ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ዐበይት ጉዳዮች መወያያ ጉባኤ

የኢትዮጵያ ዐበይት ጉዳዮች መወያያ ጉባኤ ለሶስት ዓመታት ያህል ኣንድነታዊ ዓለም-አቀፍ የሕዝብ ማህበራት ንቅናቄ ለመመስረት ሲጥር ቆይቷል። የተሰባሰበውም በአምስት ዓብይ መርሆዎች ላይ ነው። እነዚሁም፦ የኢትዮጵያን ድንበሮችንና ልዕልና ማስከበር፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ማክበር፤ በዓለም-አቀፍ እውቅና ያላቸውን የዚጎች መብቶችን ማሳወቅና ማስከበር፤ የግል ሃብት ዋስትና እንዲረጋገጥና፤ ሚዛናዊና አስተማማኝ ቁጥጥር የሚያንጸባርቁ መንግስታዊ መዋቅራት እንዲዘረጉ የሚሉ ናቸው።

ለመጀመሪያ ጊዜ መብት-ተኮር የሲቪክ ማህበራትን ባሰባሰበው በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ የተሳተፉት አስር የሲቪክ ድርጅቶች ተወካዮች ትናንት ሙሉ ቀን የፈጀ ሰፊ ውይይት አካሂደው አንድነት ለመፍጠር ተስማምተዋል። በመሆኑም በኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት ሁሉን-አቀፍ በሆነ ሰፊ መሰረት ላይ የተገነባ የፖለቲካ ድርጅቶችንና አገር-ውዳድ ዜጎችን ለሚያካትት ሕዝባዊ ንቅናቄ ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚያስችላቸውን ዉህድትና አንድነት ለመፍጠር እንዲቻል የሚከተሉትን ዉሳኔዎች ማሳለፉን ስናበስር በታላቅ ኩራትና ደስታ ነው፦

1ኛ) የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የዜጎች ቃል-ካዳን ሰነድ ተቀብሏል። ይህም ማለት ነጻ ዜግነትንና ኢትዮጵያዊነትን ያማከለ አገርህን አድን ጥሪ በሰንደቅነት ጉባዔው አጽድቆታል።

2ኛ) ከሚዋሓዱ የሲቪክ ማህበራት አባላትና ወደፊት በስፋት በሚሳትፉ ግለሰቦች የሚመሰረት አነድ-ወጥ አዲስ ድርጅት እንዲዋቀርና የተለየ ትኩረት ካላቸው የሙያ ማህበራት ጋር የቅርብ ትስስር እንዲፈጠር ጉባዔው ወስኖአል።

3ኛ) ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ዐዓበይት ዓላማዎች፡ ስልቶች፡ የመተዳደሪያ ደንብና ድርጅታዊ መዋቅርን የሚያዘጋጅና የሚያስተባበር የድርጅት ተወካዮች የሚሳተፉበት ኮሚቴ ተቋቁሟል። የአዲሱ የሲቪክ ድርጅቶችም መጠሪያ፡
“ኢትዮያዊነት፦ የመብት ማስከበሪያ ጉባዔ” እንዲባል ተወስኖአል።

የዜጎች ቃል ኪዳን ሰነድ ታትሞ በአንድ ወር ዉስጥ ይፋ ይሆናል። እስከዚያም የሰነዱን ረቂቅ ከድህረ-ገጻችን ማግኘት ይቻላል፦ www.enpcp.org ወይም or www.enpcp.net.