ቢደርስባችሁ ምን እርምጃ ትወስዳላችሁ
ይህቺን አጭር ጽሁፍ ለአንባቢያን አስተያየት እንዲሰጡበት ታደርግልኝ ዘንድ በመተማመን ነው፡፡
እኔ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ሠራተኛ ስሆን ባለቤቴ የመንግሥት ሠራተኛ ነው፡፡ እኔና ባለቤቴ የ4 ልጆች የአብራካችን ክፋዬች አሉን ፡፡ ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ ቤታችን ሰላም በማጣት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን፡፡ ቤቴንና ልጆቼን ጥዬ እንዳልወጣ በልጆቼ ላይ የሚደርሰው የሥነ ልቦና ቀውስ ከባድ መሆኑ ይታየኛል፡፡ ሁሉን ችዬ ልኑር ብዬ ሳስብ እስከመቼ ሰው በአንድ ጣሪያ ሥራ እየኖረ ቢያንስ ስለልጆች ጉዳይ እንኳን ሣይነጋገር ለዓመታት ይቻላል፡፡
ልጆቼ በእርግጥ አሁን በትምህርታቸው ዩኒቨርሲቲ ደረጃ የደረሱ ናቸው፡፡ ልጆቹ ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ልቻልና ላስጨርስ ብል የማየው ነገር ማለት በር ዘግቶ መቀመጥ፣ ምግብ መኝታ ቤት ድረስ እየተወሰደለት እኔ የሠራሁትን እየበላ እኔን ለዓይኑ እየጠላ የሚያደርገው ነገር እኔን በጣም እያበሳጨኝ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ዝምታ ወርቅ አይደለም በሚል ርዕስ በተጻፈው ሥር የኔን ቤት አስቀምጬ ስመለከተው እስከመቼ ድረስ ልቀጥል እችላለሁ የሚል መልስ የማላገኝለት ጥያቄ ያስጨንቀኛል፡፡
ተነጋግሬ ያለብንን ችግር የመፍታትም ሆነ የመለያየት ነገር የሚኖረው የቤቱ ምሰሶዎች ሲነጋገሩ ብቻ መሆኑ በእርግጠኝነት ባምንበትም ከሱ በኩል ግን የማገኘው ምላሽ ምንም የለም ለመነጋገርም ፈቃደኝነት የለም፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምንድነው ብትሉኝ እባክህ ለቤታችን ሰላም የማትሰጥ ሴት ገብታለችና ከሷ ጋር ሌላ ግንኙነት ባይኖርህም ከሥራ ስትወጣና ስትገባ በሰፈር ውስጥ መታየት ለኔም ሆነ ለአንተ በአጠቃላይ ለቤተሰባችን እዚህ ጋር ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው /ሴትየዋ ባል የሌላት በመሆኗ ነው/ ጥሩ ባለመሆኑ በአንድ ሠርቪስ ብትጠቀሙም አብረህ አትታይ አትውጣ አትግባ ብዬ በመናገሬ ይኸው ለ3 ተከታታይ ዓመታት ቤቴ ሰላም አጥቶ ልጆቼም ግራ እንደገባቸው ይገኛሉ፡፡
ሶስቱ የተሳሳቱ ምዕራፎች የሚለውን ሰኔ 8/2012 የጻፍከውን አንብቤ እስኪ ይሄ የሚመልሰው ከሆነ ላድርገው ብዬ ከራሴ ጋር ብነጋገርም ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጊዜ እባክህ ቤታችን አይበተን ልጆች ጐዳና አይውጡ ይሄንን ኩርፊያህን ትተህ ወደነበርንበት ሰላማዊ ኑሮ እንመለስ ብዬ ይቅርታ የጠየቅሁ በመሆኔ ድርጊቱን ለመፈጸም ጭራሽ ተሸናፊነት ሆኖ ነው የተሰማኝ፡፡ ከዚህ በሚተርፈው ግን ከሴትየዋ ጋር ያለህን መውጣትና መግባት ግን እንዲተው ያደረኩት ይሄው ኩርፊያው ምክንያት የሆነችው ከሷ ጋር ሲሄድና ሲመለስ ምንም ዓይነት የመናደድም ሆነ የማኩረፍ ጸባይ ስለማላይበትና እኔ ላይ ይሄንን ድርጊት በማድረጉ በመሆኑ ነው እንጂ ያየሁትም ሆነ የሰማሁበት ሌላ ጸባይ ኖሮ አልነበረም፡፡
ይህ የመቀራረብ ነገር ምናልባትም አዝማሚያው ወደማልፈልገው አቅጣጫ ሄዶ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ራሴን እንዳልጐዳ በሚል እንጂ አድርጓል ብዬ እርግጠኛ የምሆንበት ምንም ማስረጃ በሌለኝ እሱን ለመወንጀል ራሴን ንጹህ ለማድረግ ብዬ አይደለም፡፡ አሁን በቤት ውስጥ ያለን ግንኙነት የጠላት ያህል እንጂ እውነት ልጆች አፍርተን ክፉ ደጉን ተነጋግረን ተሳስቀን ያሳለፍን ሰዎች አንመስልም፡፡ ልጆች ገብተው እንዲያወያዩን ባደረኩት ጥረት ጭራሽ ልጆቹ ላይ የጥላቻ ስሜት የወገናዊነት ስሜት ያሣዩ አድርጐ ስላሰበው በዚህ ጉዳይ ዳግመኛ እንዳይገቡ እኔም እነሱም ወሰኑ፡፡ በሃይማኖቴ የኦርቶዶክ ሃይማኖት ተከታይ ነኝ ጉዳዩን ወደ አባቶች ሊመክሩት ቢሞክሩም ስልኩን ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ እነርሱን ይቅርታ ጠይቄ ተውኩት፡፡ እስኪ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ቢደርስባችሁ ምን እርምጃ ትወስዳላችሁ፡፡
ከአዳማ