ዕውቀት እንረዳለን
አራተኛ ክፍል እያለሁ የሂሳብ መጽሐፍ ለአራት ነበር የሚታደለን፡፡ ታድያ የቤት ሥራ የተሰጠ ቀን መጽሐፉን ለመውሰድ ተረኞች ያልነበርነው ሦስታችን የቤት ሥራውን ስንገለብጥ ከተማሪው ሁሉ ወደ ኋላ እንቀር ነበር፡፡ ሕፃናት ስለ ነበርን፣ ከዚያም የተሻለ ስላላየን መጽሐፍን ለአራት ለአምስት መውሰድ የዓለም ሥርዓት መስሎን ነበር ያደግነው፡፡ የመጽሐፍ ኮንደሚኒየም አትሉም፡፡
የሚገርመው ነገር ይህ አሠራር በሁለተኛ ደረጃም ሆነ በኮሌጅ ደረጃ ሳይሻሻል ነው እኛ ትምህርት «ጨርሰን» የወጣነው፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ እያለሁ እንድናነብ የሚሰጠንን መጽሐፍ ቤተ መጻሕፍት ሄዶ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሌላ ሰው ቀድሞ ያወጣውና ወረፋ ያዙ እንባላለን፡፡ ወረፋው ሳይደርሰን ፈተናው ቀድሞ ይደርሳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከነ አካቴው መጽሐፉ አይኖርም፡፡ ምነው? ስንል «መምህሩ አውጥቶታል» እንባላለን፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ «በኮርስ አውት ላይኑ» ላይ ያለው የመረጃ መጻሕፍት ዝርዝር ከሌላ የተገለበጠ ይሆንና ቤተ መጻሕፍቱ እንኳን ሊኖረው ሰምቷቸውም አያውቅ፡፡
እንዲህ እኛ መጽሐፍ ብርቅ ሆኖብን አድገን በኋላ ገዝታችሁ አንብቡ ስንባል ውቃቤ ሊቀርበን አልቻለም፡፡ እኛ በመጽሐፍ መከራ እንጂ መች ደስታ አይተን እናውቅና፡፡ ታች ክፍል እያለን መጽሐፉን እንድንጠቀምበትና እንድንፈተፍተው የሚፈቅድልን አልነበረም፡፡ ወላጆቻችንም አነበባችሁ? ከሚሉን ይልቅ «ዋ መጽሐፉ ይቀደድና የሚከፍልልህ አታገኝም» ነበር የሚሉን፡፡
እንዲያውም አምስተኛ ክፍል አንድ ጓደኛችን ትዝ ይለኛል፡፡ በዓመቱ መጀመርያ ለሦስትም ይሁን ለአምስት ከሌሎች ጋር መጽሐፍ ወስዶ ነበር፡፡ አንድ ሦስቱ መጽሐፍ ለግል ይሰጥ ነበር መሰል፡፡ ታድያ ለግል የሚሰጠውን መጽሐፍ የቤት ሥራውን ከሌሎች ተማሪዎች ሲገለብጥ እናየው ነበር፡፡
በዓመቱ መጨረሻ መጽሐፍ ልንመልስ ስንሰለፍ የርሱ መጽሐፍ አበባ እንደመሰለ ነበር፡፡ አንዳንድ ጓደኞቻችን ተናደዱበት፡፡ «አንተ በኛ መጽሐፍ የምትሠራው የራስህ እንዳይበላሽ ነው አይደል?» እያሉ አፋጠጡት፡፡ እርሱ ግን «ማርያምን» እያለ ይምል ይገዘት ነበር፡፡ ግን ማን ይመነው፡፡ ሲጨንቀውና ከጓደኞቹ ሊቃቃር ሲሆን ጊዜ እውነቱን ነገረን፡፡ «እማዬ ስለቆለፈችበት ነው» አለን፡፡ አንድ ላይ «ለምን?» አልነው፡፡ «ከተበላሸ የምከፍለው የለኝም ብላ ቆለፈችበት»፡፡ አለን አንገቱን አቀርቅሮ፡፡
ምን ያድርግ ለእርሱ እናት ዋናው ነገር ልጃቸው ያመጣው መጽሐፍ ሳይበላሽና ተጨማሪ ወጭ ሳያስ ከትል መመለሱ እንጂ መጠቀሙ አይደለም፡፡ ልጅ እንዳያጠፋ እንጂ እያጠፋም ቢሆን እንዲሠራ ማን ይፈቅድለታል?፡፡ ትምህርት ቤቱም ቢሆን የሚያስጠነቅቀን እንድንጠቀምበት ሳይሆን እንዳናበላሸው ነው፡፡ እኛም የምንጨነቀው ላለማበላሸት እንጂ ለማንበብ አልነበረም፡፡
ይህንን ሁሉ ያመጣው የኢኮኖሚና የአስተሳሰብ ድህነት ነው፡፡ ሀገሪቱ ለመጽሐፍ የምመድበው በቂ በጀት የለኝም፤ ስለዚህ ያላችሁን አብቃቁ ትላለች፡፡ [እዚህ ላይ አንድ የመንገድ ላይ ትዝታ ላውጋችሁ፡፡ አራት ልጆች ወደ አንድ ከተማ ለሥራ ጉዳይ ሲሄዱ አንድ የምሳ መመገቢያ ከተማ ይደርሳሉ፡፡ እዚያ ከተማ ሲደርሱ ከግራ ከቀኝ የመጡት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ምግብ ቤቶችን ሁሉ ከአፍ እስከ ገደብ ጢም አድርገዋቸዋል፡፡
ያልተጨናነቀ ቦታ ሲፈልጉ ሁለት ለግላጋ ሕፃናት ቦታ እናሳያችሁ ብለው በተለምዶ «ማዘር ቤት» የሚባል ቤት ውስጥ ወሰዷቸው፡፡ እናት ምግብ ሠሪ፣ ልጅ አስተናጋጅ ሆነው አገኟቸው፡፡ ምግብ አዘዙ፡፡ አንዱ ቀይ ወጥ፣ አንዱ አልጫ፣ አንዱ ቅቅል፣ አንዱ ደግሞ ጥብስ፡፡ ልጅቱ ትእዛዝ ተቀብላ ከመሄዷ እናትዬዋ ወገባቸውን በመቀነት ታጥቀው መጡ፡፡ «እኔ አበራሽ አራት ዓይነት ወጥ አልሠራም፤ ተስማሙና አንድ አድርጋችሁ እዘዙ» አሏቸው፡፡
ልጆቹም እየሳቁም፣ እየተገረሙም በቀይ ወጡ ጸኑ፡፡ ጥቂት ጊዜ ወስደው በትልቅ ትሪ ከአራት እንጀራ ጋር አመጡላቸው፡፡ በወጣት አበላል ላፍ ላፍ አደረጉና ቀና ሲሉ እንጀራው ከወጡ በልጦ አገኙት፡፡ «ወጥ አስጨምሪልን» አሏት ልጅቱን፡፡ ገባች ወደ ጓዳ፡፡ አሁንም እናት ወገባቸውን ይዘው መጡ፡፡ አሁን ቀጥ ብለው ወደ ትሪው ነው የሄዱት፡፡ እጃቸውን ሰደዱና በወጥ የራሰውን እንጀራ በጣታቸው እየፈተፈቱ «ምነው አበራሽ፣ ይሄ ወጥ አይደለም? የነካካውን ብሉ፡፡ ወጥ የሚጣፍጠው ሲያብቃቁት ነው» እያሉ ፈተፈቱላቸው፡፡ ወይ እጅ መታጠብ፤ ሦስተኛ ክፍል ቀረ፡፡]
ይሄው መመርያ ነበር የሀገሪቱም መመርያ «አብቃቁት» የሚል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የአስተሳሰብ ድህነት የፈጠረብን ነው፡፡ ወላጆችም፣ መምህራኑም፣ የትምህርት አስተዳ ደሩም እጥረቱን እንደ አርባ ቀን ዕድል ተቀብለውት ያለ መፍትሔ ይቀመጣሉ፡፡ የመጽሐፍ ርዳታ ለመሰ ብሰብ፣ የቀድሞ ተማሪዎችን አስተባብሮ አብያተ መጻሕፍትን ለማጠናከር፣ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድ ተልሞ የመጻሕፍትን ቁጥር ለመጨመር ሲጥር የሚታይ አልነበረም፡፡
በተለይማ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ የ2000 ዓምን ኮርስ በ1965 ዓም መጽሐፍ መማር እንደ ነውር አይታይም ነበር፡፡ በውጭ ሀገር ካሉት መጽሐፍ ተርፏቸው መጣያ ካጡት ተቋማት ጋር በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ነበሩ፡፡ ግን ምን ያደርጋል ውጭ ሀገር ተምረው የሚመጡት የዩኒቨርሲቲ አመራሮችና መምህራን የስኮላር ሺፑን ያህል አላሳሰባቸውም፡፡ አንዳንዱ የኮሌጅ ቤተ መጻሕፍት «ቤተ መዛግብት» እስከመሆን የደረሰውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ ለዐቅመ ኮሌጅ ያልደረሱ ተማሪዎች ደግሞ «በውሻ እራት ውሻ ቆሞባት» እንደ ሚባለው ያቺኑ ያለችውን መጽሐፍ እየገነጠሉና እየሰረቁ፣ በላይዋ ላይ እየጻፉና እያሠመሩ ደብዛዋን ያጠፏታል፡፡
ኮሌጆቻችን ከሕዝብ ርቀው፣ ንጽሕ ጠብቀው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ምሁራኑም «ዝጉሐውያን ባሕታውያን» ናቸው፡፡ ኮሌጆቹን ሕዝቡ ምን እንደሚሠሩና ምን እንደሚጠቅሙም እንዲያውቅ አይደረግም፡፡ በመን ግሥት በጀት እንጂ በሕዝብ ድጋፍ አይቋቋሙም፡፡ ሕዝቡ የኔ ናቸው፡፡ ልደግፋቸው ይገባል እንዲላቸው አይፈልጉም፡፡ አንድም ቀን ከአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ጋር ተዋውቀው አያውቁም፡፡ በዚህም ምክንያት ከሕዝብ በስጦታ፣ በውርስ፣ በበጀት ድጋፍ፣ በርዳታ፣ በገጽታ ግንባታና በአመራር ሊያገኙ የሚችሉትን ድጋፍ አላገኙም፡፡
ምሁራኑም ለአካዳሚያዊ ክበቡ እንጂ ለሕዝብ የተገለጡ አይደሉም፡፡ የሚጽፉት በእንግሊዝኛ፣ የሚያሳ ትሙት በጆርናሎች፣ የሚከራከሩት በክፍል ውስጥ በመሆኑ ሕዝቡ በዙርያቸው እንጂ አብሯቸው አይደ ለም፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ ምሁር ሞተ ከሚሉት አንድ የዕድር ዳኛ ሞተ ቢሉት ሕዝቡ አብዝቶ ያዝናል፡፡ የማን ሞት እንደሚጎዳው የሚያውቀው እርሱ ነውና፡፡
እንዲህ ሆነን ግን እስከ መቼ? መቼም ሮም በአንድ ቀን አልተሠራችምና ችግሩን ሁሉ በአንድ ጊዜ ላንቀርፈው እንችል ይሆናል፡፡ ግን ለመቅረፍ መጀመር አለብን፡፡ «ሺ ገ!ዜ ጨለማን ከመውቀስ አንድ ሻማ ማብራት ይበልጣል» እንዳለው ኮንፊሽየስ ያልሆነበትን ምክንያት ብቻ እያነሣን ከምናትት እስኪ መለወጡን ከራሳችን እንጀምረው፡፡ በተለይ በውጭ ካለው ዳያስጶራ፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ በየትምህርት ቤቱና ኮሌጆቹ ዓመቱ ሲጠናቀቅ መጻሕፍቱ ይቀየራሉ፡፡ አዳዲስ እትሞች ይመጣሉ፡፡ ያለፉት እትሞች ወይ በርካሽ ይሸጣሉ ያለበለዚያም ደግሞ በነጻ ይሰጣሉ፤ ከባሰም ወደ «ድጌ ቤት» (Recycle house) ይላካሉ፡፡
እናም እስኪ ምናለበት የዕውቀት ርዳታ ለሀገራችን ብንጀምር፡፡ በምን መንገድ አትሉኝም፡፡ በየአካባቢያችን ከሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች በርካሽ የምናገኛቸውን መጻሕፍት እንሰብስብ፡፡ በአንዳንድ ኮሌጆች እንዲያውም አፍሪካውያን ተማሪዎች መግለጫና ካርቶን እያስቀመጡ በነጻ ከሚሰጡ ተማሪዎች ሲሰበስቡ አይቻለሁ፡፡ በምዕራቡ ዓለም አንድን ነገር ለብዙ ጊዜ ማስቀመጥ እዳው የቦታ ጥበት ነውና በቶሎ እንዲ ወገድ ይመከራል፡፡ እኛም ይህንን ባህል እንጠቀም፡፡ መጻሕፍቱን እንሰበስብ፡፡
እያንዳንዱ የውጭ ነዋሪም ለራሱ ቃል ይግባ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በሄደ ቁጥር ቢያንስ ሦስት መጽሐፍ ይዞ ለመሄድና በአካባቢው ለሚገኝ በመጽሐፉ ለመጠቀም ለሚችል ትምህርት ቤት ለመስጠት፡፡ ሌላው ቢቀር በአካባቢያችን ለሚማሩ ወጣቶች እንስጣቸው፡፡ በሕዝብ ቤተ መጻሕፍት እናስቀምጣቸው፡፡ ለሠፈራችን ጎበዝ ተማሪዎች እንሸልማቸው፡፡ አያሌ ተማሪዎችን አስፈትኖ መልካም ውጤት ላመጣ ትምህርት ቤት ዳያስጶራው መጻሕፍት ይሸልም፡፡
ቢያንስ በየዓመቱ ወደ አሥር ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ከውጭ ይመጣሉ፡፡ እያንዳን ዳቸው ሦስት መጽሐፍ ቢይዙ፤ በዓመት ሠላሳ ሺ መጽሐፍ ወደ ሀገር ይገባል ማለት ነው፡፡ በዐሥር ዓመት ስናስበው ደግሞ 300,000 መጽሐፍ ይሆናል፡፡ ከዚህ በላይ ምን የዕውቀት ርዳታ አለ፡ ሀገሪቱስ ይህንን ያህል በጀት ለመጽሐፍ መመደብ ትችላለች ብላችሁ ነው?
ትምህርት ቤቶች ላይ ካልሠራን ስለ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት፣ ስለ ሥልጣኔና ዕድገት ማውራቱ ቅዠት ይሆናል፡፡ ዕውቀት አጠር ሆኖ ያደገን ትውልድ ሥልጣኔ አጠር አትሁን ማለት ያልተወለደን ልጅ እንደማሳደግ ይቆጠራል፡፡
እስኪ በቤታችሁ ግደግዳ ላይ፣ ወይም በፍሪጃችሁ በር ላይ «ዕውቀት እንረዳለን» ብላችሁ ለጥፉ፡፡ ለሚጠይቋችሁ አስረዱ፡፡ በፌስ ቡካችሁ ላይ ለጥፉ፣ በቢሯችሁ ጠረጲዛ ላይ ጻፉ፡፡ በመኪኖቻችሁ ላይ እንደ ጌጥ ስቀሉ፡፡ ሀገር የሚለወጠው በዕውቀት ነው፡፡ ለውጥ የሚጀመረው ደግሞ ከትምህርት ቤት፡፡
እስኪ ቃል እንግባ፡፡
ሽሮ እናስመጣለን፤ በርበሬ እናስልካለን፣ እኛም በተራችን ዕውቀት እንረዳለን፡፡
ኦክላንድ፣ ካሊፎርንያ
