ጠ/ሚኒስትሩ እንዴት ቀልድ ጨምራል ጃል!

በቤቴ ኢቲቪ አይከፈትም፡፡ ከወያኔ ጋር ንክኪ ያለው ሬዲዮም እንዲሁ፡፡ ትክክል እንዳልሆንኩ ይገባኛል፡፡ ምን ላድርግ? ስለሚያመኝ እኮ ነው፤ ወድጄን መሰላችሁ? ይህቺን አልፎ አልፎ የምሞነጫጭራትን ነገር እንካEን የማቀራስመው ባብዛኛው በስማ በለው ከማገኘውና ከውጭ ሚዲያዎች ከምከታተለው ነው፡፡ ይሁንና እኔ አልሰማም ብልም ሰው እያመጣ ሳልወድ በግዴ ይነግረኛል፡፡ እምቢ አልል ነገር ከሰው ጋር ነው የምውል፡፡

ጋደኞቼ እየተናደዱ ትናንት ማታ ‹እገሌ እንዲህ አለ፤ እገሊት እንዲህ አለች› ሲሉ ስለምሰማ አንዳንዴ እቤቴ አለማዳመጤን ሳስበው አልሸሹም ዘወር አሉ ዓይነት ነገር ይሆንብኛል፡፡ ጠበል ሄጄ ትግስቱን እንዲሰጠኝ ልለማመን ይሆን? በእስካሁኑ ሁኔታየ ከቤተሰቤ ጋር የሽንብራ ቆሬ ወይም የጉንዲት አሊያም የሰገሌ ጦርነት ይከፈታታል እንጂ እንዴት ተደርጎ ኢቲቪ በገዛ ቤቴ ይከፈታል? እንደዱሮዋ ሶቪየት ኀብረት ብንሆን ምን ይውጠን ነበር ብዬ ሳስብ ደግሞ ጭንቅ ይለኛል፡፡ የወያኔ ጆሮ ይደፈንና በዚያች ሀገር – በቀድሞው ቀፍዳጅ የሶሻሊስት ሥርዓት ዘመን – ካገራቸው የዜና ማዕከላት በስተቀር የሌላ ሀገር ሚዲያ እንዲያዳምጡ በፍጡም አይፈቀድላቸውም ነበር ይባላል፡፡ የምታስታውሱ ካላችሁ እነዚህ አውሮፓዎችና አሜሪካዎች የዚያችን የሶሻሊስት ሀገር ሕዝብ ልብ ለማሸፈት የተለያዩ ዘመቻዎችን ያካሂዱ ነበር፡፡ ከነዚያ ዘመቻዎቻቸው መካከል አንዱ ‹ሬዲዮ ፍሪ ዩሮፕ› የሚል የሬዲዮ ጣቢያ ከፍተው በኃይለኛ ሞገድ በድፍን ሶቪየት ኅብረት ሊደመጥ የሚችል ፀረ ሶሻሊዝምና ኮሚውኒዝም ቅሰቀሳ ማካሄድ ዋናው ፀረ – ኀበረተሰባዊነት(ሶሻሊዝም) ተግባራቸው ነበረ፡፡ ከዚህ ‹ሕዝብን በራዥ› ጠንቅ ሕዝባቸውን ‹ለመታደግ› ሶቪየቶች ምን ያደርጉ ነበር መሰላችሁ ታዲያ – ማንም ሰው ወደቤቱ ገብቶ መብራት ሊያበራ እስዊቹን ሲነካ የራሱን ሀገር ሬዲዮም አብሮ እንዲከፍት ተደርጎ የድምጽ መጨመሪያና መቀነሻ በሌለው ሁኔታ መብራቱንም እስካላጠፋውና በጨለማ መደናበር እስካልፈለገ ድረስ አጥፍቶ እስኪተኛ የሀገሩን ሬዲዮ ብቻ እንዲኮመኩም የሚያስችል ማብሪያ ማጥፊያ በየቤቱ ተገጠመ አሉ፡፡ አሉ ነው እንግዲህ፡፡ በአሉ ክስና ወቀሳ የለም፡፡ ሌላ ሬዲዮም ሆነ ቲቪ እንዲኖረው አይፈቀድም ነበር አሉ፡፡ ሰውዬው ሲፈልግ በሻማና በጡዋፍ ወይም በኩራዝና በፋኖስ ይቀመጣታል እንጂ መብራት ካበራ የግዱን ያዳምጣታል፡፡ የሚያስደስተው ግን – ይህ ታሪክ እውነትም ይሁን ውሸት – ያ ጊዜ ማለፉ ነው፡፡ የኛ ብቻ አለ እንጂ እየተንቀራፈፈ፡፡ በነገራችን ላይ ይህን ታሪክ ከጨዋታነት አስበልጬ ባላየው ደስ ይለኛል፡፡

አሁን በኛ ሀገር ግና ተመስገን ነው በጥባጭ የቤተሰብ አባላት አንዴ ገመና ሌላ ጊዜ ካEስ ጨዋታ ወይም የእሁድ መዝናኛ 120 ፕሮግራም እያሉ ይጠምሱናል እንጂ የወያኔን ትውከትና ቅርሻት ላለማዳመጥ – ይቅርታ ሌላ መጣኝ ቃል ስላጣሁ ነውና በአሳቻ ሰዓት አንቡልኝ ይቺን ሐረግ – ቲቪያችንን ከነአካቴው መጠርቀም ወይም በዲሽ የፈለግነውን የውጭ ቻናል ማየት በምንችልበት ሁኔታ ላይ መገኘታችን እፎይታን ሰጥቶናል፡፡ እንደራሽያዎቹ ቤት፣ መብራት ስናበራ አብሮ የሚከፈት ቲቪና ሬዲዮ ቢኖረን ምን ይውጠን ነበር? ጉድ እኮ ነው!

ሰሞኑን መሌ መሊሻ ቀደዳዋን በስፋት ይዛዋለች፡፡ እንደሱዋ በለስ የቀናው የሀገር ‹መሪ› መቼም በዓለም ታይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ከፍ ሲል እንደተናገርኩት በቤቴ ኢቲቪ አይከፈትም ብያለሁ፡፡ ልክፈት ቢሉ እንኩዋን የወያኔን ንዴት በነሱ ላይ ነው የምወጣው፡፡ ምን ቁርጥ አድርÕቸው? ወደፊት ንስሃ ገብቼ ኃጢያቴን አወርዳለሁ እንጂ አሁን እበደልካEቸው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ መቼም ‹ሰው ነኝና› ብላEልና ዘፋኙ የይቅርታ ዘመን ሲመጣ ይቅር ይሉኝ ይሆናል፡፡ እናም ዛሬ ማታ ለአቡየ ጠበል ጠዲቅ ጎረቤት ሄጄ መሌን እንደማርካቶ ጣቃ ሲቀረደድ በዚያው በፈረደበት ‹ቲቪያችን› አየሁት፡፡ እሰው ቤት በንግድነት ተጠርቶ ሄዶ ቲቪ ዝጉ አይባል! ደግሞስ ማን ማንን ያውቃል? በከንቱ ጭዳ ልሁን? አጅሬን ምን እንደነካው አላውቅም ይህን ሰሞን በትግርኛም ባማርኛም ‹ጋዜጣዊ መግለጫ› መስጠት አብዝቶኣል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫዎቹ ግን እንደወትሮው ሁሉ በተወሰኑ ‹ጋዜጠኞች› ጠያቂነት የሚካሄዱና መልስ ሊሰጣቸው የሚፈለጉ አስቀድመው የተጠኑ ጥያቄዎች ላይ የሚያተኮሩ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡

በቀደም ዕለት የትግርኛው ጠያቂ (አንድ ብቻ ነው) ‹ የኤርትራ ሕዝብ ከሰሜን አፍሪካው ሕዝባዊ አመጽ ምን ሊማር ይችላል? ብሎ ለጠየቀው ሲመልስ ‹ አንደኛ … ሁለተኛ የኤርትራ ሕዝብ በላዩ ላይ የተጫነበት መንግሥት የአራዊት መንግሥት ስለሆነ በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ሊያወርደው የሚችልበትን ትምህርት ቀስሞኣል፡፡ ሦስተኛ …› ብሎ የመለሰው ከኅሊናየ ለምንጊዜውም አይጠፋም፡፡ ‹ይሉሽን ባልሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ› እንዳይባል መለስ የሚሠራውን በሚገባ ያውቃል፤ ግን የገባበት ዕዳ ከባድ ስለሆነና ተፈጥሮውም ውሸታም በመሆኑ ሁሉንም እውነት ከመሸምጠጥ ሌላ ምንም አማራጭ የለውም፡፡ መለስ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው #ፀሐይ በምዕራብ ወጥታ በምሥራቅ ትገባለች፤ ነጭና ነጭ ሲቀላቀል ጥቁር ይሆናል፤ ሁለትና ሁለት ሲደመር አሥራ አንድ ነው፤ ሰው ሲራብ ይጠግባል፤ ሀገር ስትጠፋ ትበለጽጋለች – ትለማለች፤ … $ ቢል ለመናገሩ እንጂ ለመታመኑ ሃሳቡ አይበላውም፡፡ ምን ዓይነት ድፍን ቅል እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ከርሱ ይልቅ ይህን ተፈጥሮውን እያወቁ ብዙ ሰዎች ከርሱ ሥር ሉጥ ሉጥ ማለታቸው በእጅጉ ይገርመናል፡፡ ‹አብሽ ልዋጩን አያጣም› የሚባለው ለካንስ ለዚህ ነው? የሚገርም ፍጡር እኮ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን – ለማየት ያብቃችሁ – ወደፊት የሰው ልጅ በአጠቃላይ የሚያፍርበት የሚሌኒየሙ አባ ስጠው አደገኛ ውሸታም ነው፡፡ አደገኛነቱም እንደኔ በየጥጋጥጉ የሚወሸከት ሳይሆን የመንግሥትን ትልቁን ሥልጣን ይዞ በ80 ሚሊዮን ሕዝብ ሕይወት ላይ የሚያፌዝና የሚቀልድ ወናፍና ማንዘርዘሪያ ወንፊት መሆኑ ነው፡፡ የተራ ዜጋ ውሸታምነት ዕዳው ቀላል ነው፡፡ በሱ የሥልጣን ቦታ ላይ ሆኖ ይህን ያህል ቅድ በርሜል መሆን ግን ለጊዜው ክፉኛ ያሳዝናል፡፡ ለወደፊቱ ግን ይህ ሰው መቼም ቢሆን መሞቱ አይቀርምና በድኑ ለሁነኛ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ተሰጥቶ አንጎሉ ከምን እንደተሠራ መፈተሸ ይኖርበታል፡፡ በበኩሌ እርግጠኛ ነኝ የዚህ ሰው አንጎል የሰው ብቻ ሳይሆን የሆነ የባዕድ ነገር ቅልቅል ሳይኖርበት የሚቀር አይመስለኝም፡፡

እንዲያ ባይሆን ኖሮ፤ #የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ ኢሕአዴግን በመምረጡና በፈለገው የምርጫ ሰዓት በዝረራ ሊጥለው እንደሚችል ስለሚረዳ የሰሜን አፍሪካው የተቃውሞ ሕዝባዊ አመጽ ኢትዮጵያን አያሰጋትም፡፡ የኛ ሥጋት የገባነውን ኮንትራት በገባነው ቃል መሠረት ማከናውናችን ነው፡፡ … እርግጥ የኤርትራ መንግሥት አዲስ አበባን ባግዳድ ለማድረግ ሤራ እየሸረበ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ይህን ህልሙን እውን ለማድረግም አንዳንድ ተቃዋሚዎችን ለመጠቀም እንደሚሞክር ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ ይህንን ተንካEሽ ድርጊቱን ደግሞ 80 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሶ ጨብጠው አይጠብቁትም፡፡ ኢሕአዴግና ሕዝቡ እጅና Õንት ሆነው የጀመሩትን ዴሞክራሲያዊ የልማት እንቅስቃሴ ሊያጨናግፍባቸው የሚመጣባቸውን ማንኛውንም ኃይል በብርቱ ክንዳቸው ይመልሱታል፡፡ ሕዝባዊ አመጽና ተቃውሞ አምባገነን መንግሥታትን እንጂ በዴሞክራሲ አግባብ ሥልጣን ላይ የወጡ እንደ ኢሕአዴግ ያሉ መንግሥታት የራስ ምታት ሊሆን አይችልም፡፡ …$ (እፍፍፍ… ደከመኝ እባካችሁ!) ብቻ – ልድገመው – እንዲያ ባይሀን ኖሮ እንዲህ በጥቅስ ውስጥ እንደተቀመጠው ያለ ከበረዶና ከአመዳይ የነጣ ነጭ ውሸት ያለ አንዳች ሀፍረት አይናገርም ነበር፡፡ ስለዚህ መለስ በሽተኛ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ማስረጃ ሊቀርብ አይችልም፡፡ በመሠረቱ አምባገነንነት በራሱ እልም ያለ የበሽታዎች ሁሉ ቁንጮ በሽታና ፈውስም የማይገኝለት ትልቁ ደዌ ነው፡፡
[email protected]