባት ዓመት አለፈን – ከ97 ወዲህ በተለይ ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ አንናገር አንጋገር ዝግትግት! መጥኔ ለኛ፡፡
በየትኛው ሀገር ይሆን ስካይፕና ትዊተር መጠቀም 15 ዓመት እሚያሳስር? በየተኛው ሀገር ነው ‹የሀገሬ ፖለቲከኞች ሆይ! እባካችሁን ተስማምታችሁ ለሕዝባችሁ የሚጠቅመውን ሥሩ› ብሎ መናገር የሚያስገድልና ከርቸሌ የሚያወርድ? ወያኔ ምነው በኢትዮጵያውያን ላይ የሚሰነዝረውን በትርና አኮርባጅ እንዲህ አፀናው? በእውኑ ይህ ነገር መነሾው ሥልጣንና ሀብት ብቻ ነው ወይንስ ሌላም አለበት? ያዋጁን በጆሮ አሉ! ሌላውና ትልቁ የወያኔ አጀንዳማ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከምድረ ገጽ ማጥፋት አይደለም እንዴ? ብቀላውና የሥር በሥር ምንጠራውም ለዚህ ነው፡፡ ኢሳት ወደኢትዮጵያ ከሚገባ የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት እየተሟጠጠ ለቻይና ቴክኖክራቶች ይከፈል – ጃም እንዲያደርጉለት – ብለው ድርቅ ያሉትስ ከዚሁ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ባላቸው የታሪክ ቁርሾ አይደል፡፡ በሰው ልጆች ታሪክ እንዲህ ዓይነት የዱርዬና የወሮበላ መንጋ በመንግሥትነት የታየበት ሀገርና ዘመን ፈጽሞውን ያለ አይመስለኝም፡፡

የመለስ አያያዝ በጭራሽ አላማረኝም፤ ለነገሩ መቼውንም አምሮኝ አያውቅም፡፡ የአሁኑ ግን ለይቶለት አብዷል፡፡ እነ በረከት አብደዋል፤ እነ ስብሃት ነጋ አብደዋል፤ እነሳሞራ አብደዋል፤አማካሪም አጥተዋል – ምክር መስማት የማይፈልጉ አፄ እንደልቡዎች መሆናቸው የታወቀ ቢሆንም፡፡ በጥቅሉ ወያኔዎች ይሠሩትን አጥተው በጅምላም በችርቻሮም ከፍተኛው የዕብደት ደረጃ ደርሰዋል ማለት እንችላለን፡፡ ዕብደቱ በነሱ ብቻ ቢቆም ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን በሥራቸው ያለ አሽከርና ሎሌ ሁሉ እንደነሱው በነሱው የውሻ ዕብደት በሚመስል የተጋቦት ልክፍት ተለክፎ ሕዝቡንም በሁሉም ረገድ እያሳበደው ነው፡፡ የነሱ ዕብደት መነሻው የያዙት ጥቅምና ሥልጣን እንዳይነካና በሠሩትም ወንጀልና ጥፋት እንዲሁም ሙስና እንዳይጠየቁ ነው – የፊት ለፊቱ መነሻ መሆኑ ነው፡፡ የኛ ዕብደት መሠረት በየሴኮንዱ ሽቅብ የሚወነጨፈው የኑሮ ውድነትና አንዳችም ፍትህ የሌለበት ወያኔያዊው መሪር አገዛዝ ነው፡፡ ዋ! የዚህ ሁሉ ግፍና በደል መጨረሻ ሲደርስ ታዲያ ግፈኞች የሚከፈላቸው ምንዳ ይታየኛል፡፡የሠራተኛ ደመወዙ ይከፈለዋል፡፡ የማንም ላብ እንዲሁ አይቀርም፡፡ እናም በሠሩት ልክ ማግኘታቸው የሚጠበቅ እንጂ በአቋራጭ የሚያመልጡት አይሆንም፡፡ እኛም እንዳለቀስን አንቀርም፡፡ የውሻን ደም በከንቱ የማያስቀር ጌታ ዕንባችንን የሚያብስበት ጊዜ ሲመጣ፣ ደማችንን የሚጠርግበት ወቅት ሲብት፣ ቁስላችንን የሚያጠግበትና ስብራታችንን የሚጠግንበት አበቅቴ ሲጠባ፣ የጠገበን ሊያበርድ የተገፋንና ደም ያለቀስን ሊክስ መንበረ ሥልጣኑን ለደጋግና ቅን አሳቢ ዜጎች ሲሰጥ ያኔ እኚህ የአጋንንት ውላጆች፣ እኚህ ሀገርና ወገን ካጆች የሚገቡበትን ለማየት ያብቃን፡፡ ቀኑ ደርሷል፡፡ እንዲህ ያቅነዘነዛቸው የቀኑ መቅረብ መሆን አለበት፡፡ ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ ይላል አማራ – የዛሬውን አያድርገውና፡፡ ዛሬማ ምኑን ተረተው፡፡ እንደእባብ አናት አናትን እየተቀጠቀጡ ተረት የለም ወዳጄ፡፡ ግን ለበጎ ነው፡፡ በዚያውም የንስሃ ማውረጃ ሱባኤ ቢጤ መያዣ ጊዜ ነው፡፡ ሆኖም ቢሆን ግን አብዬ ሙጬ አጠፉ በተባለ ጥፋት እኔ ልጃቸው ታረቀኝ ይህን ያህል ባልበደል ደስ ባለኝ ነበር፤ በእስካሁኑ ካለፈልኝም እሰዬው ነው፡፡ ጥሩ ነው – አንዳንድ አጋጣሚዎች ራስን ለመመርመርና ከመስመር የወጣ ነገር ካለ ወደ መስመር ለመመለስ ይረዳል፡፡ ችግሩ የስሙኒን ስህተት በሚሊዮንና ቢሊዮን በሚገመት ሂሳብ ማወራረዱ ላይ ነው – የላይኛውን – የላይኛውን- የፈጣሪን በመዘንጋት! ‹ታሞ የተነሳ ፈጣሪን እረሳ፡፡

ውድ የወያኔ አገልጋዮች!

በተለይም በ‹ደኅንነት›፣ በፖሊስና በመከላከያ ውስጥ የምታገለግሉ ወገኖቻችን፤
ሁሉም ነገር ያልፋል፡፡ ብትገድሉንም ባትገድሉንም ያው ነው፤ አንዴውኑ ዕጣ ፋንታችን በወያኔው ግዛት ከወደቀ ወዲህ በቁማችን ሞተናል – በተውሶ ዐረፍተ ነገር “አልሞትንም ብለን አንዋሽም” በማለት የሚሊዮኖችን ብሶት መግለጽም እችላለሁ፡፡ በመንፈስ የሞተ ሰው ደግሞ በአካልም ቢደገም ዐረፈ እንጂ አልሞተም – ከሞተ ሰነባብቷልና፡፡ የምትገድሉን ሬሣችንን ነው – ነፍሳችንን እንደሆነ መቼም ቢሆን መግደል አይቻላችሁም፡፡ ከፈጣሪ ባይፈቀድላችሁም ኖሮ በወያኔው የጦር አዛዥነት ይህን ያህል ጥፋትና ውድመት በሀገርና በዜጎች ላይ ልታደርሱ ባልተቻላችሁ ነበር፡፡ ፈጣሪ ሲቆጣ ጨካኝ መንግሥት እንደሚሾም ዱሮውንም እናውቃለን፤ሊክስ ሲፈልግ ደግሞ አለቆቻችሁ እንደወገብ ቅማል ሰግጠው እንደያዟቸው እንደእምዬ ምንሊክ ያለ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሆኑና አፍቃሬ ሀገር ወሕዝብ የሆኑ መሪዎችን ያነግሣል፡፡ አዲስ ነገር አልነገርኳችሁም፡፡ ይህን ነባራዊ እውነታ አዛዦቻችሁም እናንተም ታውቃላችሁ፡፡ ይህን ብቻ ሳይሆን በተለይ የጥፋት ሠራዊት መሪ የሆኑት እነመለስና ሣሞራ የመጨረሻ ዕጣቸውንና ፈጣሪ የመደበላቸውን ዋጋም ያውቃሉ፡፡ ለዚህ ነው ጨንገራቸውና ልምጫቸው የጠነከረብን፡፡ የኛንና የእነሱን የመጨረሻ ዋጋ የውስጠኛ ማንነታቸው (ሰብኮንሸስ) ስለሚያውቅ ነው ጭካኔያቸው በቅናት መልክ የበዛብን፤ ሀቁ ይህ ነው ዕወቁት – ይወቁት፡፡ የጋራ ሀገራችን በሁሉም ረገድ ከሞተች ቆይታለች፡፡ አሁን እንዳለን አንቆጠርም፡፡ ፈጣሪን የሚፈራ የሃይማኖት አባት ከጠፋ፣ የወንጀለኞችን ዕኩይ ድርጊት በሰይጣናዊ መስቀል የሚባርክና የሚቀድስ ጳጳስና ፓትርያርክ የመንበረ ጴጥሮስን የነፍስ ማሰርና መፍታት ሥልጣን ከያዘ – በየደረጃው የሚገኙ ተከታዮቹንም በራሱ መልክ ቀርፆ ለጥፋት ካሰማራ፣ ሕዝብ ተበደለ ሀገር ቆረቆዘ ብሎ የሚጨነቅ መሪና የተዋረድ ባለሥልጣናት ከሌሉ፣ ወጣቱን ገደል የሚከት አዲስ ባህልና መጤ ልማድን ይሁነኝ ብሎ የሚያስፋፋ የመንግሥት ተቋም ከተዘረጋ፣ የሞራልና የመልካም ሥነ ምግባር ዕሴቶች ደብዛቸው እየጠፋ አምልኮተ ገንዘብና አምልኮተ ዘውግ በመንግሥትነት ከተሰየመ፣ ሕዝብን ወደ ከብትነትና አልፎም ወደ ግዑዝ ድንጋይነት የሚለውጥ ሰይጣናዊ የመንግሥት አመራር ከተተከለ… አንድ ሕዝብ እንደሕዝብ የመኖር ዕጣው ለጊዜውም ቢሆን ያቆማል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውን ያለንበት ወቅታዊ አሳዛኝ ሁኔታ ይህን ይመስላል፡፡ እስከዚያው ብርታትን ይስጠን እንጂ ወደሜዳው እየዘለቅን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡

ከፍ ሲል የተጠቀሳችሁ አብዛኞቹ የዚህ ሥርዓት አገልጋዮችም የኛኑ ዕጣ የምትጋሩ እንደሆናችሁ እናምናለን፤ ሌላው ቢቀር እንደኛውና ከኛው ጋር የሚቀጠቀጡ ዘመድ አዝማዶች አሏችሁ፡፡ የሁላችን መሪ ሆኖ በገዛ ጉልበቱና በታሪክ አጋጣሚ እላያችን ላይ የተጎመረው መለስ ዜናዊ ደግሞ ማንንም የማይምር በሰው አምሳል የተፈጠረ ብዔል ዘቡል ለመሆኑ እማኝ መቁጠር ሳያስፈልገን ባለፉት 21 ዓመታት በሀገራችን ውስጥ በዚሁ ሰው የበላይ አመራር ሰጪነት የተከናወኑትን ወገንን የመከፋፈልና ሀገርን የመሸጥ ዕኩይ ተግባራት በመመልከት መረዳት እንችላለን – የፊትን ቅርጽና ባህላዊውን የኮከብ ቆጠራ ውጤት ትተን፡፡

ስለዚህ ዕጣችሁ ከዕጣችን አንድ ከሆነ ዘንድ ለዚህ ለይቶለት ያበደ ለሚመስል ግለሰብና ቦንግል ጎጠኛ ሥርዓት ስትሉ ቋሚ ቅርሳችሁን – ማለትም ሕዝቡን – በምንም መንገድ ልትከዱትና ልትጎዱት አይገባም – የበላችሁበትን ወጪት ከመስበር ታቀቡ፡፡ እናንተ ረዳችሁትም አልረዳችሁትም ፈጣሪና ታሪክ ቅጣቱን በሚሰነዝሩ ጊዜ ይህ የአጋንንት ውላጅ የሰንበት ጽንስ ሰውዬ የሚገባውን ዋጋ ማግኘቱ በፍጹም የማይቀር ነው፡፡ እንዲህ በስሜት ሞገድ ተውጬ በቁጡ ቃላት መናገሬ ሰውዬው ከሠራቸውና እየሠራቸው ካለው መጥፎ ድርጊቶች በመነሳት እንጂ ክፋትን በክፋት ለመቃወም እንዳልሆነ በአክብሮት ልገልጽ እወዳለሁ፡፡

የእናንተ ንስሃ መግቢያ ጊዜ አሁን ነው፡፡ በዘርም ይሁን በጥቅም ከአምባገነኖች ጋር ወግኖ መቆም መጨረሻው እንደማያምር ዓለማችን በተደጋጋሚ እያስተማረችን ነው – መገንዘብና ማገናዘብ አቃተን እንጂ፡፡ በቅርቡ አይሆኑ ሆኖ ከ42 ዓመት የዙፋን አልጋው የተወገደውን ጋዳፊን ማየት ይቻላል፡፡ የሦርያውን ባሽር አላሳደን ማየት ይቻላል፡፡ የየመኑን አብደላ ሳለህን ማየት ይቻላል፡፡ የግብጹን ሆስኒ ሙባረክን ማየት ይቻላል፡፡ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ዘርዝረን አንጨርሳቸውም፡፡ ከነዚህ የታሪክ አጥቆች መረዳት የሚቻለው ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት ወይም በገንዘቡ ኃይል ወይም በወዳጅ ሀገራት የስለላና ወታደራዊ ትብብር ሊድን እንደማይችል ነው፡፡ ከዘረኝነትና ከሃይማኖታዊ ወገንተኝነት ጋር የተገመደ አምባገነንነት ደግሞ በሕዝብና በሀገር ላይ ብዙ ጥፋትና ውድመት አስከትሎ ነው በእውነት አሸናፊነት ፍልሚያው የሚደመደም፡፡ ለምሳሌ የአላሳድ ጉዳይ የሣምንታት ወይም የጥቂት ወራት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ያለቀለት ለመሆኑ ከአካሄዱ ያስታውቃል፤ በአንድ ሌሊት የሚፈጸሙ ታሪካዊ ክንውኖች ጥቂቶች ናቸው – ብዙዎቹ በቂና አመቺ ጊዜን ይፈልጋሉ፡፡ ቋቱ አልሞላ ብሏቸው እንጂ ሰውዬው ፀሐያዊ የዘመን አክሊሉን አገባድዶ እሾህ አሜከላዊ የጨለማ ጉዞውን ከተያያዘና የሚገባውን ምንዳ ሊያገኝ የመቃብር ዋሻው ከተከፈተ ትንሽ ሰንብቷል፤ ሰውዬውም ሆነ አድሎኣዊ ሥርዓቱ ያሉ ይመስላል እንጂ የሉም – ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል -ዓይነት ነው፡፡ በተለይ እንደነዚህ ያሉ ትግሎች በባሕርያቸው አስቸጋሪና እልህ አስጨራሽ ናቸው – ዘርና ሃይማኖት ያቆላለፋቸው ጥቅመኞች በትግሉ ውስጥ ስለሚሸረቡበትና ፍጻሜያቸውን በራሳቸው ትርጓሜ አንድ አድርገው ስለሚመለከቱ ነው የአስቸጋሪነቱ መነሻ፡፡ ይህችን የጥቅምና የዓላማ ትስስራቸውን እንደልዩ ሥልት እስከመጨረሻው በመጠቀም ብዙ ውድመት ካደረሱ በኋላ ይወገዳሉ – በመቃብራቸውም ላይ አዲስ ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ ችግሩ እነሱ ከተወገዱም በኋላ ትተውት የሚያልፉት ጠባሳና የባለወተራዎች ርኩቻ ወይም የሥልጣን ጠለፋ ነው፡፡ የኛዋን ጨምሮ ብዙዎች ሀገሮች ለዚህ ዓይነቱ ወረርሽኝ ተጠቂ ሆነዋል፤ እየሆኑም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደርገውን አጥቶ የፈዘዘ መስሎ እሚታየው ለዚህ ዓይነቱ የረቀቀ መንግሥታዊ ሥርዓት ልምድ ስለሌለውና ትግሉ ለሚፈልገው መስዋዕትነት የሚያዘጋጀው የተማከለ የትግል ስትራቴጂስት – በእስካሁኑ ሁኔታና በተለይ በሀገር ውስጥ- ባለማግኘቱ ነው፡፡ እንዲህ እንደሆነ ይቀጥላል ማለት ግን አይደለም፡፡ ጊዜና ፈጣሪ ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ አላቸው፡፡ መፍትሔዎች መናፍስት ናቸው፡፡ በሉ ሲላቸው ይከሰታሉ፤ በሉ ካላላቸው ይሠወራሉ – ተገቢውንና ሁነኛውን አስፈጻሚና ፈጻሚ እስኪያገኙ፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሕዝብ ጥሩዎች ነን፡፡ እንደሕዝብ ይቅር ባዮች ነን፡፡ እንደሕዝብ ሰውኛ ባሕርያችን ጎልቶ የሚታይ በጣም የሚያስቀና ማኅበራዊ ሕይወትም ያለን ታሪካዊ ሕዝብ ነን፡፡ መለስ ዜናዊ ከአንጋቾቹ ጋር ‹ተጋደሉ፤ ተጨፋጨፉ፤ የማን አባት ገደል ገባ፣ አማራ ገዳይ – ትግሬ ገዳይ – አህያ ገዳይ – አይጥ ማራኪ…› እያለና እያስባለ በተለዬ ፀያፍ ስብዕናው ለአካለ መጠን ከደረስ ጊዜ ጀምሮ ቢወተውተንም ሰምተን እንዳልሰማን በመሆን እስካሁን፣ አሁንምና ወደፊትም ቢሆን በዕድር፣ በጽዋ ማኅበር፣ በዕቁብ፣ በጉርብትና፣ በአበልጅነት፣በሰንበቴ፣በቡና ተርቲብ፣በሠርግ፣ በልደት፣ … በጥቅሉ በመከራችንም ሆነ በደስታችን አልተለያየንም – ሃሌ ሉያ! እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡ ይህ ውብና ፈተናን ቻይ ጠባያችን(resilience) የኅልውናችን መሠረት – ጨርሰንም እንዳንጠፋ እየረዳን ነውና በያለንበት አክብረን እንያዘው – በሚገባ ጠብቀነውም ለትውልድ እናስተላልፈው፡፡ ሕዝብ ደግሞ እንደሕዝብ አጥፊ ያለው አይመስለኝም – ጥፋት ካለም በአብዛኛው ከአመራር ጉድለት ነው፡፡ አጥፊው ተማርኩ ብሎ በጥሬና ብስል መካከል ያለው ነገር ፈታይ ዜጋ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በቋንቋና በፊደሉ ገብተው ሊከፋፍሉት የሞከሩት – ለምሳሌ – የሕዝቡን ፈቃድና ይሁንታ አግኝተው ሳይሆን የወያኔን አጀንዳ ለማስፈጸም ዘብ በቆሙ ጥቂት መሠሪዎች አማካይነት መሆኑ ይታወሰኛል፡፡ ይህ ሁሉ ይስተካከላል፡፡ ከልብ እናምናለን፡፡ እስኪያልፍ ያለፋናል እንጂ ኢትዮጵያችን ከቀድሞው በተሻለና በበለጠ ሁኔታ አብባና አፍርታ እናያታለን፡፡

ይህችን ኢትዮጵያ ለማየት ግን ከእያንዳንዳችን ብዙ እንደሚጠበቅ መረዳት አለብን – በተለይ ከጦሩና ከደኅንነት ከፖሊሱም፡፡ ሰሞኑን ኃይለኛ የተኩስ ልምምድ ላይ እንደምትገኙ እናውቃለን፡፡ ሌሊትና ቀን በፈረቃ ነው እየተለማመዳችሁ ያላችሁት – ይህንንም እናውቃለን፡፡ የምትለማመዱትም እኛኑ – ደመወዝ የምንከፍላችሁን – የገዛ ወንድም እህት አባትና እናታችሁን – በገዛ ገንዘባችን በተገዛ መሣሪያና ጥይት ልትገድሉ ነው፤ ይህ የግፍ ግፍ መሆኑን ልትረዱ ይገባል፡፡ ዛሬን ብቻ አይደለም ማየት፡፡ ዐይናቸሁን ክፈቱ – ትናንትናንና ነገንም ቃኙ፡፡ ተመሳሳይ ጥፋት የሠሩ የት ገቡ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ የግፍ ዕዳ ለእናንተም ሆነ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ አታስቀምጡ፡፡ የቀደመው ስህተታችሁን ፈጣሪ ይቅር ይላችሁ ዘንድ እኛም ስለፈጣሪ ብለን ይቅር እንላችሁ ዘንድ አደራችሁን ከእንግዲህ ወዲህ በቁም የሞተ በድናችን ላይ እየተኮሳችሁ ለብዙ ጊዜኛ አትግደሉን፤ እስኪ እናሳዝናችሁ፤ መግደልም ይሰልቻችሁ፤ ማሰርና ማሰቃየትም ይሰልቻችሁ፤ መግረፍም ይብቃችሁ፡፡ ትውልድ ይትረፍ በእኛም ይብቃ፡፡ ይህን ምክር ባትሰሙ ይበልጥ ተጎጂዎቹ እናንተ እንጂ እኛ አይደለም፡፡ እኛማ ዘጠኝ ሞት መጣባችሁ ስንባልና አንዱን አስገባው ስንል ነው የኖርነው፡፡ ምን ሊቀርብን? እናም አሁንም ልድገመው በፈጠራችሁ ይሁንባችሁ መግደል ይሰልቻችሁ፡፡ መለስ የተፈጠረበት ስለሆነ ካልገደለና ካልዋሸ ጤንነት አይሰማውም – መግደልና መዋሸት ከባሕርይ አባቱ ከዲያብሎስ የታዘዙለት የዕድሜ ማራዘሚያ መድሐኒቶቹ ናቸው፡፡ ደግሞም እኮ ሰሞኑን ስታዩት – ያ አበበ ገላው የተባለ የጋራ እናታችን ልጅ በጌቶቹ መሀል ቀልቡን ከገፈፈው ወዲህ አባቱ ሰይጣን ከድቶት ጤና ርቆታል፡፡ ከአንገቷ በላይ የምትታይ የገረጣች ፍየል መስሎ አላያችሁትም? ያን ምስሉን እስኪ ከባለ አምስት ጫፍ የሰይጣን ዓርማ ጋር አስተያዩት – አንደኛው ጫፍ ወደመሬት ከሚያመለክተውና የፍየልን ምሳሌ ከሚያጣቅሰው የጨለማው ንጉሥ ዓርማ ጋር ስናስተያየው ቆሌ የራቀው ፎቶና የኮከቡ ምስል ቁርጥ ቁምጥ አንድ ናቸው – ራቅ ቀረብ እያደረጋችሁ ተመልከቱት፡፡ ገብቶ እሚወጣው መቼም በዲያቢሎስ እርዳታ መሆኑን ሳታውቁ አትቀሩም፡፡ መግደል፣ መዋሸት፣ማታለልና ማጭበርበር፣ አልጠግብ ባይነት፣ ትምክህትና ትዕቢት፣ ዕብሪትና ማንአለብኝነት… የሰይጣን እንጂ የእግዚአብሔር ገንዘቦች እንዳልሆኑ እናውቃለን፡፡

በሚዲያው ውስጥ ያላችሁትም ብትሆኑ በፍጥነት ከዚህ አሳፋሪ የወያኔ ፕሮፓጋንዲስትነት ውጡ፡፡ በልታችሁ ላትጠግቡ፣ ጠግባችሁ ሰውነት ላይሆናችሁ ስም አይሁንባችሁ፡፡ ብትችሉ ሌላ የተሻለ ወይም ተቀራራቢ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ፈልጉ፡፡ ያም ባይሆን የቀን ሥራ ሥሩና ነፍሳችሁን አውላችሁ አሳድሩ፡፡ የሚያስዋሽና ኅሊናን የሚያስደብቅ ሆድ ነው፡፡ የሆነ ቢሆን ግን ለሆድ ወይም ለማይረባ ወፍ ዘራሽ ወያኔያዊ ዓላማ ብላችሁ ታሪካችሁን አትግደሉ፡፡ ልጆቻችሁ አንገታቸውን ደፍተው የሚሄዱበት ዘመን በሩጫ እየመጣ ነው፡፡ ሁለቱ የኢትዮጵያ ጠላቶች በተመሳሳይ ወቅት የጤና ችግር ውስጥ መገኘታቸው ራሱ ምልክት ይሁናችሁ፡፡ ሰው ጠላ እግዜር ጠላ፡፡ ለየትኛው ጊዜ ብላችሁ እጃችሁን በደም ታጨማልቃላችሁ?ኧረ ወደዚያ ይቅርባችሁ፡፡

በውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ከተኛችሁበት ንቁ፡፡ በረባ ባልረባው ስትጨቃጨቁ ጀምበር እንዳትጠልቅባችሁ አስተሳሰባችሁንና አመለካከታችሁን ለሕዝብ ፍላጎት በሚቀርብ መልክ ቃኙ፡፡ ሕዝቡ ትቷችሁ ሄዷል፤ ግን ለጊዜው ሞኝና ፈሪ ሊመስል ይችላል፡፡ እናንተ – ዛሬ በተመስገን ጦማር እንዳየሁት – እጠቅሳለሁ “(መቼም ከላይ የተጠቀሱትን ሀገርና ድርጅቶች በጨረፍታም ቢሆን የሚያውቅ ግለሰብ እነዚህ ኃይሎች ‹ፍትህን መደገፍ› በሚል አጀንዳ ቀርቶ፣ በሀገሪቱ የቀን አቆጣጠር ሥርዓት እንኳ በጋራ እንደማይስማሙ ይረዳል። ለዚህም ነው አዲስ ዘመን እንዲህ በአንድ ላይ ሊያሰልፋቸው የቻለበትን ምክንያት ከጋዜጣው አለቆች ባሻገር ሰይጣንም ቢሆን አያውቀውም እያልኳችሁ ያለሁት)” ሲል እንደጠቀሰው ከሆናችሁና ይህ አባባሉ ውሃ እሚያነሳ እውነታ ያለው ከሆነ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የምትገኙ ትመስሉኛላችሁና ጀምበር ሳትጠልቅባችሁ ዕወቁበት፡፡ ለቀን አቆጣጠር ስምምነት አሥር ዓመት፣ ለፊደል አሥር ዓመት፣ ለሀገር ስያሜ አሥር ዓመት፣ ለፌዴራል ክልል አሥር ዓመት፣ ኢትዮጵያዊነት ለመቀበል ለሚደረግ ድርድር ሃያ ዓመት፣… እየተባለ ጊዜ የሚመደብና የሚባክን ከሆነ እንኳንስ ከመቶዎች ዓመታት በኋላ አሁን በምንገኝበት ሁኔታና በወያኔው አያያዝ ከአምስት ዓመት በኋላም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከዓለም ካርታ ትጠፋለች(ቋንቋ ለማሳመር ነው ባካችሁ – እንኳን ልትጠፋ ገና የብዙዎች መጠጊያ ትሆናለች!)፡፡ ደግሞም እንዲህ ስል አታኩረፉኝ፡፡ እውነትን እንደወረደ እንነጋገር፡፡ ማኩረፍ በምንም መንገድ መቅረት አለበት – ይህንን ዘመን ሊሻገር አይገባም፡፡ እረኞችና ሕጻናት እንኳን ትተውታል አሉ፡፡ ቃልን በቃል፣ሐረግን በሐረግ፣ ዐረፍተ ነገርን ባረፍተ ነገር፣ አንቀጽን ባንቀጽ፣ ግጥምን በግጥም … በሰላማዊ መንገድ መመለስ እንለማመድ፡፡ ግንፍልተኝነትና ፍረጃ ይቅር፡፡ ‹አሃ! እንዲህ ስለሆነ አይደል?…›ማለት ይቅር፡፡ ምናባዊና እውናዊ የሸሚዝ እጅጌን መሰብሰብ ከእንግዲህ ይቅርብን – አንድ ጋትም ወደፊት ሊያነቃንቀን አልቻለም፤ በዚህ የጀብደኝነትና የእልህ ባህል ተመርዘን ባለንበትም መሄድ አቅቶን የኋሊት ሽምጥ እየጋለብን እንገኛለን፡፡ የምንፈርጀውን ዓይነት ሰው ቢሆንስ? ምን አለበት? የምንቃወመው ሃሳቡን ነው ወይንስ ሰውነቱን?… ሃሳቦቻችን ይጋጩ፤ይፋጩ፡፡ ከዚያም በአብዛኛ ድምፅ ነጥረው አሸናፊዎቹ ወደ አደባባይ ይውጡ፡፡ ኧረ ጥቂት ጥቂት እንሰልጥን! አእምሮኣዊና ቁሣዊ ሥልጣኔ አልናፈቀንም? እስከመቼ ጅራትና የዓለም መሣቂያና መሣለቂያ ሆነን እንኑር?
ለሁሉም ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነው ነገሩ፡፡ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ሁሉም ያልፋል፤ በጥባጩ ይሞታል – በተፈጥሮና በአደጋም ቢሆን – ደህናውም ይወለዳል፡፡ ያኔ ጠማሞቹ የእፉኝት ልጆች ቦታ ቦታቸውን ሲይዙ በጠራው ሰማይ በመላእክቱ ከዋክብት አጀብ የሚወለዱት (የተወለዱት) እነእንስፍስፍ አንጀቶች የሀገሪቱን የሥልጣን ሥፍራ ይረከባሉ – ከየጎሣና ነገዱ፡፡ የዘረኝነትና የሃይማኖት ልዩነት ተንቆ ሰብኣዊነትና ብሔራዊ ስሜት ገዢዎቻችን ይሆናሉ፡፡ ባለፈ አስቀያሚ ታሪክ የምናፍር በአዲስ የጋራ ስብዕና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የምንተጋ እንሆናለን፡፡ አሁን ያን ምን አስቀላመደኝ ልጄ? ወጡ ሳይወጠወጥ አሉ!
ታምረኛው ረጋ ሠራሽና እጅግ አስቂኙ ወያኔ ለተመስገን ደሳለኝ በቀሺም ደራሲ ተጽፎ የተላከው ኢሜይል ይህ ነው፡-(የቋንቋውን ነገር አታንሱት – በሁሉም ማፈሪያዎች!)

“To Ato Temesgen Desalegne
Chief Editor of Fitih magazine
Ethiopia

It has to be remembered that AlShebab has assigned me secretly to make propagation activities in Ethiopia, Somaliland, Kenya and Uganda. To accomplish the task we have agreed with you through your representative Ato Mamush Sentie in Eritrea to publish propaganda articles against the Ethiopian government, against the interest of the Ethiopian people and the American government. It has to be remembered that we have paid US dollar 24,000 for 30 consecutive editions. Now alshebab has made strategic change to accomplish its tasks. Therefore we need the 14 edition charges US dollar 11,200 dollar to alshebab. We believe that you will return back the money to our organization. If this is not fulfilled on time you will bear a cost on your representative Ato Mamush Sentie and your life according to the rule of the organization.
Alshebab wins
Ahmedin Nasir”