አቶ መለስ ይቺን ጽሑፍ ቢያነብልኝ ዕድለኛ ነኝ! ፍቅር ይበልጣል
አሁን ይህችን ጽሑፍ ስከትብ አዲስ አበባ አካባቢ ዝናብ እያካፋ ነው፡፡ በውጭ ለምትኖሩ ይህ ወሬ መልካም ዜና ነው፡፡ ፀሐይዋ አናት እየበሳች ተቸግረን ከረምን፡፡ የዝናብ መጥፋት በቅድሚያ ለእህል ዘር መጥፎ ነው፡፡ ቀጥሎም የአካባቢ ሙቀትን በመጨመር ለአየር ንብረት መዛባትና ለበረሃነት መስፋፋት እንዲሁም ለሰውና ለእንስሳት ሕይወት መጥፎ ነው፡፡ አሳስቦን ነበር ተመስገን፡፡ በዚሁ ያዝልቅልን፡፡ በሁሉም መበደል አይገባንም፡፡ ፈጣሪ እንዲህ ፊቱን ሲመልስልንና የተቃጠለውን ምድር ቀዝቀዝ ሲያደርገው እሰዬው ማለትና ማመስገን ተገቢ ነው፡፡ የዝናመ ምሕረቱን ፊት መለስ እንዳደረገልን ሁሉ የመለስንም ጭካኔና ዕብሪት በነካ ዕጁ ከላያችን እንዲያነሳልን እንለምነው፡፡ የሚሳነው ነገር ስለሌለ ዳንኤልን ከአንበሣ ጉሮሮ፣ አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል እንዳወጣቸው ሁሉ እኛንም ከተማገድንበት ወያኔያዊ እቶን ባፋጣኝ ነጻ እንዲያወጣንና ከፍጻሜው በፊት ጥቂትም ቢሆን ጊዜ ሰጥቶን ቅጥ ያለው ሕይወት እንድንኖር በኪነ ጥበቡ ይታደገን፤ በፀጋውም ይገብኘን፡፡
በነገራችን ላይ ስሜ የቀድሞውን የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅር ይበልጣልን መሰለብኝ እንጂ እርሱ እንዳልሆንኩ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ እርሱ አምላክ ልመናውን ሰምቶት በደህና ጊዜ ከሀገር ኮብልሎ ከእሳት አምልጦኣል፡፡ አለን እንጂ እኛ በኢሕአዴግ የፍም አለንጋ በዕድሜ ይፍታህ እየተሞሸለቅን የምንኖር፡፡
ጥሩ ነገር ልናገር አንደበቴን አላላውስም፡፡ ጥሩ ነገር ስለሌለ፡፡ ጥሩ ነገር የሌለው በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለምም ነው፡፡ የኛ የሚለየው የደርግ መንግሥት አርሶና አለስልሶ ባዘጋጀው የፖለቲካ ቅብቅብ ላይ በቅሎ የጎመራው የወያኔ መንጋ ያ የ69 እና የ70 ዓ.ም. የቀይና የነጭ ሽብር የታሪክ ጠባሳችን ትቶት ያለፈውን አእምሮን ዳተኛ የሚያደርግ ጭፍግ ሁኔታ በመጠቀም ሕዝቡን ባልተወለደ አንጀት በመሪር አገዛዝ እንደባብ ራስ ራሱን መቀጥቀጡ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በገሃድ ከሚታየው የዘረኛ አገዛዝ የአድልዖና የፍትህ መዛባት ያንንም ተከትሎ ከተከሰተው የሙስናና ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በስተቀር እንደኢራቅና እንደአፍጋኒስታን በየቀኑ የብዙዎችን ዜጎች ደም አለመገበራችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ወያኔ የሚሠራው ግፍና በደል በተጠቀሱት ሀገሮች ከምንሰማው የየዕለት ዕልቂትና ውድመት የማይተናነስ ከባድ ሸክም መሆኑ ባይካድም በለየለት ሁኔታ እንደነዚያ እቶናዊ የእሳተ ገሞራ ሀገሮች ብንሆን ችግራችን ቦሃ ላይ ቆረቆር ሊሆን እንደሚችል ለመጠቆም ወድጄ እንጂ የኛም ችግር በራሱ በዓለም ተወዳዳሪ እንደሌለው ዘንግቼው አይደለም፡፡
ምሥራቅ ሊቢያ ነገር ከተቆሰቆሰ አንድ ወር ገደማ ሆነው፡፡ ምሥራቅ ጃፓን ደግሞ ተፈጥሮ ጦሩን ከሰበቀባት አምስት ቀናት አለፉ፡፡ ሁለቱንም ሰው ሠራሽና ተፈጥሮኣዊ ክስተቶች በየደቂቃው እየተከታተልን ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ከነዚህም ሆነ እነዚህን ከመሰሉ ሌሎች ዓለም አቀፍ ክስተቶች ሌሎቻችን ብዙ ልንማር በቻልን ነበር፡፡ ግን እንዳንማር ልባችን ከድንጋይ የተሠራ ይመስል ደደረብን፡፡ የፋሲካ በግ በገና በግ ይስቃል እንደሚባል ብዙዎቻችን የዓለም ዜጎች በሩቅ የምናየው እሳት አጠገባችን ደርሶ እስኪፈጀን ድረስ አይገባንም፡፡ ምን ዓይነት ተፈጥሮ እንደሆነ ይገርማል፡፡
ሊቢያ ለምን እንደዚያ ያለ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ገባች? ከጋዳፊ ምን መማር ይቻላል? ከሕዝቡስ? ከቱኒዚያ፣ ከባሕሬን፣ ከግብጽ፣ ከየመን፣ ከኮት ዲቫEር፣ ከኢራቅ፣ ከአፍጋኒስታን፣ ከጃፓንና ባጠቃላይ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ተንሰራፍተው ከሚገኘባቸው ሀገሮች ምን ትምህርት መቅሰም ይቻላል? ዓለም ወዴት እያመራች ነው? ለምን? በዚህ ዓይነት ስፋትና ጥልቀት ያለው ሁኔታ ዓለም በመከራና በመቅሰፍቶች ተወጥራ ስትናጥ ታይታ ታውቃለች ወይ? ይሄ ሁሉ ጣር የምን ምልክት ነው? መጨረሻውስ ምን ሊሆን ይችላል? ከአደጋ ማምለተ የሚችልስ ማን ነው? የሠለጠነ ሀገርና ሕዝብ ወይንስ ሁዋላ ቀር ሀገርና ሕዝብ? ይሄ ሁሉ ትርምስ የምን ውጤት ነው? የክፉ ስራ ወይንስ ጽድቅ? ለበረከት መጣ ወይንስ ለመርገምት?
ትናንት ማታ በሰላም እራት በልተው የተኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከማግሥቱ ጀምሮ ባልታሰበና ባልተጠበቀ አደጋ በሞት ሲነጠቁ እያየን፣ ከመኖሪያቸው በመፈናቀል በድንካEንና በሜዳ ላይ ለዝናብና ለጎርፍ ለርሃብና ለጥማት ሲዳረጉ ባይናችን በብረቱ እየተመለከትን መጪውን ጊዜ ማስተዋል ያቃተን ለምን ይሆን? ምን ዓይነት የዝንጉነት ቃል ኪዳን ይሆን በየልባችን የተሰነቀረውና ነገን እንዳንመለከት የብረት ግርዶሽ የሆነብን? ሁላችን እናስበው እስኪ፡፡
የጃፓን ብዙ ጠረፋማ አካባቢዎች ከዓለም ካርታ ተፍቀዋል – ከነነዋሪዎቹና በላያቸው ላይ ከነበረው ሀብትና ንብረት ጭምር፡፡ ቀሪዎቹም በኒኩሌር ስጋት ተወጥረው ከቤት እንዳይወጡ ታዘዋል፡፡ ጃፓን እየተናጠች ነው፡፡ የነገውን እሱ ይወቅ፡፡ እንዲያውም የኒኩሌር ጣጣና መዘዝ በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ ነግ ከነግ ወዲያ የሥጋቱ መጠን የትኛውን የዓለም ክልል ሊሸፍን እንደሚችልም መተንበይ አይቻልም፡፡ እናም ችግሩ ተወጠነ እንጂ መጠኑ ወይም ልኩ ገና አልታወቀም፡፡ የተፈጥሮ አደጋውም እንዲሁ በጃፓን ጀመረ እንጂ ነገ የት ሊቀጥል እንደሚችል መገመት ያስቸግራል፡፡ አንድ ነገር በርግጠኝነት ማለት የሚቻለው ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 መሠረት ከእንግዲህ የሚቀጥል እንጂ የሚያቆም የተፈጥሮ ሠራዊት ሊኖር እንደማይችል ነው፡፡ የተፈጥሮ ሠራዊት ደግሞ እሳት፣ ውሃና ንፋስ ናቸው፡፡ እሳትና ውሃ ካለተፈጥሮኣቸው በአንድ የጦር ዐውድ ተሠልፈው ምን ያህል ውድመት እንዳደረሱ በቀደም ዕለት በጃፓን ተመልክተናል፡፡ የሚገርም ቅንብር፡፡ የሚያስደንቅ ታዛዥነት፡፡ እሳትና ውሃ ተቃራኒ ሆነው ሳለ በፈጣሪ ትዕዛዝ ኅብረት ፈጥረው አንዱን ሲያቃጥሉ ሌላውን ሲያጥለቀልቁና በአሥር ሜትር ከፍታ የአምባላይ ፈረስ ሽምጥ ግልቢያ ትላልቅ ጀልባዎችንና ሕንጻዎችን እንዳልነበሩ ሲያደርጉ አይተናል፤ የምፀዓት ቀን ነው የሚመስለው፡፡ ይህ የተቃራኒዎች ኅብረት እያስከተለ ያለው መዘዝ ምንድነው? ሰውስ ቆም ብሎ ፤ ‹አሃ! ምንድን ነው እያየሁት ያለሁት?› በማለት ወደየኅሊናው የማይመለሰውና በተለይ ክፋትን የማይተወው ለምን ይሆን? እኔም አንቺም እሱም ሁላችንም ለምን ይሆን ፍቅርን እርግፍ አድርገን ትተን በጭራሽ የማይጠቅመንን ጠብን ሙጭጭ አድርገን የያዝነው? እነሱም እነዚህም እኒያኛዎቹም እኒህኛዎቹም ለምን ይሆን እሳቱ እበራፋቸው መጥቶ እስኪያንገበግባቸው የሚጠብቁት? ስንት ዓመት ለመኖር? ከፍቅርና ከጠብ የትኛው ይበልጥ የሚያተርፍ ሆኖ ይሆን?
እንደ አቶ መለስ የሰሞኑ ቅጥ ያጣ ውሸት ውስጥ ተዘፍቆ ማንንም ላያታልሉና ላያሞኙ በከንቱ ትዝብት ውስጥ መግባቱ ለምንና ከአሁን በሁዋላስ ስንት ሺህ ዓመት ለመኖር ነው? ያ ሁሉ የጋዳፊ ንብረት ምን ዱብ ዕዳ እንደደረሰበት ማየት አይበቃም? ያ ሁሉ የጋዳፊና የመሰሎቹ በትዕቢት መነፋትና መሬትን እየተጸየፉ እንደነብር መቆነንና እንዳንበሣ መቆለል የት አደረሳቸው? አሁን አልተዋረዱም? ‹ቦዕ ጊዜ ለኩሉ›ምን አላስታወሱንም? በአንጻራዊ አነጋገር ያ ሁሉ ጃፓናዊ የምቾት ነዋሪ ሕዝብ በሴከንዶች ውስጥ የዶግ አመድ ሲሆን ማየቱ አንዳች ትምህርት አይሰጥ ይሆን? ረ አቅል ይስጠን የተወደዳችሁ ወገኖች! በእውኑ ምን ነክቶን ይሆን በተለይ እኛን ኢትዮጵያውያኑን እንዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈጩ ጥሬ የምንሆነው?
‹ምክር የድሃ ነበርሽ ማን ቢሰማሽ› ይባላል፡፡ አቶ መለስም ሆነ የርሱን መንገድ የሚከተሉ ሁሉ አሁንም ቢሆን ወደ ኅሊናቸው ተመልሰው የዓለምን ወቅታዊ ሁኔታ በጥሞና ቢያጤኑና የነገውን ክስተት ቢገምቱ ይጠቅማቸዋል እላለሁ፡፡ አቶ መለስ የዐይነ ልቦናውና የዕዝነ ኀሊናው ታምቡሮች ጨርሶውኑ ካልተበጣጠሱ በስተቀር አሁን የማስተዋል ጊዜ ላይ መድረስ ይገባው እንደነበር በፍጹም ልቤ አምናለሁ፡፡ በነገራችን ላይ መለስ ወደፈጣሪ ይመለሳል የሚል ህልምና ቅዠት ባይኖረኝም አንድ ቀን ወደኅሊናው ተመልሶ ከሚያደርጋቸው ጠያፍ ኢሰብኣዊ ተግባራቱ ይቆጠባል የሚል ተስፋና ምኞት ግን ነበረኝ፡፡ አሁን አሁን ግን ተስፋየ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየማEሸሸ መጥቶ ከነጭርሱ በንኖ ጠፍቶኣል፡፡ በተለይ ከሰሞኑ ቃለ ምልልስ ተብዬ የተገነዘብኩት ነገር መለስ ከእንግዲህ በምንም ዓይነት መንገድ የጤናማ ኀሊና ባለቤት ይሆናል ብሎ መጠበቅ በጭራሽ ዘበት መሆኑን ነው፡፡ የጋዳፊን እንዲያ መዋረድ፣ የቤን አሊን እንዲያ መዋረድ፣ የሙባረክን እንዲያ መዋረድ፣ የሳለህን እንዲያ መዋረድ፣ የዚህን ሁሉ አጭበርባሪና አምባገነን መሪ መዋረድ ባይኑ በብረቱ እያየ ቅንጣት ትምህርት መውሰድ ያልቻለና እንዲያውም ይባስ ብሎ የነዚህን መሪዎች ኢዴሞክራሲያዊነት በመግለጽ እሱ ግን በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሣጥን ወደሥልጣን እንደወጣ የሚለፍፍ ሰውዬ ከአሁን በሁዋላ ልብ ይገዛል ማለት በፍጹም አይቻልም፡፡ ሰውው አንድም ራሱን ኤውቅም አለበለዚም እኛን አያውቀንም፡፡ ውሸት ለከት አለው፤ ውሸት ገደብና ይሉኝታም አለው፡፡ የመለስን ቅጥ ያጣ ውሸት ግን ሌላ ስም ልንፈልግለት ይገባል እንጂ በምናውቀው ቃል እንዳለ በቁሙ ‹ውሸት› ማለቱ በጣም ያንሰዋል፤ በጭራሽ አይገልጸውምም፡፡ እንዴ? እንዲጠየቅ የሚፈልገውን ጥያቄ ብቻ በሚፈልጋቸው ጠያቂዎች እየተጠየቀ # ደመወዜ 6ሺህ 400 ብር ናት፤ አዲሱን ጭማሪ ገና አልበላሁም፡፡ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ጭማሪው ድሃውን ሳይሆን ሀብታሙን ነው የሚጎዳው፡፡ ሕዝቡ ኢሕአዲግን በሙሉ ድምጽ በመረጠ ገና በአሥር ወሩ የተዋዋልንበት ፊርማ ሳይደርቅ ኮንትራቱን ሊቃወም ስለማይችል ኢሕአዲግ ሕዝባዊ ተቃውሞ አያሰጋውም፡፡ የሚያሰጋው በኮንትራት ውሉ መሠረት ሥራውን መሥራት አለመሥራቱ ነው፡፡ ሕዝቡ ሲፈልግ ከአራት ዓመት በሁዋላ በሚደረገው ምርጫ ኢሕአዲግን በዝረራ ሊያስወግደው ወይም ቀጥል ሊለው ስለሚችል የምርጫ ካርዱን ይጠቀማል እንጂ ሥራ ፈትቶ ኢሕአዲግን ለመቃወም ለአመጽ አይጋበዝም፡፡ … $ የሚል የፕሮፌሽናል ውሸት ፋብሪካ እንዴት በቀላል አገላለጽ ‹ውሸታም› ብቻ ተብሎ ሊታለፍ ይችላል?
ለማንኛውም እሱ በወደደው መንገድ መሄድን ከመረጠ የራሱ ምርጫ ነው፤ እንደኛና ስለኛ ከሆነ ግን ይህን ምርጫ ባይከተል ከብዙ ኪሣራ እንድን ነበር ብለን መቆጨት እንችላለን፡፡
ይሁንና ከእርሱ ጋር ላላችሁ የጦሩም ሆነ የጸጥታውና የሲቪል ሠራተኞች አጭር መልእክት ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ ከዓለም ወቅታዊ ተጫባጭ ሁኔታ ተማሩና ሠልፋችሁን በቶሎ አስተካክሉ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ፍቅር እንደሚበልጥ ዕወቁ፡፡ ሕዝብ ፍቅር ነው፡፡ ከሕዝብ የሚያፈነግጥ ግን እርኩሰት የተጠናወተው የአምባገነኖች አሽከርና ሎሌ ነው፡፡ መጨረሻውም አያምርም፡፡ እነሱ ሲወገዱ መውደቂያ የሌለው ተንከራታች ሆኖ ይቀራል፡፡ በምሳሌ ጊዜ አላባክንም እንጂ በርካታ ምሳሌዎችን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ መጥቀስ በተቻለኝ፡፡ ዋናው ግን ለአንዲት እንጀራ ብላችሁ ታሪካችሁንና የልጆቻችሁን ሀገራዊ ኩራት አታበላሹ፡፡ በመለስ ቆዳ እንደማትቀበሩ ተረዱ፡፡ ለቁራሽ እንጀራ ብላችሁ ወርቃማ ዕድላችሁን አታጥፉ፡፡ ሚናችሁን ለይታችሁ ተቀመጡና ሕዝቡ እምቢዬው አምባገነንነት በቃኝ ሲል ደጀን ሁኑት፡፡ አቅሙና ድፍረቱ ካላችሁም ሕዝቡን ሳትጠብቁ የጀግንነት ሥራ ሠርታችሁ በታሪክ ተመዝግባችሁ እለፉ፡፡ ማለፍ ደግሞ መቼም ቢሆን አይቀርም፡፡ በጉንፋንና በእንቅፋት ምርቀዛም ሰው ይሞታል፡፡ ቤት ለእንግዳ ከተባልኩ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡ ለዛሬ ደህና ሁኑልኝ፡፡ በዱር በገደል በስደትና በእንግልት ላይ ያሉ ሁሉንም ልጆችዋን ጨምሮ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ሁላችንንም ለትንሣኤዋ ያድርሰን፡፡ አሜን፡፡